ኢሳይያስ 53:1-12
53 ከእኛ የሰማውን* ነገር ያመነ ማን ነው?+
የይሖዋስ ክንድ+ ለማን ተገለጠ?+
2 እሱ በፊቱ* እንደ ቅርንጫፍ፣+ በደረቅ ምድር እንዳለ ሥር ይበቅላል።
የሚያምር ቁመናም ሆነ ግርማ ሞገስ የለውም፤+ባየነውም ጊዜ መልኩ አልሳበንም።*
3 ሰዎች የናቁትና ያገለሉት፣+ሥቃይን ያየ፣* ሕመምንም የሚያውቅ ሰው ነበር።
ፊቱ የተሰወረብን ያህል ነበር።*
ሰዎች ናቁት፤ እኛም ከቁብ አልቆጠርነውም።+
4 በእርግጥም እሱ ራሱ ሕመማችንን ተሸከመ፤+ሥቃያችንንም ተቀበለ።+
እኛ ግን እንደተቀሰፈ፣ በአምላክ እንደተመታና እንደተጎሳቆለ አድርገን ቆጠርነው።
5 እሱ ግን ስለ መተላለፋችን+ ተወጋ፤+ስለ በደላችን ደቀቀ።+
በእሱ ላይ የደረሰው ቅጣት ለእኛ ሰላም አስገኘልን፤+በእሱም ቁስል የተነሳ እኛ ተፈወስን።+
6 ሁላችንም እንደ በጎች ተቅበዘበዝን፤+እያንዳንዳችን በየራሳችን መንገድ ሄድን፤ይሖዋም የሁላችንንም በደል እሱ እንዲሸከም አደረገ።+
7 ግፍ ተፈጸመበት፤+ መከራም ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነ፤+ነገር ግን አፉን አልከፈተም።
እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ፤+በሸላቾቿ ፊት ዝም እንደምትል በግ፣እሱም አፉን አልከፈተም።+
8 ፍትሕ ተነፈገ፤* በአግባቡም ሳይዳኝ ተወሰደ፤ትኩረት ሰጥቶ ትውልዱን በዝርዝር ለማወቅ* የሚሞክር ማን ነው?
ከሕያዋን ምድር ተወግዷልና፤+በሕዝቤ መተላለፍ የተነሳ ተመታ።*+
9 ምንም ዓይነት በደል* አልፈጸመም፤እንዲሁም ከአንደበቱ የማታለያ ቃል አልወጣም፤+ሆኖም በሚሞትበት ጊዜ የመቃብር ቦታውከክፉዎችና+ ከሀብታሞች*+ ጋር ይሆናል።*
10 ይሁንና እሱን ማድቀቅ የይሖዋ ፈቃድ ነበር፤* ለሕመም እንዲዳረግም ፈቅዷል።
ሕይወቱን* የበደል መባ አድርገህ የምታቀርበው ከሆነ+ዘሩን ያያል፤ ዘመኑን ያስረዝማል፤+እንዲሁም በእሱ አማካኝነት ይሖዋ ደስ የሚሰኝበት ነገር* ይከናወናል።+
11 በእሱ ላይ ከደረሰው ሥቃይ* የተነሳ፣ በሚያየው መልካም ነገር ይደሰታል።
ጻድቅ አገልጋዬ+ በእውቀቱ አማካኝነትብዙ ሰዎች ጻድቅ ሆነው እንዲቆጠሩ ይረዳል፤+በደላቸውንም ይሸከማል።+
12 ስለዚህ ከብዙዎች ጋር ድርሻውን እሰጠዋለሁ፤ምርኮውን ከኃያላን ጋር ይካፈላል፤ሕይወቱን* እስከ ሞት ድረስ አፍስሷልና፤+ከሕግ ተላላፊዎችም ጋር ተቆጥሯል፤+የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸክሟል፤+ስለ ሕግ ተላላፊዎችም ማልዷል።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “እኛ የሰማነውን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “በፊቱ” የሚለው ቃል፣ ማንኛውንም ተመልካች ወይም አምላክን ሊያመለክት ይችላል።
^ ወይም “እሱን እንድንፈልግ የሚያደርግ የተለየ መልክ አልነበረውም።”
^ ወይም “ሥቃይን የሚረዳ።”
^ “ሰዎች ፊታቸውን የሚያዞሩበት ዓይነት ሰው ነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ተገደለ።”
^ ወይም “ስለ አኗኗሩ በዝርዝር ለማወቅ።”
^ ወይም “ተጨቆነ።”
^ ወይም “ግፍ።”
^ ቃል በቃል “ከሀብታም ሰው።”
^ ወይም “በሚሞትበት ጊዜ ከክፉዎችና ከሀብታሞች ጋር እንዲሆን አንድ ሰው መቃብሩን ይሰጣል።”
^ ወይም “ይሁንና ይሖዋ እሱን በማድቀቅ ደስ ተሰኝቷል።”
^ ወይም “የይሖዋ ፈቃድ።”
^ ወይም “ነፍሱን።”
^ ወይም “በነፍሱ ላይ ከደረሰው ችግር።”
^ ወይም “ነፍሱን።”