ነህምያ 8:1-18

  • ሕጉ ለሕዝቡ ተነበበ፤ እንዲሁም ተብራራ (1-12)

  • የዳስ በዓል ተከበረ (13-18)

8  ሕዝቡም ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ከውኃ በር+ ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ተሰበሰቡ፤ ከዚያም የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ* የሆነው ዕዝራ+ ይሖዋ ለእስራኤል የሰጠውን ትእዛዝ+ የያዘውን የሙሴን ሕግ+ መጽሐፍ እንዲያመጣላቸው ጠየቁት።  በመሆኑም ካህኑ ዕዝራ በሰባተኛው ወር+ የመጀመሪያ ቀን ላይ ወንዶችን፣ ሴቶችንና የሚነገረውን ነገር ሰምተው ማስተዋል የሚችሉትን ሁሉ ወዳቀፈው ጉባኤ ሕጉን አመጣ።+  እሱም ከውኃ በር ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ በተሰበሰቡት ወንዶች፣ ሴቶችና ሰምተው ማስተዋል በሚችሉ ሁሉ ፊት ድምፁን ከፍ አድርጎ ከማለዳ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ሕጉን አነበበ፤+ ሕዝቡም የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ በትኩረት አዳመጡ።+  የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ* የሆነው ዕዝራ ለዝግጅቱ ተብሎ በተሠራው የእንጨት መድረክ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከጎኑም በስተ ቀኝ በኩል ማቲትያህ፣ ሼማ፣ አናያ፣ ኦርዮ፣ ኬልቅያስ እና ማአሴያህ ቆመው ነበር፤ በስተ ግራው ደግሞ ፐዳያህ፣ ሚሳኤል፣ ማልኪያህ፣+ ሃሹም፣ ሃሽባዳናህ፣ ዘካርያስ እና መሹላም ቆመው ነበር።  ዕዝራ ከሕዝቡ ሁሉ ከፍ ብሎ ቆሞ ስለነበር ሁሉም እያዩት በፊታቸው መጽሐፉን ከፈተ። መጽሐፉንም ሲከፍት ሕዝቡ ሁሉ ተነስቶ ቆመ።  ከዚያም ዕዝራ ታላቁንና እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን አመሰገነ፤ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ “አሜን!* አሜን!”+ በማለት መለሰ፤ ሁሉም እጃቸውን ወደ ላይ ዘረጉ፤ መሬት ላይ በግንባራቸው ተደፍተውም ለይሖዋ ሰገዱ።  ሌዋውያን የሆኑት የሹዋ፣ ባኒ፣ ሸረበያህ፣+ ያሚን፣ አቁብ፣ ሻበታይ፣ ሆዲያህ፣ ማአሴያህ፣ ቀሊጣ፣ አዛርያስ፣ ዮዛባድ፣+ ሃናን እና ፐላያህ ደግሞ ሕዝቡ እዚያው ቆሞ ሳለ ሕጉን ለሕዝቡ ያብራሩ ነበር።+  እነሱም ከመጽሐፉ ይኸውም ከእውነተኛው አምላክ ሕግ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማንበብ ሕጉን በግልጽ ያብራሩና ትርጉሙ ምን እንደሆነ ይናገሩ ነበር፤ በዚህ መንገድ የተነበበውን ነገር ማስተዋል እንዲችል ሕዝቡን ይረዱት ነበር።+  በወቅቱ ገዢ* የነበረው ነህምያ፣ የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ* የሆነው ካህኑ ዕዝራና+ ሕዝቡን ያስተምሩ የነበሩት ሌዋውያን ሕዝቡን ሁሉ “ይህ ቀን ለአምላካችሁ ለይሖዋ ቅዱስ ቀን ነው።+ አትዘኑ ወይም አታልቅሱ” አሉ። ይህን ያሉት ሕዝቡ ሁሉ የሕጉ ቃል ሲነበብ በሚሰማበት ጊዜ ያለቅስ ስለነበር ነው። 10  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሂዱ፤ ምርጥ የሆኑትን* ነገሮች ብሉ፤ ጣፋጩንም ጠጡ፤ ምንም የተዘጋጀ ነገር ለሌላቸውም ምግብ ላኩላቸው፤+ ይህ ቀን ለጌታችን ቅዱስ ነውና፤ የይሖዋ ደስታ ምሽጋችሁ* ስለሆነ አትዘኑ።” 11  ሌዋውያኑም “ይህ ቀን ቅዱስ ስለሆነ ዝም በሉ! አትዘኑ” በማለት ሕዝቡን ያረጋጉ ነበር። 12  በመሆኑም ሕዝቡ ሁሉ ሊበላ፣ ሊጠጣ፣ ምግቡን ለሌሎች ሊያካፍልና ሊደሰት ሄደ፤+ ምክንያቱም የተነገራቸውን ቃል ተረድተውት ነበር።+ 13  በሁለተኛውም ቀን የሕዝቡ ሁሉ የአባቶች ቤት መሪዎች፣ ካህናቱና ሌዋውያኑ የሕጉን ቃል ይበልጥ በጥልቀት ለማስተዋል የቅዱሳን መጻሕፍት ገልባጭ* በሆነው በዕዝራ ዙሪያ ተሰበሰቡ። 14  ከዚያም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ባዘዘው ሕግ ውስጥ እስራኤላውያን በሰባተኛው ወር በሚከበረው በዓል ወቅት ዳስ*+ ውስጥ መቀመጥ እንዳለባቸው የሚገልጽ ሐሳብ ተጽፎ አገኙ፤ 15  እንዲሁም “ወደ ተራራማው አካባቢ ውጡና በተጻፈው መሠረት ዳሶችን ለመሥራት ከወይራ ዛፍ፣ ከዘይት ዛፍ፣ ከአደስ ዛፍ፣ ከዘንባባና ከሌሎች ዛፎች ቅጠል ያላቸውን ቅርንጫፎች አምጡ” የሚል አዋጅ በከተሞቻቸው በሙሉና በመላው ኢየሩሳሌም ማወጅ እንዳለባቸው+ የሚገልጽ ሐሳብ ተጽፎ አገኙ። 16  ስለዚህ ሕዝቡ ወጥቶ እነዚህን ቅጠሎች በማምጣት እያንዳንዱ ሰው በቤቱ ጣሪያ ላይ እንዲሁም በግቢውና በእውነተኛው አምላክ ቤት ግቢ ውስጥ፣+ በውኃ በር+ አደባባይና በኤፍሬም በር+ አደባባይ ለራሱ ዳሶች ሠራ። 17  በዚህም መንገድ ከምርኮ የተመለሱትን ሰዎች ያቀፈው መላው ጉባኤ ዳሶችን ሠራ፤ በዳሶቹም ውስጥ ተቀመጠ፤ እስራኤላውያን ከነዌ ልጅ ከኢያሱ+ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ በዓሉን በዚህ መንገድ አክብረው አያውቁም ነበር፤ ስለሆነም ደስታቸው ታላቅ ሆነ።+ 18  የእውነተኛው አምላክ ሕግ+ መጽሐፍም ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ በየዕለቱ ይነበብ ነበር። እነሱም በዓሉን ለሰባት ቀን አከበሩ፤ በደንቡ መሠረትም በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ተደረገ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ጸሐፊ።”
ወይም “ጸሐፊ።”
ወይም “ይሁን!”
ወይም “ጸሐፊ።”
ወይም “ቲርሻታ።” ለአንድ የአውራጃ ገዢ የሚሰጥ የፋርሳውያን የማዕረግ ስም ነው።
ቃል በቃል “የሰቡትን።”
ወይም “ብርታታችሁ።”
ወይም “ጸሐፊ።”
ወይም “ጊዜያዊ መጠለያ።”