ምሳሌ 18:1-24

  • ራስን ማግለል ራስ ወዳድነትና ጥበብ የጎደለው ነው (1)

  • “የይሖዋ ስም ጽኑ ግንብ ነው” (10)

  • ሀብት ጥበቃ አያስገኝም (11)

  • ሁለቱንም ወገኖች መስማት ጥበብ ነው (17)

  • “ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ” (24)

18  ራሱን የሚያገል ሰው ሁሉ የራስ ወዳድነት ምኞቱን ያሳድዳል፤ጥበብንም* ሁሉ ይቃወማል።*  2  ሞኝ ሰው ማስተዋል አያስደስተውም፤ይልቁንም በልቡ ያለውን ሐሳብ ይገልጣል።+  3  ክፉ ሰው ሲመጣ ንቀትም ይመጣል፤ከውርደትም ጋር ኀፍረት ይመጣል።+  4  ከሰው አፍ የሚወጣ ቃል ጥልቅ ውኃ ነው።+ የጥበብ ምንጭ የሚንዶለዶል ጅረት ነው።  5  ለክፉ ሰው ማድላት፣ጻድቁንም ፍትሕ መንፈግ+ መልካም አይደለም።+  6  የሞኝ ሰው ንግግር ጠብ ያስነሳል፤+አፉም ዱላ ይጋብዛል።+  7  የሞኝ አንደበት መጥፊያው ነው፤+ከንፈሮቹም ለሕይወቱ* ወጥመድ ናቸው።  8  ስም አጥፊ የሚናገረው ቃል ጣፋጭ እንደሆነ ቁራሽ ምግብ ነው፤*+በፍጥነት ተውጦ በቀጥታ ወደ ሆድ ይገባል።+  9  በሥራው ታካች የሆነ ሰው ሁሉ፣የአጥፊ ወንድም ነው።+ 10  የይሖዋ ስም ጽኑ ግንብ ነው።+ ጻድቅ ወደዚያ በመሮጥ ጥበቃ ያገኛል።*+ 11  የባለጸጋ ሰው ሀብት የተመሸገ ከተማው ነው፤በሐሳቡም ጥበቃ እንደሚያስገኝ ግንብ አድርጎ ይመለከተዋል።+ 12  ሰው ለውድቀት ከመዳረጉ በፊት ልቡ ይታበያል፤+ትሕትና ግን ክብርን ትቀድማለች።+ 13  እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።+ 14  ጠንካራ መንፈስ ያለው ሰው ሕመሙን መቋቋም ይችላል፤+የተደቆሰን መንፈስ* ግን ማን ሊቋቋም ይችላል?+ 15  የአስተዋይ ሰው ልብ እውቀትን ያገኛል፤+የጥበበኛም ጆሮ እውቀትን ለማግኘት ይጥራል። 16  ስጦታ ለሰጪው መንገዱን ይከፍትለታል፤+በታላላቅ ሰዎችም ፊት መቅረብ ያስችለዋል። 17  ክሱን አስቀድሞ ያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤+ይህም ሌላው ወገን መጥቶ እስኪመረምረው ድረስ ነው።+ 18  ዕጣ መጣል ጭቅጭቅ እንዲያበቃ ያደርጋል፤+ኃይለኛ ባላንጣዎችንም ይገላግላል። 19  የተበደለ ወንድም ከተመሸገች ከተማ ይበልጥ የማይበገር ነው፤+እንደ ግንብ በሮች መቀርቀሪያም የጠነከረ ጠብ አለ።+ 20  ሰው በአፉ ፍሬ ሆዱ ይሞላል፤+ከንፈሩም በሚያስገኘው ምርት ይረካል። 21  አንደበት የሞትና የሕይወት ኃይል አላት፤+ሊጠቀምባት የሚወድ ፍሬዋን ይበላል።+ 22  ጥሩ ሚስት ያገኘ ጥሩ ነገር አግኝቷል፤+የይሖዋንም ሞገስ* ያገኛል።+ 23  ድሃ እየተለማመጠ ይናገራል፤ሀብታም ግን በኃይለ ቃል ይመልሳል። 24  እርስ በርስ ከመጠፋፋት ወደኋላ የማይሉ ጓደኛሞች አሉ፤+ነገር ግን ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ አለ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

^ ወይም “ማስተዋል የታከለበትንም ጥበብ።”
^ ወይም “ይንቃል።”
^ ወይም “ለነፍሱ።”
^ ወይም “ተስገብግበው እንደሚውጡት ነገር ነው።”
^ ቃል በቃል “ከፍ ይላል።” ግለሰቡ እንደማይደረስበትና ከአደጋ እንደሚጠበቅ ያመለክታል።
^ ወይም “ከባድ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን።”
^ ወይም “በጎ ፈቃድ።”