በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሀ4

መለኮታዊው ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ

ከባቢሎን ግዞት በፊት መለኮታዊው ስም በጥንታዊው የዕብራይስጥ ፊደላት የተጻፈበት መንገድ

ከባቢሎን ግዞት በኋላ መለኮታዊው ስም በዕብራይስጥ ፊደላት የተጻፈበት መንገድ

በአራት የዕብራይስጥ ተነባቢ ፊደላት (יהוה) የሚወከለው መለኮታዊው ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቴትራግራማተን በመባል የሚታወቁትን እነዚህን አራት ፊደላት “ይሖዋ” ብሎ ተርጉሟቸዋል። ይህ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሌሎች ስሞች ይበልጥ በብዛት ተጠቅሶ ይገኛል። መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ መሪነት የጻፉት ሰዎች አምላክን “ሁሉን ቻይ፣” “ልዑል” እና “ጌታ” እንደሚሉት ባሉ የተለያዩ የማዕረግ ስሞችና ማንነቱን በሚገልጹ መጠሪያዎች የጠሩት ቢሆንም አምላክን ለይተው ለማሳወቅ የተጠቀሙበት ብቸኛው የግል መጠሪያ ስም ቴትራግራማተን ተብሎ የሚታወቀው ነው።

ይሖዋ ራሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን በስሙ እንዲጠቀሙ መርቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ኢዩኤልን “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ብሎ እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶታል። (ኢዩኤል 2:32) በተጨማሪም አንድ መዝሙራዊ “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ” ብሎ እንዲጽፍ አድርጓል። (መዝሙር 83:18) እንዲያውም መለኮታዊው ስም የአምላክ ሕዝቦች እንዲዘምሩትና በቃላቸው እንዲወጡት ታስቦ በግጥም መልክ በተቀናበረው በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ብቻ 700 ጊዜ ያህል ተጠቅሷል። ታዲያ የአምላክ ስም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ የማይገኘው ለምንድን ነው? ይህ ትርጉም “ይሖዋ” የሚለውን አጠራር ለመጠቀም የመረጠው ለምንድን ነው? ይሖዋ የሚለው መለኮታዊ ስም ትርጉምስ ምንድን ነው?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የመጀመሪያ አጋማሽ ከተዘጋጀ የሙት ባሕር ጥቅልል ላይ የተወሰደ የመዝሙር መጽሐፍ ቁራጭ። ይህ ጽሑፍ የተጻፈው ከባቢሎን ግዞት በኋላ ጥቅም ላይ ይውል በነበረው የዕብራይስጥ የፊደል አጣጣል ቢሆንም ቴትራግራማተን በመባል የሚታወቁት አራት ፊደላት ግን በጥንታዊው የዕብራይስጥ ሆሄያት ለየት ባለ መንገድ በተደጋጋሚ ተጽፈው ይገኛሉ

የአምላክ ስም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ የማይገኘው ለምንድን ነው? ለዚህ የሚቀርቡት ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው። አንዳንዶች ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ማንነቱን የሚያሳውቅ ልዩ ስም መጠቀም እንደማያስፈልገው ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ የአምላክን ስም ከመጠቀም የተቆጠቡት የአይሁዳውያን አጉል ልማድ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው ሊሆን ይችላል፤ አይሁዳውያን ይህን ያደርጉ የነበረው ስሙን እንዳያረክሱ በመፍራት ሳይሆን አይቀርም። አንዳንዶች ደግሞ ማንም ሰው የአምላክን ስም ትክክለኛ አጠራር በእርግጠኝነት መናገር ስለማይችል “ጌታ” እና “አምላክ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች መጠቀም የተሻለ እንደሆነ ያምናሉ። ሆኖም ከሚከተሉት ነጥቦች አንጻር ስናያቸው ከላይ የቀረቡት ሐሳቦች ምክንያታዊ አይደሉም፦

  • ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ልዩ ስም አያስፈልገውም ብለው የሚከራከሩ ሰዎች፣ ከክርስቶስ ዘመን በፊት የተዘጋጁትን ጨምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቀው የቆዩት የአምላክ ቃል ጥንታዊ ቅጂዎች የአምላክን የግል ስም እንደያዙ የሚያሳየውን ማስረጃ ከግምት ሳያስገቡ ቀርተዋል። ቀደም ብሎ እንደተገለጸው አምላክ፣ ስሙ በቃሉ ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል እንዲጠቀስ አድርጓል። ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አምላክ ስሙን እንድናውቅና በስሙ እንድንጠቀም ይፈልጋል።

  • ለአይሁዳውያን ልማድ ካላቸው አክብሮት የተነሳ ስሙን ላለመጠቀም የመረጡ ተርጓሚዎች አንድ ወሳኝ እውነታ ዘንግተዋል። አንዳንድ አይሁዳውያን ጸሐፍት የአምላክን ስም መጥራት ባይፈልጉም ከመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎቻቸው ውስጥ ግን አላወጡትም። በሙት ባሕር አቅራቢያ በኩምራን በተገኙት ጥንታዊ ጥቅልሎች ላይ የአምላክ ስም በብዙ ቦታዎች ተጠቅሶ ይገኛል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መለኮታዊው ስም ይገኝ በነበረባቸው ቦታዎች ላይ “ጌታ” እና “እግዚአብሔር” እንደሚሉት ያሉ ስያሜዎችን ሲተኩ ለየት ባለ የፊደል አጣጣል በመጻፍ ስሙ በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ ይገኝ እንደነበር ለመጠቆም ሞክረዋል። ይሁንና የሚከተሉት ጥያቄዎች ምላሽ ያሻቸዋል፦ እነዚህ ተርጓሚዎች የአምላክ ስም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ሺህ ጊዜ ተጠቅሶ እንደሚገኝ እያወቁ ስሙን በሌላ የመተካት ወይም ከነጭራሹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማውጣት ነፃነት እንዳላቸው የተሰማቸው ለምንድን ነው? የአምላክን ስም በሌላ እንዲተኩ ማን ሥልጣን ሰጣቸው? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የሚችሉት እነሱ ብቻ ናቸው።

  • የመለኮታዊው ስም ትክክለኛ አጠራር ስለማይታወቅ ልንጠቀምበት አይገባም የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች ኢየሱስ የሚለውን ስም ግን በነፃነት ይጠቀሙበታል። ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የኢየሱስን ስም ይጠሩ የነበረበት መንገድ ዛሬ አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ስሙን ከሚጠሩበት መንገድ በመጠኑ ይለያል። አይሁዳውያን የሆኑ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የሚለውን ስም ይጠሩ የነበረው የሹአ ብለው ሳይሆን አይቀርም። “ክርስቶስ” የሚለውን የማዕረግ ስም የሚጠሩት ደግሞ ማሺያህ ወይም “መሲሕ” ብለው ነበር። ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ ክርስቲያኖች የሶስ ክሪስቶስ፣ ላቲን ተናጋሪ የሆኑ ክርስቲያኖች ደግሞ የሱስ ክርስቶስ ብለው ይጠሩት ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች በመንፈስ መሪነት መጽሐፍ ቅዱስን ሲጽፉ በቋንቋቸው የተለመደውን የኢየሱስን ስም ግሪክኛ አጠራር መጠቀማቸው ትክክለኛውን አካሄድ እንደተከተሉ ያሳያል። በተመሳሳይም የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ፣ የጥንት ዕብራውያን ይጠቀሙበት ከነበረው የአምላክ ስም አጠራር ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ ነው ባይባልም “ይሖዋ” በሚለው የስሙ አጠራር መጠቀምን ምክንያታዊ ሆኖ አግኝቶታል።

አዲስ ዓለም ትርጉም “ይሖዋ” የሚለውን አጠራር ለመጠቀም የመረጠው ለምንድን ነው? ቴትራግራማተን (יהוה) ተብለው የሚጠሩት አራት ፊደላት በአማርኛ የሐወሐ በሚሉት ተነባቢ ፊደላት ይወከላሉ። በጥንታዊው የዕብራይስጥ ቋንቋ የአጻጻፍ ስልት መሠረት አንድ ቃል ሲጻፍ አናባቢዎች እንደማይገቡለት ሁሉ ቴትራግራማተንም አናባቢዎች አልነበሩትም። ጥንታዊው የዕብራይስጥ ቋንቋ የሰዎች የዕለት ተዕለት መግባቢያ በነበረበት ዘመን አንባቢዎች አንድን ቃል ሲያነቡ ተስማሚ የሆኑትን አናባቢዎች በቀላሉ አስገብተው ማንበብ ይችሉ ነበር።

የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ተጽፈው ካበቁ ከአንድ ሺህ ዓመት ገደማ በኋላ አይሁዳውያን ምሁራን የዕብራይስጥ ቋንቋ በሚነበብበት ጊዜ የትኞቹን አናባቢዎች መጠቀም እንደሚገባ የሚጠቁሙና የፊደሉን አጠራር የሚያሳዩ ነጥቦችን ወይም ምልክቶችን ሥራ ላይ ማዋል ጀመሩ። ሆኖም በወቅቱ ብዙዎቹ አይሁዳውያን የአምላክን ስም መጥራት ተገቢ አይደለም የሚል አጉል እምነት ስለነበራቸው ሌሎች ምትክ ስያሜዎችን ይጠቀሙ ነበር። ከዚህም የተነሳ ጸሐፊዎቹ ቴትራግራማተንን በሚገለብጡበት ጊዜ የምትክ ስያሜዎቹን አናባቢዎች መለኮታዊውን ስም በሚወክሉት በአራቱ ተነባቢዎች ላይ መጨመር የጀመሩ ይመስላል። በመሆኑም እነዚህ አናባቢ ምልክቶች የገቡባቸው በእጅ የተጻፉ ጥንታዊ ቅጂዎች የአምላክ ስም በመጀመሪያው የዕብራይስጥ ጽሑፍ ላይ እንዴት ይነበብ እንደነበር ለማወቅ አይረዱም። አንዳንዶች ስሙ “ያህዌህ” ተብሎ መነበብ እንዳለበት ይሰማቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ከዚህ የተለዩ አጠራሮችን ይመርጣሉ። የዘሌዋውያንን መጽሐፍ ግሪክኛ ትርጉም በከፊል የያዘው የሙት ባሕር ጥቅልል መለኮታዊውን ስም ያኦ በማለት በግሪክኛ ፊደላት ጽፎታል። የጥንቶቹ ግሪካውያን ጸሐፊዎች ከዚህ አጠራር ሌላ እንደ ያኤ፣ ያቤ እና ያኦአ ያሉ አማራጭ አጠራሮችም ትክክል እንደሆኑ ይገልጻሉ። ያም ሆነ ይህ አንድ ሰው ትክክለኛው አጠራር ይህ ብቻ ነው የሚል ድርቅ ያለ አቋም የሚይዝበት ምንም ምክንያት የለም። ለምን ቢባል የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች የአምላክን ስም በዕብራይስጥ ምን ብለው ይጠሩት እንደነበር በውል ማወቅ አንችልም። (ዘፍጥረት 13:4፤ ዘፀአት 3:15) በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር አምላክ ከሕዝቡ ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ ስሙን በተደጋጋሚ ይጠቀምና አገልጋዮቹም በዚህ ስም ይጠሩት እንደነበር ነው፤ ይህ ብቻ ሳይሆን የአምላክ አገልጋዮች ከሌሎች ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜ ስሙን በነፃነት ይጠቀሙበት ነበር።–ዘፀአት 6:21 ነገሥት 8:23፤ መዝሙር 99:9

ታዲያ ይህ ትርጉም “ይሖዋ” የሚለውን አጠራር ለመጠቀም የመረጠው ለምንድን ነው? ሰዎች በአማርኛ ቋንቋ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲጠቀሙበት የነበረው አጠራር ይህ ስለሆነ ነው። ሌሎች ቋንቋዎችም ብዙ ጊዜ ሲሠራበት የነበረውን የስሙን አጠራር ተጠቅመዋል።

በ1530 ዊልያም ቲንደል ባዘጋጀው የፔንታቱክ ትርጉም በዘፍጥረት 15:2 ላይ የሚገኘው የአምላክ ስም

ለምሳሌ ያህል፣ በእንግሊዝኛ በተዘጋጁት መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ የአምላክ የግል ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በ1530 ዊልያም ቲንደል ባዘጋጀው የፔንታቱክ ትርጉም ላይ ነው። ቲንደል የተጠቀመው “የሆአህ” የሚለውን አጠራር ነበር። በጊዜ ሂደት የእንግሊዝኛ ቋንቋ እየተለወጠ በመሄዱ መለኮታዊው ስም ከዘመናዊው የአጻጻፍ ስልት ጋር የሚስማማ ይዘት እንዲኖረው ተደረገ። ለምሳሌ ያህል፣ በ1612 ሄንሪ ኤንስዎርዝ መዝሙር መጽሐፍን ሲተረጉሙ በሁሉም ቦታ ላይ “የሆቫህ” የሚለውን አጠራር ተጠቅመዋል። ከዚያም በ1639 ይህ ትርጉም ተሻሽሎ ሲወጣና ከፔንታቱክ ጋር አብሮ ሲታተም “ጀሆቫ” በሚለው አጠራር ተተካ። በ1901 አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያዘጋጁት ተርጓሚዎች በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ መለኮታዊው ስም ባለበት ቦታ ሁሉ “ጀሆቫ” የሚለውን አጠራር ተጠቅመዋል።

ጆሴፍ ብርያንት ሮዘርሃም በ1911 ባሳተሙት ስተዲስ ኢን ዘ ሳልምስ በተባለው መጽሐፍ ላይ “ያህዌህ” ከሚለው ይልቅ “ጀሆቫ” የሚለውን አጠራር ለመጠቀም የመረጡት ለምን እንደሆነ ሲናገሩ “አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች የሚያውቁትን (ደግሞም ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያለውን) የመለኮታዊውን ስም አጠራር” ለመጠቀም ስለፈለጉ መሆኑን ገልጸዋል። በ1930 አሌክሳንደር ፍራንሲስ ኪሪክፓትሪክ “ጀሆቫ” የሚለውን አጠራር መጠቀምን በተመለከተ እንደሚከተለው ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል፦ “በዘመናችን ያሉ የሰዋስው ምሁራን ያህቬህ ወይም ያሃቬህ ተብሎ መነበብ አለበት በማለት ይከራከራሉ፤ ይሁንና ጀሆቫ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ውስጥ በደንብ ሥር የሰደደ ይመስላል፤ ደግሞም ዋናው ቁም ነገር ትክክለኛውን አጠራር የማወቁ ጉዳይ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይህ ስም ‘ጌታ’ እንደሚለው የማዕረግ ስም ሳይሆን የተጸውኦ ስም መሆኑን አምኖ መቀበሉ ነው።”

ቴትራግራማተን፣ የሐወሐ፦  “እንዲሆን ያደርጋል”

ሐወሐ የሚለው ግስ፦ “መሆን”

ይሖዋ የሚለው መለኮታዊ ስም ትርጉም ምንድን ነው? በዕብራይስጥ ቋንቋ ይሖዋ የሚለው ስም “መሆን” የሚል ትርጉም ካለው ግስ የተገኘ ሲሆን አንዳንድ ምሁራን የግሱ አገባብ አስደራጊነትን እንደሚያመለክት ይገልጻሉ። በመሆኑም የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ የአምላክ ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም እንዳለው ያምናል። ምሁራን ይህን በተመለከተ የተለያየ አመለካከት ስላላቸው በዚህ ረገድ ድርቅ ያለ አቋም መያዝ አስፈላጊ አይደለም። ይሁን እንጂ ይህ ፍቺ፣ ይሖዋ የሁሉ ነገር ፈጣሪ በመሆን የተጫወተውን ሚና እና ዓላማውን ዳር የማድረስ ችሎታውን ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። ይሖዋ፣ ጽንፈ ዓለምና የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ወደ ሕልውና እንዲመጡ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ፈቃዱም ሆነ ዓላማው ፍጻሜውን እንዲያገኝ ማድረጉን ቀጥሏል።

በመሆኑም ይሖዋ የሚለው ስም ትርጉም በዘፀአት 3:14 ላይ የሚገኘው ከስሙ ጋር የተያያዘ ግስ በሚያስተላልፈው ሐሳብ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ጥቅሱ “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” ወይም “የምሆነውን እሆናለሁ” ይላል። ጉዳዩን በጥልቀት ካየነው እነዚህ ቃላት የአምላክን ስም ትርጉም በተሟላ ሁኔታ አይገልጹም። ከዚህ ይልቅ የአምላክን ባሕርይ አንዱን ገጽታ ይኸውም አምላክ በማንኛውም ሁኔታ ሥር ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚሆን የሚያሳዩ ናቸው። ይሖዋ የሚለው ስም ይህን ሐሳብ የሚያጠቃልል ቢሆንም እንኳ የስሙ ትርጉም እሱ መሆን የሚፈልገውን እንደሚሆን የሚገልጽ ብቻ አይደለም። የስሙ ትርጉም፣ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ፍጥረታቱ እሱ የሚፈልገውን እንዲሆኑ እንደሚያደርግም ያመለክታል።