በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፍቻ

  • ሂሶጵ

    በመንጻት ሥርዓት ወቅት ደም ወይም ውኃ ለመርጨት ያገለግል የነበረ ቀጫጭን ቅርንጫፎችና ቅጠሎች ያሉት ተክል ነው። ምናልባትም ማርጆራም (ኦሪጋነም ማሩ፤ ኦሪጋነም ሲሪያከም) በመባል የሚታወቀው ተክል ሊሆን ይችላል። በዮሐንስ 19:29 ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ የሚገልጸው በዘንጋዳ አገዳ ላይ ስለታሰረ የማጆራም ተክል ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም ዘንጋዳ የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ የተነከረውን ሰፍነግ ወደ ኢየሱስ አፍ ለማቅረብ የሚያስችል ረጅም አገዳ አለው።–ዘፀ 12:22መዝ 51:7

  • ሂን

    የፈሳሽ ነገር መለኪያ ሲሆን ዕቃው ራሱም በዚህ ስያሜ ይጠራል። አንድ ሂን 3.67 ሊትር ነው። (ዘፀ 29:40)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ሂጋዮን

    ሙዚቃ ለመምራት የሚያገለግል ከሙዚቃ ሙያ ጋር የተያያዘ ቃል ነው። መዝሙር 9:16 ላይ ከተሠራበት መንገድ አንጻር ቃሉ የአምልኮ ሥርዓት በሚከናወንበት ጊዜ በሚቀርብ መዝሙር ላይ በመዝሙሩ መሃል የሚሰማን ወፈር ያለ የበገና ድምፅ ወይም ለማሰላሰል ሲባል መዝሙሩ ለአፍታ ቆም እንዲል የሚደረግበትን ጊዜ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

  • ሄርሜስ

    የዙስ ልጅ ሲሆን የግሪካውያን አምላክ ነው። ጳውሎስ በልስጥራ ሳለ ሕዝቡ እሱን እንደ ሄርሜስ፣ የአማልክት መልእክተኛና የርቱዕ አንደበት አምላክ እንደሆነ አድርገው ስለተመለከቱት ሄርሜስ በማለት የተሳሳተ ስያሜ ሰጥተውት ነበር።–ሥራ 14:12

  • ሄሮድስ

    በሮማውያን ተሹሞ በአይሁዳውያን ላይ ይገዛ የነበረ የአንድ ሥርወ መንግሥት የቤተሰብ ስም ነው። ታላቁ ሄሮድስ የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ መልሶ በመገንባት እንዲሁም ኢየሱስን ለማስገደል ሲል ሕፃናት እንዲጨፈጨፉ ባስተላለፈው ትእዛዝ የሚታወቅ ሰው ነው። (ማቴ 2:16፤ ሉቃስ 1:5) የታላቁ ሄሮድስ ልጆች የሆኑት ሄሮድስ አርኬላዎስና ሄሮድስ አንቲጳስ በተወሰነው የአባታቸው ግዛት ላይ ተሹመው ነበር። (ማቴ 2:22) ክርስቶስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንዲሁም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 12 ላይ ያለው ዘገባ እስከተፈጸመበት ዘመን ድረስ የገዛው አንቲጳስ፣ ቴትራርክ (የአንድ አራተኛው ክፍል ገዢ) ቢሆንም “ንጉሥ” ተብሎ ተጠርቷል። (ማር 6:14-17፤ ሉቃስ 3:1, 19, 20፤ 13:31, 32፤ 23:6-15፤ ሥራ 4:27፤ 13:1) ከዚያ በኋላ የታላቁ ሄሮድስ የልጅ ልጅ የሆነው ሄሮድስ አግሪጳ ለጥቂት ጊዜ ከገዛ በኋላ የአምላክ መልአክ ቀሰፈው። (ሥራ 12:1-6, 18-23) ከዚያም ልጁ ዳግማዊ ሄሮድስ አግሪጳ የነገሠ ሲሆን እሱም አይሁዳውያን በሮም ላይ እስካመፁበት ጊዜ ድረስ ገዝቷል።–ሥራ 23:3525:13, 22-2726:1, 2, 19-32

  • ሆሜር

    ከቆሮስ መስፈሪያ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የደረቅ ነገር መለኪያ ሲሆን የባዶስ መለኪያን መሠረት በማድረግ ሲሰላ አንድ ሆሜር 220 ሊትር ነው። (ዘሌ 27:16)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ለቅሶ፤ ሐዘን

    አንድ ሰው የሚወደውን ሰው በሞት በሚያጣበት ወይም በራሱ ላይ አንድ ዓይነት መከራ በሚደርስበት ጊዜ ስሜቱን አውጥቶ የሚገልጽበት መንገድ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ለተወሰነ ጊዜ ሐዘን መቀመጥ የተለመደ ነበር። ያዘኑ ሰዎች ሐዘናቸውን ለመግለጽ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከማልቀሳቸውም በተጨማሪ ለየት ያለ የሐዘን ልብስ ይለብሱ፣ በራሳቸው ላይ አመድ ይነሰንሱ፣ ልብሳቸውን ይቀድዱና ደረታቸውን ይደቁ ነበር። በአንዳንድ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ ሙሾ አውራጆች እንዲገኙ ይጠሩ ነበር።–ዘፍ 23:2አስ 4:3፤ ራእይ 21:4

  • ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየው ቅዱስ ምልክት

    “ቅድስና የይሖዋ ነው” የሚል ጽሑፍ በላዩ ላይ የተቀረጸበት ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ የሚያብረቀርቅ ጠፍጣፋ ወርቅ ነው። ይህ ወርቅ በሊቀ ካህናቱ ጥምጥም ላይ ከፊት በኩል ይደረግ ነበር። (ዘፀ 39:30)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ን ተመልከት።

  • ለአምላክ ያደሩ መሆን

    ለይሖዋ አምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየትን፣ አምልኮ ማቅረብንና እሱን ማገልገልን የሚያሳይ ሲሆን ለአጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱ ታማኝ መሆንን ይጠይቃል።–1ጢሞ 4:82ጢሞ 3:12

  • ሊቀ ካህናት

    በሙሴ ሕግ መሠረት ሊቀ ካህናቱ ሕዝቡን ወክሎ አምላክ ፊት ይቀርብ እንዲሁም ሌሎች ካህናትን በበላይነት ይቆጣጠር ነበር። “የካህናት አለቃ” ተብሎም ይጠራል። (2ዜና 26:20ዕዝራ 7:5) ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ወይም ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ይኸውም ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መግባት የሚፈቀድለት እሱ ብቻ ነበር። ይህን የሚያደርገውም በዓመታዊው የስርየት ቀን ብቻ ነበር። “ሊቀ ካህናት” የሚለው መጠሪያ ለኢየሱስም ተሠርቶበታል።–ዘሌ 16:2, 1721:10ማቴ 26:3ዕብ 4:14

  • ሌዊ፤ ሌዋዊ

    ያዕቆብ ከሚስቱ ከሊያ የወለደው ሦስተኛ ወንድ ልጅ ነው። የሌዋውያን ሦስት ዋና ዋና ምድቦች የተሰየሙት በሌዊ ሦስት ወንዶች ልጆች ስም ነው። አንዳንድ ጊዜ “ሌዋውያን” የሚለው መጠሪያ ነገዱን በአጠቃላይ ለማመልከት የሚሠራበት ቢሆንም ብዙውን ጊዜ፣ በክህነት የሚያገለግለው የአሮን ቤተሰብ እዚህ ውስጥ አይካተትም። የሌዊ ነገድ በተስፋይቱ ምድር ርስት ባያገኝም በሌሎቹ ነገዶች በተያዙት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ 48 ከተሞች ተሰጥተውት ነበር።–ዘዳ 10:81ዜና 6:1፤ ዕብ 7:11

  • ሌዋታን

    ብዙውን ጊዜ ከውኃ አካላት ጋር ተያይዞ የሚገለጽ ሲሆን በውኃ ውስጥ የሚኖር እንስሳ እንደሆነ ይገመታል። በኢዮብ 3:8 እና 41:1 ላይ አዞን ወይም በውኃ ውስጥ የሚኖርን ግዙፍና ከፍተኛ ጥንካሬ ያለው ሌላ እንስሳ የሚያመለክት ይመስላል። በመዝሙር 104:26 ላይ ደግሞ የዓሣ ነባሪ ዝርያን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። በሌሎች ቦታዎች ላይ ግን ቃሉ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል፤ በመሆኑም አንድን የተወሰነ እንስሳ አያመለክትም።–መዝ 74:14ኢሳ 27:1

  • ሌፕተን

    የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በተጻፉበት ዘመን ይገኝ የነበረ ትንሹ የአይሁዳውያን የመዳብ ወይም የነሐስ ሳንቲም ነው። (ማር 12:42፤ ሉቃስ 21:2 የግርጌ ማስታወሻዎች)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ሎግ

    በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ ትንሹ የፈሳሽ ነገር መለኪያ ነው። በአይሁዳውያን ታልሙድ ውስጥ የሂን 1/12 እንደሆነ ተገልጿል፤ በዚህ መሠረት ሲሰላ ሎግ 0.31 ሊትር ይይዛል። (ዘሌ 14:10)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ሐዋርያ

    የቃሉ መሠረታዊ ትርጉም “የተላከ” የሚል ሲሆን ሰዎችን እንዲያገለግሉ የተላኩትን ኢየሱስንና ሌሎች ደቀ መዛሙርትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። አብዛኛውን ጊዜ የተሠራበት ኢየሱስ የእሱ ወኪሎች እንዲሆኑ በቀጥታ የመረጣቸውን 12ቱን ደቀ መዛሙርት ለማመልከት ነው።–ማር 3:14ሥራ 14:14

  • ሐዲስ

    “ሲኦል” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ያለው ግሪክኛ ቃል ነው።–መቃብር የሚለውን ተመልከት።

  • ሕግ

    ሕግ የሚለው አገላለጽ እንደየአገባቡ የሙሴን ሕግ፣ የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ወይም ደግሞ የሙሴ ሕግ የያዛቸውን ትእዛዛት በተናጠል አሊያም ሕጉ የያዘውን መሠረታዊ ሥርዓት ሊያመለክት ይችላል።–ዘኁ 15:16ዘዳ 4:8፤ ማቴ 7:12፤ ገላ 3:24

  • ሕግ አስከባሪዎች

    በባቢሎን መንግሥት ውስጥ ሕግ አስከባሪዎች የሚባሉት በየአውራጃው ያሉ ሕጉን የሚያውቁና የተወሰነ የመፍረድ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ነበሩ። በሮማውያን ግዛት ውስጥ ደግሞ ሕግ አስከባሪዎች የሚባሉት በመንግሥት የተሾሙ አስተዳዳሪዎች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የሚያከናውኑት ሥራ ሥርዓት ማስከበርን፣ የመንግሥትን ገቢና ወጪ መቆጣጠርንና በሕግ ተላላፊዎች ላይ ቅጣት መበየንን ይጨምራል።–ዳን 3:2ሥራ 16:20

  • መለከት

    ጥሪ ለማስተላለፍና ሙዚቃ ለመጫወት የሚያገለግል ከብረት የሚሠራ የትንፋሽ መሣሪያ። ዘኁልቁ 10:2 እንደሚገልጸው ይሖዋ ሁለት የብር መለከቶች እንዲሠሩ አዝዞ ነበር፤ በእነዚህ መለከቶች አማካኝነት ማኅበረሰቡን ለመሰብሰብ፣ ሕዝቡ ከሰፈረበት ቦታ ተነስቶ እንዲጓዝ ለማድረግ ወይም ለጦርነት እንዲነሳ ለመቀስቀስ የተለያየ ድምፅ በማሰማት ምልክት ይሰጡ ነበር። ከእንስሳ ቀንድ ከሚሠሩት የተጠማዘዘ ቅርጽ ያላቸው ቀንደ መለከቶች በተለየ እነዚህ መለከቶች ቀጥ ያሉ ሳይሆኑ አይቀሩም። በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይጠቀሙባቸው ከነበሩት የሙዚቃ መሣሪያዎች መካከል የተሠሩበት መንገድ በግልጽ የማይታወቅ መለከቶችም ይገኙ ነበር። ብዙውን ጊዜ፣ የመለከት ድምፅ የይሖዋን ፍርድ ወይም መለኮታዊ ምንጭ ያላቸውን ሌሎች ጉልህ ክንውኖች ከማወጅ ጋር በተያያዘ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል።–2ዜና 29:26ዕዝራ 3:10፤ 1ቆሮ 15:52፤ ራእይ 8:7 እስከ 11:15

  • መላእክት

    መልአኽ ከሚለው የዕብራይስጥ ቃልና አጌሎስ ከሚለው ግሪክኛ ቃል የተገኘ ነው። ሁለቱም ቃላት ቃል በቃል ሲተረጎሙ “መልእክተኛ” የሚል ፍቺ ያላቸው ሲሆን መንፈሳዊ አካል ያላቸው መልእክተኞችን ለማመልከት ሲሠራባቸው ደግሞ “መልአክ” ተብለው ይተረጎማሉ። (ዘፍ 16:7፤ 32:3፤ ያዕ 2:25፤ ራእይ 22:8) መላእክት ሰዎች ከመፈጠራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት አምላክ የፈጠራቸው ኃያላን የሆኑ መንፈሳዊ ፍጥረታት ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “አእላፋት ቅዱሳን፣” ‘የአምላክ ልጆች’ እና “አጥቢያ ከዋክብት” ተብለውም ተጠርተዋል። (ዘዳ 33:2፤ ኢዮብ 1:6፤ 38:7) በተፈጠሩበት ጊዜ መሰላቸውን የመተካት ችሎታ አልተሰጣቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ሁሉም አንድ በአንድ የተፈጠሩ ናቸው። ቁጥራቸው ከመቶ ሚሊዮን በላይ ነው። (ዳን 7:10) መጽሐፍ ቅዱስ የግል መጠሪያና ተለይተው የሚታወቁባቸው የየራሳቸው ባሕርያት እንዳሏቸው ይጠቁማል፤ ይሁንና ትሑት ከመሆናቸው የተነሳ አምልኮ ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም፤ እንዲያውም አብዛኞቹ ስማቸውን እንኳ ከመናገር ተቆጥበዋል። (ዘፍ 32:29፤ ሉቃስ 1:26፤ ራእይ 22:8, 9) የተለያየ ማዕረግና የሥራ ምድብ አላቸው፤ ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች መካከል በይሖዋ ዙፋን ፊት ሆነው ማገልገል፣ ከእሱ መልእክት ተቀብለው ማስተላለፍ፣ በምድር ላይ የሚገኙትን የይሖዋ አገልጋዮች መርዳት፣ የአምላክን ፍርድ ማስፈጸምና ምሥራቹን የማወጁን ሥራ መደገፍ ይገኙበታል። (2ነገ 19:35፤ መዝ 34:7፤ ሉቃስ 1:30, 31፤ ራእይ 5:11፤ 14:6) ወደፊት ደግሞ በአርማጌዶን ጦርነት ከኢየሱስ ጎን ተሰልፈው ይዋጋሉ።–ራእይ 19:14, 15

  • መሐላ

    አንድ ሰው የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን አስረግጦ ለመግለጽ ሲል የሚምለውን መሐላ ወይም አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ላለማድረግ የሚገባውን ቃል ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ ሥልጣን ላለው አካል በተለይ ደግሞ ለአምላክ ቃል መግባትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የተጋባውን ቃል ኪዳን በመሐላ አጽንቶታል።–ዘፍ 14:22ዕብ 6:16, 17

  • መሠዊያ

    ከአፈር፣ ከድንጋይ፣ ከዓለት ወይም በብረት ከተለበጠ እንጨት ከመሬት ከፍ ብሎ የሚገነባ ነገር ወይም መድረክ ሲሆን የአምልኮ ሥርዓት በሚከናወንበት ወቅት ልዩ ልዩ መሥዋዕቶች ወይም ዕጣን ለማቅረብ ያገለግላል። በማደሪያ ድንኳኑም ሆነ በቤተ መቅደሱ የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ዕጣን የሚጨስበት አነስተኛ የሆነ “የወርቅ መሠዊያ” ይገኝ ነበር። መሠዊያው ከእንጨት ተሠርቶ በወርቅ የተለበጠ ነው። ግቢው ውስጥ ደግሞ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች የሚቀርቡበት ትልቅ “የመዳብ መሠዊያ” ይገኝ ነበር። (ዘፀ 27:1፤ 39:38, 39፤ ዘፍ 8:20፤ 1ነገ 6:20፤ 2ዜና 4:1ሉቃስ 1:11)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ንና ለ8ን ተመልከት።

  • መሥዋዕት

    አንድ ሰው አምላክን ለማመስገን፣ በአምላክ ላይ በደል መፈጸሙን አምኖ እንደተቀበለ ለማሳየትና ከአምላክ ጋር የነበረውን ጥሩ ግንኙነት መልሶ ለማደስ ሲል ለአምላክ የሚያቀርበው መባ ነው። ከአቤል ጀምሮ ሰዎች እንስሳትን ጨምሮ የተለያዩ መሥዋዕቶችን በፈቃደኝነት ሲያቀርቡ የቆዩ ቢሆንም የሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን ከተቋቋመ በኋላ ግን መሥዋዕት ማቅረብ ከአንድ ሰው የሚጠበቅ ግዴታ ሆኗል። ኢየሱስ ሕይወቱን ፍጹም መሥዋዕት አድርጎ ከሰጠ በኋላ እንስሳትን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ቀርቷል፤ ያም ቢሆን ክርስቲያኖች ለአምላክ መንፈሳዊ መሥዋዕት ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።–ዘፍ 4:4ዕብ 13:15, 16፤ 1ዮሐ 4:10

  • መሲሕ

    ይህ ቃል “የተቀባ” ወይም “ቅቡዕ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ ነው። የግሪክኛው አቻ ቃል ደግሞ “ክርስቶስ” ነው።–ዳን 9:25ዮሐ 1:41

  • መሳፍንት

    በእስራኤል ላይ ሰብዓዊ ነገሥታት ከመንገሣቸው ቀደም ብሎ ይሖዋ ሕዝቡን ለመታደግ ያስነሳቸው ሰዎች ናቸው።–መሳ 2:16

  • መቀባት

    የዕብራይስጡ ቃል “በፈሳሽ መቀባት” የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። አንድ ሰው ወይም አንድ ነገር ለአንድ ልዩ ዓላማ እንዲያገለግል መወሰኑን ለማመልከት ዘይት ይቀባ ነበር። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይህ ቃል ለሰማያዊ ተስፋ በተመረጡ ሰዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ መፍሰሱን ለማመልከት ተሠርቶበታል።–ዘፀ 28:411ሳሙ 16:13፤ 2ቆሮ 1:21

  • መቃረም

    አጫጆች ሆን ብለው የተዉትንም ሆነ ሲያጭዱ የወደቀውን እህል ከማሳ ላይ መልቀምን ያመለክታል። የሙሴ ሕግ ሕዝቡ የማሳቸውን ዳር ሙልጭ አድርገው እንዳያጭዱና የወይራም ሆነ የወይን ፍሬ ሲለቅሙ ሁሉንም እንዳያራግፉ ያዛል። አምላክ ድሆች፣ የተቸገሩ ሰዎች፣ የባዕድ አገር ነዋሪዎች፣ አባት የሌላቸው ልጆችና መበለቶች አዝመራ በሚሰበሰብበት ጊዜ እንዲቃርሙ መብት ሰጥቷቸው ነበር።–ሩት 2:7

  • መቃብር

    እንደየአገባቡ የአንድን ሰው መቃብር ወይም የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። ከዚህም በተጨማሪ “ሲኦል” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃልና “ሐዲስ” ከሚለው ግሪክኛ ቃል ጋር ተመሳሳይ ትርጉም አለው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተሠራበት አንጻር ይህ ቃል ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የሌለበትን እንዲሁም ማሰብም ሆነ ማቀድ የማይቻልበትን ምሳሌያዊ ቦታ ወይም ሁኔታ ያመለክታል።–ዘፍ 47:30መክ 9:10፤ ሥራ 2:31

  • መቄዶንያ

    በታላቁ እስክንድር ዘመን ታዋቂነት ያገኘ ከግሪክ በስተ ሰሜን የሚገኝ አካባቢ ሲሆን በሮማውያን ቁጥጥር ሥር እስከዋለበት ጊዜ ድረስ ራሱን የቻለ ግዛት ሆኖ ቆይቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ በሄደበት ወቅት መቄዶንያ የሮማውያን ግዛት ነበር። ጳውሎስ ወደዚህ ቦታ ሦስት ጊዜ ሄዷል። (ሥራ 16:9)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ13ን ተመልከት።

  • መቅደስ

    ለአምልኮ የተለየን ማንኛውንም ቅዱስ ስፍራ ያመለክታል። ይሁን እንጂ በአብዛኛው የሚያመለክተው በኢየሩሳሌም ይገኝ የነበረውን የማደሪያ ድንኳን ወይም ቤተ መቅደስ ነው። በተጨማሪም ቃሉ በሰማይ ያለውን የአምላክ ማደሪያ ለማመልከት ተሠርቶበታል።–ዘፀ 25:8, 92ነገ 10:25፤ 1ዜና 28:10፤ ራእይ 11:19

  • መቆንጠጫዎች

    በማደሪያ ድንኳኑና በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚበሩትን መብራቶች ለማጥፋት የሚያገለግሉ (ምናልባትም ጉጠት የሚመስሉ) ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎች ናቸው።–ዘፀ 37:23

  • መተላለፍ

    የተደነገገን ሕግ መጣስ፤ ሕግን ባለማክበር የሚፈጸም ድርጊት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው “ኃጢአት” ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው።–መዝ 51:3ሮም 5:14

  • መተት

    ከክፉ መናፍስት በሚገኝ ኃይል የሚከናወን ነገር ነው።–2ዜና 33:6

  • መታሰቢያ መቃብር

    የሞተ ሰው አስከሬን የሚቀበርበትን የመቃብር ስፍራ ያመለክታል። መታሰቢያ መቃብር ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ምኒሚይኦን ሲሆን “ማስታወስ” የሚል ፍቺ ካለው ግስ የተገኘ ነው። ይህም የሞተው ሰው እንደሚታወስ ይጠቁማል።–ዮሐ 5:28, 29

  • መና

    እስራኤላውያን ለ40 ዓመት በምድረ በዳ በቆዩበት ጊዜ ይመገቡት የነበረው ዋነኛ ምግብ ነው። መናውን የሰጣቸው ይሖዋ ነበር። በተአምር ይገኝ የነበረው ይህ ምግብ ከሰንበት ቀን በስተቀር በየማለዳው ምድሩን ከሚያለብሰው ጠል ሥር ተጋግሮ ይገኝ ነበር። እስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዩት “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ወይም በዕብራይስጥ“ማን ሁ?” በማለት ጠይቀው ነበር። (ዘፀ 16:13-15, 35) መና በሌሎች ቦታዎች ላይ ‘የሰማይ እህል’ (መዝ 78:24)፣ ‘ከሰማይ የወረደ ምግብ’ (መዝ 105:40) እና ‘የኃያላን ምግብ’ (መዝ 78:25) ተብሎ ተጠርቷል። በተጨማሪም ኢየሱስ መናን በምሳሌያዊ መንገድ ተጠቅሞበታል።–ዮሐ 6:49, 50

  • መናፍስታዊ ድርጊት

    ሰው ከሞተ በኋላ መንፈሱ ከአካሉ ተለይቶ በሕይወት እንደሚቀጥልና በሕይወት ካሉ ሰዎች ጋር እንደሚነጋገር በማመን የሚፈጸም ድርጊት ነው። አብዛኛውን ጊዜ ይህ ድርጊት የሚፈጸመው ለመናፍስት ተጽዕኖ በተጋለጠ ሰው (አገናኝ) አማካኝነት ነው። “መናፍስታዊ ድርጊት” ተብሎ የተተረጎመው ፋርማኪያ የተባለው ግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ባለ መድኃኒት” ማለት ነው። በጥንት ዘመን ሰዎች ለመጠንቆል የሚያስችል ኃይል ለማግኘት አጋንንትን በሚለማመኑበት ጊዜ መድኃኒት ይጠቀሙ ስለነበር ይህ ቃል መናፍስታዊ ድርጊትን ለማመልከት ይሠራበት ጀመር።–ገላ 5:20ራእይ 21:8

  • መናፍስት ጠሪ

    ሙታንን የማነጋገር ችሎታ አለኝ የሚል ሰው።–ዘሌ 20:27ዘዳ 18:10-12፤ 2ነገ 21:6

  • መንገድ

    ይህ ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ያለውን ወይም የሌለውን አኗኗር ወይም ምግባር ለማመልከት በምሳሌያዊ ሁኔታ ተሠርቶበታል። የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ የሆኑ ሰዎች “የጌታን መንገድ” እንደተከተሉ ተገልጿል፤ ይህም የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል በእሱ ላይ ባላቸው እምነት ዙሪያ የሚያጠነጥን የሕይወት መንገድ መከተላቸውን ያሳያል።–ሥራ 19:9

  • መንፈስ

    ሩአህ የሚለው የዕብራይስጥ ቃልና ኒውማ የሚለው የግሪክኛ ቃል አብዛኛውን ጊዜ “መንፈስ” ተብለው የሚተረጎሙ ቢሆንም የተለያዩ ነገሮችን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። እነዚህ ቃላት በተለያየ መንገድ ቢሠራባቸውም በጥቅሉ ሲታይ በሰው ዓይን የማይታይንና በእንቅስቃሴ ላይ ያለን ኃይል ያመለክታሉ። የዕብራይስጡና የግሪክኛው ቃላት ከሚከተሉት ነገሮች ጋር በተያያዘ ተሠርቶባቸዋል፦ (1) ነፋስ፤ (2) በምድር ላይ በሚኖሩ ፍጥረታት ውስጥ ያለ የሕይወት ኃይል፤ (3) ከሰው ምሳሌያዊ ልብ የሚመነጭና ግለሰቡ የሆነ ነገር እንዲናገር ወይም እንዲያደርግ የሚገፋፋ ኃይል፤ (4) በዓይን ከማይታይ አካል የመነጨ በመንፈስ መሪነት የተነገረ ቃል፤ (5) መንፈሳዊ አካላት እና (6) የአምላክ ኃይል ወይም መንፈስ ቅዱስ።–ዘፀ 35:21መዝ 104:29፤ ማቴ 12:43፤ ሉቃስ 11:13

  • መንፈስ ቅዱስ

    አምላክ ፈቃዱን ለማስፈጸም የሚጠቀምበት በዓይን የማይታይ ኃይል ነው። ቅዱስ የተባለው፣ የዚህ መንፈስ ምንጭ እጅግ ንጹሕና ጻድቅ የሆነው ይሖዋ ስለሆነና እሱም ቅዱስ የሆኑ ነገሮችን ለማከናወን ስለሚጠቀምበት ነው።–ሉቃስ 1:35ሥራ 1:8

  • መካከለኛ

    ሁለት ወገኖችን ለማስታረቅ መካከለኛ ሆኖ የሚያገለግልን አካል ያመለክታል። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሙሴ ለሕጉ ቃል ኪዳን፣ ኢየሱስ ደግሞ ለአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆነው እንዳገለገሉ ተገልጿል።–ገላ 3:191ጢሞ 2:5

  • መኮስተሪያዎች

    ከወርቅ፣ ከብር ወይም ከመዳብ የተሠሩ ዕቃዎች ሲሆኑ በማደሪያ ድንኳኑም ሆነ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ዕጣን ለማጠን እንዲሁም ከመሠዊያው ላይ ፍም ለመውሰድና በወርቅ መቅረዙ ላይ ካሉት የመብራት ክሮች የሚረግፈውን አመድ ለማንሳት ያገለግሉ ነበር። ጥናዎች ተብለውም ይጠራሉ።–ዘፀ 37:23፤ 2ዜና 26:19፤ ዕብ 9:4

  • መውቃት፤ አውድማ

    መውቃት የሚለው ቃል እህልን ከአገዳና ከገለባ ለመለየት የሚከናወነውን ሥራ የሚያመለክት ሲሆን ሥራው የሚከናወንበት ቦታ ደግሞ አውድማ ይባላል። በዱላ በመምታት እህል መውቃት የሚቻል ከመሆኑም ሌላ እህሉ ብዙ በሚሆንበት ጊዜ በእንስሳ በሚጎተት ማሄጃ ወይም መዳመጫ ይወቃል። ገበሬዎቹ መሣሪያውን አውድማው ላይ ባለው እህል ላይ ያስኬዱታል። አውድማ አብዛኛውን ጊዜ ከፍ ያለና ለነፋስ የተጋለጠ ከመሆኑም ሌላ ክብ የሆነ ጠፍጣፋ ቦታ ነው።–ዘሌ 26:5ኢሳ 41:15፤ ማቴ 3:12

  • መዝሙር

    ለአምላክ የሚቀርብ የውዳሴ መዝሙር ነው። መዝሙራት በሙዚቃ መልክ ይቀናበሩና በይሖዋ አምላኪዎች ይዘመሩ የነበረ ሲሆን በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ለይሖዋ አምላክ በሚቀርበው አምልኮ ላይም ይዘመሩ ነበር።–ሉቃስ 20:42ሥራ 13:33፤ ያዕ 5:13

  • መያዣ

    አንድ ሰው የተበደረውን መልሶ እስኪከፍል ድረስ ለአበዳሪው እንደ ዋስትና አድርጎ የሚሰጠው ንብረት ነው። የሙሴ ሕግ ድሆችና ረዳት የሌላቸው ሰዎች በደል እንዳይደርስባቸው ለመከላከል መያዣን በተመለከተ ዝርዝር መመሪያ ይሰጣል።–ዘፀ 22:26፤ ሕዝ 18:7

  • መገኘት

    በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ባሉ አንዳንድ ጥቅሶች ላይ ይህ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በዓይን በማይታይ ሁኔታ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ በዙፋን ላይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ ባሉት በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ በንጉሣዊ ሥልጣኑ መገኘቱን ያመለክታል። የክርስቶስ መገኘት የሚለው ሐሳብ ኢየሱስ መጥቶ ወዲያውኑ እንደሚመለስ የሚያመለክት ሳይሆን የተወሰነ የጊዜ ርዝመት የሚሸፍን ክንውን ነው።–ማቴ 24:3

  • መጋረጃ

    በማደሪያ ድንኳኑም ሆነ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቅድስቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ የሚለየውንና የኪሩቦች ምስል የተጠለፈበትን ውብ ሆኖ የተሸመነ ጨርቅ ያመለክታል። (ዘፀ 26:31፤ 2ዜና 3:14ማቴ 27:51፤ ዕብ 9:3)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ን ተመልከት።

  • ሙሾ

    ሰዎች ዘመድ ወይም የሚወዱት ሰው ሲሞትባቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በግጥምና በዜማ የሚገልጹበት መንገድ ነው፤ የሐዘን እንጉርጉሮም ይባላል።–2ሳሙ 1:17፤ መዝ 7:0

  • ሙትላቤን

    በመዝሙር 9 አናት ላይ ባለው መግለጫ ውስጥ የሚገኝ የዕብራይስጥ ቃል ነው። ይህ ቃል በተለምዶ “ስለ ወንድ ልጅ ሞት” የሚል ትርጉም እንዳለው ተደርጎ ይታሰባል። አንዳንዶች ቃሉ ይህ መዝሙር በሚዘመርበት ጊዜ በመክፈቻው ላይ የሚዜምን የተለመደ ዜማ መጠሪያ ወይም የመክፈቻ ቃላት እንደሚያመለክት ይሰማቸዋል።

  • ሚልኮም

    የአሞናውያን አምላክ ሲሆን ሞሎክ ከተባለው አምላክ ጋር አንድ ሳይሆን አይቀርም። (1ነገ 11:5, 7) ሰለሞን በንግሥናው ማብቂያ ላይ ለዚህ የሐሰት አምላክ ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችን አዘጋጅቶ ነበር።–ሞሎክ የሚለውን ተመልከት።

  • ሚክታም

    በስድስት መዝሙሮች አናት ላይ ባለው መግለጫ ውስጥ የሚገኝ የዕብራይስጥ ቃል ነው። (መዝ 16:0፤ 56:0 እስከ 60:0) “የተቀረጸ ጽሑፍ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል ጋር ተዛማጅነት ያለው ሊሆን ቢችልም የቃሉ ትርጉም በእርግጠኝነት አይታወቅም።

  • ማሃላት

    በመዝሙር 53 እና 88 አናት ላይ ባለው መግለጫ ውስጥ የሚገኝ ቃል ነው። “መድከም፤ መታመም” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ግስ ጋር ተዛማጅነት ሳይኖረው አይቀርም፤ ከዚህ አንጻር ሲታይ ቃሉ የማዘንና የመከፋት ስሜት የሚንጸባረቅበትን ቅኝት ሊያመለክት ይችላል፤ ይህም በሁለቱ መዝሙሮች ላይ ከሰፈረው የሐዘን ድባብ ያጠላበት ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው።

  • ማልካም

    የአሞናውያን ዋነኛ አምላክ የሆነው የሞሎክ ሌላ መጠሪያ ሳይሆን አይቀርም። (ሶፎ 1:5)–ሞሎክ የሚለውን ተመልከት።

  • ማስኪል

    በ13 መዝሙሮች አናት ላይ ባለው መግለጫ ውስጥ የሚገኝ ትርጉሙ በእርግጠኝነት የማይታወቅ የዕብራይስጥ ቃል ነው። “ለማሰላሰል የሚረዳ ግጥም” ማለት ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች የዚህ ቃል ትርጉም፣ ተመሳሳይ የፊደል አጣጣል ካለውና ‘በማስተዋል ማገልገል’ ተብሎ ከተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተዛማጅነት እንዳለው ይሰማቸዋል።–2ዜና 30:22መዝ 32:0

  • ማቅ

    እህል ለመያዝ የሚያገለግል ጆንያ ወይም ከረጢት ለመሥራት የሚያገለግል ሻካራ ልብስ። ብዙውን ጊዜ ከጥቁር የፍየል ፀጉር የሚሠራ ሲሆን በሐዘን ወቅት ይለበስ ነበር።–ዘፍ 37:34ሉቃስ 10:13

  • ማኅበረሰብ

    ለሆነ ዓላማ አንድ ላይ የተሰበሰቡ ሰዎችን ያመለክታል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይህ ቃል አብዛኛውን ጊዜ በሃይማኖታዊ በዓላት ወቅት ወይም ብሔሩን በሚመለከቱ አበይት ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር የሚሰበሰበውን የእስራኤል ሕዝብ ለማመልከት ተሠርቶበታል።–ዘሌ 8:31ነገ 8:5

  • ማኅተም

    የንብረት ባለቤትነትን ወይም በአንድ ነገር መስማማትን አሊያም የአንድን ነገር ትክክለኛነት ለማረጋገጥ በአብዛኛው በሸክላ ወይም በሰም ላይ ቅርጽ ለማሳረፍ የሚያገለግል መሣሪያ ነው። የጥንት ማኅተሞች የሚሠሩት ከጠንካራ ነገር (ይኸውም ከድንጋይ፣ ከዝሆን ጥርስ ወይም ከእንጨት) ሲሆን በላያቸው ላይ ፊደላት ወይም ምስል ይቀረጽባቸዋል። ማኅተም ትክክለኛነቱ የተመሠከረለትን፣ የአንድ አካል ንብረት የሆነን ወይም ደግሞ የተሰወረን አሊያም ሚስጥር የሆነን ነገር ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል።–ዘፀ 28:11ነህ 9:38፤ ራእይ 5:1፤ 9:4

  • ማንአለብኝነት

    አሴልጊያ ከሚለው ግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ሲሆን የአምላክን ሕግ በመጣስ የሚፈጸምን ከባድ ኃጢአት ለማመልከት ተሠርቶበታል፤ በተጨማሪም ማንአለብኝነት ወይም እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበትን የንቀት ዝንባሌ ያመለክታል፤ ከዚህም ሌላ ለሥልጣን፣ ለሕግና ለደንብ አክብሮት አለማሳየትን አልፎ ተርፎም የንቀት መንፈስ ማንጸባረቅን ያሳያል። ይህ አገላለጽ እምብዛም ክብደት የሌለውን የሥነ ምግባር ጉድለት የሚያመለክት አይደለም።–ገላ 5:192ጴጥ 2:7

  • ማይል

    በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በኩረ ጽሑፍ ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ይኸውም በማቴዎስ 5:41 ላይ ተጠቅሶ የሚገኝ የርቀት መለኪያ ሲሆን 1,479.5 ሜትር ርዝመት ያለውን የሮማውያን ማይል የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ማግ

    በሽመና ሥራ ላይ በሸማው ወርድ በኩል ወደ ጎን የሚሸመኑትን ክሮች ያመለክታል። እነዚህ ክሮች በድሩ ላይ ከላይና ከታች የሚጠላለፉት ወይም የሚሰባጠሩት ክሮች ሲሆኑ ድሩ ደግሞ በሸማው ቁመት ልክ ከላይ ወደ ታች የሚወርዱትን ክሮች ያመለክታል።–ዘሌ 13:59

  • ሜሮዳክ

    የባቢሎን ከተማ ዋነኛ አምላክ ነው። የባቢሎናውያን ንጉሥና ሕግ አውጪ የሆነው ሃሙራቢ ባቢሎንን የባቢሎኒያ ዋና ከተማ ካደረጋት በኋላ ሜሮዳክ (ማርዱክ) ይበልጥ እየገነነ ሄደ፤ በመጨረሻም ቀደም ሲል የነበሩትን በርካታ አማልክት በመተካት የባቢሎናውያን ዋነኛ አምላክ ለመሆን በቃ። ከጊዜ በኋላ ሜሮዳክ (ማርዱክ) የሚለው ስም “ቤሉ” (ባለቤት) በተባለው የማዕረግ ስም የተተካ ሲሆን ሰዎች ሜሮዳክ ከማለት ይልቅ ቤል እያሉ ይጠሩት ነበር።–ኤር 50:2

  • ሜዶናውያን፤ ሜዶን

    ማዳይ የተባለው የያፌት ልጅ ዘሮች ናቸው፤ ተራራማ በሆነው የኢራን አምባ ላይ ይኖሩ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ይህ አካባቢ የሜዶን ምድር ተብሎ ይጠራ ጀመር። ሜዶናውያን ከባቢሎናውያን ጋር ግንባር ፈጥረው አሦርን ድል አድርገዋል። በዚያን ወቅት ፋርስ የሜዶን ግዛት የነበረች ቢሆንም ቂሮስ በማመፁ የተነሳ ሜዶንና ፋርስ ተዋህደው የሜዶ ፋርስ መንግሥት ሊቋቋም ችሏል፤ በኋላም የሜዶ ፋርስ መንግሥት በአዲስ መልክ የተቋቋመውን የባቢሎን መንግሥት በ539 ዓ.ዓ. ድል አደረገ። በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ወቅት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሰዎች መካከል ሜዶናውያን ይገኙበት ነበር። (ዳን 5:28, 31፤ ሥራ 2:9)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ9ን ተመልከት።

  • ምልክት

    አሁን ያለንም ይሁን ወደፊት የሚመጣን ነገር በመጠቆም ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ክንውን፣ ሁኔታ ወይም ያልተለመደ ክስተት ነው።–ዘፍ 9:12, 132ነገ 20:9፤ ማቴ 24:3፤ ራእይ 1:1

  • ምሥራቹ

    በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ አምላክ መንግሥትና በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ስለሚያስገኘው መዳን የሚገልጸውን ምሥራች ያመለክታል።–ሉቃስ 4:18, 43ሥራ 5:42፤ ራእይ 14:6

  • ምሥክር

    አብዛኛውን ጊዜ “ምሥክሩ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ለሙሴ በተሰጡት ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ የተጻፉትን አሥሩን ትእዛዛት ነው።–ዘፀ 31:18

  • ምርኮ

    በጦርነት ድል ከተነሳ የጠላት ወገን ተዘርፎ የሚወሰድ የግል ንብረት ወይም የቤት ዕቃ፣ ከብት አሊያም ዋጋ ያለው ማንኛውም ቁሳቁስ።–ኢያሱ 7:2122:8ዕብ 7:4

  • ምሳሌ

    ትምህርት የሚሰጥ ወይም አንድን ጥልቅ የሆነ እውነት ግልጽ የሚያደርግ ጥበብ ያዘለ አባባል አሊያም አጭር ታሪክ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ በእንቆቅልሽ መልክ የተጻፈ ሊሆን ይችላል። ምሳሌ ብዙውን ጊዜ አንድን እውነት ከሌላ ነገር ጋር በማወዳደር ገላጭ በሆኑ ቃላት ሕያው አድርጎ ይገልጻል። ሰዎች አንዳንዶቹን የተለመዱ ምሳሌዎች በሌሎች ላይ ለማፌዝ ወይም ለአንድ ነገር ያላቸውን ንቀት ለመግለጽ ይጠቀሙባቸዋል።–መክ 12:92ጴጥ 2:22

  • ምናን

    በሕዝቅኤል ትንቢት ላይ ማኔህ ተብሎም ተጠርቷል። እንደ ክብደት መለኪያም እንደ ገንዘብም ሆኖ ያገለግል ነበር። የአርኪኦሎጂ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አንድ ምናን 50 ሰቅል ሲሆን አንድ ሰቅል ደግሞ 11.4 ግራም ነው፤ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰው ምናን 570 ግራም ይመዝናል። በወቅቱ ልክ እንደ ክንድ ሁሉ በቤተ መንግሥት ውስጥ የሚሠራበት ለየት ያለ ምናን የነበረ ይመስላል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰው ምናን ደግሞ 340 ግራም ሲሆን ከ100 ድራክማ ጋር እኩል ነው። ስልሳ ምናን አንድ ታላንት ነው። (ዕዝራ 2:69፤ ሉቃስ 19:13)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ምንዝር

    አንድ ያገባ ወንድ ወይም አንዲት ያገባች ሴት የትዳር ጓደኛቸው ካልሆነ ሰው ጋር በፈቃደኝነት የሚፈጽሙት የፆታ ግንኙነት።–ዘፀ 20:14ማቴ 5:27፤ 19:9

  • ምኩራብ

    ቃሉ “አንድ ላይ መሰብሰብ፤ ጉባኤ” የሚል ትርጉም አለው፤ ይሁንና በአብዛኞቹ ጥቅሶች ላይ አይሁዳውያን ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማንበብ፣ ለመማር፣ ስብከት ለማዳመጥና ለጸሎት የሚሰበሰቡበትን ሕንፃ ወይም ቦታ ለማመልከት ተሠርቶበታል። በኢየሱስ ዘመን ብዙ ነዋሪዎች ባሉበት በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ አንድ ምኩራብ ይገኝ የነበረ ሲሆን በትላልቆቹ ከተሞች ውስጥ ደግሞ ከአንድ በላይ ምኩራቦች ይገኙ ነበር።–ሉቃስ 4:16ሥራ 13:14, 15

  • ሞሎክ

    የአሞናውያን አምላክ ሲሆን ማልካምና ሚልኮም ከተባለው አምላክ ጋር አንድ ሳይሆን አይቀርም። ለአንድ ጣዖት የተሰጠ የግል መጠሪያ ሳይሆን የማዕረግ ስም ሊሆን ይችላል። የሙሴ ሕግ ልጆቹን ለሞሎክ መሥዋዕት የሚያደርግ ማንኛውም ሰው በሞት እንዲቀጣ ያዛል።–ዘሌ 20:2ኤር 32:35፤ ሥራ 7:43

  • ሠረገላ

    በዋነኝነት ለጦርነት የሚያገለግል በፈረስ የሚጎተት ባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪ።–ዘፀ 14:23መሳ 4:13፤ ሥራ 8:28

  • ሥርዓት

    አዮን የሚለው የግሪክኛ ቃል አንድን ወቅት፣ ጊዜ ወይም ዘመን ለይተው የሚያሳውቁ ወቅታዊ ጉዳዮችን አሊያም ሁኔታዎችን ለማመልከት በሚሠራበት ጊዜ ሥርዓት ተብሎ ይተረጎማል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአሁኑ ጊዜ ያለው ሥርዓት’ ሲል በመላው ዓለም የሰፈነውን ሁኔታና ዓለማዊ አኗኗር ማመልከቱ ነው። (2ጢሞ 4:10) አምላክ የሕጉን ቃል ኪዳን በሰጠ ጊዜ አንዳንዶች የእስራኤላውያን ወይም የአይሁዳውያን ዘመን ብለው የሚጠሩትን ሥርዓት አቋቁሟል። በተጨማሪም አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት በዋነኝነት የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ጉባኤ ያቀፈ አንድ ልዩ ሥርዓት አቋቁሟል። ይህም የሕጉ ቃል ኪዳን ጥላ የሆነላቸው እውነታዎች የተፈጸሙበት አዲስ ዘመን መጥባቱን አመላክቷል። ቃሉ በብዙ ቁጥር ሲሠራበት ከዚህ ቀደም የነበሩ ወይም ወደፊት የሚመጡ የተለያዩ ሥርዓቶችን ወይም ነባራዊ ሁኔታዎችን ያመለክታል።–ማቴ 24:3ማር 4:19፤ ሮም 12:2፤ 1ቆሮ 10:11

  • ረዓብ

    በኢዮብ፣ በመዝሙርና በኢሳይያስ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኝ ምሳሌያዊ መግለጫ ነው። ይህ ቃል በኢያሱ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰችውን ረዓብን የሚያመለክት አይደለም። በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው ረዓብ አንድን ግዙፍ የባሕር ፍጡር እንደሚያመለክት በዙሪያው ካለው ሐሳብ መረዳት ይቻላል፤ በሌሎች ቦታዎች ላይ ደግሞ ይህ ግዙፍ የባሕር ፍጡር ግብፅን ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል።–ኢዮብ 9:13መዝ 87:4፤ ኢሳ 30:7፤ 51:9, 10

  • ርኩስ

    ቃሉ በአካላዊ ሁኔታ መቆሸሽን ወይም የሥነ ምግባር ሕግ መጣስን ሊያመለክት ይችላል። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃሉ አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው ከሙሴ ሕግ አንጻር ተቀባይነት የሌለውን ወይም ንጹሕ ያልሆነን ነገር ነው። (ዘሌ 5:2፤ 13:45፤ ማቴ 10:1፤ ሥራ 10:14፤ ኤፌ 5:5)–ንጹሕ የሚለውን ተመልከት።

  • ሮማን

    ፖም የሚመስል ፍሬ ሲሆን ጫፉ ላይ ዘውድ የመሰለ ነገር አለው። ጠንካራ በሆነው ቅርፊት ውስጥ በፈሳሽ የተሞሉ ትናንሽ የዘር ከረጢቶች ይገኛሉ፤ በእያንዳንዱ ከረጢት ውስጥ ደግሞ ሐምራዊ ወይም ቀይ ቀለም ያላቸው ትናንሽ ዘሮች አሉ። ሊቀ ካህናቱ የሚለብሰው እጅጌ የሌለው ሰማያዊ ቀሚስ ዘርፍ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ መግቢያ ላይ የሚገኙት ያኪን እና ቦዔዝ የሚባሉት ዓምዶች ራስ በሮማን ቅርጽ በተሠሩ ጌጦች ያጌጡ ነበሩ።–ዘፀ 28:34ዘኁ 13:23፤ 1ነገ 7:18

  • ሰማርያ

    አሥሩን ነገዶች ያቀፈው የሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ ሆና ለ200 ዓመታት ገደማ ያገለገለች ሲሆን ክልሉ በአጠቃላይ በዚህ ስም ይጠራ ነበር። ከተማዋ የተቆረቆረችው በሰማርያ ተራራ ላይ ነበር። በኢየሱስ ዘመን ሰማርያ፣ በስተ ሰሜን በሚገኘው በገሊላና በስተ ደቡብ ባለው በይሁዳ መካከል የሚገኝ የአንድ አውራጃ ስም ነበር። ኢየሱስ ባደረጋቸው ጉዞዎች በአብዛኛው በዚህ ክልል ከመስበክ የተቆጠበ ቢሆንም አልፎ አልፎ ይህን አውራጃ አቋርጦ ሲያልፍ ነዋሪዎቹን ያነጋገረባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሳምራውያን መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉበት ወቅት ጴጥሮስ ሁለተኛውን ምሳሌያዊ የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ተጠቅሞበታል። (1ነገ 16:24፤ ዮሐ 4:7፤ ሥራ 8:14)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ10ን ተመልከት።

  • ሰቅል

    እንደ ክብደት መመዘኛም እንደ ገንዘብም ሆኖ የሚያገለግል ዕብራውያን የሚጠቀሙበት ዋነኛ መለኪያ ነበር። ክብደቱ 11.4 ግራም ነው። ‘የቅዱሱ ስፍራ ሰቅል’ የሚለው አነጋገር፣ የሚለካው ነገር ክብደት ትክክል መሆን እንዳለበት ወይም በማደሪያ ድንኳኑ ከሚገኘው መደበኛ ሚዛን ጋር እኩል ሊሆን እንደሚገባው አጽንኦት ለመስጠት የገባ አገላለጽ ሊሆን ይችላል። በዚያ ዘመን በቤተ መንግሥት ውስጥ የሚሠራበት ወይም በዚያ የሚቀመጥ ከተለመደው ሰቅል የተለየ ሰቅል ሳይኖር አይቀርም።–ዘፀ 30:13

  • ሰንበት

    “ማረፍ፤ ማቆም” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ ነው። በአይሁዳውያን ሳምንት ሰባተኛውን ቀን (ዓርብ ፀሐይ ከጠለቀችበት ጊዜ አንስቶ ቅዳሜ ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ) ያመለክታል። ሰባተኛውንና ሃምሳኛውን ዓመት ጨምሮ ሌሎቹ ዓመታዊ በዓላትም ሰንበት ተብለው ይጠሩ ነበር። በሰንበት ቀን በማደሪያው ድንኳን ከሚከናወነው የክህነት አገልግሎት በስተቀር ምንም ሥራ መሥራት አይፈቀድም ነበር። በሰንበት ዓመት መሬቱ ሳይታረስ ይተው የነበረ ሲሆን ዕዳ ያለባቸው ዕብራውያንም ዕዳቸው ይሰረዝላቸው ነበር። በሙሴ ሕግ ውስጥ የሰፈሩት ከሰንበት ጋር በተያያዘ የተጣሉት እገዳዎች ምክንያታዊ ነበሩ፤ ይሁንና የሃይማኖት መሪዎች ቀስ በቀስ በርካታ ሕጎችን ስለጨመሩባቸው በኢየሱስ ዘመን፣ ሰዎች ሰንበትን ማክበር ከባድ ሸክም ሆኖባቸው ነበር።–ዘፀ 20:8ዘሌ 25:4፤ ሉቃስ 13:14-16፤ ቆላ 2:16

  • ሰይጣን

    “ተቃዋሚ” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች በዚህ ስም ላይ ጠቃሽ አመልካች ከተጨመረ ስሙ የሚያመለክተው የአምላክ ቀንደኛ ጠላት የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን ነው።–ኢዮብ 1:6ማቴ 4:10፤ ራእይ 12:9

  • ሰዱቃውያን

    ሀብታም ባላባቶችንና ካህናትን ያቀፈው የአይሁድ ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት ሲሆኑ በቤተ መቅደሱ ከሚከናወነው ነገር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሥልጣን ነበራቸው። ፈሪሳውያን ይጠብቋቸው የነበሩትን በርካታ የቃል ወጎች ጨምሮ የፈሪሳውያንን እምነት አይቀበሉም ነበር። በትንሣኤም ሆነ በመላእክት መኖር አያምኑም። ኢየሱስንም ተቃውመውታል።–ማቴ 16:1ሥራ 23:8

  • ሱራፌል

    በሰማይ በይሖዋ ዙፋን ዙሪያ የሚቆሙ መንፈሳዊ ፍጥረታት ናቸው። ሴራፊም የሚለው የዕብራይስጥ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “የሚንበለበሉ” የሚል ፍቺ አለው።–ኢሳ 6:26

  • ሲህ

    የደረቅ ነገር መለኪያ ነው። ከዚህ መለኪያ ጋር በሚመጣጠነውና የፈሳሽ ነገር መለኪያ በሆነው በባዶስ መስፈሪያ መሠረት ሲሰላ 7.33 ሊትር ይሆናል። (2ነገ 7:1)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ሲኦል

    “ሐዲስ” ከሚለው ግሪክኛ ቃል ጋር አቻ የሆነ የዕብራይስጥ ቃል ነው።–ዘፍ 37:35መዝ 16:10ሥራ 2:31 (የግርጌ ማስታወሻዎች)

  • ሲዋን

    አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ ለሦስተኛው ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ለዘጠነኛው ወር የተሰጠ ስም ነው። ከግንቦት አጋማሽ አንስቶ እስከ ሰኔ አጋማሽ ያለውን ጊዜ ያመለክታል። (አስ 8:9)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • ሳምራውያን

    መጀመሪያ ላይ ይህ ቃል አሥሩን ነገዶች ባቀፈው ሰሜናዊ መንግሥት ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን እስራኤላውያን ያመለክት ነበር፤ ሆኖም በ740 ዓ.ዓ. ሰማርያ በአሦራውያን ድል ከተመታች በኋላ አሦራውያን ወደ ስፍራው ያፈለሷቸውን የባዕድ አገር ሰዎችም ለማመልከት ተሠርቶበታል። በኢየሱስ ዘመን ደግሞ ይህ ቃል ከዘር ወይም ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ መሆኑ ቀርቶ በጥንቷ ሴኬምና ሰማርያ አቅራቢያ ይገኝ የነበረውን ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት ለማመልከት ይሠራበት ነበር። የዚህ ቡድን አባላት ከአይሁድ እምነት ፈጽሞ የተለዩ አንዳንድ ሃይማኖታዊ አመለካከቶች ነበሯቸው።–ዮሐ 8:48

  • ሳንሄድሪን

    በኢየሩሳሌም ይገኝ የነበረ የአይሁዳውያን ከፍተኛ ሸንጎ ነው። በኢየሱስ ዘመን ይህ ሸንጎ ሊቀ ካህናቱን፣ የሊቀ ክህነት ሥልጣን የነበራቸውን ሌሎች ሰዎች፣ የሊቀ ካህናት ቤተሰብ አባላትን፣ ሽማግሌዎችን፣ የነገድና የቤተሰብ ራሶችን እንዲሁም ጸሐፍትን ጨምሮ 71 አባላት ነበሩት።–ማር 15:1ሥራ 5:34፤ 23:1, 6

  • ሴላ

    በመዝሙርና በዕንባቆም መጻሕፍት ውስጥ የሚገኝ ከሙዚቃ ወይም ከተሸመደደ ምንባብ ጋር በተያያዘ የሚሠራበት የዕብራይስጥ ቃል ነው። መዝሙር በሚዘመርበት ወቅት በጸጥታ ለማሰላሰል ወይም በመዝሙሩ ውስጥ የሚንጸባረቀው ስሜት ጎልቶ እንዲወጣ ለማድረግ ትንሽ ቆም የሚባልበትን ጊዜ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። የግሪክኛው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ዲያሳልማ ብሎ የተረጎመው ሲሆን ቃሉ “መሸጋገሪያ ሙዚቃ” የሚል ፍቺ አለው።–መዝ 3:4ዕን 3:3

  • ስርቲስ

    በሰሜን አፍሪካ፣ በሊቢያ የባሕር ዳርቻ የሚገኙ ጥልቀት የሌላቸው ሁለት ሰፋፊ ባሕረ ሰላጤዎች። የባሕር ሞገድ የአሸዋ ቁልሎቹን በየጊዜው ከቦታ ቦታ ያንቀሳቅሳቸው ስለነበር በጥንት ዘመን የነበሩ መርከበኞች ከአሸዋ ቁልል ጋር እንዳይላተሙ ስጋት ያድርባቸው ነበር። (ሥራ 27:17)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ13ን ተመልከት።

  • ስርየት

    ይህ ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሰዎች ወደ አምላክ ለመቅረብና ለእሱ አምልኮ ለማቅረብ ከሚሠዉአቸው መሥዋዕቶች ጋር በተያያዘ ተሠርቶበታል። በሙሴ ሕግ፣ ግለሰቦችም ሆኑ መላው ብሔር ኃጢአተኞች ቢሆኑም እንኳ ከአምላክ ጋር እርቅ መፍጠር እንዲችሉ በተለይ በዓመታዊው የስርየት ቀን መሥዋዕቶች ይቀርቡ ነበር። እነዚህ መሥዋዕቶች ኢየሱስ ለከፈለው መሥዋዕት ጥላ ነበሩ። የኢየሱስ መሥዋዕት የሰው ልጆችን ኃጢአት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ፣ ሙሉ በሙሉ በማስተሰረይ ሰዎች ከይሖዋ ጋር መታረቅ የሚችሉበትን አጋጣሚ ከፍቷል።–ዘሌ 5:1023:28ቆላ 1:20፤ ዕብ 9:12

  • ስንዝር

    የእጅ ጣቶች በሚዘረጉበት ጊዜ ከአውራ ጣት ጫፍ እስከ ትንሿ ጣት ጫፍ ድረስ ያለውን ርዝመት የሚያመለክት መለኪያ ነው። ወደ 44.5 ሴንቲ ሜትር የሚጠጋ ርዝመት ካለው ክንድ አንጻር ሲታይ አንድ ስንዝር 22.2 ሴንቲ ሜትር ይሆናል። (ዘፀ 28:16፤ 1ሳሙ 17:4)– ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ስእለት

    አንድ ነገር ለማድረግ፣ መባ ወይም ስጦታ ለመስጠት፣ አንድ ዓይነት አገልግሎት ለማከናወን ወይም ሕጉ የሚከለክላቸው ባይሆኑም ከአንዳንድ ነገሮች ለመታቀብ ለአምላክ ቃል መግባት። ስእለት የመሐላን ያህል ክብደት አለው።–ዘኁ 6:2መክ 5:4፤ ማቴ 5:33

  • ሶርያ፤ ሶርያውያን

    አራም፤ አራማውያን የሚለውን ተመልከት።

  • ሸሚኒት

    ቃል በቃል ሲተረጎም “ስምንተኛው” የሚል ፍቺ ያለው ከሙዚቃ ጋር የተያያዘ ቃል ሲሆን ወፈር ያለ ድምፅን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ከሙዚቃ መሣሪያ ጋር በተያያዘ ቃሉ ወፈር ያለ ድምፅ የሚያወጡ ኖታዎችን ሊያመለክት ይችላል። ከመዝሙር ጋር በተያያዘ ደግሞ ወፈር ባለ የሙዚቃ ድምፅ የሚታጀብንና የሚዘመርን መዝሙር ሳያመለክት አይቀርም።–1ዜና 15:21መዝ 6:0፤ 12:0

  • ሸምበቆ፤ መቃ

    ረግረጋማ በሆኑ ቦታዎች የሚበቅሉ የተለያየ ዝርያ ያላቸውን ዕፀዋት ለማመልከት የገባ ቃል ነው። ቃሉ በብዙ ቦታዎች ላይ የተሠራበት አሩንዶ ዶናክስ የተባለውን ተክል ለማመልከት ነው።–ኢዮብ 8:11ኢሳ 42:3፤ ማቴ 27:29፤ ራእይ 11:1

  • ሸክላ ሠሪ

    እንደ ማሰሮና ድስት ያሉ የሸክላ ዕቃዎችን የሚሠራ ሰው። ሸክላ ሠሪ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “ቅርጽ አውጪ” የሚል ፍቺ አለው። ይሖዋ በግለሰቦችም ሆነ በብሔራት ላይ ከፍተኛ ሥልጣን እንዳለው ለማመልከት ሸክላ ሠሪ በጭቃው ላይ ያለው ሥልጣን ብዙ ጊዜ ምሳሌ ሆኖ ተጠቅሷል።–ኢሳ 64:8ሮም 9:21

  • ሺባት

    አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ ለ11ኛው ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ለ5ኛው ወር የተሰጠ ስም ነው። ከጥር አጋማሽ አንስቶ እስከ የካቲት አጋማሽ ያለውን ጊዜ ያመለክታል። (ዘካ 1:7)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • ሽመና

    እንደ መን እና መወርወሪያ የመሳሰሉትን የሽመና ዕቃዎች ተጠቅሞ ልብስ መሥራት።–ዘፀ 39:27

  • ሽማግሌ

    በዕድሜ ጠና ያለን ሰው የሚያመለክት ሲሆን በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በአንድ ማኅበረሰብ ወይም ብሔር ውስጥ ኃላፊነት የተሰጠውን ሰው ለማመልከት ተሠርቶበታል። ከዚህም በተጨማሪ ቃሉ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱትን በሰማይ ያሉ ፍጥረታት ለማመልከት አገልግሏል። ፕሪስባይቴሮስ የተባለው ግሪክኛ ቃል ጉባኤውን የመምራት ኃላፊነት የተጣለባቸውን ወንዶች በሚያመለክትበት ጊዜ “ሽማግሌ” ተብሎ ተተርጉሟል።–ዘፀ 4:29ምሳሌ 31:23፤ 1ጢሞ 5:17፤ ራእይ 4:4

  • ቀንበር

    አንድ ሰው በትከሻው ላይ የሚያስቀምጠው ቀጥ ያለ እንጨት ነው፤ በግራና በቀኝ በኩል ደግሞ ሸክም ይንጠለጠልበታል። በተጨማሪም ሁለት ከብቶች ሞፈር ወይም ጋሪ በሚጎትቱበት ጊዜ አንገታቸው ላይ የሚገባን ወይም የሚታሰርንና ትከሻቸው ላይ የሚያርፍን እንጨት ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ ባሪያዎች ከባድ ሸክም ለመሸከም ቀንበር ይጠቀሙ ስለነበር ይህ ቃል ባርነትን ወይም ለሌላ ሰው መገዛትን እንዲሁም ጭቆናንና መከራን ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል። ከጫንቃ ላይ ቀንበርን ማንሳት ወይም መስበር ከባርነት፣ ከጭቆናና ከብዝበዛ ነፃ መውጣትን ያመለክታል።–ዘሌ 26:13ማቴ 11:29, 30

  • ቀንድ

    ለመጠጫነት እንዲሁም ለዘይት፣ ለቀለምና ለተለያዩ መዋቢያዎች ማስቀመጫነት ብሎም ሙዚቃ ለመጫወትም ሆነ አንድ ዓይነት መልእክት ለማስተላለፍ ያገለግል የነበረውን የእንስሳት ቀንድ ያመለክታል። (1ሳሙ 16:1, 13፤ 1ነገ 1:39፤ ሕዝ 9:2) ብዙውን ጊዜ “ቀንድ” ጥንካሬንና ድል አድራጊነትን ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል።–ዘዳ 33:17ሚክ 4:13፤ ዘካ 1:19

  • ቁባት

    የአንድን ሰው ሁለተኛ ሚስት የሚያመለክት ቃል ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ይህች ሴት ባሪያ የነበረች ልትሆን ትችላለች።–ዘፀ 21:82ሳሙ 5:13፤ 1ነገ 11:3

  • ቂጣ

    እርሾ ሳይገባበት ከዱቄት የሚጋገር ምግብ።–ዘዳ 16:3ማር 14:12፤ 1ቆሮ 5:8

  • ቃል ኪዳን

    አንድን ነገር ለመሥራት አሊያም ከአንድ ነገር ለመታቀብ በአምላክና በሰዎች ወይም በሰዎችና በሰዎች መካከል የሚፈጸም ስምምነት ወይም ውል ነው። አንዳንድ ጊዜ ግዴታ ውስጥ የሚገባው አንዱ ወገን ብቻ ሊሆን ይችላል። (ይህ የአንድ ወገን ቃል ኪዳን ነው፤ አንደኛው ወገን ብቻ ቃል መግባቱን ያመለክታል።) በሌላ ጊዜ ደግሞ ግዴታ ውስጥ የሚገቡት ሁለቱም ወገኖች ይሆናሉ። (ይህ የሁለት ወገን ቃል ኪዳን ይባላል።) መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክና በሰዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በሰዎች፣ በጎሳዎች፣ በብሔራት ወይም በሁለት ቡድኖች መካከል ስለተገቡ ቃል ኪዳኖች ይናገራል። ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ቃል ኪዳኖች መካከል አምላክ ከአብርሃም፣ ከዳዊት፣ ከእስራኤል ብሔር (የሕጉ ቃል ኪዳን) እና ከአምላክ እስራኤል (አዲሱ ቃል ኪዳን) ጋር የተጋባቸው ቃል ኪዳኖች ይገኙበታል።–ዘፍ 9:1115:1821:27ዘፀ 24:7፤ 2ዜና 21:7

  • ቃብ

    የባዶስ መለኪያን መሠረት በማድረግ ሲሰላ 1.22 ሊትር የሚይዝ የደረቅ ነገር መስፈሪያ ነው። (2ነገ 6:25)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ቄሳር

    ከጊዜ በኋላ የሮማውያን ነገሥታት የማዕረግ ስም ለመሆን የበቃ የአንድ ሮማዊ ቤተሰብ መጠሪያ ነው። አውግስጦስ፣ ጢባርዮስ እና ቀላውዴዎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስም ተጠቅሰዋል፤ ኔሮ በስም ባይጠቀስም ይህ የማዕረግ ስም ለእሱም ያገለግላል። በተጨማሪም “ቄሳር” የሚለው ስያሜ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ወይም የአገሪቱን መንግሥት ለማመልከት ተሠርቶበታል።–ማር 12:17ሥራ 25:12

  • ቅዱሳን መጻሕፍት

    የአምላክን ቃል የያዙ ቅዱስ የሆኑ መጻሕፍትን ያመለክታል። ይህ አገላለጽ የሚገኘው በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብቻ ነው።–ሉቃስ 24:272ጢሞ 3:16

  • ቅዱስ ሚስጥር

    የዚህ ሚስጥር ምንጭ አምላክ ሲሆን የአምላክ ዓላማ አንዱ ገጽታ ነው፤ አምላክ ሚስጥሩን የሚገልጠው በራሱ ጊዜና ሊገልጥላቸው ለፈለገው ሰዎች ብቻ ነው።–ማር 4:11ቆላ 1:26

  • ቅዱስ፤ ቅድስና

    ከይሖዋ ባሕርያት አንዱ ሲሆን ፍጹም የሆነ የሥነ ምግባር ንጽሕናን ያመለክታል። (ዘፀ 28:36፤ 1ሳሙ 2:2፤ ምሳሌ 9:10፤ ኢሳ 6:3) የዕብራይስጡ ቃል ከሰዎች (ዘፀ 19:6፤ 2ነገ 4:9)፣ ከእንስሳት (ዘኁ 18:17)፣ ከተለያዩ ነገሮች (ዘፀ 28:38፤ 30:25፤ ዘሌ 27:14)፣ ከቦታዎች (ዘፀ 3:5፤ ኢሳ 27:13)፣ ከጊዜያት (ዘፀ 16:23፤ ዘሌ 25:12) እና ከተለያዩ ሥራዎች (ዘፀ 36:4) ጋር በተያያዘ ሲሠራበት ቅዱስ ለሆነው አምላክ መለየትን ወይም መቀደስን እንዲሁም ለይሖዋ አገልግሎት ብቻ እንዲውል መደረግን ያመለክታል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥም “ቅዱስ” እና “ቅድስና” ተብለው የተተረጎሙት ቃላት ለአምላክ የተለዩ መሆንን ያመለክታሉ። በተጨማሪም እነዚህ ቃላት የአንድን ሰው ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል።–ማር 6:202ቆሮ 7:1፤ 1ጴጥ 1:15, 16

  • ቅዱስ አገልግሎት

    አንድ ሰው ለአምላክ ከሚያቀርበው አምልኮ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ቅዱስ የሆነ አገልግሎት ወይም ሥራ ነው።–ሮም 12:1ራእይ 7:15

  • ቅድስተ ቅዱሳን

    በማደሪያ ድንኳኑም ሆነ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይገኝ የነበረ የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚቀመጥበት ውስጠኛ ክፍል ነው። በሙሴ ሕግ መሠረት ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ እንዲገባ የሚፈቀድለት ሊቀ ካህናቱ ብቻ ሲሆን እሱም ወደዚያ መግባት የሚችለው በዓመታዊው የስርየት ቀን ብቻ ነበር።–ዘፀ 26:33ዘሌ 16:2, 17፤ 1ነገ 6:16፤ ዕብ 9:3

  • ቅድስቱ

    በማደሪያ ድንኳኑ ወይም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከውስጠኛው ክፍል ይኸውም ከቅድስተ ቅዱሳኑ በፊት የሚገኘውን ሰፊ ክፍል ያመለክታል። በማደሪያ ድንኳኑ ቅድስት ውስጥ የወርቅ መቅረዝ፣ የወርቅ የዕጣን መሠዊያ፣ ገጸ ኅብስት የሚቀመጥበት ጠረጴዛና ሌሎች የወርቅ ዕቃዎች ይገኙ ነበር፤ በቤተ መቅደሱ ቅድስትም ውስጥ የወርቅ መሠዊያ፣ አሥር የወርቅ መቅረዞችና ገጸ ኅብስት የሚቀመጥባቸው አሥር ጠረጴዛዎች ይገኙ ነበር። (ዘፀ 26:33፤ ዕብ 9:2)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ን እና ለ8ን ተመልከት።

  • ቆሮስ

    የደረቅና የፈሳሽ ነገሮች መለኪያ ሲሆን የባዶስ መለኪያን መሠረት በማድረግ ሲሰላ አንድ ቆሮስ 220 ሊትር ነው። (1ነገ 5:11)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • በትረ መንግሥት

    አንድ ገዢ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ለማሳየት በእጁ የሚይዘውን ዘንግ ወይም በትር ያመለክታል።–ዘፍ 49:10ዕብ 1:8

  • በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት

    –ገጸ ኅብስት የሚለውን ተመልከት።

  • በኩር

    ቃሉ በዋነኝነት የሚያመለክተው የአንዲትን እናት የመጀመሪያ ወንድ ልጅ ሳይሆን የአንድን አባት የመጀመሪያ ወንድ ልጅ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የበኩር ልጅ በቤተሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን አባትየው በሚሞትበት ጊዜ የቤቱን የራስነት ሥልጣን የሚረከበው እሱ ነው። በተጨማሪም ይህ ቃል አንድ እንስሳ መጀመሪያ የሚወልደውን ተባዕት ግልገል ለማመልከት ተሠርቶበታል።–ዘፀ 11:513:12ዘፍ 25:33፤ ቆላ 1:15

  • ቡል

    በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ ስምንተኛው ወር ሲሆን በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ሁለተኛው ወር ነው። ስያሜው “ምርት፤ ፍሬ” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ካለው ቃል የተገኘ ነው፤ ይህ ወር ከጥቅምት አጋማሽ አንስቶ እስከ ኅዳር አጋማሽ ያለውን ጊዜ ያመለክታል። (1ነገ 6:38)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • ባለ ራእይ

    አምላክ፣ መለኮታዊውን ፈቃድ እንዲያስተውል ዓይኑን የከፈተለትን ወይም ሌሎች ሰዎች ሊረዱት ያልቻሉትን ነገር የገለጠለትን ሰው ያመለክታል። የዕብራይስጡ ቃል በምሳሌያዊ መንገድም ይሁን ቃል በቃል “ማየት” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ካለው ቃል የተወሰደ ነው። ሰዎች ችግር ሲያጋጥማቸው ጥበብ ያለበት ምክር ለማግኘት ወደ ባለ ራእይ ይሄዱ ነበር።–1ሳሙ 9:9

  • ባአል

    የሰማይ ባለቤት እንዲሁም ዝናብ የሚያዘንብና ምድሪቱን ልምላሜ የሚያላብስ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰብ የከነአናውያን አምላክ ነው። “ባአል” የሚለው መጠሪያ በአካባቢው ያሉ ሌሎች አነስተኛ አማልክትንም ለማመልከት ያገለግል ነበር። የዕብራይስጡ ቃል “ባለቤት፤ ጌታ” የሚል ትርጉም አለው።–1ነገ 18:21ሮም 11:4

  • ባዶስ

    ይህ ስም የተጻፈባቸው በአርኪኦሎጂ የተገኙ የማሰሮ ስብርባሪዎች እንደሚጠቁሙት 22 ሊትር ገደማ የሚይዝ የፈሳሽ መለኪያ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት አብዛኞቹ የደረቅና የፈሳሽ መለኪያዎች የሚሰሉት የባዶስ መለኪያን መሠረት በማድረግ ነው። (1ነገ 7:38፤ ሕዝ 45:14)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ቤተ መቅደስ

    ከቦታ ወደ ቦታ ይጓጓዝ የነበረውን የማደሪያ ድንኳን በመተካት የእስራኤላውያን የአምልኮ ማዕከል ሆኖ ያገለገለ በኢየሩሳሌም የተገነባ ሕንፃ። የመጀመሪያውን ቤተ መቅደስ የገነባው ሰለሞን ነበር፤ ሆኖም ባቢሎናውያን ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሰውታል። አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ ሁለተኛውን ቤተ መቅደስ የገነባው ዘሩባቤል ሲሆን ከጊዜ በኋላ ታላቁ ሄሮድስ መልሶ ገንብቶታል። አብዛኛውን ጊዜ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ቤተ መቅደሱ፣ ‘የይሖዋ ቤት’ ተብሎ ተጠርቷል። (ዕዝራ 1:3፤ 6:14, 15፤ 1ዜና 29:1፤ 2ዜና 2:4ማቴ 24:1)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ8ንና ለ11ን ተመልከት።

  • ቤዛ

    ከእስር፣ ከቅጣት፣ ከሥቃይ፣ ከኃጢአት ወይም ከአንድ ዓይነት ግዴታ ነፃ ለማውጣት ሲባል የሚከፈልን ዋጋ ያመለክታል። የሚከፈለው ዋጋ ገንዘብ ብቻ ነው ማለት አይደለም። (ኢሳ 43:3) ቤዛ መክፈልን የሚጠይቁ የተለያዩ ሁኔታዎች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል የእስራኤላውያን የበኩር ወንዶች ልጆችና ተባዕት የሆኑ የእንስሶቻቸው በኩሮች በሙሉ ለይሖዋ የተሰጡ ስለነበሩ ለእሱ አገልግሎት ብቻ መዋል ነበረባቸው፤ በመሆኑም ከዚህ ነፃ እንዲሆኑ ከተፈለገ ቤዛ ሊከፈልላቸው ይገባ ነበር። (ዘኁ 3:45, 46፤ 18:15, 16) አንድ ሰው የመዋጋት አመል ያለውን በሬውን ሳይጠብቀው ቀርቶ በሬው ሰው ቢገድል ባለቤቱ ከሚደርስበት የሞት ቅጣት ሕይወቱን ለመታደግ ቤዛ እንዲከፍል ይጠየቅ ነበር። (ዘፀ 21:29, 30) ሆኖም አንድ ሰው ሆነ ብሎ የሰው ሕይወት ቢያጠፋ ቤዛ በመክፈል ሕይወቱን ማዳን አይችልም። (ዘኁ 35:31) መጽሐፍ ቅዱስ በዋነኝነት የሚናገረው ክርስቶስ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ሲል መሥዋዕታዊ ሞት በመሞት ስለከፈለው ቤዛ ነው።–መዝ 49:7, 8ማቴ 20:28፤ ኤፌ 1:7

  • ብራና

    ከበግ፣ ከፍየል ወይም ከጥጃ ቆዳ የሚሠራ ለመጻፊያነት የሚያገለግል ነገር ነው። ከደንገል ከተሠራ ወረቀት ይልቅ ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽ መቆየት የሚችል ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅልሎችን ለማዘጋጀት አገልግሏል። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን እንዲያመጣለት የጠየቀው ብራናዎች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት መካከል የተወሰነውን ክፍል የያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ከሙት ባሕር ጥቅልሎች መካከል አንዳንዶቹ በብራና ላይ የተጻፉ ናቸው።–2ጢሞ 4:13

  • ብርጉድ

    ከቀረፋ ዛፍ ጋር የሚዛመድ ከብርጉድ የዛፍ ቅርፊት (ኪናሞሙም ካስያ) የሚገኝ ቅመም ነው። ብርጉድ ለሽቶነትና ቅዱሱን የቅብዓት ዘይት ለመቀመም ያገለግል ነበር።–ዘፀ 30:24መዝ 45:8፤ ሕዝ 27:19

  • ብዔልዜቡል

    የአጋንንት አለቃ ወይም ገዢ ለሆነው ለሰይጣን የተሰጠ ስያሜ ነው። ፍልስጤማውያን በኤቅሮን ያመልኩት የነበረው ባአል የተባለው አምላክ ይኸውም የባአልዜቡብ ትንሽ ለወጥ ያለ አጠራር ሊሆን ይችላል።–2ነገ 1:3ማቴ 12:24

  • ተራፊም

    የቤተሰብ አማልክት ወይም ጣዖታት። አንዳንድ ጊዜም ለመጠንቆል ይጠቀሙባቸው ነበር። (ሕዝ 21:21) አንዳንዶቹ በሰው ቁመትና ቅርጽ ይሠሩ የነበረ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ትናንሽ ነበሩ። (ዘፍ 31:34፤ 1ሳሙ 19:13, 16) በሜሶጶጣሚያ በአርኪኦሎጂ የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የተራፊም ምስሎች ባለቤት የሆነ ሰው የቤተሰቡን ንብረት የመውረስ አጋጣሚው ሰፊ ነበር። (ራሔል የአባቷን ተራፊም የወሰደችው ለዚህ ሊሆን ይችላል።) በእስራኤል ግን እንዲህ ያለ ሁኔታ የነበረ አይመስልም፤ ይሁንና በመሳፍንትም ሆነ በነገሥታት ዘመን ተራፊምን ለጣዖት አምልኮ ይጠቀሙበት ነበር። ታማኙ ንጉሥ ኢዮስያስ ካስወገዳቸው ነገሮች መካከል የተራፊም ቅርጻ ቅርጾች ይገኙበታል።–መሳ 17:52ነገ 23:24፤ ሆሴዕ 3:4

  • ተአምራት

    ከሰው በላይ በሆነ ኃይል የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ወይም ክስተቶችን ያመለክታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ምልክቶች” እና “ድንቅ ነገሮች” የሚሉት አገላለጾች አልፎ አልፎ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ተሠርቶባቸዋል።–ዘፀ 4:21ሥራ 4:22፤ ዕብ 2:4

  • ቲሽሪ

    ኤታኒም የሚለውንና ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • ታላቁ መከራ

    “መከራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከሚፈጥሩት ውጥረት የተነሳ በጭንቀት መዋጥን ያመለክታል። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ውስጥ ስለሚከሰተው በተለይ ደግሞ ‘በክብር በሚመጣበት’ ጊዜ በሰው ዘር ሁሉ ላይ ስለሚደርሰው ታይቶ የማይታወቅ “ታላቅ መከራ” ተናግሮ ነበር። (ማቴ 24:21, 29-31) ጳውሎስ ይህን መከራ፣ አምላክ እሱን “በማያውቁትና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች በማይታዘዙት ላይ” የሚወስደው የጽድቅ እርምጃ እንደሆነ አድርጎ ገልጾታል። ራእይ ምዕራፍ 19 ኢየሱስ ‘በአውሬው፣ በምድር ነገሥታትና በሠራዊታቸው’ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሰማይ ሠራዊትን እየመራ እንደሚመጣ ይናገራል። (2ተሰ 1:6-8፤ ራእይ 19:11-21) ከዚህ መከራ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እንደሚተርፍ ተገልጿል። (ራእይ 7:9, 14)–አርማጌዶን የሚለውን ተመልከት።

  • ታላንት

    ዕብራውያን ይጠቀሙበት የነበረ የመጨረሻው ከፍተኛ የክብደት መለኪያና ገንዘብ ነበር። አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። የግሪክ ታላንት መጠኑ አነስ ያለ ሲሆን 20.4 ኪሎ ግራም ይመዝን ነበር። (1ዜና 22:14፤ ማቴ 18:24)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ታሙዝ

    (1) በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ከሃዲ ዕብራውያን ሴቶች ያለቀሱለት ጣዖት ስም ነው። ታሙዝ ከሞተ በኋላ እንደ አምላክ መታየት የጀመረ ንጉሥ እንደነበር ይነገራል። በሱሜሪያ ጽሑፍ ላይ ዱሙዚ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ከመሆኑም ሌላ የመራባት እንስት አምላክ የሆነችው የኢናና (ባቢሎናውያን ኢሽታር ብለው ይጠሯታል) ባል ወይም ፍቅረኛ እንደሆነ ተገልጿል። (ሕዝ 8:14) (2) ከባቢሎን ምርኮ በኋላ በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ ለአራተኛው የጨረቃ ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ለአሥረኛው ወር የተሰጠ ስም ነው። ይህ ወር ከሰኔ አጋማሽ እስከ ሐምሌ አጋማሽ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል።–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • ታማኝ ፍቅር

    አብዛኛውን ጊዜ ታማኝ ፍቅር ተብሎ የተተረጎመው ኼሴድ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል በከፍተኛ ቅንዓት፣ በጽኑ አቋም፣ በታማኝነትና ከልብ በመነጨ የመውደድ ስሜት ተነሳስቶ ፍቅር ማሳየትን ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ አምላክ ለሰዎች ያለውን ፍቅር ለማመልከት የተሠራበት ቢሆንም በሰዎች መካከል ያለውንም ፍቅር ሊያመለክት ይችላል።–ዘፀ 34:6ሩት 3:10

  • ቴቤት

    ከባቢሎን ምርኮ በኋላ በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ ለአሥረኛው ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ለአራተኛው ወር የተሰጠ ስም ነው። ከታኅሣሥ አጋማሽ እስከ ጥር አጋማሽ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። ይህ ወር በደፈናው “አሥረኛ ወር” ተብሎ ይጠራል። (አስ 2:16)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • ትንሣኤ

    ከሞት መነሳት ማለት ነው። አናስታሲስ የተባለው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “መቆም፤ መነሳት” የሚል ፍቺ አለው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት እንዳስነሳው የሚናገረውን ዘገባ ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ከሞት እንደተነሱ ተገልጿል። ምንም እንኳ ሌሎቹን ሰዎች ከሞት ያስነሱት ኤልያስ፣ ኤልሳዕ፣ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስና ጳውሎስ ቢሆኑም እነዚህን ተአምራት የፈጸሙት ከአምላክ ባገኙት ኃይል እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል። “ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” በምድር ላይ ትንሣኤ ማግኘታቸው በአምላክ ዓላማ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል። (ሥራ 24:15) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “የመጀመሪያው ትንሣኤ” ተብሎ ስለተጠራው ስለ ሰማያዊው ትንሣኤ ይናገራል፤ ይህም በመንፈስ የተቀቡ የኢየሱስ ወንድሞች የሚያገኙትን ትንሣኤ የሚያመለክት ነው።–ፊልጵ 3:11ራእይ 20:5, 6፤ ዮሐ 5:28, 29፤ 11:25

  • ትንቢት

    በመንፈስ መሪነት የሚነገር መልእክት ሲሆን መለኮታዊው ፈቃድ በራእይ መገለጡን ወይም መለኮታዊው ፈቃድ መታወጁን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ትንቢት፣ በመንፈስ መሪነት የተነገረ የሥነ ምግባር ትምህርት፣ መለኮታዊ ትእዛዝ ወይም ፍርድ አሊያም ወደፊት ስለሚመጣ ነገር የሚገልጽ አዋጅ ሊሆን ይችላል።–ሕዝ 37:9, 10ዳን 9:24፤ ማቴ 13:14፤ 2ጴጥ 1:20, 21

  • ቸነፈር

    በፍጥነትና በስፋት የሚዛመትን ማንኛውም ዓይነት ገዳይ በሽታ ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ የመለኮታዊ ቁጣ አንዱ መገለጫ እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል።–ዘኁ 14:12ሕዝ 38:22, 23፤ አሞጽ 4:10

  • ነቢይ

    አምላክ ዓላማውን ለሰዎች ለመግለጽ የሚጠቀምበትን ግለሰብ ያመለክታል። ነቢያት፣ ትንቢት በመተንበይ ብቻ ሳይሆን የይሖዋን ትምህርቶች፣ ትእዛዞችና የፍርድ መልእክቶች ለሰዎች በመናገር የአምላክ ቃል አቀባይ ሆነው አገልግለዋል።–አሞጽ 3:72ጴጥ 1:21

  • ነጭ ዕጣን

    ከቦስዌልያ ዝርያዎች ከሚመደቡ የዛፍ ወይም የቁጥቋጦ ዓይነቶች የሚገኝ የደረቀ የዛፍ እንባ (ሙጫ)። በሚጨስበት ጊዜ ጥሩ መዓዛ አለው። በማደሪያ ድንኳኑም ሆነ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቅዱሱን ዕጣን ለማዘጋጀት ያገለግል ነበር። በተጨማሪም ከእህል መባ ጋር አብሮ ይቀርብ የነበረ ሲሆን በቅድስቱ ውስጥ ተነባብሮ በሚቀመጠው ገጸ ኅብስት፣ በእያንዳንዱ ረድፍ ላይ ይደረግ ነበር።–ዘፀ 30:34-36ዘሌ 2:1፤ 24:7፤ ማቴ 2:11

  • ነፃ ሰው፤ ነፃ የወጣ ሰው

    በሮማውያን የግዛት ዘመን ‘ነፃ ሰው’ ይባል የነበረው ሙሉ የዜግነት መብት ያለው ነፃ ሆኖ የተወለደ ሰው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ‘ነፃ የወጣ ሰው’ የሚባለው ከባርነት ነፃ እንዲሆን የተደረገ ሰው ነው። በደንቡ መሠረት ነፃ የወጣ ሰው የሮማ ዜግነት መብት የሚያገኝ ቢሆንም የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ ብቁ አይሆንም። ደንቡን ባልጠበቀ መንገድ ነፃ የወጣ ሰው ከባርነት ሊላቀቅ ቢችልም ሙሉ የዜግነት መብት ግን አይኖረውም።–1ቆሮ 7:22

  • ነፍስ

    ነፈሽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃልና ፕስኺ የተባለው ግሪክኛ ቃል ብዙውን ጊዜ “ነፍስ” ተብለው ይተረጎማሉ። እነዚህ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት እንደተሠራባቸው ስንመረምር ቃላቱ በዋነኝነት (1) ሰዎችን፣ (2) እንስሳትን ወይም (3) የሰውን ወይም የእንስሳን ሕይወት እንደሚያመለክቱ መረዳት እንችላለን። (ዘፍ 1:20፤ 2:7፤ ዘኁ 31:28፤ 1ጴጥ 3:20፤ የግርጌ ማስታወሻዎቹንም ተመልከት) “ነፍስ” የሚለው ቃል በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ ከሚሰጠው ትርጉም በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ ነፈሽ እና ፕስኺ የሚሉት ቃላት በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታትን ይኸውም በዓይን የሚታዩ፣ የሚዳሰሱና ሟች የሆኑ ነገሮችን ለማመልከት እንደተሠራባቸው ይጠቁማል። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ በበኩረ ጽሑፉ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ቃላት እንደየአገባባቸው “ሕይወት፣” “ፍጥረት፣” “ሁለንተና” ተብለው ተተርጉመዋል፤ ወይም ደግሞ በተውላጠ ስም (ለምሳሌ፣ “ነፍሴ” የሚለውን “እኔ” በማለት) ተተክተዋል። በብዙዎቹ ቦታዎች ላይ “ነፍስ” የሚለው ቃል በግርጌ ማስታወሻ ገብቷል። በዋናው ጽሑፍም ሆነ በግርጌ ማስታወሻው ላይ “ነፍስ” የሚል ቃል በምናገኝበት ጊዜ የቃሉን ፍቺ ከላይ በተሰጠው ማብራሪያ መሠረት መረዳት ይኖርብናል። አንድን ነገር በሙሉ ነፍስ ማድረግ ሲባል ሥራውን በሙሉ ልብ ማከናወንን፣ መላ ሕይወትን በሥራው ማስጠመድን ወይም ሁለንተናን ለዚያ ነገር መስጠትን ያመለክታል። (ዘዳ 6:5፤ ማቴ 22:37) በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኙት እነዚህ ቃላት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የአንድን ሕያው ፍጡር ምኞት ወይም ፍላጎት ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። በተጨማሪም የሞተን ሰው ወይም አስከሬንን ሊያመለክቱ ይችላሉ።–ዘኁ 6:6ምሳሌ 23:2፤ ኢሳ 56:11፤ ሐጌ 2:13

  • ኑፋቄ፤ ቡድን

    አንድን ሃይማኖታዊ ትምህርት ወይም መሪ በጥብቅ የሚከተልና የራሱን እምነት የሚያራምድ ቡድን። ሁለቱን የታወቁ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ማለትም ፈሪሳውያንንና ሰዱቃውያንን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች የክርስትናን እምነት “ኑፋቄ” ወይም “የናዝሬታውያን ኑፋቄ” በማለት ይጠሩት ነበር፤ ምናልባትም እንዲህ ይሉ የነበረው የክርስትና እምነት ከአይሁድ እምነት ተገንጥሎ የወጣ እንደሆነ አድርገው ስለሚያስቡ ሳይሆን አይቀርም። ከጊዜ በኋላ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተለያዩ ኑፋቄዎች የተነሱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በራእይ መጽሐፍ ውስጥ “የኒቆላዎስ ኑፋቄ” በስም ተጠቅሷል።–ሥራ 5:1715:524:528:22ራእይ 2:6፤ 2ጴጥ 2:1

  • ኒሳን

    ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ለአቢብ ወር የተሰጠ አዲስ ስም ሲሆን በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ የመጀመሪያው ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ሰባተኛው ወር ነው። ይህ ወር ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። (ነህ 2:1)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • ናርዶስ

    ከናርዶስ ተክል (ናርዶስታኪስ ጃታማንሲ) የሚገኝ እጅግ ውድ የሆነና ጥሩ መዓዛ ያለው ቅባት ሲሆን ፈዘዝ ያለ ቀይ ቀለም አለው። የናርዶስ ዘይት እጅግ ውድ ስለነበር ሰዎች ርካሽ ከሆኑ ዘይቶች ጋር ይቀላቅሉት እንዲሁም አስመስለው ይሠሩት ነበር። ማርቆስና ዮሐንስ፣ በኢየሱስ ላይ የፈሰሰው ዘይት “ንጹሕ ናርዶስ” እንደሆነ የገለጹት ለዚህ ሊሆን ይችላል።–ማር 14:3ዮሐ 12:3

  • ናታኒም

    እስራኤላውያን ያልሆኑ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ነበሩ። የዕብራይስጡ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “የተሰጡ ሰዎች” የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የተሰጡ መሆናቸውን ያመለክታል። አብዛኞቹ ናታኒሞች፣ ኢያሱ “ለማኅበረሰቡና ለይሖዋ መሠዊያ እንጨት ለቃሚዎችና ውኃ ቀጂዎች” ያደረጋቸው የገባኦናውያን ዘሮች ሳይሆኑ አይቀሩም።–ኢያሱ 9:23, 271ዜና 9:2፤ ዕዝራ 8:17

  • ናዝራዊ

    ለአንድ ነገር “የተለየ” ወይም “የተወሰነ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ ነው። ናዝራውያን በሁለት ይመደባሉ፤ እነሱም በፈቃደኝነት ራሳቸውን ለዚህ መብት ያቀረቡና አምላክ ናዝራዊ እንዲሆኑ የመረጣቸው ናቸው። አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት ለተወሰነ ጊዜ ናዝራዊ ሆነው ለመኖር ለይሖዋ ልዩ ስእለት ሊሳሉ ይችላሉ። በፈቃደኝነት ይህን ስእለት የሚሳሉ ሰዎች በዋነኝነት የሚከተሉትን ሦስት ግዴታዎች መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፦ የአልኮል መጠጥ መጠጣትም ሆነ ከወይን ፍሬ የተዘጋጀን ማንኛውም ነገር መብላት የለባቸውም፤ ፀጉራቸውን መቆረጥ አይኖርባቸውም፤ እንዲሁም አስከሬን መንካት የለባቸውም። ይሖዋ ናዝራዊ እንዲሆኑ የመረጣቸው ሰዎች ዕድሜ ልካቸውን ናዝራዊ ሆነው የሚኖሩ ሲሆን ይሖዋ ከእነሱ ምን እንደሚጠብቅም በዝርዝር ተናግሯል።–ዘኁ 6:2-7መሳ 13:5

  • ኔሂሎት

    በመዝሙር 5 አናት ላይ ባለው መግለጫ ውስጥ የሚገኝ ትርጉሙ በእርግጠኝነት የማይታወቅ ቃል ነው። አንዳንዶች ይህን ቃል ኻሊል (ዋሽንት) ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተዛማጅነት እንዳለው ስለሚሰማቸው ኔሂሎት የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ ስም እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ቃሉ የአንድ ዜማ ስያሜም ሊሆን ይችላል።

  • ኔፍሊም

    ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ሥጋ ከለበሱ መላእክትና ከሰዎች ሴቶች ልጆች የተወለዱ ዲቃላዎች ሲሆኑ ጨካኞችና ጉልበተኞች ነበሩ።–ዘፍ 6:4

  • ንስሐ

    ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት አንድ ሰው በቀድሞ አካሄዱ፣ በፈጸመው መጥፎ ድርጊት ወይም ሳያደርግ በቀረው ነገር ከልብ ተጸጽቶ የአመለካከት ለውጥ ማድረጉን ለማመልከት ነው። እውነተኛ ንስሐ ፍሬ ያፈራል፤ ማለትም ግለሰቡ በአካሄዱ ላይ ለውጥ እንዳደረገ በግልጽ ይታያል።–ማቴ 3:8ሥራ 3:19፤ 2ጴጥ 3:9

  • ንጹሕ

    ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አካላዊ ንጽሕናን ብቻ ሳይሆን ያለእንከንና ያለነቀፋ መመላለስን ወይም ከእንከንና ከነቀፋ መንጻትን እንዲሁም አንድን ሰው በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ሊያቆሽሽ፣ ሊበክል ወይም ሊያጎድፍ ከሚችል ከየትኛውም ነገር ነፃ መሆንን ያመለክታል። በሙሴ ሕግ መሠረት ቃሉ ሕጉ በሚያዘው መሠረት የመንጻት ሥርዓት መፈጸምን ለማመልከት ተሠርቶበታል።–ዘሌ 10:10መዝ 51:7፤ ማቴ 8:2፤ 1ቆሮ 6:11

  • አላሞት

    “ልጃገረዶች፤ ወጣት ሴቶች” የሚል ትርጉም ያለው ከሙዚቃ ጋር የተያያዘ ቃል ሲሆን ወጣት ሴቶች ሲዘምሩ የሚያወጡትን ከፍ ያለ ድምፅ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ቃሉ አንድን ሙዚቃ ወይም የማጀቢያ ዜማ ከፍ ባለ ድምፅ መጫወት እንደሚያስፈልግ ለመጠቆም ይሠራበት የነበረ ይመስላል።–1ዜና 15:20መዝ 46:0

  • አልባስጥሮስ

    ትንሽ ለሆነ የሽቶ መያዣ ብልቃጥ የተሰጠ ስያሜ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ብልቃጥ ቀደም ሲል ግብፅ ውስጥ አልባስጥሮን በሚባል ቦታ አቅራቢያ ከሚገኝ ድንጋይ ይሠራ ነበር። ይህ ብልቃጥ አብዛኛውን ጊዜ ቀጭን አንገት እንዲኖረው ተደርጎ የሚሠራ ከመሆኑም ሌላ ይታሸግ ነበር፤ ይህም ውድ የሆነው ሽቶ በኖ እንዳያልቅ ለማድረግ ይረዳል። በኋላም ብልቃጡን ለመሥራት የሚያገለግለው ድንጋይ በዚሁ ስያሜ መጠራት ጀመረ።–ማር 14:3

  • አልፋና ኦሜጋ

    የመጀመሪያውና የመጨረሻው የግሪክኛ ፊደላት የሚጠሩበት ስያሜ ነው፤ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ሦስት ቦታ ላይ የአምላክ የማዕረግ ስም ሆነው ተጠቅሰዋል። በእነዚህ ቦታዎች ላይ ይህ አባባል “የመጀመሪያውና የመጨረሻው” እንዲሁም “ፊተኛውና ኋለኛው” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል።–ራእይ 1:821:6፤ 22:13

  • አሜን

    “ይሁን” ወይም “በእርግጥ” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ቃል “ታማኝ፣ እምነት የሚጣልበት” የሚል ትርጉም ካለው አማን ከሚለው የዕብራይስጥ ሥርወ ቃል የመጣ ነው። አንድ ሰው “አሜን” የሚለው በአንድ መሐላ፣ ጸሎት ወይም ሐሳብ መስማማቱን ለመግለጽ ነው። ቃሉ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የኢየሱስ የማዕረግ ስም ሆኖ አገልግሏል።–ዘዳ 27:261ዜና 16:36፤ ራእይ 3:14

  • አሥራት

    አብዛኛውን ጊዜ ለሃይማኖታዊ ዓላማ በግብር መልክ የሚሰጥ ወይም የሚከፈል አንድ አሥረኛ ወይም ከመቶ አሥር እጅ። አንድ ሰው ይህን ሲያከናውን አሥራት ሰጠ ወይም አስገባ ይባላል። (ሚል 3:10፤ ዘዳ 26:12፤ ማቴ 23:23) በሙሴ ሕግ መሠረት ምድሪቱ ከምታስገኘው ምርት አንድ አሥረኛው እንዲሁም የእንስሳቱ መንጋ እየበዛ ሲሄድ ከጭማሪው ላይ አንድ አሥረኛው ሌዋውያንን ለመደገፍ በየዓመቱ ይሰጥ ነበር። ሌዋውያን ደግሞ በተራቸው ከዚህ አሥራት ላይ አንድ አሥረኛውን የአሮን ዘር ለሆኑት ካህናት ድጋፍ እንዲሆን ይሰጡ ነበር። እስራኤላውያን የሚሰጧቸው ሌሎች አሥራቶችም ነበሩ። ክርስቲያኖች አሥራት የመስጠት ግዴታ የለባቸውም።

  • አረማይክ

    ከዕብራይስጥ ቋንቋ ጋር በጣም የሚቀራረብና አንድ ዓይነት ፊደላት የሚጠቀም ሴማዊ ቋንቋ ነው። መጀመሪያ ላይ አራማውያን ይናገሩት የነበረ ቋንቋ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ደግሞ በአሦራውያንና በባቢሎናውያን ግዛቶች ውስጥ ለንግድ ሥራም ሆነ ለመግባቢያነት የሚያገለግል ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ ሆኖ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በፋርስ ግዛት ውስጥ የመንግሥት ቋንቋ ሆኖ አገልግሏል። (ዕዝራ 4:7) የዕዝራ፣ የኤርምያስና የዳንኤል መጻሕፍት የተወሰኑ ክፍሎች የተጻፉት በአረማይክ ነው።–ዕዝራ 4:8 እስከ 6:187:12-26ኤር 10:11፤ ዳን 2:4ለ እስከ 7:28

  • አራም፤ አራማውያን

    የሴም ልጅ የሆነው የአራም ዘሮች ሲሆኑ ዋነኛ መኖሪያ ስፍራቸው ከሊባኖስ ተራሮች አንስቶ እስከ ሜሶጶጣሚያ እንዲሁም በስተ ሰሜን ካሉት የቶረስ ተራሮች አንስቶ በስተ ደቡብ እስከ ደማስቆና ከዚያ አልፎ እስካለው ምድር ድረስ ያለውን አካባቢ ያካትት ነበር። በዕብራይስጥ አራም ተብሎ የሚጠራው ይህ ስፍራ ከጊዜ በኋላ ሶርያ የሚል ስያሜ ተሰጠው፤ ነዋሪዎቹ ደግሞ ሶርያውያን ይባላሉ።–ዘፍ 25:20ዘዳ 26:5፤ ሆሴዕ 12:12

  • አርማጌዶን

    ቃሉ የተገኘው “የመጊዶ ተራራ” የሚል ትርጉም ካለው ሃር መጊዶን ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ነው። ይህ ቃል ‘የዓለም ነገሥታት ሁሉ’ ከይሖዋ ጋር ለመዋጋት የሚሰበሰቡበትን ‘ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ ቀን የሚካሄደውን ጦርነት’ ለማመልከት ተሠርቶበታል። (ራእይ 16:14, 16፤ 19:11-21)–ታላቁ መከራ የሚለውን ተመልከት።

  • አርዮስፋጎስ

    አቴንስ ውስጥ ከአክሮፖሊስ በስተ ሰሜን ምዕራብ የሚገኝ ከፍ ያለ ኮረብታ ነው። ይህ ቃል በዚህ ስፍራ የሚሰበሰበውን ምክር ቤት (ሸንጎ) ለማመልከትም ተሠርቶበታል። የኢስጦይክና የኤፊቆሮስ ፈላስፎች፣ ስለሚያምንባቸው ነገሮች ማብራሪያ እንዲሰጥ ጳውሎስን ወደ አርዮስፋጎስ ወስደውት ነበር።–ሥራ 17:19

  • አሴልጊያ

    ማንአለብኝነት የሚለውን ተመልከት።

  • አስተዳዳሪ

    በባቢሎን መንግሥት ውስጥ ከአውራጃ ገዢ ያነሰ ሥልጣን ያለው ሹም ነበር። አስተዳዳሪዎች በባቢሎን ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትን ጠቢባን የመቆጣጠር ሥልጣን እንደነበራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። እነዚህ አስተዳዳሪዎች በሜዶናዊው በንጉሥ ዳርዮስ የግዛት ዘመንም ነበሩ።–ዳን 2:486:7

  • አስታሮት

    የባአል ሚስት የሆነች የከነአናውያን የጦርነትና የመራባት ሴት አምላክ።–1ሳሙ 7:3

  • አቢብ

    በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ (ቀደም ሲል) ለመጀመሪያው ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ለሰባተኛው ወር የተሰጠ ስም ነው። ቃሉ “(የእህል) እሸት” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። ይህ ወር አይሁዳውያን ከባቢሎን ከተመለሱ በኋላ ኒሳን ተብሎ ተጠርቷል። (ዘዳ 16:1)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • አብ

    ከባቢሎን ምርኮ በኋላ በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ ለ5ኛው ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ለ11ኛው ወር የተሰጠ ስም ነው። ይህ ወር ከሐምሌ አጋማሽ እስከ ነሐሴ አጋማሽ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የዚህ ወር ስም ተጠቅሶ አናገኝም፤ ከዚህ ይልቅ “አምስተኛው ወር” ተብሎ ተጠርቷል። (ዘኁ 33:38፤ ዕዝራ 7:9)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • አንበጦች

    በብዛት ሆነው የሚጓዙ የፌንጣ ዓይነቶች ናቸው። በሙሴ ሕግ ላይ ለመብል ከተፈቀዱ ንጹሕ እንስሳት መካከል ተመድበዋል። በሄዱበት ሁሉ ያገኙትን ዕፀዋት ጠራርገው ይበላሉ፤ እንደ መቅሰፍት ተደርገውም ይቆጠሩ ነበር።–ዘፀ 10:14ማቴ 3:4

  • አካይያ

    ይህ ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሮም ግዛት ሥር የነበረውን ደቡባዊውን የግሪክ ምድር ያመለክታል፤ ዋና ከተማው ቆሮንቶስ ነበረች። አካይያ መላውን የፔሎፖኒስ ምድርና የግሪክን ማዕከላዊ ክፍል ያካትት ነበር። (ሥራ 18:12)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ13ን ተመልከት።

  • አዛዜል

    ይህ የዕብራይስጥ ቃል “የሚጠፋ ፍየል” የሚል ትርጉም ሳይኖረው አይቀርም። በስርየት ቀን አዛዜል የሚሆነው ፍየል ወደ ምድረ በዳ የሚላክ ሲሆን ይህም ብሔሩ በዓመት ውስጥ የፈጸማቸውን ኃጢአቶች ፍየሉ ተሸክሞ መሄዱን የሚያሳይ ምሳሌያዊ ድርጊት ነበር።–ዘሌ 16:8, 10

  • አይሁድ

    አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ከወደቀ በኋላ ከይሁዳ ነገድ የሆነን ሰው ለማመልከት ተሠርቶበታል። (2ነገ 16:6) አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ነፃ ከወጡ በኋላ ደግሞ ወደ እስራኤል የተመለሱትን ከተለያየ ነገድ የተውጣጡ እስራኤላውያን ለማመልከት ይሠራበት ጀመር። (ዕዝራ 4:12) ከጊዜ በኋላ ቃሉ በመላው ዓለም እስራኤላውያንን ከአሕዛብ ለይቶ ለማመልከት ተሠርቶበታል። (አስ 3:6) በተጨማሪም ጳውሎስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የዘር ጉዳይ ምንም ቦታ እንደሌለው ለማስረዳት ሲል ይህን ቃል በምሳሌያዊ መንገድ ተጠቅሞበታል።–ሮም 2:28, 29ገላ 3:28

  • አዳር

    ከባቢሎን ምርኮ በኋላ በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ ለ12ኛው ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ለ6ኛው ወር የተሰጠ ስም ነው። ይህ ወር ከየካቲት አጋማሽ እስከ መጋቢት አጋማሽ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። (አስ 3:7)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • አጃ

    ስንዴ የሚመስል የእህል ዓይነት (ትሪቲከም ስፔልታ) ሲሆን ፍሬውን ከገለባው መለየት አስቸጋሪ ነው።–ዘፀ 9:32

  • አጋንንት

    ከሰው የላቀ ኃይል ያላቸው በዓይን የማይታዩ ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ናቸው። በዘፍጥረት 6:2 ላይ “የእውነተኛው አምላክ ልጆች፣” በይሁዳ 6 ላይ ደግሞ “መላእክት” ተብለው የተጠሩት እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት ክፉ ሆነው የተፈጠሩ አልነበሩም፤ ከዚህ ይልቅ በኖኅ ዘመን የአምላክን ትእዛዝ በመጣስና ሰይጣን በይሖዋ ላይ ባካሄደው ዓመፅ ተባባሪ በመሆን ራሳቸውን የአምላክ ጠላት ያደረጉ መላእክት ናቸው።–ዘዳ 32:17ሉቃስ 8:30፤ ሥራ 16:16፤ ያዕ 2:19

  • አጥቢያ ኮከብ

    የንጋት ኮከብ የሚለውን ተመልከት።

  • ኡሪምና ቱሚም

    ከይሖዋ መልስ የሚያሻውና ብሔሩን የሚመለከት አቢይ ጉዳይ በሚነሳበት ጊዜ ዕጣ ከመጣል ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ሊቀ ካህናቱ የሚጠቀምባቸው ነገሮች። ሊቀ ካህናቱ ወደ ማደሪያው ድንኳን በሚገባበት ጊዜ ኡሪሙንና ቱሚሙን በደረት ኪሱ ውስጥ ያስቀምጣቸው ነበር። ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ባወደሙ ጊዜ እስራኤላውያን በኡሪምና በቱሚም መጠቀም ሳያቆሙ አይቀሩም።–ዘፀ 28:30ነህ 7:65

  • ኢትዮጵያ

    ከግብፅ በስተ ደቡብ ትገኝ የነበረች ጥንታዊ አገር ናት። የዛሬዋን ግብፅ አብዛኛውን ደቡባዊ ክፍልና የአሁኗን ሱዳን ሰሜናዊ ግዛት በከፊል ትሸፍን ነበር። አንዳንድ ጊዜ ይህ ስያሜ “ኩሽ” የሚለውን የዕብራይስጥ መጠሪያ ለማመልከት ተሠርቶበታል።–አስ 1:1

  • ኢዮቤልዩ

    እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡበት ጊዜ አንስቶ በየሃምሳ ዓመቱ የሚከበር በዓል ነው። ኢዮቤልዩ፣ ማሳ ሳይታረስ የሚተውበት፣ ዕብራውያን ባሮች ነፃ የሚወጡበትና የተሸጠ ርስት ለባለቤቱ የሚመለስበት ዓመት ነበር። ኢዮቤልዩ ዓመቱን ሙሉ የሚከበር በዓል ነው ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም ይህ ወቅት አምላክ የእስራኤልን ብሔር መጀመሪያ ባቋቋመበት ጊዜ የነበረው ሁኔታ ተመልሶ እንዲመጣ የሚያደርግ የነፃነት ዓመት ነበር።–ዘሌ 25:10

  • ኢፍ

    እህል ለመስፈር የሚያገለግል የደረቅ ነገር መለኪያ ሲሆን ዕቃው ራሱም በዚህ ስያሜ ይጠራል። ፈሳሽ ነገር ከሚሰፈርበት ከባዶስ መስፈሪያ ጋር እኩል ሲሆን 22 ሊትር ነው። (ዘፀ 16:36፤ ሕዝ 45:10)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ኤሉል

    አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ ለ6ኛው ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ለ12ኛው ወር የተሰጠ ስም ነው። ከነሐሴ አጋማሽ አንስቶ እስከ መስከረም አጋማሽ ያለውን ጊዜ ያመለክታል። (ነህ 6:15)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • ኤታኒም

    በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ ለሰባተኛው ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ለመጀመሪያው ወር የተሰጠ ስም ነው። ይህ ወር ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት አጋማሽ ያለውን ጊዜ ያመለክታል። አይሁዳውያን ከባቢሎን ከተመለሱ በኋላ ቲሽሪ ተብሏል። (1ነገ 8:2)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • ኤዶም

    ለይስሐቅ ልጅ ለኤሳው የተሰጠ ሌላ ስም ነው። የኤሳው ዘሮች በሙት ባሕርና በአቃባ ባሕረ ሰላጤ መካከል ባለው ተራራማ አካባቢ ይኸውም ሴይር በሚባለው ክልል ይኖሩ ነበር። ከጊዜ በኋላ ይህ አካባቢ ኤዶም ተብሎ ይጠራ ጀመር። (ዘፍ 25:30፤ 36:8)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ3ን እና ለ4ን ተመልከት።

  • ኤፉድ

    ካህናት የሚለብሱት እንደ ሽርጥ ያለ ልብስ ነው። ሊቀ ካህናቱ ከፊት በኩል የደረት ኪስ ያለው ልዩ የሆነ ኤፉድ የሚለብስ ሲሆን በደረት ኪሱ ላይ ደግሞ 12 የከበሩ ድንጋዮች ተደርድረው ይገኛሉ። (ዘፀ 28:4, 6)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ን ተመልከት።

  • ኤፍራጥስ

    በደቡባዊ እስያ የሚገኝ ረጅምና ታዋቂ ወንዝ ሲሆን በሜሶጶጣሚያ ከሚገኙት ሁለት ታላላቅ ወንዞች አንዱ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በዘፍጥረት 2:14 ላይ ነው፤ ጥቅሱ ይህ ወንዝ ከኤደን አራት ወንዞች አንዱ እንደሆነ ይገልጻል። ብዙውን ጊዜ “ወንዙ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዘፍ 31:21) በተጨማሪም እስራኤላውያን የወረሱት ምድር ሰሜናዊ ወሰን ሆኖ አገልግሏል። (ዘፍ 15:18፤ ራእይ 16:12)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ2ን ተመልከት።

  • ኤፍሬም

    የዮሴፍ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ስም ነው፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከእስራኤል ነገዶች መካከል የአንዱ መጠሪያ ሆኖ አገልግሏል። ኤፍሬም ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነገድ ስለነበር እስራኤላውያን ከተከፋፈሉ በኋላ የአሥሩ ነገድ መንግሥት በዚህ ስም ይጠራ ነበር።–ዘፍ 41:52ኤር 7:15

  • እልዋሪቆን

    ከግሪክ በስተ ሰሜን ምሥራቅ ትገኝ የነበረች የሮም ግዛት ናት። ጳውሎስ አገልግሎቱን ሲያከናውን እስከዚህ ቦታ ድረስ ርቆ እንደተጓዘ የተገለጸ ቢሆንም በእልዋሪቆን ውስጥ ይስበክ ወይም እስከዚያ ድረስ ሰብኮ ብቻ ይመለስ የተጠቀሰ ነገር የለም። (ሮም 15:19)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ13ን ተመልከት።

  • እርሾ

    ሊጥ እንዲቦካ ወይም አንድ መጠጥ እንዲፈላ ለማድረግ ያገለግላል፤ በተለይ ቀደም ብሎ ከነበረው ሊጥ ላይ የቀረ፣ የቦካ ሊጥ ለዚህ አገልግሎት ይውላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ኃጢአትንና ብልሹ ምግባርን ለማመልከት የተሠራበት ሲሆን በድብቅ ውስጥ ውስጡን የሚያድግ ነገርንም ለመግለጽ አገልግሏል።–ዘፀ 12:20ማቴ 13:33፤ ገላ 5:9

  • እርግማን

    በአንድ ሰው ላይ መጥፎ ነገር እንዲደርስ ተብሎ የተነገረ መጥፎ ቃል ወይም ምኞት። ከስድብ ወይም ከኃይለኛ ቁጣ ጋር አንድ ተደርጎ መታየት የለበትም። አብዛኛውን ጊዜ እርግማን በአንድ አካል ላይ የሚነገር የውግዘት ቃል ወይም መጥፎ ነገር እንዲደርስበት መመኘትን የሚያመለክት ሲሆን እርግማኑን የተናገረው አካል አምላክ ወይም መብት ያለው ሰው ከሆነ እርግማኑ ትንቢታዊ ፍጻሜና ክብደት ይኖረዋል።–ዘፍ 12:3ዘኁ 22:12፤ ገላ 3:10

  • እስራኤል

    አምላክ ለያዕቆብ ያወጣለት ስም ነው። በየትኛውም ዘመን ይኖሩ የነበሩትን የያዕቆብ ዘሮች በቡድን ደረጃ ለማመልከትም ተሠርቶበታል። የያዕቆብ 12 ወንዶች ልጆች ዘሮች ብዙውን ጊዜ የእስራኤል ልጆች፣ የእስራኤል ቤት፣ የእስራኤል ሕዝብ ወይም እስራኤላውያን ተብለው ተጠርተዋል። በተጨማሪም እስራኤል የሚለው መጠሪያ ከደቡባዊው መንግሥት የተገነጠለውንና አሥሩን ነገዶች ያቀፈውን ሰሜናዊ መንግሥት ለማመልከት የተሠራበት ሲሆን ከጊዜ በኋላ ደግሞ ቃሉ ‘የአምላክ እስራኤል’ ተብለው የተጠሩትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለማመልከት አገልግሏል።–ገላ 6:16ዘፍ 32:28፤ 2ሳሙ 7:23፤ ሮም 9:6

  • እስያ

    ይህ ስያሜ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ፣ የተወሰነውን የሮም ግዛት ለማመልከት የተሠራበት ሲሆን ቦታው በዛሬው ጊዜ በቱርክ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘውን ክልል እንዲሁም እንደ ሳሞስና ጳጥሞስ ያሉትን አንዳንድ ደሴቶች ያካትታል። የእስያ ዋና ከተማ ኤፌሶን ነበረች። (ሥራ 20:16፤ ራእይ 1:4)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ13ን ተመልከት።

  • እቶን፤ ምድጃ

    የብረት አፈር ወይም ብረት ለማቅለጥ የሚያገለግል ምድጃ ነው፤ የሸክላ ዕቃዎችን ለመተኮስም ያገለግላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እነዚህ ምድጃዎች የሚሠሩት ከጡብ ወይም ከድንጋይ ነበር። የሸክላ ዕቃዎችን ለመተኮስና ኖራ ለማመስ የሚያገለግለው ምድጃ የሸክላ መተኮሻ ምድጃ ተብሎ ይጠራል።–ዘፍ 15:17ዳን 3:17፤ ራእይ 9:2

  • እንጦሮጦስ

    በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ይህ ቃል በኖኅ ዘመን ያመፁት መላእክት የተጣሉበትን እንደ እስር ቤት ያለ ሁኔታና የደረሰባቸውን ውርደት ያመለክታል። በሁለተኛ ጴጥሮስ 2:4 ላይ የገባው ታርታሮኦ (“ወደ እንጦሮጦስ መጣል”) የሚለው ግስ ‘ኃጢአት የሠሩት መላእክት’ በአረማውያን አፈ ታሪክ ወደሚነገረው እንጦሮጦስ (ማለትም ከመሬት በታች ወደሚገኝ እስር ቤትና ታናናሽ አማልክት ወደሚኖሩበት የጨለማ ስፍራ) እንደተጣሉ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ አምላክ በሰማይ የነበራቸውን ቦታና መብት እንዲያጡ በማድረግ እንዳዋረዳቸው እንዲሁም ድንቅ የሆኑትን የአምላክ ዓላማዎች እንዳይረዱ አእምሯቸው በድቅድቅ ጨለማ እንዲዋጥ ማድረጉን ያሳያል። በተጨማሪም ጨለማው መጨረሻ ላይ የሚጠብቃቸውን ቅጣት ይኸውም ቅዱሳን መጻሕፍት በሚገልጹት መሠረት ከገዢያቸው ከሰይጣን ዲያብሎስ ጋር የሚደርስባቸውን ዘላለማዊ ጥፋት ያመለክታል። በመሆኑም እንጦሮጦስ ዓመፀኞቹ መላእክት የደረሰባቸውን ከፍተኛ ውርደት የሚያመለክት ቃል ነው። ራእይ 20:1-3 ላይ የተጠቀሰው “ጥልቁ” ከእንጦሮጦስ የተለየ ነው።

  • እንጨት

    ቅጣት የተበየነበት ሰው የሚሰቀልበት ቀጥ ያለ ግንድ። አንዳንድ ብሔራት ሰውን በሞት ለመቅጣት እና/ወይም አስከሬኑን መቀጣጫ ለማድረግ አሊያም በሕዝብ ፊት ውርደት እንዲከናነብ ለማድረግ ግንድ ላይ ይሰቅሉ ነበር። በጭካኔያቸው የሚታወቁት አሦራውያን በውጊያ የማረኳቸውን ሰዎች ሆድ በሾለ እንጨት ወግተው እስከ ደረታቸው ድረስ በመሰቅሰቅ ሰውነታቸውን እንጨቱ ላይ ያንጠለጥሉት ነበር። በአንጻሩ ግን በአይሁዳውያን ሕግ መሠረት አምላክን እንደመሳደብ ወይም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ከባድ ጥፋት የፈጸሙ ሰዎች መጀመሪያ በድንጋይ ተወግረው ወይም በሌላ መንገድ ከተገደሉ በኋላ ለሌሎች መቀጣጫ እንዲሆን አስከሬናቸው እንጨት ላይ አሊያም ግንድ ላይ ይሰቀል ነበር። (ዘዳ 21:22, 23፤ 2ሳሙ 21:6, 9) ሮማውያን፣ አንዳንድ ጊዜ ሞት የተፈረደበትን ሰው እንጨት ላይ በማሰር በርከት ላሉ ቀናት በሥቃይ፣ በጥም፣ በረሃብና በሐሩር ተጎሳቁሎ እንዲሞት ያደርጉ ነበር። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ የተወነጀለውን ሰው እጅና እግር እንጨት ላይ በምስማር በመቸንከር ይገድሉ ነበር፤ ኢየሱስ የተገደለው በዚህ መንገድ ነው። (ሉቃስ 24:20፤ ዮሐ 19:14-16፤ 20:25፤ ሥራ 2:23, 36)–የመከራ እንጨት የሚለውን ተመልከት።

  • እውነተኛው አምላክ

    በብዙ ቦታዎች ላይ የዕብራይስጡ ቃል፣ ከሐሰት አማልክት በተለየ ይሖዋ ብቻ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ለይቶ ለመግለጽ ጠቃሽ አመልካች (ዴፍኒት አርቲክል) የሚጠቀም በመሆኑ እውነተኛው አምላክ ተብሎ ተተርጉሟል። የዕብራይስጡ ቃል እንዲህ ባሉ ጥቅሶች ላይ “እውነተኛው አምላክ” ተብሎ መተርጎሙ ቃሉ የያዘውን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ለማስተላለፍ ያስችላል።–ዘፍ 5:22, 2446:3ዘዳ 4:39

  • እጅ መጫን

    አንድን ሰው ለአንድ ልዩ ኃላፊነት ለመሾም፣ ለመባረክ፣ ለመፈወስ ወይም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንዲቀበል ለማድረግ በግለሰቡ ላይ እጅ ይጫን ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንስሳት መሥዋዕት ሆነው ከመቅረባቸው በፊት እጅ ይጫንባቸው ነበር።–ዘፀ 29:15ዘኁ 27:18፤ ሥራ 19:6፤ 1ጢሞ 5:22

  • እግር ግንድ

    አንድን ሰው አስሮ ለመቅጣት የሚያገለግል መሣሪያ። አንዳንዶቹ መሣሪያዎች እግር ብቻ የሚታሰርባቸው ሲሆኑ ሌሎቹ ግን እግርን፣ እጅንና አንገትን በማሰር ግለሰቡ ለሰውነቱ አመቺ ባልሆነ አጉል ሁኔታ እንዲቆይ የሚያደርጉ ነበሩ።–ኤር 20:2ሥራ 16:24

  • ኦሜር

    የደረቅ ነገር መለኪያ ሲሆን ከ2.2 ሊትር ወይም ከአንድ አሥረኛ ኢፍ ጋር እኩል ነው። (ዘፀ 16:16, 18)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ከሞሽ

    የሞዓባውያን ዋነኛ አምላክ።–1ነገ 11:33

  • ከርቤ

    ኮሚፈራ ከተባሉ የዛፍ ዝርያዎች ከሚመደቡ እሾሃማ ቁጥቋጦዎች ወይም አነስተኛ ዛፎች የሚገኝ ጥሩ መዓዛ ያለው ሙጫ ነው። ከርቤ ቅዱሱን የቅብዓት ዘይት ለመቀመም ከሚያገለግሉት ቅመሞች አንዱ ነበር። ልብስ ወይም አልጋ ጥሩ ጠረን እንዲኖረው ለማድረግ ያገለግል የነበረ ሲሆን ለገላ መታሻነትና ለቅባትነት ይውል በነበረው ዘይት ውስጥም ይጨመር ነበር። በተጨማሪም አስከሬንን ለቀብር ለማዘጋጀት ያገለግል ነበር።–ዘፀ 30:23ምሳሌ 7:17፤ ዮሐ 19:39

  • ከነአን

    የኖኅ የልጅ ልጅ ሲሆን የካም አራተኛ ልጅ ነው። ከከነአን የተገኙት 11 ነገዶች ከጊዜ በኋላ ከሜድትራንያን በስተ ምሥራቅ በግብፅና በሶርያ መካከል ባለው ምድር መኖር ጀመሩ። ይህ አካባቢ ‘የከነአን ምድር’ በመባል ይጠራል። (ዘሌ 18:3፤ ዘፍ 9:18፤ ሥራ 13:19)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ4ን ተመልከት።

  • ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ

    በአብዛኛው በኮረብታ ወይም በተራራ አናት ላይ የሚገኝን ስፍራ አሊያም ሰዎች የሚሠሩትን ከፍ ያለ መድረክ ያመለክታል። ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ከፍ ባሉ ቦታዎች ላይ ለእውነተኛው አምላክ አምልኮ ይቀርብ የነበረ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ቦታዎች የተጠቀሱት ለሐሰት አማልክት ከሚቀርብ አረማዊ አምልኮ ጋር በተያያዘ ነው።–ዘኁ 33:521ነገ 3:2፤ ኤር 19:5

  • ኪሩቤል

    ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸውን ልዩ ሥራ የሚያከናውኑ መላእክት ያመለክታል። ከሱራፌል የተለዩ ናቸው።–ዘፍ 3:24፤ ዘፀ 25:20፤ ኢሳ 37:16፤ ዕብ 9:5

  • ኪስሌው

    አይሁዳውያን ከባቢሎን ከተመለሱ በኋላ በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ ለዘጠነኛው ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ለሦስተኛው ወር የተሰጠ ስም ነው። ይህ ወር ከኅዳር አጋማሽ እስከ ታኅሣሥ አጋማሽ ያለውን ጊዜ ያመለክታል። (ነህ 1:1፤ ዘካ 7:1)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • ካህን

    ካህን ለሆነለት ሕዝብ አምላክን ወክሎ የሚያገለግል ሰው ሲሆን ሕዝቡን ስለ አምላክና ስለ ሕጎቹ ያስተምራል። በተጨማሪም ካህናት ለሕዝቡ መሥዋዕት በማቅረብ፣ አማላጅ በመሆንና በመጸለይ ሕዝቡን ወክለው በአምላክ ፊት ይቀርባሉ። የሙሴ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት የቤተሰብ ራሶች ለቤተሰባቸው ካህን ሆነው ያገለግሉ ነበር። የሙሴ ሕግ ከተሰጠ በኋላ ግን ከሌዊ ነገድ በሆነው በአሮን ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ወንዶች፣ ካህናት ሆነው ያገለግሉ ነበር። የቀሩት ሌዋውያን ወንዶች ደግሞ እነሱን ይረዷቸው ነበር። አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራውን በጀመረበት ጊዜ መንፈሳዊው እስራኤል የካህናት ብሔር ለመሆን በቅቷል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ ብሔር ሊቀ ካህናት ነው።–ዘፀ 28:41ዕብ 9:24፤ ራእይ 5:10

  • ክህደት

    ግሪክኛው ቃል (አፖስታሲያ) ቃል በቃል ሲተረጎም “ከ . . . ርቆ መቆም” የሚል ፍቺ ካለው ግስ የመጣ ነው። ቃሉ በስም መልክ ሲሠራበት “ጥሎ መሄድ፣ መተው ወይም ማመፅ” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ክህደት” የሚለው ቃል በዋነኝነት የተሠራበት ከእውነተኛው አምልኮ ካፈነገጡ ሰዎች ጋር በተያያዘ ነው።–ምሳሌ 11:9ሥራ 21:21፤ 2ተሰ 2:3

  • ክርስቲያን

    አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ያወጣላቸው ስም ነው።–ሥራ 11:2626:28

  • ክርስቶስ

    የኢየሱስ የማዕረግ ስም ሲሆን ክሪስቶስ ከሚለው ግሪክኛ ቃል የተገኘ ነው፤ “መሲሕ” ወይም “የተቀባ” ተብሎ ከተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተመሳሳይ ፍቺ አለው።–ማቴ 1:16ዮሐ 1:41

  • ክንድ

    ከክርን እስከ መካከለኛው ጣት ጫፍ ድረስ የሚሆን የርዝመት መለኪያ ነው። እስራኤላውያን በአብዛኛው ይጠቀሙበት የነበረው ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ከዚህ አንድ ጋት የሚረዝምን ክንድ ይኸውም 51.8 ሴንቲ ሜትር ገደማ ርዝመት ያለውን መለኪያ ይጠቀሙ ነበር። (ዘፍ 6:15፤ ሉቃስ 12:25)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ክፉው

    አምላክንና የጽድቅ መሥፈርቶቹን ለሚጻረረው ለሰይጣን ዲያብሎስ የተሰጠ ስያሜ።–ማቴ 6:131ዮሐ 5:19

  • ኮሬብ፤ የኮሬብ ተራራ

    በሲና ተራራ ዙሪያ የሚገኝ ተራራማ አካባቢ ሲሆን የሲና ተራራ ሌላ መጠሪያ ነው። (ዘፀ 3:1፤ ዘዳ 5:2)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ3ን ተመልከት።

  • ኮከብ ቆጣሪ

    የፀሐይን፣ የጨረቃንና የከዋክብትን እንቅስቃሴ በማጥናት ወደፊት የሚከሰቱ ነገሮችን የሚተነብይ ሰው።–ዳን 2:27ማቴ 2:1

  • ወንጭፍ

    ከጠፍር፣ ከጅማት፣ ከቄጤማ ወይም ከፀጉር የሚሠራ ሲሆን መሐሉ ላይ ያለው ሰፋ ያለ ክፍል የሚወረወረውን ነገር (በአብዛኛው ድንጋይ ነው) ለማስቀመጥ ያስችላል። የወንጭፉ አንዱ ጫፍ እጅ ላይ ይታሰራል፤ ሌላኛው ጫፍ ደግሞ በእጅ ተይዞ ድንጋዩ በሚወነጨፍበት ጊዜ ይለቀቃል። በጥንት ዘመን የነበሩ ብሔራት በጦር ሠራዊታቸው ውስጥ ወንጭፍ የሚወነጭፉ ተዋጊዎችን ይቀጥሩ ነበር።–መሳ 20:161ሳሙ 17:50

  • ወደ ላይ የመውጣት መዝሙር

    ከመዝሙር 120 እስከ 134 ባሉት መዝሙራት አናት ላይ የሚገኝ መግለጫ ነው። ይህን ሐረግ በተመለከተ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም እነዚህ 15 መዝሙራት እስራኤላውያን ሦስቱን ታላላቅ ዓመታዊ በዓላት ለማክበር በይሁዳ ተራሮች አናት ላይ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ‘በሚወጡበት’ ጊዜ በደስታ የሚዘምሯቸው መዝሙራት እንደሆኑ ብዙዎች ያምናሉ።

  • ወደ ይሁዲነት የተለወጠ

    ሃይማኖቱን የለወጠ ሰው። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይህ አገላለጽ የአይሁድን እምነት የተቀበለን ሰው ለማመልከት የተሠራበት ሲሆን ግለሰቡ ወንድ ከሆነ መገረዝ ይጠበቅበታል።–ማቴ 23:15ሥራ 13:43

  • ዋና ወኪል

    ግሪክኛው ቃል “ዋና መሪ” የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። ይህ ሐረግ በዋነኝነት የተሠራበት ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆችን፣ ኃጢአት ከሚያስከትለው መዘዝ ነፃ አውጥቶ ወደ ዘላለም ሕይወት በመምራት ረገድ የሚጫወተውን ጉልህ ሚና ለማመልከት ነው።–ሥራ 3:155:31ዕብ 2:10፤ 12:2

  • ዋግ

    በፈንገስ አማካኝነት ከሚመጡ በርካታ የዕፀዋት በሽታዎች አንዱ ነው።–1ነገ 8:37

  • ዓምድ

    አንድን ነገር ደግፎ የሚያቆም ምሰሶ ወይም ቀጥ ያለ ሐውልት ነው። አንዳንዶቹ ዓምዶች ለአንድ ታሪካዊ ክንውን መታሰቢያነት የቆሙ ነበሩ። በቤተ መቅደሱም ሆነ በሰለሞን ቤተ መንግሥት ውስጥ ቤቱን ደግፈው የሚያቆሙ ዓምዶች ነበሩ። አረማውያን የሐሰት አምልኳቸውን ለማከናወን የማምለኪያ ዓምዶችን ያቆሙ የነበረ ሲሆን እስራኤላውያንም ይህን ልማድ የተከተሉበት ጊዜ ነበር። (መሳ 16:29፤ 1ነገ 7:21፤ 14:23)–የዓምድ ራስ የሚለውን ተመልከት።

  • ዕብራዊ፤ ዕብራይስጥ

    ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ ስያሜ የተሰጠው ለአብራም (ለአብርሃም) ሲሆን በአካባቢው ከነበሩት አሞራውያን ለይቶ ያሳውቀው ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ በአብርሃም የልጅ ልጅ በያዕቆብ በኩል የተገኙትን የአብርሃም ዝርያዎችና ቋንቋቸውን ለማመልከት ተሠርቶበታል። በኢየሱስ ዘመን በዕብራይስጥ ቋንቋ ውስጥ በርካታ የአረማይክ አገላለጾች የተካተቱ ሲሆን ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱም ይህን ቋንቋ ይናገሩ ነበር።–ዘፍ 14:13ዘፀ 5:3፤ ሥራ 26:14

  • ዕጣን

    ሲጨስ ጥሩ መዓዛ ያለው የሙጫና የበለሳን ቅይጥ ነው። በማደሪያ ድንኳኑና በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚጨሰው ልዩ ዕጣን ከአራት ቅመሞች የተቀመመ ነበር። በቅድስቱ ውስጥ ጠዋትና ማታ፣ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ደግሞ በስርየት ቀን ዕጣን ይጨስ ነበር። ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የሚያቀርቡትን ተቀባይነት ያለው ፀሎት ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል። ክርስቲያኖች ዕጣን የማጨስ ግዴታ የለባቸውም።–ዘፀ 30:34, 35ዘሌ 16:13፤ ራእይ 5:8

  • ዕጣ

    እንደ ጠጠር ወይም ትናንሽ የእንጨት ቁርጥራጮች ያሉ ነገሮችን ተጠቅሞ አንድ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል ዘዴ ነው። እነዚህ ነገሮች በልብስ እጥፋት ወይም በአንድ ዕቃ ውስጥ ከተቀመጡ በኋላ ልብሱ ወይም ዕቃው እንዲወዛወዝ ይደረጋል፤ ከዚያም ከልብሱ ወይም ከዕቃው ውስጥ ወጥቶ የወደቀው ወይም በእጅ የተነሳው ጠጠር እንደ ዕጣ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ብዙውን ጊዜ ይህ ከመከናወኑ በፊት ጸሎት ይቀርባል። “ዕጣ” የሚለው ቃል የአንድን ሰው ‘ድርሻ’ ወይም ‘ፋንታ’ ለማመልከት ቃል በቃልም ሆነ በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል።–ኢያሱ 14:2መዝ 16:5፤ ምሳሌ 16:33፤ ማቴ 27:35

  • ዙስ

    ብዙ አማልክትን ያመልኩ በነበሩት ግሪካውያን ዘንድ ከሁሉ የላቀ ተደርጎ ይታይ የነበረ አምላክ። የልስጥራ ነዋሪዎች በርናባስ፣ ዙስ እንደሆነ አድርገው አስበው ነበር። በልስጥራ አቅራቢያ፣ “የዙስ ካህናት” እና “የፀሐይ አምላክ ዙስ” የሚሉ ቃላት የሰፈሩባቸው ጥንታዊ የሆኑ የተቀረጹ ጽሑፎች ተገኝተዋል። ጳውሎስ ማልታ ደሴት ላይ የተሳፈረባት መርከብ “የዙስ ልጆች” የሚል ዓርማ የነበራት ሲሆን እነዚህ ልጆች መንትያ ወንድማማቾች የሆኑት ካስተር እና ፖለክስ ናቸው።–ሥራ 14:1228:11

  • ዚፍ

    በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ ላይ ለሁለተኛው ወር፣ በመደበኛው የቀን መቁጠሪያ ላይ ደግሞ ለስምንተኛው ወር የተሰጠ ስም ነው። ከሚያዝያ አጋማሽ እስከ ግንቦት አጋማሽ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። በአይሁዳውያን ታልሙድ ላይና ከባቢሎን ምርኮ በኋላ በተዘጋጁ ሌሎች ጽሑፎች ላይ ኢያር ተብሎ ተጠርቷል። (1ነገ 6:37)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።

  • ዛጎል (ኮራል)

    ከጥቃቅን የባሕር እንስሳት አፅም የተሠራ ድንጋይ የሚመስል ጠንካራ ነገር ነው። በባሕር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ቀይን፣ ነጭንና ጥቁርን ጨምሮ የተለያዩ ቀለማት አሉት። በተለይም ደግሞ ቀይ ባሕር ውስጥ በብዛት ይገኛል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ቀይ ዛጎል በጣም ተፈላጊ የነበረ ሲሆን ዶቃና ሌሎች ጌጣጌጦችን ለመሥራት ያገለግል ነበር።–ምሳሌ 8:11

  • ዝሙት አዳሪ

    ከጋብቻ ውጭ በተለይም ደግሞ ለገንዘብ ሲል የፆታ ግንኙነት የሚፈጽምን ሰው ያመለክታል። (“ዝሙት አዳሪ” ተብሎ የተተረጎመው ፖርኒ የሚለው ግሪክኛ ቃል “መሸጥ” የሚል ፍቺ ካለው ቃል የተገኘ ነው።) ቃሉ በአብዛኛው ዝሙት አዳሪ የሆነችን ሴት ለማመልከት የሚሠራበት ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዝሙት አዳሪ የሆኑ ወንዶችም ተጠቅሰዋል። በሙሴ ሕግ ውስጥ ዝሙት አዳሪነት የተወገዘ ተግባር ነበር፤ እንዲሁም ለዝሙት አዳሪ የተከፈለን ዋጋ መዋጮ አድርጎ ወደ ይሖዋ መቅደስ ማምጣት ተቀባይነት አልነበረውም፤ በዘመኑ የነበሩት አረማውያን ግን የቤተ መቅደስ ዝሙት አዳሪነትን እንደ አንድ የገቢ ምንጭ አድርገው ይመለከቱት ነበር። (ዘዳ 23:17, 18፤ 1ነገ 14:24) ቃሉ አምላክን እናመልካለን እያሉ በሆነ ዓይነት የጣዖት አምልኮ የሚካፈሉ ሕዝቦችን፣ ብሔራትን ወይም ድርጅቶችን ለመግለጽ በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ያህል “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ የምትጠራው ሃይማኖታዊ ተቋም በራእይ መጽሐፍ ላይ አመንዝራ ተብላ ተጠርታለች፤ ይህም የሆነው ሥልጣንና ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ስትል ከዚህ ዓለም ገዢዎች ጋር ተገቢ ያልሆነ ጥምረት ስለመሠረተች ነው።–ራእይ 17:1-518:31ዜና 5:25

  • ዝሙት

    የፆታ ብልግና የሚለውን ተመልከት።

  • የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች

    ሄሮዳውያን በመባልም ይታወቃሉ። በሮማውያን ሥር ያለውን የሄሮድስን ሥርወ መንግሥት የፖለቲካ አቋም የሚደግፍ አንድ ቡድን አባላት ናቸው። ከሰዱቃውያን መካከል አንዳንዶቹ የዚህ ቡድን አባላት ሳይሆኑ አይቀሩም። ሄሮዳውያን ከፈሪሳውያን ጋር በማበር ኢየሱስን ተቃውመውት ነበር።–ማር 3:6

  • የሊባኖስ የተራራ ሰንሰለት

    በሊባኖስ ከሚገኙት ሁለት የተራራ ሰንሰለቶች አንዱ ነው። የሊባኖስ የተራራ ሰንሰለት በስተ ምዕራብ፣ የአማና የተራራ ሰንሰለት ደግሞ በስተ ምሥራቅ ይገኛል። በሁለቱ የተራራ ሰንሰለቶች መካከል ለም የሆነ ረጅም ሸለቆ ይገኛል። የሊባኖስ የተራራ ሰንሰለት የሚጀምረው በሜድትራንያን የባሕር ጠረፍ አካባቢ ሲሆን ከፍታው በአማካይ ከ1,800 እስከ 2,100 ሜትር ይደርሳል። በጥንት ዘመን ሊባኖስ ውስጥ ትላልቅ የሆኑ አርዘ ሊባኖሶች በብዛት ይገኙ ነበር። አርዘ ሊባኖስ በአካባቢው ባሉ ብሔራት ዘንድ ከፍተኛ ተፈላጊነት ነበረው። (ዘዳ 1:7፤ መዝ 29:6፤ 92:12)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ7ን ተመልከት።

  • የሕይወት ዛፍ

    በኤደን የአትክልት ስፍራ ይገኝ የነበረ ዛፍ። መጽሐፍ ቅዱስ የዛፉ ፍሬ በራሱ ሕይወት የመስጠት ችሎታ እንዳለው አይናገርም፤ ከዚህ ይልቅ የሕይወት ዛፍ አምላክ ከፍሬው እንዲበሉ የሚፈቅድላቸው ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ የሰጠውን ዋስትና ያመለክታል።–ዘፍ 2:93:22

  • የመለኪያ ዘንግ

    አንድ የመለኪያ ዘንግ ስድስት ክንድ ርዝመት አለው። በመደበኛው ክንድ ሲሰላ 2.67 ሜትር፣ በረጅሙ ክንድ ሲሰላ ደግሞ 3.11 ሜትር ይሆናል። (ሕዝ 40:3, 5፤ ራእይ 11:1)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • የመላእክት አለቃ

    በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ስያሜ በነጠላ ቁጥር ብቻ መጠቀሱ አንድ የመላእክት አለቃ ብቻ እንዳለ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የመላእክት አለቃ ሚካኤል ብሎ ይጠራዋል።–ዳን 12:1ይሁዳ 9ራእይ 12:7

  • የመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ

    በኤደን የአትክልት ስፍራ ይገኝ የነበረ ዛፍ ሲሆን አምላክ “መልካም” እና “ክፉ” የሆነውን ነገር በተመለከተ ለሰው ልጆች መሥፈርት የማውጣት መብት እንዳለው ለማሳየት የተጠቀመበት ዛፍ ነው።–ዘፍ 2:9, 17

  • የመማጸኛ ከተሞች

    ሳያስበው ሰው የገደለ ግለሰብ ከደም ተበቃዩ ሸሽቶ የሚሸሸግባቸው የሌዋውያን ከተሞች ነበሩ። በይሖዋ መመሪያ መሠረት በመጀመሪያ ሙሴ፣ ከዚያም ኢያሱ በመላዋ የተስፋይቱ ምድር ስድስት ከተሞች ለዚህ ዓላማ እንዲለዩ አድርገው ነበር። ሸሽቶ ለመሸሸግ ወደ እነዚህ ከተሞች የመጣ ሰው እዚያ ሲደርስ በከተማዋ በር ላሉት ሽማግሌዎች ጉዳዩን ካስረዳ በኋላ እንዲገባ ይፈቀድለታል። ሆነ ብለው የሰው ሕይወት ያጠፉ ሰዎች በዚህ ዝግጅት አላግባብ እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ሲባል በከተማዋ ለመሸሸግ ጥገኝነት የሚጠይቀው ሰው ንጹሕ መሆኑን ለማጣራት ግድያው በተፈጸመባት ከተማ ለፍርድ ይቀርባል። ንጹሕ መሆኑ ከተረጋገጠ ወደ መማጸኛ ከተማዋ ተመልሶ እንዲገባና ሕይወቱን ሙሉ ወይም ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ ከከተማዋ ክልል ሳይወጣ እንዲኖር ይደረጋል።–ዘኁ 35:6, 11-15, 22-29ኢያሱ 20:2-8

  • የመሠዊያው ቀንዶች

    በመሠዊያው አራት ጎኖች ላይ ያሉትን እንደ ቀንድ ወጣ ያሉ ጉጦች ያመለክታል። (ዘሌ 8:15፤ 1ነገ 2:28)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ን እና ለ8ን ተመልከት።

  • የመታደስ በዓል

    አንታይከስ ኢፒፋነስ ቤተ መቅደሱን ካረከሰው በኋላ የቤተ መቅደሱን መንጻት አስመልክቶ የሚከበር ዓመታዊ በዓል ነው። በዓሉ መከበር የሚጀምረው በኪስሌው 25 ሲሆን ለስምንት ቀናት ይቆያል።–ዮሐ 10:22

  • የመከራ እንጨት

    ስታውሮስ ለሚለው የግሪክኛ ቃል የተሰጠ ፍቺ፤ ኢየሱስ የተሰቀለበትን ዓይነት ቀጥ ያለ እንጨት ወይም ግንድ ያመለክታል። የግሪክኛው ቃል አረማውያን፣ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ሃይማኖታዊ ምልክት አድርገው ይጠቀሙበት የነበረውን መስቀል እንደሚያመለክት የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም። የግሪክኛው ቃል “የመከራ እንጨት” ተብሎ መተርጎሙ ቃሉ የያዘውን ሙሉ ሐሳብ ለማስተላለፍ ያስችላል፤ ምክንያቱም ስታውሮስ የሚለው ቃል የኢየሱስ ተከታዮች የሚደርስባቸውን መከራ፣ ሥቃይና ውርደት ለማመልከትም ተሠርቶበታል። (ማቴ 16:24፤ ዕብ 12:2)–እንጨት የሚለውን ተመልከት።

  • የመከር በዓል፤ የሳምንታት በዓል

    ጴንጤቆስጤ የሚለውን ተመልከት።

  • የመዝሙር መግለጫ

    በመዝሙር አናት ላይ የሚገኝ መግለጫ ሲሆን የጸሐፊውን ማንነትና መቼቱን ይገልጻል። ከሙዚቃ ጋር የተያያዙ መመሪያዎች የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ የመዝሙሩን ጥቅም ወይም ዓላማ ይጠቁማል።–መዝሙር 3:04:05:06:07:030:038:060:092:0102:0 ላይ የሚገኙትን መግለጫዎች ተመልከት።

  • የመገናኛ ድንኳን

    የሙሴ ድንኳንና በምድረ በዳ ተተክሎ የነበረው ቅዱሱ የማደሪያ ድንኳን በዚህ ስያሜ ይጠሩ ነበር።–ዘፀ 33:739:32

  • የመጠጥ መባ

    በመሠዊያ ላይ የሚፈስና ከአብዛኞቹ መባዎች ጋር አብሮ የሚቀርብ የወይን ጠጅ መባ ነው። ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ ጥቅም ሲል ራሱን ሳይቆጥብ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ለመግለጽ በምሳሌያዊ መንገድ ተጠቅሞበታል።–ዘኁ 15:57ፊልጵ 2:17

  • የመጨረሻዎቹ ቀናት

    ይህን አባባል ጨምሮ “በዘመኑ መጨረሻ” እንደሚሉት ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ የተጠቀሱ አገላለጾች፣ ታሪካዊ ክንውኖች ወደ ፍጻሜያቸው የሚመጡበትን ጊዜ ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። (ሕዝ 38:16፤ ዳን 10:14፤ ሥራ 2:17) እንደ ትንቢቱ ሁኔታ ይህ ጊዜ ጥቂት ወይም ረጅም ዓመታትን የሚሸፍን ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አገላለጽ በዋነኝነት የሚጠቀመው ኢየሱስ በዓይን በማይታይ ሁኔታ በሚገኝበት ወቅት ያለውን ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀናት’ ለማመልከት ነው።–2ጢሞ 3:1ያዕ 5:3፤ 2ጴጥ 3:3

  • የሙሴ ሕግ

    ይሖዋ በ1513 ዓ.ዓ. በሲና ምድረ በዳ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ሕግ ያመለክታል። ሕጉ የሚለው መጠሪያ ብዙውን ጊዜ የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ለማመልከት ተሠርቶበታል።–ኢያሱ 23:6ሉቃስ 24:44

  • የሙዚቀኞች ቡድን መሪ

    በመዝሙር መጽሐፍ ላይ ከተሠራበት አንጻር የዕብራይስጡ ቃል መዝሙሮችን የሚያቀናብር፣ ሙዚቃውን የሚመራ እንዲሁም ሌዋውያን ዘማሪዎችን መዝሙር የሚያለማምድና የሚያሠለጥን አልፎ ተርፎም በሕዝብ ፊት የሚቀርቡ መዝሙሮችን የሚመራን ሰው የሚያመለክት ይመስላል።–መዝ 4:05:0

  • የሚቃጠል መባ

    ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ስጦታ ሆኖ እንዲቀርብ በመሠዊያ ላይ የሚቃጠል የእንስሳ መሥዋዕት ሲሆን ግለሰቡ መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበው እንስሳ ላይ (በሬ፣ አውራ በግ፣ ተባዕት ፍየል፣ ርግብ ወይም የዋኖስ ጫጩት ሊሆን ይችላል) የትኛውንም ብልት ለራሱ አያስቀርም።–ዘፀ 29:18ዘሌ 6:9

  • የሚወዘወዝ መባ

    አንድ የይሖዋ አምላኪ የሚያቀርበው መባ ሲሆን ግለሰቡ መሥዋዕቱን ይዞ ወዲያና ወዲህ በሚወዘውዝበት ጊዜ ካህኑ እጆቹን ከሥር ይዘረጋል፤ ወይም ካህኑ ራሱ መባውን ይወዘውዛል። ይህ ድርጊት መሥዋዕት ሆነው የተሰጡት መባዎች ለይሖዋ እንደቀረቡ ያሳያል።–ዘሌ 7:30

  • የማምለኪያ ዓምድ

    ብዙውን ጊዜ ከድንጋይ የተቀረጸ ቀጥ ያለ ዓምድ ሲሆን ባአልን ወይም ሌሎች የሐሰት አማልክትን የሚወክል በወንድ ብልት ቅርጽ የተሠራ ሐውልት እንደሆነ ይታመናል።–ዘፀ 23:24

  • የማምለኪያ ግንድ

    የዕብራይስጡ ቃል (አሼራህ) (1) አሼራህ የተባለችውን የከነአናውያን የመራባት ሴት አምላክ የሚወክልን የማምለኪያ ግንድ ወይም (2) የራሷን የአሼራህን ምስል የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። የማምለኪያ ግንዶቹ ቀጥ ብለው የቆሙና ቢያንስ በከፊል ከእንጨት የተሠሩ ሳይሆኑ አይቀሩም። ይህ አገላለጽ ያልተጠረቡ ግንዶችን አልፎ ተርፎም ባሉበት ያሉ ዛፎችን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።–ዘዳ 16:21መሳ 6:26፤ 1ነገ 15:13

  • የማኅተም ቀለበት

    በጣት ላይ የሚጠለቅ ወይም በክር የሚንጠለጠል (ምናልባትም አንገት ላይ ሊሆን ይችላል) የማኅተም ዓይነት ነው። የአንድን ገዢ ወይም ሹም ሥልጣን የሚያሳይ ምልክት ሆኖ ያገለግል ነበር። (ዘፍ 41:42)–ማኅተም የሚለውን ተመልከት።

  • የማዕዘን ድንጋይ

    የአንድ ሕንፃ ሁለት ግድግዳዎች በሚጋጠሙበት ማዕዘን ላይ የሚቀመጥና ግድግዳዎቹን በማያያዝ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ድንጋይ ነው። ዋናው የማዕዘን ድንጋይ ደግሞ በሕንፃው መሠረት ላይ የሚቀመጠው የማዕዘን ድንጋይ ነው፤ በተለይም ትላልቅ ሕንፃዎችንና የከተማ ቅጥሮችን ለመገንባት ጠንካራ የሆነ የማዕዘን ድንጋይ ይመረጥ ነበር። ይህ ሐረግ በምሳሌያዊ መንገድ የምድርን አመሠራረት ለመግለጽ የተሠራበት ሲሆን ኢየሱስ በመንፈሳዊ ቤት ለተመሰለው የክርስቲያን ጉባኤ የማዕዘን “የመሠረት ድንጋይ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል።–ኤፌ 2:20ኢዮብ 38:6

  • የማደሪያ ድንኳን

    እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ለአምልኮ ይጠቀሙበትና ከቦታ ወደ ቦታ ይዘውት ይጓዙ የነበረ ድንኳን። የአምላክን መገኘት ይወክል የነበረው የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት በውስጡ ይቀመጥ የነበረ ከመሆኑም ሌላ መሥዋዕትና አምልኮ የሚቀርብበት ቦታ ሆኖ አገልግሏል። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ‘የመገናኛ ድንኳን’ ተብሎ ተጠርቷል። ድንኳኑ ከእንጨት የተሠሩ ተሸካሚዎች የነበሩት ሲሆን ኪሩቦች የተጠለፉበት ከበፍታ የተሠራ መሸፈኛ ይለብስ ነበር። የማደሪያው ድንኳን ሁለት ክፍሎች ነበሩት፤ የመጀመሪያው ቅድስት፣ ሁለተኛው ደግሞ ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ ይጠራል። (ኢያሱ 18:1፤ ዘፀ 25:9)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ን ተመልከት።

  • የምሕረት ስጦታ፤ ምጽዋት

    የተቸገረን ሰው ለመርዳት የሚሰጥ ስጦታን ያመለክታል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በቀጥታ ባይጠቀስም ሕጉ እስራኤላውያን ድሆችን ለመርዳት ማድረግ ያለባቸውን ነገር በተመለከተ ዝርዝር መመሪያ ይሰጣል።–ማቴ 6:2

  • የምስጋና መባ

    አምላክ ላደረጋቸው ነገሮችና ላሳየው ታማኝ ፍቅር እሱን ለማመስገን የሚቀርብ የኅብረት መባ ነው። በዚህ ወቅት መባ ሆኖ የሚቀርበው እንስሳ ሥጋ እንዲሁም እርሾ የገባበትም ሆነ ያልገባበት ቂጣ ይበላ ነበር። ሥጋው በዚያው ቀን መበላት ነበረበት።–2ዜና 29:31

  • የሥርዓቱ መደምደሚያ

    በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ሥርዓት ወደ ፍጻሜው የሚያመራበትን ጊዜ ያመለክታል። ይህ ጊዜ ክርስቶስ ከሚገኝበት ዘመን ጋር ተመሳሳይ ነው። መላእክት ኢየሱስ በሚሰጣቸው መመሪያ መሠረት “ክፉዎችን ከጻድቃን ይለያሉ።” (ማቴ 13:40-42, 49) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሥርዓቱ “መደምደሚያ” መቼ እንደሚሆን ለማወቅ ጓጉተው ነበር። (ማቴ 24:3) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት ለተከታዮቹ እስከዚያ ዘመን ድረስ ከእነሱ ጋር እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸዋል።–ማቴ 28:20

  • የሥጋ ደዌ

    አስከፊ የሆነ የቆዳ በሽታ ነው። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰው የሥጋ ደዌ በዘመናችን በዚህ ስም ከሚጠራው በሽታ የተለየ ሲሆን ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ልብስንና ቤትን ሊበክል የሚችል ነበር።–ዘሌ 14:54, 55ሉቃስ 5:12

  • የሮም አገረ ገዢ

    በሮም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በሚተዳደር አንድ አውራጃ ላይ ዋና ገዢ ሆኖ የተሾመ ሰው ነው። የመፍረድም ሆነ የጦር ሠራዊቱን የመቆጣጠር ሥልጣን ነበረው፤ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አገረ ገዢው የሚያከናውናቸውን ነገሮች የሚገመግም ቢሆንም ገዢው በሚያስተዳድረው አውራጃ ላይ የፈለገውን የማድረግ ሥልጣን ነበረው።–ሥራ 13:718:12

  • የሰለሞን መተላለፊያ

    በኢየሱስ ዘመን በውጨኛው ግቢ በስተ ምሥራቅ በኩል ይገኝ የነበረውን መጠለያ ያለው መተላለፊያ ያመለክታል፤ ብዙዎች ይህ መተላለፊያ ሰለሞን ያሠራው ቤተ መቅደስ በወደመበት ወቅት ከመጥፋት የተረፈ እንደሆነ ያምናሉ። ኢየሱስ ‘በክረምት ወቅት’ በዚያ እንዳለፈና የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለአምልኮ እዚያ ይሰበሰቡ እንደነበር ተጠቅሷል። (ዮሐ 10:22, 23፤ ሥራ 5:12)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ11ን ተመልከት።

  • የሰማይ ንግሥት

    በኤርምያስ ዘመን፣ ከሃዲ የሆኑ እስራኤላውያን ያመልኳት የነበረች ጣዖት ናት። አንዳንዶች ይህች ጣዖት ባቢሎናውያን ያመልኳት ከነበረችው ከኢሽታር (ከአስታርቲ) ጋር አንድ እንደሆነች ያምናሉ። የእሷ አቻ የሆነችው የሱሜሪያውያን ጣዖት ኢናና ትባል የነበረ ሲሆን ትርጉሙ “የሰማይ ንግሥት” ማለት ነው። ይህች ጣዖት የሰማይ ንግሥት ተብላ ከመጠራቷም በተጨማሪ የመራባት ሴት አምላክ እንደሆነች ተደርጎ ይታመን ነበር። አስታርቲም በአንድ የግብፃውያን የተቀረጸ ጽሑፍ ላይ “የሰማይ እመቤት” ተብላ ተጠርታለች።–ኤር 44:19

  • የሰው ልጅ

    በወንጌሎች ውስጥ 80 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። ይህ መጠሪያ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማመልከት የተሠራበት ሲሆን ይህም ኢየሱስ በምድር ላይ ሰው ሆኖ በተወለደበት ጊዜ ሥጋ የለበሰ መንፈሳዊ ፍጡር ሳይሆን በእርግጥ ሰው እንደነበር የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም ይህ ሐረግ ኢየሱስ በዳንኤል 7:13, 14 ላይ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ እንደሚያደርግ የሚጠቁም ነው። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሕዝቅኤልና ዳንኤልም በዚህ መጠሪያ ተጠርተዋል፤ ይህም የሚናገሩት መልእክት ምንጭ በሆነው በአምላክና ሟች በሆኑት በእነዚህ ቃል አቀባዮቹ መካከል ያለውን ልዩነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል።–ሕዝ 3:17ዳን 8:17፤ ማቴ 19:28፤ 20:28

  • የስርየት መክደኛ

    የቃል ኪዳኑ ታቦት መክደኛ ሲሆን ሊቀ ካህናቱ በስርየት ቀን የኃጢአት መባ ሆኖ የቀረበውን እንስሳ ደም በመክደኛው ላይ ይረጨዋል። የዕብራይስጡ ቃል “(ኃጢአትን) መሸፈን፣” ምናልባትም “(ኃጢአትን) መደምሰስ” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ካለው ግስ የተገኘ ነው። የታቦቱ መክደኛ ሙሉ በሙሉ ከወርቅ የተሠራ ሲሆን በመክደኛው ጫፍና ጫፍ ላይ ሁለት የወርቅ ኪሩቦች ይገኛሉ። አንዳንድ ጊዜ “መክደኛው” ተብሎ ተጠርቷል። (ዘፀ 25:17-22፤ 1ዜና 28:11፤ ዕብ 9:5)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ን ተመልከት።

  • የስርየት ቀን

    እስራኤላውያን የሚያከብሩት ታላቅ በዓል ሲሆን ዮም ኪፐር ተብሎም ይጠራል፤ (ይህ ስያሜ የተገኘው ዮም ሃክ ኪፕ ፑሪም፣ “የመሸፈኛ ቀን” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።) በዓሉ የሚከበረው በኤታኒም ወር 10ኛ ቀን ላይ ነው። ሊቀ ካህናቱ ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ቤተ መቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን የሚገባው በዚህ ቀን ብቻ ነበር። በዚያም ለራሱ ኃጢአት፣ ለሌሎቹ ሌዋውያን ኃጢአትና ለሕዝቡ ኃጢአት የመሥዋዕቱን ደም ያቀርባል። ቀኑ ቅዱስ ጉባኤ የሚደረግበትና የሚጾምበት ወቅት እንዲሁም ከመደበኛ ሥራ የሚታረፍበት ሰንበት ነው።–ዘሌ 23:27, 28

  • የስእለት መባ

    ከአንዳንድ ስእለቶች ጋር በተያያዘ በፈቃደኝነት የሚቀርብ መባ።–ዘሌ 23:381ሳሙ 1:21

  • የቂጣ በዓል

    እስራኤላውያን ከሚያከብሯቸው ሦስት ዋና ዋና በዓላት መካከል የመጀመሪያው ነው። በዓሉ የሚጀምረው ከፋሲካ ቀን በኋላ ማለትም በኒሳን 15 ሲሆን ለሰባት ቀናት ይቆያል። እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ የወጡበትን ጊዜ ለማሰብ ሲባል በዚህ ወቅት ቂጣ ብቻ ይበሉ ነበር።–ዘፀ 23:15ማር 14:1

  • የቃል ኪዳኑ ታቦት

    ከግራር እንጨት ተሠርቶ በወርቅ የተለበጠ ሣጥን ሲሆን በማደሪያ ድንኳኑ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሰለሞን በገነባው ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ይቀመጥ ነበር። ፊት ለፊት የሚተያዩ ሁለት ኪሩቦች ያሉበት ከወርቅ የተሠራ መክደኛ ነበረው። አሥሩን ትእዛዛት የያዙት ሁለት ጽላቶች በውስጡ ይቀመጡ ነበር። (ዘዳ 31:26፤ 1ነገ 6:19፤ ዕብ 9:4)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ንለ8ን ተመልከት።

  • የበላይ ተመልካች

    በዋነኝነት ጉባኤውን የመንከባከብና የመጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበትን ሰው ያመለክታል። ኤጲስቆጶስ የሚለው ግሪክኛ ቃል መሠረታዊ ሐሳብ አንድን ነገር ከጉዳት ለመጠበቅ ሲባል በቅርብ መከታተልን የሚያመለክት ነው። “የበላይ ተመልካች” እና “ሽማግሌ” (ፕሪስባይቴሮስ) የሚሉት መጠሪያዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ተመሳሳይ የኃላፊነት ቦታን የሚያመለክቱ ሲሆኑ “ሽማግሌ” የሚለው መጠሪያ፣ የተሾመው ግለሰብ በመንፈሳዊ ጎልማሳ መሆኑን፣ “የበላይ ተመልካች” የሚለው መጠሪያ ደግሞ ይህ ግለሰብ የተጣለበትን ኃላፊነት ጎላ አድርጎ ያሳያል።–ሥራ 20:281ጢሞ 3:2-7፤ 1ጴጥ 5:2

  • የበደል መባ

    አንድ ሰው ለሠራው ኃጢአት የሚያቀርበው መሥዋዕት ነው። ከሌሎቹ የኃጢአት መባዎች የተወሰነ ልዩነት አለው፤ ይህ መባ የሚቀርበው ኃጢአት ሠርቶ ንስሐ የገባው ሰው ያጣቸውን ከቃል ኪዳኑ ጋር የተያያዙ አንዳንድ መብቶች መልሶ እንዲያገኝና ቅጣት ይደርስብኛል ከሚል ስጋት እንዲገላገል ለማድረግ ነው።–ዘሌ 7:3719:22ኢሳ 53:10

  • የተርሴስ መርከቦች

    መጀመሪያ ላይ ወደ ጥንቷ ተርሴስ (ዘመናዊቷ ስፔን) ይጓዙ የነበሩ መርከቦች ይጠሩበት የነበረ ስያሜ ነው። ከጊዜ በኋላ ግን ረጅም ርቀት የሚጓዙ ትላልቅ መርከቦች በዚህ ስያሜ መጠራት የጀመሩ ይመስላል። ሰለሞንና ኢዮሳፍጥ እነዚህን መርከቦች ለንግድ ተጠቅመውባቸዋል።–1ነገ 9:2610:2222:48

  • የኃጢአት መባ

    አንድ ሰው ፍጹም ባልሆነው ሥጋው ድክመት ምክንያት ባለማወቅ ለፈጸመው ኃጢአት የሚያቀርበው መሥዋዕት ነው። ኃጢአቱ የሚሰረይለት ሰው እንደ አቅሙና እንደ ሁኔታው ከበሬ አንስቶ እስከ ርግብ ድረስ የቻለውን እንስሳ መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ይችላል።–ዘሌ 4:27, 29ዕብ 10:8

  • የኅብረት መሥዋዕት

    ከይሖዋ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር ሲባል ለእሱ የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ሰው፣ ቤተሰቡ፣ የመሥዋዕቱን ሥርዓት የሚያከናውነው ካህንና በወቅቱ በሥራ ላይ ያሉት ካህናት በሙሉ ከመሥዋዕቱ ይካፈላሉ። ይሖዋ በመሠዊያው ላይ የሚጨሰውን ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ያለው ስብ እንደተቀበለ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ሕይወትን የሚወክለው ደምም ቢሆን ለእሱ ይሰጣል። ካህናቱ፣ መሥዋዕቱን ያቀረቡት ሰዎችና ይሖዋ በአንድ ማዕድ ዙሪያ ተቀምጠው እንደተመገቡ ስለሚቆጠር በመካከላቸው ሰላማዊ ግንኙነት መኖሩን ይጠቁማል።–ዘሌ 7:29, 32ዘዳ 27:7

  • የናዝሬት ሰው

    ኢየሱስ ከናዝሬት ከተማ የመጣ በመሆኑ የተሰጠው ስያሜ ነው። ይህ ቃል በኢሳይያስ 11:1 ላይ “ቡቃያ” ተብሎ ከተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተዛማጅነት ሳይኖረው አይቀርም። ከጊዜ በኋላ የኢየሱስ ተከታዮች መጠሪያ ሆኖም አገልግሏል።–ማቴ 2:23ሥራ 24:5

  • የንጋት ኮከብ

    “አጥቢያ ኮከብ” ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት በምሥራቃዊው አድማስ ላይ የሚታየው የመጨረሻው ኮከብ ሲሆን አዲስ ቀን መጥባቱን ያበስራል።–ራእይ 22:162ጴጥ 1:19

  • የአምላክ መንግሥት

    ይህ ሐረግ በዋነኝነት የተሠራበት ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ በሚያስተዳድረው መንግሥት የሚወከለውን የአምላክን ሉዓላዊነት ለማመልከት ነው።–ማቴ 12:28ሉቃስ 4:43፤ 1ቆሮ 15:50

  • የአሮን ልጆች

    የሌዊ የልጅ ልጅ የሆነውና በሙሴ ሕግ ሥር የመጀመሪያው ሊቀ ካህናት ሆኖ እንዲያገለግል የተመረጠው የአሮን ዘሮች ናቸው። የአሮን ልጆች በማደሪያ ድንኳኑና በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከክህነት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ያከናውኑ ነበር።–1ዜና 23:28

  • የአውራጃ ገዢ

    በባቢሎንና በፋርስ ግዛቶች ውስጥ እንደራሴ ሆኖ የሚሾም ሰው ነው። አንድን የአውራጃ ገዢ፣ ዋና አስተዳዳሪ አድርጎ የሚሾመው ንጉሡ ነበር።–ዕዝራ 8:36ዳን 6:1

  • የኢስጦይክ ፈላስፎች

    ደስታ የሚገኘው አሳማኝ ከሆኑ ነገሮችና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ በመኖር ነው የሚል እምነት የሚያራምዱ የግሪክ ፈላስፎች ናቸው። በእነሱ አስተሳሰብ እውነተኛ ጥበብ ያለው ሰው ለሥቃይም ሆነ ለደስታ ምንም ቦታ አይሰጥም።–ሥራ 17:18

  • የኤፊቆሮስ ፈላስፎች

    ኤፊቆሮስ የተባለው የግሪክ ፈላስፋ (341-270 ዓ.ዓ.) ተከታዮች ናቸው። የእነዚህ ሰዎች ፍልስፍና ‘የአንድ ሰው ዋነኛ የሕይወት ግብ ራሱን ማስደሰት ነው’ በሚለው ሐሳብ ላይ ያተኮረ ነበር።–ሥራ 17:18

  • የእሳት ሐይቅ

    ‘በእሳትና በድኝ የሚቃጠልን’ ምሳሌያዊ ቦታ የሚያመለክት ሲሆን ‘ሁለተኛው ሞት’ ተብሎም ተጠርቷል። ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች፣ ዲያብሎስ አልፎ ተርፎም ሞትና መቃብር (ወይም ሐዲስ) ወደዚህ ቦታ ይወረወራሉ። እሳት ምንም ጉዳት ሊያደርስባቸው የማይችል መንፈሳዊ ፍጥረታት እንዲሁም ሞትና ሐዲስ እዚህ ሐይቅ ውስጥ እንደሚጣሉ መገለጹ ይህ የእሳት ሐይቅ ዘላለማዊ የሥቃይ ቦታ ሳይሆን ዘላለማዊ ጥፋትን የሚያመለክት ምሳሌያዊ አነጋገር መሆኑን ያሳያል።–ራእይ 19:2020:14, 1521:8

  • የእሳት ማጥፊያ

    በማደሪያ ድንኳኑና በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ከወርቅ ወይም ከመዳብ የተሠራ ዕቃ ነው። የመብራት ክር ለመቀንጠብ የሚያገለግል መቀስ የሚመስል ነገር ሳይሆን አይቀርም።–2ነገ 25:14

  • የከለዳውያን ምድር፤ ከለዳውያን

    በጤግሮስና በኤፍራጥስ ወንዞች አካባቢ የሚገኘውን ደለላማ መሬትና በዚያ ይኖሩ የነበሩትን ጥንታዊ ነዋሪዎች ያመለክታል፤ ከጊዜ በኋላ ይህ መጠሪያ መላውን የባቢሎን ምድርና ሕዝቧን ለማመልከት ተሠርቶበታል። በተጨማሪም “ከለዳውያን” የሚለው መጠሪያ ሳይንስን፣ ታሪክን፣ ቋንቋንና ሥነ ፈለክን የሚያጠናውን ሆኖም በአስማትና በኮከብ ቆጠራ የሚካፈለውን የተማረ የኅብረተሰብ ክፍል ያመለክታል።–ዕዝራ 5:12ዳን 4:7፤ ሥራ 7:4

  • የከበሩ ድንጋዮች

    ለሼም፦ ምንነቱ በእርግጠኝነት የማይታወቅ የከበረ ድንጋይ ሲሆን አምበርን፣ ያክንትን፣ ኦፓልን ወይም ቱርማሊንን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። መረግድ፦ በውስጡ ለማየት የሚያስችል አረንጓዴ ድንጋይ። ሩቢ፦ ቀይ ቀለም ያለው በውስጡ ለማየት የሚያስችል ድንጋይ። ሰርድዮን፦ ቀይ ቡኒ ቀለም ያለው ብርሃን የሚያስተላልፍ ድንጋይ። ሰርዶንክስ፦ ነጭና በውስጡ ለማየት የሚያስችል ቀይ ቀለም ያላቸው ንብርብሮች አሉት፤ አንዳንድ ጊዜ በቀዩ ፋንታ ወርቅማ ወይም ቡናማ ቀለም ሊኖረው ይችላል። ሰንፔር፦ ሰማያዊ ቀለም ያለው ሳይሆን አይቀርም። በሉር፦ አብዛኛውን ጊዜ ሰማያዊ የተቀላቀለበት አረንጓዴ ቀለም አለው። ቢረሌ፦ አብዛኛውን ጊዜ ቢጫማ አረንጓዴ ቀለም ያለው፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ሌሎች ቀለማት ሊኖሩት ወይም ቀለም የሌለው ሊሆን ይችላል። ቶጳዝዮን፦ ምንም ቀለም የሌለው ወይም የተለያዩ ቀለማት ያሉት ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ወደ ቢጫ ያደላ ቀለም አለው። አሜቴስጢኖስ፦ ሐምራዊ ወይም ወይን ጠጅ ቀለም አለው። አካትም፦ ብዙ ቀለማት ያሉት፤ ብርሃን የሚያስተላልፍ ሆኖም ጥርት ያለ ምስል ማየት የማይቻልበት። ኢያስጲድ፦ በዘመናችን በዚህ ስም የሚታወቀው ማዕድን በተለያዩ ቀለማት የሚገኝ ጥርት ያለ ምስል ማየት የማይቻልበት ድንጋይ ነው። ራእይ 21:11 ላይ ብርሃን የሚያስተላልፍ ድንጋይ ተጠቅሷል፤ አንዳንዶች እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ቃል አልማዝን እንደሚያመለክት ይናገራሉ። ኦኒክስ፦ ጠንካራ የሆነ የአካትም ዓይነት ወይም በቀለማት የተዋበ የኬልቄዶን ዓይነት ድንጋይ ነው። የኦኒክስ ድንጋይ በነጭ መደብ ላይ ጥቁር፣ ቡኒ፣ ቀይ፣ ግራጫ ወይም አረንጓዴ ቀለም ያለበት ሊሆን ይችላል። የሊቀ ካህናቱን ልብስ ለመሥራት ካገለገሉት ነገሮች አንዱ ነው። ኬልቄዶን፦ የተለያዩ ቀለማት ያሉት፣ በውስጡ ለማየት የሚያስችል ወይም ብርሃን የሚያስተላልፍ ድንጋይ። ክሪስታል፦ ጥርት ያለና ምንም ቀለም የሌለው ድንጋይ። ክርስቲሎቤ፦ ቢጫ ወይም አረንጓዴ ቀለም ያለው በውስጡ ለማየት የሚያስችል ወይም ብርሃን የሚያስተላልፍ ድንጋይ። ክርስጵራስስ፦ ብርሃን የሚያስተላልፍ ቢጫማ አረንጓዴ ቀለም ያለው ድንጋይ። ያክንት፦ ጥቁር ሰማያዊ ቀለም አለው። ጄድ፦ አብዛኛውን ጊዜ አረንጓዴ ቀለም ያለው ሲሆን በሌሎች በርካታ ቀለሞችም ይገኛል፤ ብርሃን የሚያስተላልፍ ሆኖም ጥርት ያለ ምስል ማየት የማይቻልበት።–ዘፀ 28:9, 12, 17-201ዜና 29:2፤ ኢዮብ 28:16፤ ራእይ 21:19, 20

  • የከብት መውጊያ

    ገበሬዎች አንድን ከብት ወደ ፊት እንዲሄድ ለመቀስቀስ የሚጠቀሙበት ጫፉ ላይ ሹል ብረት ያለው ዘንግ ነው። የከብት መውጊያ አንድ ሰው የተሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር በተግባር እንዲያውል ሊያነሳሳው ከሚችል የጠቢብ ሰው ቃል ጋር ተመሳስሏል። “መውጊያውን መቃወም” የሚለው አገላለጽ አንድ ዓመፀኛ በሬ ሲወጋ መውጊያውን ለመራገጥ የሚያደርገውን ሙከራ የሚያሳይ ሲሆን እንዲህ ማድረጉ በሬውን ለበለጠ ጉዳት ይዳርገዋል።–ሥራ 26:14መሳ 3:31

  • የካህናት አለቃ

    በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ሊቀ ካህናት” ከሚለው ስያሜ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ደግሞ “የካህናት አለቃ” የሚለው አገላለጽ በክህነት አገልግሎት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸውን ሰዎች እንደሚያመለክት ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ በተጨማሪም ከክህነት ሥራቸው የተገለሉ ሊቀ ካህናትንና የ24ቱን የክህነት ምድቦች መሪዎች ሳያመለክት አይቀርም።–2ዜና 26:20ዕዝራ 7:5፤ ማቴ 2:4፤ ማር 8:31

  • የክብር ዘብ

    የሮም ንጉሠ ነገሥት የግል ጠባቂ እንዲሆን የተመደበ ወታደራዊ ቡድን ነው። ይህ የክብር ዘብ ንጉሡ በሥልጣን ላይ እንዲቆይም ሆነ ከሥልጣን እንዲወርድ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት የፖለቲካ ኃይል ነበር።–ፊልጵ 1:13

  • የወር መባቻ፤ አዲስ ጨረቃ

    በአይሁዳውያን የቀን መቁጠሪያ ላይ የወሩ የመጀመሪያ ቀን ሲሆን ሰዎች አንድ ላይ ተሰብስበው በመደሰትና መሥዋዕት በማቅረብ ይህን ቀን ያከብሩታል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ቀኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ብሔራዊ በዓል ሆነ፤ በዚህ ቀን ሰዎች ሥራ አይሠሩም ነበር።–ዘኁ 10:102ዜና 8:13ቆላ 2:16

  • የወንድምን ሚስት ማግባት

    ከጊዜ በኋላ በሙሴ ሕግ ውስጥ የተካተተ ልማድ ሲሆን አንድ ሰው የሥጋ ወንድሙ፣ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ከሞተ የሟቹን ሚስት አግብቶ ልጆች በመውለድ የወንድሙ የዘር ሐረግ እንዳይቋረጥ ማድረግ ይጠበቅበት ነበር። የዋርሳነት ግዴታ በመባልም ይታወቃል።–ዘፍ 38:8ዘዳ 25:5

  • የወይን መጭመቂያ

    አብዛኛውን ጊዜ፣ በተፈጥሮ ከሚገኝ የኖራ ድንጋይ ተፈልፍለው የሚሠሩ ሁለት ጉድጓዶች የሚኖሩት ሲሆን አንደኛው ከሌላው ከፍ እንዲል ተደርጎ ይሠራል፤ እንዲሁም ሁለቱን ጉድጓዶች የሚያገናኝ ትንሽ ቦይ ይኖራል። ከፍ ብሎ በተሠራው ጉድጓድ ውስጥ የወይን ፍሬዎቹ ሲረገጡ ጭማቂው ከታች ወዳለው ጉድጓድ ይፈስሳል። ቃሉ የአምላክን ፍርድ ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል።–ኢሳ 5:2ራእይ 19:15

  • የወይን ጠጅ አቁማዳ

    እንደ ፍየል ወይም በግ ካለ እንስሳ ሙሉ ቆዳ የሚሠራና የወይን ጠጅ ለማስቀመጥ የሚያገለግል መያዣ። የወይን ጠጅ እየፈላ ሲሄድ የሚያመነጨው የካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ አቁማዳውን ስለሚወጥረው የወይን ጠጅ የሚቀመጠው በአዲስ አቁማዳ ነበር። አዲስ አቁማዳ የመለጠጥ ባሕርይ ሲኖረው ያረጀው ግን የቆረፈደ በመሆኑ የወይን ጠጁ ሲወጥረው ይፈነዳል።–ኢያሱ 9:4ማቴ 9:17

  • የወፍጮ ድንጋይ

    እህል ለመፍጨት የሚያገለግል በሌላ ተመሳሳይ ክብ ድንጋይ ላይ የሚቀመጥ ክብ ድንጋይ ነው። በታችኛው ድንጋይ መሃል ላይ የሚሰካው እንጨት ለላይኛው ድንጋይ መሽከርከሪያ ሆኖ ያገለግላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሴቶች እህል የሚፈጩበት በእጅ የሚሽከረከር የወፍጮ ድንጋይ በአብዛኞቹ ቤቶች ውስጥ ይገኝ ነበር። የወፍጮ ድንጋይ አንድ ቤተሰብ የዕለት ምግቡን ለማዘጋጀት የሚጠቀምበት ወሳኝ መሣሪያ ስለነበር የሙሴ ሕግ የወፍጮ ድንጋዩንም ሆነ መጁን መያዣ አድርጎ መውሰድን ይከለክል ነበር። በዚያ ዘመን በእንስሳት ጉልበት የሚንቀሳቀሱ በተመሳሳይ መንገድ የሚሠሩ ትላልቅ የወፍጮ ድንጋዮችም ነበሩ።–ዘዳ 24:6ማር 9:42

  • የዓምድ ራስ

    በዓምድ አናት ላይ የሚገኝ ጌጥ። በሰለሞን ቤተ መቅደስ መግቢያ ላይ በነበሩት ያኪንና ቦዔዝ በተባሉት ሁለት ዓምዶች አናት ላይ ትላልቅ የዓምድ ራሶች ነበሩ። (1ነገ 7:16)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ8ን ተመልከት።

  • የዝግጅት ቀን

    ከሰንበት ቀን በፊት ላለው ቀን የተሰጠ ስያሜ ሲሆን በዚህ ዕለት አይሁዳውያን አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን ያደርጉ ነበር። ዓርብ ዕለት ፀሐይ ስትጠልቅና የሰንበት ቀን ሲጀምር ይህ ቀን ያበቃል። በአይሁዳውያን አንድ ቀን የሚባለው ከምሽት አንስቶ እስከ ቀጣዩ ቀን ምሽት ያለው ጊዜ ነው።–ማር 15:42ሉቃስ 23:54

  • የደረት ኪስ

    የእስራኤል ሊቀ ካህናት ወደ ቅድስቱ በሚገባበት ጊዜ ሁሉ በደረቱ ላይ የሚያደርገው በከበሩ ድንጋዮች ያጌጠ ኪስ ነው። የይሖዋን ፍርድ ለማወቅ የሚያገለግሉት ኡሪምና ቱሚም በዚህ ኪስ ውስጥ ይቀመጡ ስለነበር ‘የፍርድ የደረት ኪስ’ ተብሎም ተጠርቷል። (ዘፀ 28:15-30)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ን ተመልከት።

  • የዱቱን

    በመዝሙር 3962 እና 77 አናት ላይ ባሉት መግለጫዎች ውስጥ የሚገኝ ትርጉሙ በውል የማይታወቅ ቃል ነው። እነዚህ መግለጫዎች የመዝሙሩን ስልት ምናልባትም አዘማመሩን ወይም የሙዚቃ መሣሪያውን የሚገልጹ መመሪያዎችን የያዙ ሳይሆኑ አይቀሩም። የዱቱን የሚባል ሌዋዊ ዘማሪ ስለነበር ይህ የአዘማመር ስልት ወይም የሙዚቃ መሣሪያ ከእሱ ወይም ከወንዶች ልጆቹ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።

  • የዳስ በዓል

    የመከር በዓል ተብሎም ይጠራል። በዓሉ የሚከበረው ከኤታኒም 15 እስከ 21 ነበር። ይህ በዓል የሚከበረው እስራኤላውያን በዓመቱ የእርሻ ወቅት ማብቂያ ላይ ምርት በሚሰበስቡበት ጊዜ ላይ የነበረ ሲሆን ወቅቱ እስራኤላውያን የሚደሰቱበትና ይሖዋ አዝመራቸውን ስለባረከላቸው ለእሱ ምስጋና የሚያቀርቡበት ጊዜ ነበር። ሕዝቡ ከግብፅ ነፃ የወጣበትን ጊዜ ለማስታወስ በዓሉ በሚከበርባቸው ቀናት ሁሉ ዳስ ውስጥ ይቀመጥ ነበር። እስራኤላውያን ወንዶች በዓመት ሦስት ጊዜ በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም መውጣት የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህ በዓል ከእነዚህ ወቅቶች አንዱ ነው።–ዘሌ 23:34ዕዝራ 3:4

  • የዳዊት ልጅ

    ይህ ሐረግ ብዙውን ጊዜ ኢየሱስን ለማመልከት የተሠራበት ሲሆን ኢየሱስ ከዳዊት የዘር ሐረግ በሚመጣ ሰው ፍጻሜውን የሚያገኘው የመንግሥት ቃል ኪዳን ወራሽ መሆኑን ጎላ አድርጎ ይገልጻል።–ማቴ 12:2321:9

  • የዳዊት ከተማ

    ዳዊት የኢያቡስን ከተማ ከያዛትና ቤተ መንግሥቱን በዚያ ከገነባ በኋላ ለከተማዋ የተሰጣት ስያሜ ነው። ጽዮን ተብላም ትጠራለች። የዳዊት ከተማ ተብሎ ይጠራ የነበረው የኢየሩሳሌም ደቡባዊ ምሥራቅ ክፍልና አሮጌው ከተማ ነው።–2ሳሙ 5:71ዜና 11:4, 5

  • የጉባኤ አገልጋይ

    ዲያኮኖስ ከሚለው ግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ሲሆን ይህ ቃል በብዙ ቦታዎች ላይ “አገልጋይ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። “የጉባኤ አገልጋዮች” የሚለው መጠሪያ በጉባኤ ውስጥ ላለው የሽማግሌዎች አካል ድጋፍ የሚሰጡ ወንዶችን ያመለክታል። እነዚህ ወንዶች ይህን የአገልግሎት መብት ለማግኘት ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።–1ጢሞ 3:8-10, 12

  • የጌታ ራት

    የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚወክል ቂጣና ወይን ጠጅ የሚቀርብበት ራት ሲሆን የኢየሱስ ሞት የሚታሰብበት በዓል ነው። ይህን በዓል ክርስቲያኖች እንዲያስቡትና እንዲያከብሩት መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያዝዝ “መታሰቢያ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው።–1ቆሮ 11:20, 23-26

  • የጦር ትጥቅ

    ወታደሮች ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል የሚለብሱት ትጥቅ ሲሆን የራስ ቁርን፣ ጥሩርን፣ ቀበቶን፣ ገምባሌንና ጋሻን ያካትታል።–1ሳሙ 31:9፤ ኤፌ 6:13-17

  • የፆታ ብልግና፤ ዝሙት

    ፖርኒያ ከሚለው ግሪክኛ ቃል የተወሰደ ሲሆን ይህ ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተሠራበት አምላክ የሚከለክላቸውን አንዳንድ ወሲባዊ ድርጊቶች ለማመልከት ነው። ምንዝርን፣ ዝሙት አዳሪነትን፣ ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን፣ ግብረ ሰዶማዊነትንና ከእንስሳት ጋር የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን ይጨምራል። ይህ አገላለጽ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ ከምትጠራ ዝሙት አዳሪ የሆነች ሃይማኖታዊ ተቋም ጋር በተያያዘ በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል፤ ይህች ሃይማኖታዊ ተቋም በዚህ መንገድ የተገለጸችው ሥልጣንና ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ስትል ከዚህ ዓለም ገዢዎች ጋር ተገቢ ያልሆነ ጥምረት ስለመሠረተች ነው። (ራእይ 14:8፤ 17:2፤ 18:3፤ ማቴ 5:32፤ ሥራ 15:29፤ ገላ 5:19)–ዝሙት አዳሪ የሚለውን ተመልከት

  • የፍሬ በኩራት፤ በኩራት

    በመከር ወቅት፣ መጀመሪያ ላይ የሚደርሰውን ፍሬ እንዲሁም የማንኛውንም ነገር የመጀመሪያ ምርት ወይም ውጤት ያመለክታል። ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ከሰውም ይሁን ከእንስሳ ወይም ከምድር ፍሬ፣ የፍሬያቸውን በኩራት ለእሱ እንዲሰጡ ይጠብቅባቸው ነበር። በቂጣ በዓልና በጴንጤቆስጤ በዓል ወቅት እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ የፍሬያቸውን በኩራት ለአምላክ ያቀርቡ ነበር። በተጨማሪም “በኩራት” የሚለው አገላለጽ ክርስቶስንና ቅቡዓን ተከታዮቹን ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል።–1ቆሮ 15:23ዘኁ 15:21፤ ምሳሌ 3:9፤ ራእይ 14:4

  • የፍርድ ቀን

    የተወሰኑ ቡድኖች፣ ብሔራት ወይም መላው የሰው ዘር በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ የሚሆንበትን አንድ የተወሰነ ቀን ወይም ጊዜ ያመለክታል። ሞት ይገባቸዋል ተብሎ የተፈረደባቸው ሰዎች ቅጣታቸውን የሚቀበሉበት፣ ሌሎቹ ደግሞ መዳንና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ የሚያስችል ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ በሕያዋን ላይ ብቻ ሳይሆን በሙታንም ላይ ፍርድ የሚሰጥበት ‘የፍርድ ቀን’ እንደሚመጣ ጠቁመዋል።–ማቴ 12:36

  • የፍርድ ወንበር

    ብዙውን ጊዜ ከቤት ውጭ የሚገኝ፣ መወጣጫ ደረጃ ያለው ከፍ ያለ መድረክ ሲሆን ባለሥልጣናት እዚያ ላይ ተቀምጠው ለሕዝቡ ንግግር ያቀርባሉ እንዲሁም ውሳኔያቸውን ያሳውቃሉ። ‘የአምላክ የፍርድ ወንበር’ እና ‘የክርስቶስ የፍርድ ወንበር’ የሚሉት አገላለጾች ይሖዋ በሰው ዘር ላይ ለመፍረድ ያደረገውን ዝግጅት የሚያሳዩ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ናቸው።–ሮም 14:102ቆሮ 5:10፤ ዮሐ 19:13

  • ያዕቆብ

    የይስሐቅና የርብቃ ልጅ ነው። ከጊዜ በኋላ አምላክ እስራኤል የሚል ስም ያወጣለት ሲሆን የእስራኤል ሕዝብ (እስራኤላውያን ወይም አይሁዳውያን ተብለውም ይጠራሉ) አባት ለመሆን በቅቷል። ያዕቆብ 12 ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህ ልጆችና ዘሮቻቸው 12 ነገዶችን ያቀፈውን የእስራኤልን ብሔር አስገኝተዋል። ያዕቆብ የሚለው ስም የእስራኤልን ብሔር ወይም ሕዝብ ለማመልከት ሲሠራበት ቆይቷል።–ዘፍ 32:28ማቴ 22:32

  • ይሁዳ

    ያዕቆብ ከሚስቱ ከሊያ የወለደው አራተኛ ወንድ ልጅ ነው። ያዕቆብ በሞት አፋፍ ላይ ሳለ ከይሁዳ የዘር ሐረግ ታላቅና ዘላለማዊ ገዢ እንደሚወጣ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ ሰው ሆኖ የተወለደው ከይሁዳ የዘር ሐረግ ነበር። በተጨማሪም ይሁዳ የሚለው ስያሜ የይሁዳን ነገድና ከጊዜ በኋላ ደግሞ በስሙ የተሰየመውን መንግሥት ለማመልከት ተሠርቶበታል። ደቡባዊው መንግሥት በመባል የሚታወቀው የይሁዳ መንግሥት ከእስራኤል ነገዶች መካከል ይሁዳንና ቢንያምን እንዲሁም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ያቀፈ ነበር። ይሁዳ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን ጨምሮ የአገሪቱን ደቡባዊ ክፍል የያዘ ነበር።–ዘፍ 29:3549:101ነገ 4:20፤ ዕብ 7:14

  • ይሖዋ

    በብዙዎች ዘንድ የተለመደው የቴትራግራማተን (የአምላክን የግል ስም የሚወክሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት) አማርኛ አጠራር ሲሆን በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ ከ7,000 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል።–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ4ን እና ሀ5ን ተመልከት።

  • ደረቅ ወንዝ

    በዝናብ ወቅት ካልሆነ በስተቀር አብዛኛውን ጊዜ ውኃ የማይገኝበት ሸለቆ ወይም ጅረት የሚፈስበት ወለል፤ ቃሉ በቀጥታ ጅረቱን ለማመልከትም ሊሠራበት ይችላል። አንዳንድ ጅረቶች ውኃ የሚያገኙት ከምንጭ በመሆኑ በቋሚነት ውኃ ሊኖራቸው ይችላል። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደረቅ ወንዝ “ሸለቆ” ተብሎ ተገልጿል።–ዘፍ 26:19ዘኁ 34:5፤ ዘዳ 8:7፤ 1ነገ 18:5፤ ኢዮብ 6:15

  • ደንገል

    በውኃ ዳር የሚበቅልና እንደ ቅርጫት፣ ዘንቢልና ታንኳ የመሳሰሉ ነገሮችን ለመሥራት የሚያገለግል ቄጠማ የሚመስል ተክል ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለመጻፊያነት የሚያገለግል እንደ ወረቀት ያለ ነገር ይሠራበት ነበር፤ እንዲሁም ብዙ ጥቅልሎችን ለማዘጋጀት አገልግሏል።–ዘፀ 2:3

  • ዲናር

    ክብደቱ 3.85 ግራም ገደማ የሆነ የሮማውያን የብር ሳንቲም ሲሆን በአንዱ ገጹ ላይ የቄሳር ምስል ተቀርጾበታል። የአንድ ሠራተኛ የቀን ደሞዝ ከመሆኑም ሌላ ሮማውያን ከእያንዳንዱ አይሁዳዊ ላይ የሚሰበስቡት ‘የግብር’ ሳንቲም ነበር። (ማቴ 22:17፤ ሉቃስ 20:24)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ዲካፖሊስ

    ይህ መጠሪያ መጀመሪያ ላይ አሥር የግሪክ ከተሞችን (በግሪክኛ ዲካ ማለት “አሥር” ሲሆን ፖሊስ ደግሞ “ከተማ” ማለት ነው) ያመለክት የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ በርከት ያሉ የግሪክ ከተሞችን ለመግለጽ ተሠርቶበታል። በተጨማሪም ስያሜው ከእነዚህ ከተሞች መካከል አብዛኞቹ ይገኙበት የነበረውን ከገሊላ ባሕርና ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ያለውን ክልል ያመለክት ነበር። እነዚህ ከተሞች የግሪካውያን ባሕልና ንግድ የተስፋፋባቸው ነበሩ። ኢየሱስ በዚህ ክልል አልፎ እንደሄደ የታወቀ ቢሆንም ወደ እነዚህ ከተሞች ገብቶ እንደነበር የሚጠቁም ዘገባ ግን የለም። (ማቴ 4:25፤ ማር 5:20)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ7ን እና ለ10ን ተመልከት።

  • ዲያብሎስ

    በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኝ ለሰይጣን የተሰጠ፣ ተግባሩን የሚገልጽ ስም ሲሆን “ስም አጥፊ” የሚል ትርጉም አለው። ሰይጣን ይህ ስም የተሰጠው በይሖዋና መልካም በሆነው ቃሉ ላይ የሐሰት ክስ በመሰንዘርም ሆነ የአምላክን ቅዱስ ስም በማጥፋት ረገድ ግንባር ቀደም ስለሆነ ነው።–ማቴ 4:1ዮሐ 8:44፤ ራእይ 12:9

  • ዳሪክ

    ክብደቱ 8.4 ግራም የሆነ የፋርሳውያን የወርቅ ሳንቲም ነው። (1ዜና 29:7)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ዳጎን

    የፍልስጤማውያን አምላክ ነው። የቃሉ አመጣጥ በእርግጠኝነት የማይታወቅ ቢሆንም አንዳንድ ምሁራን ቃሉ ዳግ (ዓሣ) ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ እንደሆነ ይናገራሉ።–መሳ 16:231ሳሙ 5:4

  • ድራክማ

    በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይህ ቃል በወቅቱ 3.4 ግራም የሚመዝንን የግሪካውያን የብር ሳንቲም ያመለክታል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከዳሪክ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ በፋርሳውያን ዘመን ይሠራበት የነበረ የወርቅ ድራክማ ተጠቅሷል። (ነህ 7:70፤ ማቴ 17:24)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ድር

    በሽመና ሥራ ላይ በሸማው ቁመት ልክ፣ ከላይ ወደ ታች የሚወርዱትን ክሮች ያመለክታል። በድሩ ላይ በወርዱ በኩል ከላይና ከታች የሚጠላለፉት ወይም የሚሰባጠሩት ክሮች ደግሞ ማግ ይባላሉ።–መሳ 16:13

  • ጃንደረባ

    ቃል በቃል ሲወሰድ የተሰለበን ወንድ ያመለክታል። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያሉ ወንዶች በቤተ መንግሥት ውስጥ አገልጋዮች ወይም የንግሥቲቱና የንጉሡ ቁባቶች ሞግዚት ሆነው እንዲያገለግሉ ይሾሙ ነበር። በተጨማሪም ይህ ስያሜ ቃል በቃል የተሰለበ ባይሆንም በቤተ መንግሥት ውስጥ አንዳንድ ሥራዎችን እንዲያከናውን የተሾመን ባለሥልጣን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ከዚህም ሌላ በአምላክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ራሱን ለማስጠመድ ሲል ከአንዳንድ ነገሮች የታቀበን ሰው ይኸውም ‘ለመንግሥተ ሰማያት ሲል ጃንደረባ’ የሆነን ግለሰብ ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል።–ማቴ 19:12አስ 2:15፤ ሥራ 8:27

  • ገሃነም

    ከጥንቷ ኢየሩሳሌም በስተ ደቡብና በስተ ደቡብ ምዕራብ ይገኝ ለነበረው ለሂኖም ሸለቆ የተሰጠ ከግሪክኛ ቃል የተገኘ ስም ነው። (ኤር 7:31) አስከሬን የሚጣልበት ቦታ እንደሚሆን ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ኤር 7:32፤ 19:6) እንስሳት ወይም ሰዎች በሕይወት እያሉ ወደዚያ ተጥለው እንዲቃጠሉ ወይም እንዲሠቃዩ ይደረግ እንደነበር የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም። በመሆኑም የሰው ነፍስ ለዘላለም በእሳት የሚሠቃይበት በዓይን የማይታይ ቦታ እንደሆነ ተደርጎ መገለጹ ተገቢ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ‘በሁለተኛው ሞት’ የተመሰለውን ዘላለማዊ ቅጣት ይኸውም ዘላለማዊ ጥፋትን ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ተጠቅመውበታል።–ራእይ 20:14ማቴ 5:22፤ 10:28

  • ገለባ

    እህል ከተወቃ በኋላ ለነፋስ ሲዘራ ከፍሬው የሚለየው ክፍል። በዘይቤያዊ አነጋገር ገለባ የማይረባና የማይፈለግ ነገርን ለማመልከት ይሠራበታል።–መዝ 1:4ማቴ 3:12

  • ገነት

    አንድን ያማረ የአትክልት ስፍራ ወይም መናፈሻ ያመለክታል። እንዲህ ያለው የመጀመሪያው የአትክልት ስፍራ በኤደን ይገኝ የነበረው ነው፤ ይሖዋ ይህን የአትክልት ስፍራ ያዘጋጀው ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት መኖሪያነት ነበር። ኢየሱስ ከጎኑ ተሰቅለው ከነበሩት ወንጀለኞች ለአንዱ የተናገረው ነገር ወደፊት መላዋ ምድር ገነት እንደምትሆን ይጠቁማል። በ2 ቆሮንቶስ 12:4 ላይ የሚገኘው ገነት የሚለው ቃል ወደፊት የሚመጣን ገነት እንደሚያመለክት ግልጽ ነው፤ ራእይ 2:7 ደግሞ ስለ ሰማያዊ ገነት ይናገራል።–መኃ 4:13ሉቃስ 23:43

  • ገጸ ኅብስት

    በማደሪያ ድንኳኑና በቤተ መቅደሱ ቅድስት ውስጥ ባለው ጠረጴዛ ላይ ስድስት ስድስት ሆነው በሁለት ረድፍ ተነባብረው ይቀመጡ የነበሩትን አሥራ ሁለት ዳቦዎች ያመለክታል። ‘የሚነባበር ዳቦ’ እና ‘በአምላክ ፊት የሚቀርብ ኅብስት’ ተብሎም ይጠራል። ለአምላክ የሚቀርበው ይህ መባ በየሰንበቱ በትኩስ ዳቦዎች ይተካል። ከጠረጴዛው ላይ የሚነሱትን ዳቦዎች በደንቡ መሠረት የሚበሉት ካህናቱ ብቻ ናቸው። (2ዜና 2:4፤ ማቴ 12:4፤ ዘፀ 25:30፤ ዘሌ 24:5-9፤ ዕብ 9:2)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ን ተመልከት።

  • ጉባኤ

    ለአንድ ዓላማ ወይም ተግባር አንድ ላይ የተሰበሰቡ ሰዎችን ያመለክታል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በአብዛኛው የእስራኤልን ብሔር ለማመልከት ተሠርቶበታል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ደግሞ እያንዳንዱን ክርስቲያን ጉባኤ በተናጠል ለማመልከት የተሠራበት ሲሆን ብዙውን ጊዜ ግን የክርስቲያን ጉባኤን በአጠቃላይ ለማመልከት አገልግሏል።–1ነገ 8:22ሥራ 9:31፤ ሮም 16:5

  • ጉብታ

    በዕብራይስጥ “ሚሎ” ሲሆን ይህ የዕብራይስጥ ቃል “መሙላት” የሚል ትርጉም ካለው ሥርወ ቃል የተገኘ ነው። የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ይህን ቃል “ግንብ” በማለት ተርጉሞታል። ጉብታ የሚለው ቃል የዳዊት ከተማ ትገኝበት የነበረውን ቦታ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም፤ ይሁንና ትክክለኛ ምንነቱ አይታወቅም።–2ሳሙ 5:91ነገ 11:27

  • ጊልያድ

    በዋነኝነት ከያቦቅ ሸለቆ በስተ ሰሜንና በስተ ደቡብ ተንጣሎ የሚገኘውንና ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ለም ምድር ያመለክታል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ይኖሩበት የነበረውን ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን የእስራኤል ግዛት በሙሉ ለማመልከት ተሠርቶበታል። (ዘኁ 32:1፤ ኢያሱ 12:2፤ 2ነገ 10:33)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ4ን ተመልከት።

  • ጊቲት

    ትክክለኛ ትርጉሙ በእርግጠኝነት የማይታወቅ የሙዚቃ ቃል ሲሆን ጋት ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ይመስላል። አንዳንዶች ጋት የሚለው ቃል የወይን መጭመቂያን ስለሚያመለክት ጊቲት የሚለው ቃል ወይን ከመጭመቅ ጋር በተያያዘ ከሚዜሙ ዜማዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ይሰማቸዋል።–መዝ 81:0

  • ጌራ

    ክብደቱ 0.57 ግራም ሲሆን ከ1/20 ሰቅል ጋር ተመጣጣኝ ነው። (ዘሌ 27:25)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ግሪክ፤ ግሪክኛ

    ግሪካውያን የሚናገሩትን ቋንቋ እንዲሁም የግሪክ ተወላጆችን ወይም የግሪክ የዘር ሐረግ ያላቸውን ሰዎች ያመለክታል። ይህ ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከዚህ ሰፋ ባለ መንገድ ይኸውም አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችን ወይም የግሪክ ቋንቋና ባሕል ተጽዕኖ ያሳደረባቸውን ሰዎች ለማመልከት ተሠርቶበታል።–ኢዩ 3:6ዮሐ 12:20

  • ግርዘት

    የወንድ ብልት ሸለፈትን ቆርጦ ማስወገድን ያመለክታል። አብርሃምና ዘሮቹ መገረዝ ይጠበቅባቸው የነበረ ቢሆንም ክርስቲያኖች ግን እንዲህ የማድረግ ግዴታ የለባቸውም። በተለያዩ ጥቅሶች ላይ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድም ተሠርቶበታል።–ዘፍ 17:101ቆሮ 7:19፤ ፊልጵ 3:3

  • ግቢ

    በማደሪያ ድንኳኑ ዙሪያ የሚገኘውን የታጠረ ቦታ ያመለክታል፤ በኋላም በቤተ መቅደሱ ዋነኛ ሕንፃ ዙሪያ ይገኝ የነበረውን በግንብ የታጠረ ቦታ ለማመልከት ተሠርቶበታል። የሚቃጠል መባ የሚቀርብበት መሠዊያ የሚገኘው በማደሪያ ድንኳኑ ግቢ ውስጥና በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ግቢ ነበር። (ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ5ንለ8ንና ለ11ን ተመልከት።) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ግቢ ስላላቸው ቤቶችና ቤተ መንግሥቶች ይናገራል።–ዘፀ 8:1327:91ነገ 7:12፤ አስ 4:11፤ ማቴ 26:3

  • ግብር

    አንድ አገር ወይም ገዢ ለሌላ አገር ተገዢ መሆኑን ለማሳየት የሚሰጠው ክፍያ ሲሆን ይህን የሚያደርገው በመካከላቸው ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ወይም ጥበቃ ለማግኘት ነው። (2ነገ 3:4፤ 18:14-16፤ 2ዜና 17:11) ግለሰቦች በነፍስ ወከፍ የሚከፍሉትን ቀረጥ ለማመልከትም ተሠርቶበታል።–ነህ 5:4ሮም 13:7

  • ግዞት

    ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው በወራሪዎች ተገዶ ከአገሩ ወይም ከቤቱ እንዲወጣ መደረጉን ያመለክታል። የዕብራይስጡ ቃል “ለቆ መሄድ” የሚል ትርጉም አለው። እስራኤላውያን ሁለት ጊዜ ለግዞት ተዳርገዋል። አሥሩን ነገዶች ያቀፈው ሰሜናዊው መንግሥት በአሦራውያን በግዞት ተወስዷል፤ ቆየት ብሎ ደግሞ ሁለቱን ነገዶች ያቀፈው መንግሥት በባቢሎናውያን ለግዞት ተዳርጓል። የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ከእነዚህ ግዞቶች በሕይወት የተረፉት ሰዎች ወደ ምድራቸው እንዲመለሱ አድርጓል።–2ነገ 17:624:16ዕዝራ 6:21

  • ጠባቂ

    አብዛኛውን ጊዜ በሌሊት በሰዎች ወይም በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚጠብቅና አስጊ ሁኔታ ሲከሰት የማስጠንቀቂያ ድምፅ የሚያሰማ ሰው። ጠባቂዎች ወደ ከተማዋ እየመጡ ያሉ ሰዎች በጣም ከመቅረባቸው በፊት ሁኔታውን መከታተል እንዲችሉ በአብዛኛው በከተማ ግንቦችና ማማዎች ላይ ሆነው ይጠብቃሉ። በውትድርና መስክ የተሰማራ ጠባቂ፣ ዘብ ተብሎ ይጠራል። ነቢያት ጥፋት እየመጣ መሆኑን በመግለጽ የእስራኤልን ሕዝብ ያስጠነቅቁ ስለነበር በምሳሌያዊ አነጋገር ጠባቂዎች ሆነው አገልግለዋል።–2ነገ 9:20ሕዝ 3:17

  • ጠንቋይ

    ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ እንዳለው የሚናገር ሰው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስማተኛ ካህናት፣ ሟርተኞች፣ ኮከብ ቆጣሪዎችና ሌሎች በዚህ ውስጥ ተመድበዋል።–ዘሌ 19:31ዘዳ 18:11፤ ሥራ 16:16

  • ጣዖት፤ የጣዖት አምልኮ

    ጣዖት ሰዎች ለአምልኮ የሚጠቀሙበትን በእውኑ ዓለም ያለም ይሁን በምናብ የተፈጠረን የማንኛውም ነገር ምስል ያመለክታል። የጣዖት አምልኮ ደግሞ አንድን ጣዖት ማክበርን፣ መውደድን ወይም ማምለክን ያመለክታል።–መዝ 115:4ሥራ 17:16፤ 1ቆሮ 10:14

  • ጥልቁ

    ጥልቁ ተብሎ የተተረጎመው አቢሶስ የሚለው ግሪክኛ ቃል “እጅግ ጥልቅ” ወይም “የማይደረስበት፣ መጨረሻ የሌለው” የሚል ፍቺ አለው። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንደ እስር ቤት ያለን ቦታ ወይም ሁኔታ ለማመልከት ተሠርቶበታል። ይህ ቃል መቃብርን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ነገሮችንም ያመለክታል።–ሉቃስ 8:31ሮም 10:7፤ ራእይ 20:3

  • ጥምቀት፤ ማጥመቅ

    ግሱ “ማጥለቅ” ወይም ውኃ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መንከር የሚል ትርጉም አለው። ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲጠመቁ አዟል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዮሐንስ ጥምቀት፣ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ስለመጠመቅ እንዲሁም ስለ ሌሎች ዓይነት ጥምቀቶች ይናገራል።–ማቴ 3:11, 1628:19ዮሐ 3:23፤ 1ጴጥ 3:21

  • ጥምጥም

    ራስ ላይ የሚጠመጠምና እንደ ሻሽ የሚደረግ ጨርቅ። ሊቀ ካህናቱ ከጥሩ በፍታ የተሠራ ጥምጥም ያደርግ ነበር፤ ከፊት በኩል ጥምጥሙ ላይ በሰማያዊ ገመድ የሚታሰር ጠፍጣፋ ወርቅ ይደረጋል። ንጉሡ ደግሞ ራሱ ላይ ከሚደፋው አክሊል ሥር ጥምጥም ያደርግ ነበር። ኢዮብ የፍትሕ አቋሙን ከጥምጥም ጋር በማመሳሰል ቃሉን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል።–ዘፀ 28:36, 37ኢዮብ 29:14ሕዝ 21:26

  • ጥቅልል

    ረጅም በሆነ ብራና ወይም ከደንገል በተሠራ ወረቀት ላይ በአንዱ በኩል ከተጻፈበት በኋላ በአብዛኛው በእንጨት ላይ ተጠቅልሎ የሚቀመጥን ጽሑፍ ያመለክታል። ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፉትም ሆነ ከአንድ ቅጂ ወደ ሌላ ቅጂ ይገለበጡ የነበረው በጥቅልሎች ላይ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን አብዛኛውን ጊዜ መጻሕፍት የሚዘጋጁት በዚህ መልክ ነበር።–ኤር 36:4, 18, 23ሉቃስ 4:17-20፤ 2ጢሞ 4:13

  • ጭቁኝ

    እጅግ የሚመር ጣዕምና የሚሰነፍጥ ሽታ እንዲሁም ጠንካራ አገዳ ያላቸው የተለያዩ ዕፀዋት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጭቁኝ የሥነ ምግባር ብልግና፣ ባርነት፣ የፍትሕ መጓደልና ክህደት የሚያስከትሏቸውን መራራ ውጤቶች ለመግለጽ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። ራእይ 8:11 ላይ የተጠቀሰው “ጭቁኝ” የሚለው ቃል መራራና መርዛማ የሆነን ንጥረ ነገር ያመለክታል፤ አብሲንት ተብሎም ይጠራል።–ዘዳ 29:18ምሳሌ 5:4፤ ኤር 9:15፤ አሞጽ 5:7

  • ጴንጤቆስጤ

    አይሁዳውያን ወንዶች በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ማክበር ከሚጠበቅባቸው ሦስት ዋና ዋና በዓላት መካከል ሁለተኛው ነው። ጴንጤቆስጤ “ሃምሳኛ (ቀን)” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የመከር በዓል ወይም የሳምንታት በዓል በመባል ለሚታወቀው በዓል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተሰጠ ስያሜ ነው። ይህ በዓል ኒሳን 16 በዋለ በ50ኛው ቀን ላይ ይከበራል።–ዘፀ 23:1634:22ሥራ 2:1

  • ጸሐፊ

    የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ይገለብጥ የነበረ ሰው። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ዘመን ይህ ቃል ሕጉን ጠንቅቀው የተማሩ ሰዎችን ያቀፈን አንድ ቡድን ያመለክት ነበር። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ተቃውመውታል።–ዕዝራ 7:6 የግርጌ ማስታወሻ፤ ማር 12:38, 39፤ 14:1

  • ጸጋ

    የግሪክኛው ቃል ደስ የሚያሰኝና የሚማርክ የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። ብዙውን ጊዜ ቃሉ የደግነት ስጦታን ወይም ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ መስጠትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ይህ ቃል የአምላክን ጸጋ ለማመልከት በሚሠራበት ጊዜ አምላክ ምንም ብድራት ሳይጠብቅ በልግስና ተነሳስቶ በነፃ የሚሰጠውን ስጦታ ያሳያል። በመሆኑም አምላክ ለሰው ልጆች በልግስና መስጠቱን እንዲሁም ታላቅ ፍቅርና ደግነት ማሳየቱን የሚገልጽ ቃል ነው። የግሪክኛው ቃል “ሞገስ” እና “የደግነት ስጦታ” ተብሎም ተተርጉሟል። ተቀባዩ ይገባኛል ወይም የደከምኩበት ነው ብሎ የሚጠይቀው ነገር ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በሰጪው ልግስና ላይ የተመካ ስጦታ ነው።–2ቆሮ 6:1ኤፌ 1:7

  • ጽዮን፤ የጽዮን ተራራ

    በኢየሩሳሌም ደቡባዊ ምሥራቅ ኮረብታ ላይ ለምትገኘውና ኢያቡስ ተብላ ለምትጠራው የኢያቡሳውያን የተመሸገች ከተማ የተሰጠ ስያሜ። ዳዊት ከተማዋን ከያዘ በኋላ ቤተ መንግሥቱን በዚያ የገነባ ሲሆን ከተማዋም “የዳዊት ከተማ” ተብላ ትጠራ ጀመር። (2ሳሙ 5:7, 9) ዳዊት ታቦቱን ወደዚያ ባመጣው ጊዜ ጽዮን ለይሖዋ የተቀደሰች ተራራ ሆነች። ከጊዜ በኋላ ጽዮን የሚለው ስያሜ በሞሪያ ተራራ ላይ የተገነባውን ቤተ መቅደስ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መላውን የኢየሩሳሌም ከተማ የሚያካትት ሆነ። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ጽዮን የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ የተሠራበት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ነው።–መዝ 2:61ጴጥ 2:6፤ ራእይ 14:1

  • ጽድቅ

    ይህ ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተሠራበት አምላክ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ባወጣው መሥፈርት መሠረት ትክክል የሆነውን ነገር ለማመልከት ነው።–ዘፍ 15:6ዘዳ 6:25፤ ምሳሌ 11:4፤ ሶፎ 2:3፤ ማቴ 6:33

  • ጾም

    ለተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ከምግብ መታቀብን ያመለክታል። እስራኤላውያን በስርየት ቀን፣ አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸውና መለኮታዊ መመሪያ ማግኘት ሲፈልጉ ይጾሙ ነበር። አይሁዳውያን በታሪክ ዘመናቸው ያጋጠሟቸውን አሳዛኝ ሁኔታዎች ለማሰብ በዓመት ውስጥ አራት ጊዜ ይጾሙ ነበር። ክርስቲያኖች የመጾም ግዴታ የለባቸውም።–ዕዝራ 8:21ኢሳ 58:6፤ ሉቃስ 18:12

  • ፀረ ክርስቶስ

    ግሪክኛው ቃል ሁለት ትርጉም አለው። ቃሉ ክርስቶስን መጻረርን ወይም መቃወምን ያመለክታል። በተጨማሪም ሐሰተኛ ክርስቶስን ማለትም የክርስቶስን ቦታ የወሰደን አካል ያመለክታል። በሐሰት ክርስቶስን እንወክላለን ወይም መሲሕ ነን የሚሉ አሊያም ክርስቶስንና ደቀ መዛሙርቱን የሚቃወሙ ሰዎች፣ ድርጅቶች ወይም ቡድኖች በሙሉ ፀረ ክርስቶሶች ናቸው።–1ዮሐ 2:22

  • ፈሪሳውያን

    በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረ ታዋቂ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ቡድን ነው። ፈሪሳውያን የካህናት ዘሮች ባይሆኑም የሙሴን ሕግ፣ እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ሳይቀር በጥብቅ ይከተሉ የነበረ ሲሆን በቃል ለሚተላለፉ ወጎችም የዚያኑ ያህል ትልቅ ግምት ይሰጡ ነበር። (ማቴ 23:23) የግሪክ ባሕል በሕዝቡ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ይቃወሙ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሕጉንም ሆነ የተለያዩ ወጎችን ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት ነበራቸው። (ማቴ 23:2-6) በተጨማሪም አንዳንዶቹ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ነበሩ። ፈሪሳውያን ብዙውን ጊዜ ኢየሱስን ‘ሰንበትን አያከብርም፣ የአባቶችን ወግ አይጠብቅም እንዲሁም ከኃጢአተኞችና ከቀረጥ ሰብሳቢዎች ጋር ይበላል’ በማለት ይቃወሙት ነበር። የጠርሴሱ ሳኦልን ጨምሮ አንዳንዶቹ ፈሪሳውያን የክርስትናን እምነት ተቀብለዋል።–ማቴ 9:1112:14ማር 7:5ሉቃስ 6:2፤ ሥራ 26:5

  • ፈርዖን

    ለግብፃውያን ነገሥታት የሚሰጥ የማዕረግ ስም ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምስት ፈርዖኖች (ሺሻቅ፣ ሶህ፣ ቲርሃቅ፣ ኒካዑ እና ሆፍራ) በስም የተጠቀሱ ቢሆንም ከአብርሃም፣ ከሙሴና ከዮሴፍ ታሪክ ጋር በተያያዘ የተጠቀሱትን ጨምሮ ሌሎቹ ፈርዖኖች ስማቸው አልተገለጸም።–ዘፀ 15:4ሮም 9:17

  • ፊም

    የክብደት መለኪያ እንዲሁም ፍልስጤማውያን የተለያዩ የብረት መሣሪያዎችን ለመሳል ያስከፍሉት የነበረ ክፍያ ነው። በእስራኤል በተደረጉ አርኪኦሎጂያዊ ቁፋሮዎች በተገኙ በርካታ የድንጋይ መለኪያዎች ላይ “ፊም” የሚለው ቃል በጥንቱ የዕብራይስጥ ተነባቢ ፊደላት ተጽፎባቸዋል፤ የድንጋዮቹ አማካይ ክብደት 7.8 ግራም ሲሆን ይህም ሁለት ሦስተኛ ሰቅል ገደማ ነው።–1ሳሙ 13:20, 21

  • ፋርስ፤ ፋርሳውያን

    ብዙውን ጊዜ ከሜዶናውያን ጋር ተያይዞ የሚጠቀስ አገርና ሕዝብ ሲሆን ይህም በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ጥብቅ ትስስር እንደነበር ይጠቁማል። ከቀድሞ ታሪካቸው መረዳት እንደሚቻለው ፋርሳውያን የሚኖሩት በኢራን አምባ ደቡባዊ ምዕራብ አካባቢ ብቻ ነበር። በታላቁ ቂሮስ (አንዳንድ ጥንታዊ የታሪክ ምሁራን አባቱ ፋርሳዊ፣ እናቱ ደግሞ ሜዶናዊ እንደነበሩ ይገልጻሉ) ዘመን ምንም እንኳ መንግሥቱ ጥምር መንግሥት ሆኖ ቢቀጥልም ፋርሳውያን በሜዶናውያን ላይ የበላይነት ነበራቸው። ቂሮስ በ539 ዓ.ዓ. የባቢሎንን መንግሥት ድል ያደረገ ሲሆን በግዞት ተወስደው የነበሩት አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቅዶላቸዋል። የፋርሳውያን ግዛት በስተ ምሥራቅ ከሚገኘው ከኢንደስ ወንዝ አንስቶ በስተ ምዕራብ እስከሚገኘው የኤጅያን ባሕር ድረስ ያለው ነበር። ታላቁ እስክንድር ፋርሳውያንን ድል እስካደረገበት እስከ 331 ዓ.ዓ. ድረስ አይሁዳውያን በፋርሳውያን አገዛዝ ሥር ነበሩ። የፋርስ መንግሥት ለዳንኤል በራእይ ከተገለጡለት መንግሥታት አንዱ ከመሆኑም ሌላ በዕዝራ፣ በነህምያና በአስቴር መጻሕፍት ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል። (ዕዝራ 1:1፤ ዳን 5:28፤ 8:20)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ9ን ተመልከት።

  • ፋሲካ

    እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ የወጡበትን ጊዜ ለማሰብ ሲባል በአቢብ ወር (በኋላ ላይ ኒሳን ተብሏል) 14ኛ ቀን ላይ የሚከበር ዓመታዊ በዓል ነው። በዓሉ በሚከበርበት ዕለት በግ (ወይም ፍየል) ታርዶ ከተጠበሰ በኋላ ሥጋው ከመራራ ቅጠልና ከቂጣ ጋር ይበላል።–ዘፀ 12:27ዮሐ 6:4፤ 1ቆሮ 5:7

  • ፋተም

    የውኃን ጥልቀት ለመለካት የሚያገለግል መለኪያ ሲሆን 1.8 ሜትር ነው። (ሥራ 27:28)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።

  • ፍልስጤም፤ ፍልስጤማውያን

    በእስራኤል ደቡባዊ ጠረፍ አካባቢ የሚገኘው ምድር ፍልስጤም ይባል ነበር። ከቀርጤስ ፈልሰው በዚያ የሰፈሩት ሰዎች ፍልስጤማውያን ተብለው ይጠሩ ነበር። ዳዊት ፍልስጤማውያን እንዲገዙለት ያደረገ ቢሆንም ራሳቸውን የቻሉ ሕዝቦች ሆነው ኖረዋል፤ እንዲሁም ከእስራኤላውያን ጋር ብዙ ዘመን የዘለቀ ጠላትነት ነበራቸው። (ዘፀ 13:17፤ 1ሳሙ 17:4፤ አሞጽ 9:7)–ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ4ን ተመልከት።

  • ፑሪም

    በአዳር ወር በ14ኛው እና በ15ኛው ቀን ላይ የሚከበር ዓመታዊ በዓል ነው። ይህ በዓል የሚከበረው በንግሥት አስቴር ዘመን አይሁዳውያን ከመጥፋት የተረፉበትን ወቅት ለማሰብ ተብሎ ነበር። ከዕብራይስጥ ሳይሆን ከሌላ ቋንቋ የተወሰደው ፑሪም የሚለው ቃል “ዕጣዎች” የሚል ትርጉም አለው። የፑሪም በዓል ወይም የዕጣ በዓል ስያሜውን ያገኘው ሐማ አይሁዳውያንን ለማጥፋት የጠነሰሰውን ሴራ የሚያስፈጽምበትን ቀን የወሰነው ፑር (ወይም ዕጣ) በመጣል ስለነበር ነው።–አስ 3:79:26

  • ፖርኒያ

    የፆታ ብልግና የሚለውን ተመልከት።