የሐዋርያት ሥራ 4:1-37

  • ጴጥሮስና ዮሐንስ ተይዘው ታሰሩ (1-4)

    • ያመኑት ወንዶች ቁጥር 5,000 ደረሰ (4)

  • በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ቀረቡ (5-22)

    • “ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም” (20)

  • ድፍረት ለማግኘት የቀረበ ጸሎት (23-31)

  • ደቀ መዛሙርቱ ያላቸው ነገር ሁሉ የጋራ ነበር (32-37)

4  ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሕዝቡ እየተናገሩ ሳሉ ካህናቱ፣ የቤተ መቅደሱ ሹምና ሰዱቃውያን+ ድንገት ወደ እነሱ መጡ።  እነሱም ሐዋርያቱ ሕዝቡን እያስተማሩና ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ በግልጽ እየተናገሩ+ ስለነበር እጅግ ተቆጡ።  በመሆኑም ያዟቸው፤ መሽቶም ስለነበር እስከ ማግስቱ ድረስ እስር ቤት አቆዩአቸው።+  ይሁን እንጂ ንግግሩን ሰምተው ከነበሩት መካከል ብዙዎቹ አመኑ፤ የወንዶቹም ቁጥር 5,000 ገደማ ሆነ።+  በማግስቱም የሕዝቡ ገዢዎች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤  የካህናት አለቃው ሐና፣+ ቀያፋ፣+ ዮሐንስ፣ እስክንድርና የካህናት አለቃው ዘመዶችም ሁሉ ከእነሱ ጋር ነበሩ።  ጴጥሮስንና ዮሐንስን በመካከላቸው አቁመው “ይህን ያደረጋችሁት በምን ሥልጣን ወይም በማን ስም ነው?” ብለው ጠየቋቸው።  በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ+ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የሕዝቡ ገዢዎችና ሽማግሌዎች፣  ዛሬ በእኛ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ያለው ለአንድ ሽባ ሰው በተደረገ መልካም ሥራ+ የተነሳ ከሆነና ይህን ሰው ያዳነው ማን እንደሆነ ማወቅ የምትፈልጉ ከሆነ፣ 10  ይህ ሰው ጤናማ ሆኖ እዚህ ፊታችሁ የቆመው፣ እናንተ በእንጨት ላይ በሰቀላችሁት+ ሆኖም አምላክ ከሞት ባስነሳው+ በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣+ ይኸውም በኢየሱስ አማካኝነት እንደሆነ እናንተም ሆናችሁ መላው የእስራኤል ሕዝብ ይወቅ። 11  ‘እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማዕዘን ራስ የሆነው ድንጋይ’ እሱ ነው።+ 12  ደግሞም መዳን በሌላ በማንም አይገኝም፤ ምክንያቱም ልንድንበት የምንችል ከሰማይ በታች ለሰዎች የተሰጠ ሌላ ስም የለም።”+ 13  ሰዎቹ ጴጥሮስና ዮሐንስ በድፍረት ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ ያልተማሩና* ተራ ሰዎች+ መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ። ከኢየሱስ ጋር እንደነበሩም ተገነዘቡ።+ 14  የተፈወሰውንም ሰው ከእነሱ ጋር ቆሞ ሲያዩት+ ምንም መልስ መስጠት አልቻሉም።+ 15  ስለዚህ ከሳንሄድሪን ሸንጎ አዳራሽ እንዲወጡ አዘዟቸው፤ ከዚያም እርስ በርሳቸው ይማከሩ ጀመር፤ 16  እንዲህም ተባባሉ፦ “እነዚህን ሰዎች ምን ብናደርጋቸው ይሻላል?+ ምክንያቱም በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ዘንድ የታወቀ አስደናቂ ነገር እንደፈጸሙ የማይታበል ሐቅ ነው፤+ ይህን ደግሞ ልንክድ አንችልም። 17  ይሁንና ይህ ነገር በሕዝቡ መካከል ይበልጥ እንዳይስፋፋ ከዚህ በኋላ በዚህ ስም ለማንም ሰው እንዳይናገሩ በማሳሰብ እናስፈራራቸው።”+ 18  ከዚያም ጠርተዋቸው በኢየሱስ ስም ፈጽሞ እንዳይናገሩ ወይም እንዳያስተምሩ አዘዟቸው። 19  ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው እንዲህ አሏቸው፦ “አምላክን ከመስማት ይልቅ እናንተን መስማት በአምላክ ፊት ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ። 20  እኛ ግን ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።”+ 21  በመሆኑም እንደገና ካስፈራሯቸው በኋላ ለቀቋቸው፤ ይህን ያደረጉት እነሱን ለመቅጣት የሚያስችል ምንም ተጨባጭ ነገር ስላላገኙና ሕዝቡን ስለፈሩ ነው፤+ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ በተፈጸመው ሁኔታ አምላክን እያከበረ ነበር። 22  በዚህ ተአምር* የተፈወሰውም ሰው ዕድሜው ከ40 ዓመት በላይ ነበር። 23  ከተለቀቁ በኋላ ወደ ወንድሞቻቸው ሄደው የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ ያሏቸውን ሁሉ ነገሯቸው። 24  እነሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ ሲሉ ወደ አምላክ ጸለዩ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ሆይ፣ ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠርክ አንተ ነህ፤+ 25  በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በአገልጋይህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለሃል፦+ ‘ብሔራት ለምን ታወኩ? ሕዝቦችስ ለምን ከንቱ ነገር ያውጠነጥናሉ? 26  የምድር ነገሥታት ተሰለፉ፤ ገዢዎችም በአንድነት ተሰብስበው በይሖዋና* እሱ በቀባው* ላይ ተነሱ።’+ 27  በእርግጥም ሄሮድስና ጳንጥዮስ ጲላጦስ+ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በዚህች ከተማ ተሰብስበው አንተ በቀባኸው+ በቅዱስ አገልጋይህ በኢየሱስ ላይ ተነሱ፤ 28  ይህም የሆነው እጅህና ፈቃድህ አስቀድመው የወሰኑት እንዲፈጸም ነው።+ 29  አሁንም ይሖዋ* ሆይ፣ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው፤ 30  ለመፈወስም የዘረጋኸውን እጅህን አትጠፍ፤ በቅዱስ አገልጋይህ በኢየሱስ ስም+ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ማድረግህንም ቀጥል።”+ 31  ምልጃ ካቀረቡም* በኋላ ተሰብስበውበት የነበረው ቦታ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው+ የአምላክን ቃል በድፍረት መናገር ጀመሩ።+ 32  በተጨማሪም ከፍተኛ ቁጥር የነበራቸው ያመኑት ሰዎች አንድ ልብና ነፍስ* ነበራቸው፤ አንዳቸውም ቢሆኑ ያላቸው ማንኛውም ንብረት የግላቸው እንደሆነ አድርገው አይቆጥሩም ነበር፤ ከዚህ ይልቅ ያላቸው ነገር ሁሉ የጋራ ነበር።+ 33  ደግሞም ሐዋርያቱ ስለ ጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ በታላቅ ኃይል መመሥከራቸውን ቀጠሉ፤+ ሁሉም የአምላክን ታላቅ ጸጋ አግኝተው ነበር። 34  ከመካከላቸውም አንድም ችግረኛ አልነበረም፤+ ምክንያቱም መሬት ወይም ቤት የነበራቸው ሁሉ እየሸጡ ገንዘቡን በማምጣት 35  ለሐዋርያት ያስረክቡ ነበር።+ ከዚያም ለእያንዳንዱ ሰው በሚያስፈልገው መጠን ይከፋፈል ነበር።+ 36  የቆጵሮስ ተወላጅ የሆነ ዮሴፍ የሚባል አንድ ሌዋዊ ነበር፤ ሐዋርያት በርናባስ+ ብለውም ይጠሩት የነበረ ሲሆን ትርጉሙም “የመጽናናት ልጅ” ማለት ነው፤ 37  እሱም መሬት ስለነበረው መሬቱን ሸጦ ገንዘቡን በማምጣት ለሐዋርያት አስረከበ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ረቢዎች ትምህርት ቤት ገብተው አለመማራቸውን ያመለክታል እንጂ መሃይም መሆናቸውን አያሳይም።
ወይም “ምልክት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “በእሱ ክርስቶስ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “አጥብቀው ከጸለዩም።”