ኢሳይያስ 30:1-33

  • ግብፅ የምትሰጠው እርዳታ ዋጋ የለውም (1-7)

  • ሕዝቡ ትንቢታዊ መልእክቱን ንቀዋል (8-14)

  • “ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ” (15-17)

  • ይሖዋ ለሕዝቡ ሞገስ ያሳያል (18-26)

    • ታላቅ አስተማሪ የሆነው ይሖዋ (20)

    • “መንገዱ ይህ ነው” (21)

  • ይሖዋ በአሦር ላይ ፍርዱን ያስፈጽማል (27-33)

30  “ግትር ለሆኑ ልጆች ወዮላቸው”+ ይላል ይሖዋ፤“በኃጢአት ላይ ኃጢአት ለመጨመርየእኔን ሳይሆን የራሳቸውን ዕቅድ ይፈጽማሉ፤+ደግሞም ኅብረት ይፈጥራሉ፤* ይህን የሚያደርጉት ግን በመንፈሴ አይደለም።   በፈርዖን ጥበቃ ሥር* ለመሸሸግናበግብፅ ጥላ ሥር ለመጠለልእኔን ሳያማክሩ*+ ወደ ግብፅ ይወርዳሉ!+   ይሁንና ፈርዖን የሚያደርግላችሁ ጥበቃ ለኀፍረት፣በግብፅ ጥላ ሥር መጠለልም ለውርደት ይዳርጋችኋል።+   መኳንንቱ በጾዓን+ ናቸውና፤መልእክተኞቹም ሃኔስ ደርሰዋል።   ምንም ሊጠቅማቸው በማይችል፣እርዳታ በማይሰጥና ጥቅም በማያስገኝ፣ይልቁንም ለውርደትና ለነቀፋ በሚዳርግ ሕዝብሁሉም ኀፍረት ይከናነባሉ።”+  በደቡብ እንስሳት ላይ የተላለፈ ፍርድ፦ አንበሳ፣ አዎ የሚያገሳ አንበሳ ባለበት፣እፉኝት እንዲሁም የሚበርና የሚያቃጥል እባብ* በሚገኙበት፣አስጨናቂና አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሞሉበት ምድርሀብታቸውን በአህያ ላይ፣ቁሳቁሳቸውንም በግመል ሻኛ ላይ ጭነው ይሄዳሉ። ሆኖም እነዚህ ነገሮች ለሕዝቡ ምንም ጥቅም አያስገኙለትም።   ግብፅ የምትሰጠው እርዳታ ምንም እርባና የለውምና።+ ስለዚህ እሷን “ረዓብ፣+ ሥራ ፈታ የምትጎለት” ብዬ ጠርቻታለሁ።   “በል ሂድ፤ ለመጪዎቹ ዘመናት፣ቋሚ ምሥክር እንዲሆንእነሱ ባሉበት በጽላት ላይ ጻፈው፤በመጽሐፍም ላይ ክተበው።+   እነሱ ዓመፀኛ ሕዝብ፣+ አታላይ ልጆችና+የይሖዋን ሕግ* ለመስማት እንቢተኛ የሆኑ ልጆች ናቸውና።+ 10  ባለ ራእዮችን ‘ከእንግዲህ ራእይ አትዩ’ ይላሉ፤ ነቢያትንም እንዲህ ይላሉ፦ ‘እውነተኛ ራእይ አትንገሩን።+ የሚጥም* ነገር ንገሩን፤ አሳሳች የሆነ ሕልም አልሙልን።+ 11  ከመንገዱ ዞር በሉ፤ ጎዳናውንም ልቀቁ። የእስራኤልን ቅዱስ በፊታችን አታድርጉ።’”+ 12  ስለዚህ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ይህን ቃል ስለናቃችሁ፣+በማጭበርበርና በማታለል ስለታመናችሁ፣በዚያም ላይ ስለተደገፋችሁ፣+ 13  ይህ በደል እንደተሰነጠቀ ቅጥር፣ሊወድቅ እንደተቃረበ ያዘመመ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል። ሳይታሰብ በድንገት ይፈርሳል። 14  ሸክላ ሠሪ እንደሠራው ትልቅ እንስራ ይሰባበራል፤እንክትክቱ ከመውጣቱ የተነሳ ከምድጃ ፍም ለመውሰድወይም ከረግረጋማ ቦታ* ውኃ ለመጨለፍ የሚያስችልአንድም ገል አይገኝም።” 15  የእስራኤል ቅዱስ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ “ወደ እኔ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ።”+ እናንተ ግን ፈቃደኞች አልሆናችሁም።+ 16  ይልቁንም “አይሆንም፣ በፈረሶች እንሸሻለን!” አላችሁ። ደግሞም ትሸሻላችሁ። “በፈጣን ፈረሶችም እንጋልባለን!” አላችሁ።+ ስለሆነም የሚያሳድዷችሁ ሰዎች ፈጣኖች ይሆናሉ።+ 17  አንድ ሰው ከሚሰነዝረው ዛቻ የተነሳ ሺዎች ይሸበራሉ፤+በተራራ አናት ላይ እንደተተከለ ምሰሶናበኮረብታ ላይ እንደቆመ ለምልክት የሚያገለግል ግንድ ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ፣አምስት ሰዎች ከሚሰነዝሩት ዛቻ የተነሳ ትሸሻላችሁ።+ 18  ይሁንና ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት* ይጠባበቃል፤+ምሕረት ሊያሳያችሁም ይነሳል።+ ይሖዋ የፍትሕ አምላክ ነውና።+ እሱን በተስፋ* የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።+ 19  ሕዝቡ በጽዮን ይኸውም በኢየሩሳሌም በሚኖርበት ጊዜ+ ፈጽሞ አታለቅሱም።+ እርዳታ ለማግኘት በምትጮኹበት ጊዜ በእርግጥ ሞገስ ያሳያችኋል፤ ጩኸታችሁን እንደሰማም ይመልስላችኋል።+ 20  ይሖዋ የጭንቀትን ምግብና የጭቆናን ውኃ ቢሰጥህም+ እንኳ ታላቁ አስተማሪህ ከእንግዲህ ራሱን አይሰውርም፤ በገዛ ዓይኖችህም ታላቁን አስተማሪህን+ ታያለህ። 21  ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ዞር ብትል ጆሮህ ከኋላህ “መንገዱ ይህ ነው።+ በእሱ ሂድ” የሚል ድምፅ ይሰማል።+ 22  የተቀረጹ ምስሎችህ የተለበጡበትን ብርና ከብረት የተሠሩ ሐውልቶችህ*+ የተለበጡበትን ወርቅ ታረክሳለህ። እንደ ወር አበባ ጨርቅ “ከዚህ ጥፉ!”* በማለት አሽቀንጥረህ ትጥላቸዋለህ።+ 23  እሱም መሬት ላይ ለምትዘራው ዘር ዝናብ ይሰጥሃል፤+ ምድሪቱም የምታፈራው እህል የተትረፈረፈና ምርጥ* ይሆናል።+ በዚያም ቀን ከብቶችህ ሰፊ በሆነ የግጦሽ መስክ ይሰማራሉ።+ 24  መሬቱንም የሚያርሱ ከብቶችና አህዮች በእንቧጮ* የተቀመመ እንዲሁም በላይዳና በመንሽ የተለየ ገፈራ ይበላሉ። 25  ብዙ እልቂት በሚደርስበትና ግንቦች በሚፈርሱበት ቀን፣ በረጅም ተራራና ከፍ ባለ ኮረብታ ሁሉ ላይ ጅረቶች ይፈስሳሉ፤+ የውኃ መውረጃ ቦዮችም ይኖራሉ። 26  የሙሉ ጨረቃ ብርሃንም እንደ ፀሐይ ብርሃን ይሆናል፤ ይሖዋ የሕዝቡን ስብራት* በሚጠግንበትና+ በእሱ ምት የተነሳ የደረሰባቸውን ከባድ ቁስል በሚፈውስበት ቀን+ የፀሐይ ብርሃን፣ እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት እጥፍ ይደምቃል።+ 27  እነሆ፣ የይሖዋ ስም በቁጣው እየነደደጥቅጥቅ ካለ ደመና ጋር ከሩቅ ይመጣል። ከንፈሮቹ በቁጣ ተሞልተዋል፤ምላሱም እንደሚባላ እሳት ነው።+ 28  መንፈሱ* እስከ አንገት ድረስ እንደሚደርስ የሚያጥለቀልቅ ወንዝ ነው፤ብሔራትን በጥፋት ወንፊት* ይነፋቸዋል፤በሕዝቦች መንጋጋም መንገድ እንዲስቱ የሚያደርግ ልጓም ይገባል።+ 29  እናንተ ግን፣ ለበዓል በምትዘጋጁበት* ጊዜ+በሌሊት እንደሚዘመረው ያለ መዝሙር ትዘምራላችሁ፤ደግሞም ወደ እስራኤል ዓለት፣+ ወደ ይሖዋ ተራራ ሲጓዝዋሽንት ይዞ* እንደሚሄድ ሰውልባችሁ ሐሴት ያደርጋል። 30  ይሖዋ ግርማ የተላበሰ ድምፁ+ እንዲሰማ ያደርጋል፤የክንዱንም ብርታት ይገልጣል፤+ይህን የሚያደርገው በሚነድ ቁጣ፣+ በሚባላ የእሳት ነበልባል፣+ሳይታሰብ በሚወርድ ዶፍ፣+ ነጎድጓድ በቀላቀለ ውሽንፍርና በበረዶ ድንጋይ+ ታጅቦ ክንዱ ጥቃት ለመሰንዘር ወደ ታች በሚወርድበት ጊዜ ነው። 31  ከይሖዋ ድምፅ የተነሳ አሦር በሽብር ይናጣልና፤+በበትርም ይመታዋል።+ 32  ይሖዋ በጦርነት ክንዱን በእነሱ ላይ በሚያነሳበት ጊዜ+በአሦር ላይ የሚያወርደውየቅጣት በትር ሁሉበአታሞና በበገና የታጀበ ይሆናል።+ 33  ቶፌቱ*+ ከወዲሁ ተዘጋጅቷልና፤ለንጉሡም ተዘጋጅቶለታል።+ የእንጨት ክምሩ ጥልቀትና ስፋት ያለው እንዲሆን አድርጓል፤ብዙ እሳትና እንጨትም አለ። የይሖዋ እስትንፋስ ልክ እንደ ድኝ ጅረትበእሳት ያያይዘዋል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የመጠጥ መባ ያፈሳሉ።” ስምምነት ማድረጋቸውን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።
ወይም “ከአፌ መመሪያ ሳይጠይቁ።”
ቃል በቃል “በፈርዖን ምሽግ።”
ወይም “ተወርዋሪ መርዘኛ እባብ።”
ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”
ቃል በቃል “ለስላሳ።”
“ከውኃ ጉድጓድ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በእርግጠኝነት።”
ወይም “በጉጉት።”
ወይም “ቀልጠው የተሠሩ ሐውልቶችህ።”
“ቆሻሻ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “የሰባና ቅባት የሞላበት።”
ጨው ጨው የሚል ጣዕም ያለው የዕፀዋት ዓይነት።
ወይም “ስንጥቅ።”
ወይም “እስትንፋሱ።”
ቃል በቃል “በከንቱነት ወንፊት።”
ወይም “ለበዓል ራሳችሁን በምትቀድሱበት።”
ወይም “የዋሽንት ድምፅ እየሰማ።”
እዚህ ላይ “ቶፌት” የሚለው ቃል እሳት የሚነድበትን ቦታ የሚያሳይ ምሳሌያዊ አገላለጽ ሲሆን ጥፋትን ያመለክታል።