ኢሳይያስ 7:1-25
7 በዖዝያ+ ልጅ፣ በኢዮዓታም ልጅ በይሁዳ ንጉሥ በአካዝ ዘመን፣ የሶርያው ንጉሥ ረጺንና የእስራኤል ንጉሥ የሆነው የረማልያህ ልጅ ፋቁሄ+ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ እሱ ግን ድል ሊያደርጋት አልቻለም።*+
2 የዳዊት ቤት፣ “ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ግንባር ፈጥራለች” የሚል ወሬ ደረሰው።
በዚህ ጊዜ የአካዝም ሆነ የሕዝቡ ልብ በነፋስ እንደሚናወጥ የዱር ዛፍ መናወጥ ጀመረ።
3 ከዚያም ይሖዋ ኢሳይያስን እንዲህ አለው፦ “እባክህ፣ አንተና ልጅህ ሸአርያሹብ*+ ከአካዝ ጋር ለመገናኘት ወደ አጣቢው እርሻ በሚወስደው መንገድ አጠገብ ወዳለው ወደ ላይኛው ኩሬ የውኃ መውረጃ ቦይ ጫፍ ውጡ።+
4 እንዲህም በለው፦ ‘አይዞህ፣ ተረጋጋ። በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱ ሁለት የግንድ ጉማጆች ማለትም በሶርያ ንጉሥ በረጺንና በረማልያህ+ ልጅ ኃይለኛ ቁጣ የተነሳ አትፍራ፤ ልብህም አይደንግጥ።
5 ሶርያ ከኤፍሬምና ከረማልያህ ልጅ ጋር እንዲህ ብላ አሲራብሃለች፦
6 “በይሁዳ ላይ እንዝመትና እንበታትነው፤* በቁጥጥራችንም ሥር እናውለው፤* የታብኤልንም ልጅ እናንግሥበት።”+
7 “‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦
“ይህ ሴራ አይሳካም፤ደግሞም አይፈጸምም።
8 የሶርያ ራስ ደማስቆ፣የደማስቆ ራስ ደግሞ ረጺን ነውና።
ኤፍሬም በ65 ዓመት ውስጥብትንትኑ ወጥቶ ሕዝብ መሆኑ ይቀራል።+
9 የኤፍሬም ራስ ሰማርያ+ ነው፤የሰማርያም ራስ የረማልያህ ልጅ ነው።+
ጠንካራ እምነት ከሌላችሁጸንታችሁ መቆም አትችሉም።”’”
10 ከዚያም ይሖዋ አካዝን እንዲህ አለው፦
11 “አምላክህ ይሖዋ ምልክት እንዲያሳይህ ጠይቅ፤+ ምልክቱም እንደ መቃብር* ጥልቅ የሆነ ወይም እንደ ሰማይ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።”
12 አካዝ ግን “አልጠይቅም፤ ይሖዋንም አልፈትንም” አለ።
13 ከዚያም ኢሳይያስ እንዲህ አለ፦ “የዳዊት ቤት ሆይ፣ እባካችሁ ስሙ። የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላክንም ትዕግሥት ልትፈታተኑ ትፈልጋላችሁ?+
14 በመሆኑም ይሖዋ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፦ እነሆ፣ ወጣቷ* ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤+ አማኑኤል* ብላም ትጠራዋለች።+
15 ክፉውን መጥላትና መልካሙን መምረጥ በሚችልበት ጊዜ ቅቤና ማር ይበላል።
16 ልጁ ክፉውን መጥላትና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት በጣም የምትፈራቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ጨርሶ የተተወ ይሆናል።+
17 ይሖዋ፣ ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት+ ጊዜ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፣ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የአሦርን ንጉሥ ያመጣልና።+
18 “በዚያ ቀን ይሖዋ በግብፅ፣ ርቀው በሚገኙት የአባይ ጅረቶች ያሉትን ዝንቦች፣ በአሦርም ምድር ያሉትን ንቦች በፉጨት ይጠራል፤
19 ሁሉም መጥተው ጥልቅ በሆኑ ሸለቆዎች፣* በየዓለቱ ንቃቃት፣ በቁጥቋጦዎች ሁሉና ውኃ ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ።
20 “በዚያም ቀን ይሖዋ በወንዙ* አካባቢ ከሚገኘው ቦታ በተከራየው ምላጭ ይኸውም በአሦር ንጉሥ+ አማካኝነት ራሱንና የእግሩን ፀጉር ይላጨዋል፤ ጢሙንም ሙልጭ አድርጎ ያስወግደዋል።
21 “በዚያም ቀን አንድ ሰው ከመንጋው መካከል አንዲት ጊደርና ሁለት በጎች በሕይወት ያተርፋል።
22 በብዛት ከሚገኘው ወተት የተነሳም ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱ መካከል የቀረው ሰው ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል።
23 “በዚያ ቀን 1,000 የብር ሰቅል የሚያወጣ 1,000 የወይን ተክል ይገኝበት የነበረው ቦታ ሁሉ ቁጥቋጦና አረም ይወርሰዋል።
24 ምድሪቱ በቁጥቋጦና በአረም ስለምትሸፈን ሰዎች ወደዚያ የሚሄዱት ቀስትና ደጋን ይዘው ነው።
25 በአንድ ወቅት በመቆፈሪያ ተመንጥረውና ከአረም ጸድተው የነበሩ ተራሮች ሁሉ ቁጥቋጦና አረም ስለሚወርሳቸው ወደዚያ መሄድ ትፈራለህ፤ እነዚህ ቦታዎች በሬዎች የሚሰማሩባቸውና በጎች የሚፈነጩባቸው ይሆናሉ።”
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “እነሱ ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “ቀሪዎች ብቻ ይመለሳሉ” የሚል ትርጉም አለው።
^ “እናሸብረው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ግንቦቹንም እንንደል።” ቃል በቃል “እንሰንጥቀውም።”
^ ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ልጃገረዷ።”
^ “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” የሚል ትርጉም አለው።
^ ወይም “ደረቅ ወንዞች።”
^ የኤፍራጥስን ወንዝ ያመለክታል።