የማቴዎስ ወንጌል 6:1-34

 • የተራራው ስብከት (1-34)

  • “ግብዞች አትሁኑ” (1-4)

  • ጸሎትን በተመለከተ የተሰጠ ትምህርት (5-15)

   • የጸሎት ናሙና (9-13)

  • ጾም (16-18)

  • በምድር ሳይሆን በሰማይ ሀብት ማከማቸት (19-24)

  • አትጨነቁ (25-34)

   • የአምላክን መንግሥት ፈልጉ (33)

6  “ሰዎች እንዲያዩላችሁ ብላችሁ+ የጽድቅ ሥራችሁን በእነሱ ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ በሰማያት ካለው አባታችሁ ምንም ብድራት አታገኙም።  በመሆኑም ምጽዋት* በምትሰጡበት ጊዜ በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለው በምኩራቦችና በጎዳናዎች ላይ አስቀድመው መለከት እንደሚያስነፉ ግብዞች አትሁኑ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል።  አንተ ግን ምጽዋት ስትሰጥ ቀኝ እጅህ የሚያደርገውን ግራ እጅህ አይወቅ፤  ይህም ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ያስችላል። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል።+  “በተጨማሪም በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤+ እነሱ ሰዎች እንዲያዩአቸው+ በምኩራቦችና በየአውራ ጎዳናው ማዕዘኖች ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል።  አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ።+ በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል።  በምትጸልዩበት ጊዜ አሕዛብ እንደሚያደርጉት አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ፤ እነሱ ቃላት በማብዛት ጸሎታቸው የሚሰማላቸው ይመስላቸዋል።  ስለዚህ እንደ እነሱ አትሁኑ፤ አባታችሁ ገና ሳትለምኑት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና።+  “እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦+ “‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ+ ይቀደስ።*+ 10  መንግሥትህ+ ይምጣ። ፈቃድህ+ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።*+ 11  የዕለቱን ምግባችንን* ዛሬ ስጠን፤+ 12  የበደሉንን* ይቅር እንዳልን በደላችንን* ይቅር በለን።+ 13  ከክፉው+ አድነን* እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።’+ 14  “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤+ 15  እናንተ ግን የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።+ 16  “በምትጾሙበት+ ጊዜ እንደ ግብዞች ፊታችሁን አታጠውልጉ፤ እነሱ መጾማቸው በሰው ዘንድ እንዲታወቅላቸው ፊታቸውን ያጠወልጋሉ።*+ እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። 17  አንተ ግን ስትጾም ራስህን ተቀባ፤ ፊትህንም ታጠብ፤ 18  እንዲህ ካደረግክ የምትጾመው በሰው ለመታየት ሳይሆን በስውር ላለው አባትህ ስትል ብቻ ይሆናል። በስውር የሚያይ አባትህም መልሶ ይከፍልሃል። 19  “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በሚችልበት በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ።*+ 20  ከዚህ ይልቅ ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና+ ሌባ ገብቶ ሊሰርቀው በማይችልበት በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ።+ 21  ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናልና። 22  “የሰውነት መብራት ዓይን ነው።+ ስለሆነም ዓይንህ በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ* ከሆነ መላ ሰውነትህ ብሩህ* ይሆናል። 23  ይሁን እንጂ ዓይንህ ምቀኛ*+ ከሆነ መላ ሰውነትህ ጨለማ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን በእርግጥ ጨለማ ከሆነ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን! 24  “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል+ ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።+ 25  “ስለዚህ እላችኋለሁ፦ ስለ ሕይወታችሁ* ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን ወይም ደግሞ ስለ ሰውነታችሁ ምን እንለብሳለን ብላችሁ+ አትጨነቁ።*+ ሕይወት* ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥም?+ 26  የሰማይ ወፎችን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤+ እነሱ አይዘሩም፣ አያጭዱም ወይም በጎተራ አያከማቹም፤ ይሁንና በሰማይ ያለው አባታችሁ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም? 27  ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ* መጨመር የሚችል ይኖራል?+ 28  ስለ ልብስስ ቢሆን ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ አይለፉም ወይም አይፈትሉም፤ 29  እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ያን ያህል ክብር የነበረው ሰለሞን+ እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዷ አላጌጠም። 30  አምላክ ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ ምድጃ የሚጣለውን የሜዳ ተክል እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም? 31  ስለዚህ ‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ አሊያም ‘ምን እንለብሳለን?’+ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ።+ 32  እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሕዛብ አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው። በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። 33  “እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤* እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።+ 34  ስለዚህ ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤+ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የምሕረት ስጦታ።” ወይም “ለድሆች ስጦታ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የተቀደሰ ይሁን፤ ብሩክ ይሁን።”
ወይም “ፈቃድህ በሰማይ እንዲሁም በምድር ይሁን።”
ቃል በቃል “ዳቧችንን።”
ቃል በቃል “የሌሎችን ዕዳ።”
ቃል በቃል “ዕዳችንን።”
ወይም “ታደገን።”
ወይም “ራሳቸውን ይጥላሉ።”
ወይም “ማከማቸት ተዉ።”
ወይም “አጥርቶ የሚያይ።” ቃል በቃል “ቀላል።”
ወይም “በብርሃን የተሞላ።”
ቃል በቃል “መጥፎ፤ ክፉ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “መጨነቃችሁን ተዉ።”
ወይም “ነፍሳችሁ።”
ለ14ን ተመልከት።
ወይም “መፈለጋችሁን ቀጥሉ።”