ሀ1
ለመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት ሆነው የሚያገለግሉ መመሪያዎች
መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈው በጥንቶቹ የዕብራይስጥ፣ የአረማይክና የግሪክኛ ቋንቋዎች ነበር። በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ሆነ በከፊል ከ3,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈባቸውን ቋንቋዎች መረዳት አይችሉም፤ ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ በቋንቋቸው መተርጎሙ የግድ ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሲተረጎም የትኞቹ መመሪያዎች ግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል? የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ሲዘጋጅ እነዚህ መመሪያዎች ሥራ ላይ የዋሉትስ እንዴት ነው?
አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል ቢተረጎም አንባቢው በኩረ ጽሑፉ የተጻፈባቸው ቋንቋዎች የሚያስተላልፉትን ሐሳብ በተሻለ ሁኔታ መረዳት እንደሚችል ይሰማቸዋል። ይሁንና ይህ ሁልጊዜ ያስኬዳል ማለት አይደለም። እንዲህ የምንልበትን ምክንያት የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፦
-
ሁለት ቋንቋዎች ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ ሰዋስው፣ የቃላት ብዛትና የዓረፍተ ነገር አወቃቀር ሊኖራቸው አይችልም። በዕብራይስጥ ቋንቋ ላይ ጥናት ያካሄዱት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ድራይቨር፣ ቋንቋዎች “የሰዋስው ሕጋቸውና አመጣጣቸው ብቻ ሳይሆን . . . ሐሳብን በዓረፍተ ነገር የሚገልጹበት መንገድም ይለያያል” ሲሉ ጽፈዋል። የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ሰዎች የሚያስቡበትም መንገድ የዚያኑ ያህል ይለያያል። ፕሮፌሰር ድራይቨር በመቀጠል “ከዚህም የተነሳ የተለያዩ ቋንቋዎች የዓረፍተ ነገር አወቃቀር የተለያየ ነው” ብለዋል።
-
በዛሬው ጊዜ የሚገኝ የትኛውም ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈባቸው የዕብራይስጥ፣ የአረማይክና የግሪክኛ ቋንቋዎች ጋር ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ የቃላት ብዛትና ሰዋስው ሊኖረው አይችልም፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል ቢተረጎም ለመረዳት የሚያስቸግር አልፎ ተርፎም የተሳሳተ ሐሳብ የሚያስተላልፍ ሊሆን ይችላል።
-
የአንድ ቃል ወይም አባባል ትርጉም እንደየአገባቡ ሊለያይ ይችላል።
አንድ ተርጓሚ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የመጀመሪያውን ቋንቋ ቃል በቃል በመተርጎም ሐሳቡን በትክክል ማስተላለፍ ይችል ይሆናል፤ ይሁንና ይህ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።
ቃል በቃል መተርጎም የተሳሳተ ሐሳብ ሊያስተላልፍ እንደሚችል የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት፦
-
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘መተኛት’ እና ‘ማንቀላፋት’ የሚሉት ቃላት፣ ቃል በቃል መተኛትን ወይም በሞት ማንቀላፋትን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። (ማቴዎስ 28:13፤ የሐዋርያት ሥራ 7:60) እነዚህ ቃላት ሞትን ለማመልከት በተሠራባቸው ቦታዎች ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ‘በሞት ማንቀላፋት’ እንደሚሉት ያሉ አንባቢው ሐሳቡን በግልጽ እንዲረዳ የሚያግዙ አገላለጾችን ሊጠቀሙ ይችላሉ።–1 ቆሮንቶስ 7:39፤ 1 ተሰሎንቄ 4:13፤ 2 ጴጥሮስ 3:4
-
ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን 4:14 ላይ ቃል በቃል “በሰዎች የዳይ ጨዋታ” ተብሎ ሊተረጎም የሚችል አባባል ተጠቅሟል። ይህ ጥንታዊ የሆነ ዘይቤያዊ አነጋገር በዳይ ጨዋታ ሌሎችን ማጭበርበርን ያመለክታል። ይሁንና ይህ አገላለጽ ቃል በቃል ቢተረጎም በብዙ ቋንቋዎች ምንም ስሜት የማይሰጥ ሊሆን ይችላል። ይህ ዘይቤያዊ አነጋገር “በሰዎች የማታለያ ዘዴ” ተብሎ መተርጎሙ ሐሳቡን ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል።
-
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም 12:11 ላይ ቃል በቃል ሲተረጎም “መንፈሱ እስኪፈላ” የሚል የግሪክኛ አባባል ተጠቅሟል። ይህ አባባል በአማርኛ በዚህ መንገድ ቢተረጎም ትክክለኛውን ሐሳብ አያስተላልፍም፤ ስለሆነም በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ “በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ” ተብሎ ተተርጉሟል።
-
ኢየሱስ ታዋቂ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ የተናገረው አንድ አባባል ብዙ ጊዜ “በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው” ተብሎ ተተርጉሟል። (ማቴዎስ 5:3 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ይሁንና በብዙ ቋንቋዎች ይህ አባባል ቃል በቃል ሲተረጎም ትክክለኛውን ሐሳብ አያስተላልፍም። እንዲያውም በአንዳንድ ቋንቋዎች ይህ አባባል ቃል በቃል ቢተረጎም “በመንፈስ ድኾች” የተባሉት ሰዎች የአእምሮ ችግር እንዳለባቸው ወይም መንፈሰ ጠንካራና ቆራጥ እንዳልሆኑ የሚያመለክት ሐሳብ ሊያስተላልፍ ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን አባባል የተጠቀመው ሰዎች ደስተኛ መሆናቸው የተመካው ቁሳዊ ፍላጎታቸውን በማርካታቸው ላይ ሳይሆን የአምላክ መመሪያ እንደሚያስፈልጋቸው በማስተዋላቸው ላይ እንደሆነ ማስተማር ፈልጎ ነው። (ሉቃስ 6:20) በመሆኑም “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ” ወይም “አምላክ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያውቁ” እንደሚሉት ያሉ ትርጉሞች መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ሊተላለፍ የተፈለገውን ሐሳብ በተሻለ መንገድ ይገልጻሉ።–ማቴዎስ 5:3 ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ
-
“ቅናት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በአብዛኛው የሚያመለክተው አንድ ሰው የቅርብ ወዳጁ ለእሱ ያለውን ታማኝነት እንዳጓደለ ሲሰማው የሚያድርበትን ብስጭት ወይም ሌሎች ባገኙት ነገር መቅናትን ነው። (ምሳሌ 6:34፤ ) ይሁን እንጂ ይህ የዕብራይስጥ ቃል አዎንታዊ በሆነ መንገድም ይሠራበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ‘መቅናቱን’ ወይም እነሱን ከጉዳት ለመጠበቅ እጅግ ከፍተኛ ፍላጎት ያለው መሆኑን ለማሳየት ሊሠራበት ይችላል፤ በተጨማሪም ይሖዋ “እሱ ብቻ እንዲመለክ” የሚፈልግ አምላክ መሆኑን ለመግለጽ ሊያገለግል ይችላል። ( ኢሳይያስ 11:13ዘፀአት 34:14፤ 2 ነገሥት 19:31፤ ሕዝቅኤል 5:13፤ ዘካርያስ 8:2) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ለእሱና ለአምልኮው ያላቸውን “ቅንዓት” ወይም ‘እሱን የሚቀናቀነውን ማንኛውንም ነገር በቸልታ እንደማያልፉ’ ለማመልከት ተሠርቶበታል።–መዝሙር 69:9፤ 119:139፤ ዘኁልቁ 25:11
-
አብዛኛውን ጊዜ የሰውን እጅ ለማመልከት የሚሠራበት የዕብራይስጥ ቃል የተለያዩ ትርጉሞች አሉት። በመሆኑም ይህ ቃል እንደየአገባቡ “ሥልጣን፣” “ልግስና” ወይም “ኃይል” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። (2 ሳሙኤል 8:3፤ 1 ነገሥት 10:13፤ ምሳሌ 18:21) እንዲያውም ይህ ቃል በአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ40 በሚበልጡ የተለያዩ ቃላት ተተርጉሟል።
ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ያለን አንድን ቃል ሁልጊዜ በተመሳሳይ ቃል ከመተካት የበለጠ ነገር ይጠይቃል። አንድ ተርጓሚ፣ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈባቸው ቋንቋዎች የሚያስተላልፉትን ሐሳብ በትክክል ሊገልጹ የሚችሉ ቃላትን በመምረጥ ረገድ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ይኖርበታል። በተጨማሪም ዓረፍተ ነገሮችን ከቋንቋው የሰዋስው ሕግ ጋር በሚስማማ ሁኔታ በማዋቀር ለንባብ በማያስቸግር መንገድ አሰካክቶ ማስቀመጥ ያስፈልገዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ተርጓሚው ወደ ሌላው ጽንፍ በመሄድ ጽሑፉን እንዳሻው ከመተርጎም መቆጠብ ይኖርበታል። አንድ ተርጓሚ ሐሳቡን እሱ በመሰለው መንገድ የሚተረጉም ከሆነ ጽሑፉ የያዘውን መልእክት ሊያዛባ ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ተርጓሚው የመጀመሪያው ጽሑፍ የያዘው ሐሳብ ይህ መሆን አለበት ብሎ በማሰብ የራሱን አመለካከት ሊጨምር ወይም ጽሑፉ የያዘውን አስፈላጊ የሆነ ዝርዝር መረጃ ሊያስቀር ይችላል። እንዲህ ያለ ትርጉም ለማንበብ ቀላል ስለሚሆን ሰዎችን ሊማርክ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ተርጓሚው ይህን ዓይነት ነፃነት ተሰምቶት የሚተረጉመው ትርጉም አንባቢው የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ መልእክት እንዳይረዳ እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል።
አንድ ተርጓሚ ሃይማኖታዊ አመለካከቱ በትርጉም ሥራው ላይ በቀላሉ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ማቴዎስ 7:13 “ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ሰፊ [ነው]” ይላል። አንዳንድ ተርጓሚዎች ሃይማኖታዊ አመለካከታቸው ካሳደረባቸው ተጽዕኖ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም “ጥፋት” ተብሎ መተርጎም ያለበትን የግሪክኛ ቃል “ሲኦል” ብለው ተርጉመውታል።
በተጨማሪም አንድ ተርጓሚ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ገበሬዎችን፣ እረኞችንና ዓሣ አጥማጆችን ጨምሮ ተራው ሕዝብ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ይጠቀምበት በነበረው ቋንቋ ነህምያ 8:8, 12፤ የሐዋርያት ሥራ 4:13) ስለዚህ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጥሩ ነው የሚባለው ባሕላቸው ወይም አስተዳደጋቸው ምንም ይሁን ምን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች መልእክቱን በቀላሉ ሊረዱት ከቻሉ ነው። በመሆኑም አብዛኞቹ ሰዎች እምብዛም የማያውቋቸውን ቃላት ከመጠቀም ይልቅ ግልጽ፣ የተለመዱና ለመረዳት ቀላል የሆኑ አገላለጾችን መጠቀሙ ይመረጣል።
መሆኑን መዘንጋት አይኖርበትም። (የአምላክ ስም በእጅ በተጻፉ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ የሚገኝ ቢሆንም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ያለ በቂ ምክንያት ስሙን ከትርጉሞቻቸው ውስጥ አውጥተውታል። (ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ4ን ተመልከት።) ብዙዎቹ ትርጉሞች የአምላክን ስም “ጌታ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች የተኩት ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ አምላክ ስም ያለው መሆኑ እንኳ እንዳይታወቅ አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንዳንድ ትርጉሞች ውስጥ በዮሐንስ 17:6, 26 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ ያቀረበው ጸሎት “ለሰጠኸኝ ሰዎች አንተን ገልጬላቸዋለሁ” እንዲሁም “አንተን አሳውቄአቸዋለሁ” ተብሎ ተተርጉሟል። ይሁንና ኢየሱስ ያቀረበው ጸሎት ትክክለኛ ትርጉም “ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ” እና “ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ” የሚል ነው።
በእንግሊዝኛ ቋንቋ በተዘጋጀው በመጀመሪያው የአዲስ ዓለም ትርጉም መቅድም ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰፍሯል፦ “ቅዱሳን መጻሕፍትን የተረጎምነው በራሳችን አባባል አይደለም። ዘመናዊው የእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚፈቅድልን እስከሆነና ቃል በቃል መተርጎማችን ሐሳቡን የማያድበሰብሰው ወይም የማያዛባው እስከሆነ ድረስ በተቻለ መጠን ቃል በቃል ለመተርጎም ጥረት አድርገናል።” በመሆኑም የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸው የመጀመሪያ ቋንቋዎች የያዙትን ሐሳብ የሚያንጸባርቁ ቃላትንና አገላለጾችን የተጠቀመ ቢሆንም ለማንበብ የሚያስቸግሩ ወይም ሐሳቡን የሚያድበሰብሱ አገላለጾችን ከመጠቀም በመቆጠብ ሚዛናዊ ለመሆን ጥረት አድርጓል። ከዚህም የተነሳ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማንበብ አስደሳች ከመሆኑም ሌላ አንባቢው አምላክ በመንፈሱ መሪነት ያስጻፈውን መልእክት በትክክል እንደሚያገኝ ሙሉ በሙሉ ሊተማመን ይችላል።–1 ተሰሎንቄ 2:13