ኢሳይያስ 27:1-13

  • ይሖዋ ሌዋታንን ይገድለዋል (1)

  • በወይን እርሻ ለተመሰለችው እስራኤል የተዘመረ መዝሙር (2-13)

27  በዚያን ቀን ይሖዋ፣ በፍጥነት እየተሳበ የሚሄደውን እባብ ሌዋታንን፣*ደግሞም እየተጥመለመለ የሚጓዘውን እባብ ሌዋታንንትልቅ፣ ኃይለኛና ምሕረት የለሽ በሆነው ሰይፉ ይቀጣዋል፤+በባሕር ውስጥ ያለውንም ግዙፍ ፍጥረት ይገድለዋል።  2  በዚያ ቀን ለእሷ* እንዲህ ብላችሁ ዘምሩ፦ “የሚፈላ የወይን ጠጅ የሚመረትባት የወይን እርሻ!+  3  እኔ ይሖዋ እጠብቃታለሁ።+ በየጊዜው ውኃ አጠጣታለሁ።+ ማንም ጉዳት እንዳያደርስባትሌት ተቀን እጠብቃታለሁ።+  4  ከእንግዲህ አልቆጣትም።+ በውጊያው ላይ ቁጥቋጦና አረም ይዞ የሚገጥመኝ ማን ነው? ሁሉንም በአንድ ላይ እረግጣቸዋለሁ፤ በእሳትም አቃጥላቸዋለሁ።  5  አለዚያ ምሽጌን የሙጥኝ ይበል። ከእኔ ጋር ሰላም ይፍጠር፤አዎ፣ ከእኔ ጋር ሰላም ይፍጠር።”  6  በመጪዎቹ ቀናት ያዕቆብ ሥር ይሰዳል፤እስራኤል ያብባል እንዲሁም ይለመልማል፤+ምድሩንም በምርት ይሞሉታል።+  7  እሱ አሁን በተመታበት ሁኔታ መመታቱ ተገቢ ነው? ወይስ የተገደሉበት ሰዎች በተፈጁበት መንገድ መገደሉ አስፈላጊ ነው?  8  እሷን በምትልካት ጊዜ በአስደንጋጭ ጩኸት ትፋለማታለህ። የምሥራቅ ነፋስ በሚነፍስበት ቀን በኃይለኛ አውሎ ነፋሱ ያስወግዳታል።+  9  በመሆኑም የያዕቆብ በደል በዚህ መንገድ ይሰረይለታል፤+ኃጢአቱ በሚወገድበት ጊዜ ፍሬው በሙሉ ይህ ይሆናል፦ የመሠዊያ ድንጋዮቹን ሁሉእንደደቀቀ የኖራ ድንጋይ ያደርጋል፤የማምለኪያ ግንዶቹም* ሆኑ የዕጣን ማጨሻዎቹ አይተርፉም።+ 10  የተመሸገችው ከተማ ትተዋለችና፤የግጦሽ መሬቱም ወና ይሆናል፤ እንደ ምድረ በዳም የተተወ ይሆናል።+ በዚያ ጥጃ ይግጣል፤ ይተኛልም፤ቅርንጫፎቿንም ይበላል።+ 11  ቀንበጦቿ በሚደርቁበት ጊዜሴቶች መጥተው ይሰብሯቸዋል፤ከዚያም ማገዶ ያደርጓቸዋል። ይህ ሕዝብ ማስተዋል ይጎድለዋልና።+ በዚህም ምክንያት ፈጣሪያቸው ምንም ምሕረት አያደርግላቸውም፤ሠሪያቸውም ምንም ዓይነት ሞገስ አያሳያቸውም።+ 12  በዚያም ቀን የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፣ ሰው ዛፍ ላይ ያሉ ፍሬዎችን አርግፎ አንድ በአንድ እንደሚለቅም ሁሉ፣ ይሖዋም ከታላቁ ወንዝ* አንስቶ እስከ ግብፅ ደረቅ ወንዝ*+ ድረስ ባለው ቦታ ሁሉ የተበተናችሁትን ይሰበስባችኋል።+ 13  በዚያም ቀን ትልቅ ቀንደ መለከት ይነፋል፤+ በአሦር ምድር+ የጠፉትና በግብፅ ምድር+ የተበተኑት መጥተው በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቅዱስ ተራራ ላይ ለይሖዋ ይሰግዳሉ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

እዚህ ላይ በአንስታይ ፆታ የተገለጸችውና በወይን እርሻ የተመሰለችው እስራኤል ልትሆን ትችላለች።
ኤፍራጥስን ያመለክታል።