ኢሳይያስ 39:1-8

  • ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች (1-8)

39  በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ፣ የባላዳን ልጅ ሜሮዳክባላዳን ሕዝቅያስ ታሞ እንደነበረና ከሕመሙ እንዳገገመ በመስማቱ ደብዳቤና ስጦታ ላከለት።+  ሕዝቅያስም መልእክተኞቹን በደስታ ተቀበላቸው፤ ከዚያም ግምጃ ቤቱን ይኸውም ብሩን፣ ወርቁን፣ የበለሳን ዘይቱን፣ ሌላውን ምርጥ ዘይት፣ የጦር መሣሪያውን ሁሉና በግምጃ ቤቶቹ+ ውስጥ ያለውን ንብረት በሙሉ አሳያቸው። ሕዝቅያስ በቤቱም* ሆነ በግዛቱ ሁሉ ያላሳያቸው ምንም ነገር አልነበረም።  ከዚያ በኋላ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ መጥቶ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? የመጡትስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “የመጡት ከሩቅ አገር፣ ከባቢሎን ነው” አለው።+  ቀጥሎም “በቤትህ* ያዩት ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “በቤቴ* ያለውን ነገር ሁሉ አይተዋል። በግምጃ ቤቶቼ ውስጥ ካለው ንብረት ሁሉ ያላሳየኋቸው ምንም ነገር የለም” ሲል መለሰለት።  በዚህ ጊዜ ኢሳይያስ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፦ “የሠራዊት ጌታ የይሖዋን ቃል ስማ፤  ‘እነሆ፣ በቤትህ* ያለው ሁሉና አባቶችህ እስካሁን ድረስ ያከማቹት ነገር ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚጋዝበት ቀን ይመጣል። አንድም የሚቀር ነገር አይኖርም’+ ይላል ይሖዋ።+  ‘ከአንተ ከሚወለዱት ከገዛ ልጆችህ መካከልም አንዳንዶቹ ይወሰዳሉ፤ በባቢሎን ንጉሥ ቤተ መንግሥትም ባለሥልጣናት ይሆናሉ።’”+  በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ ኢሳይያስን “የተናገርከው የይሖዋ ቃል መልካም ነው” አለው። አክሎም እንዲህ አለ፦ “ምክንያቱም በእኔ የሕይወት ዘመን* ሰላምና መረጋጋት* ይኖራል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በቤተ መንግሥቱም።”
ወይም “በቤተ መንግሥትህ።”
ወይም “በቤተ መንግሥቴ።”
ወይም “በቤተ መንግሥትህ።”
ቃል በቃል “ቀኖች።”
ወይም “እውነት።”