ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 12:1-21

  • ሰውነታችሁን ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ (1, 2)

  • የተለያዩ ስጦታዎች ያሉት አንድ አካል (3-8)

  • የክርስትና አኗኗርን በተመለከተ የተሰጠ ምክር (9-21)

12  እንግዲህ ወንድሞች፣ ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና+ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ እንድታቀርቡ+ በአምላክ ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።+  በተጨማሪም ይህ ሥርዓት* እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ+ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።+  እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤+ ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእያንዳንዱ በሰጠው* እምነት መሠረት ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው በተሰጠኝ ጸጋ እመክራለሁ።+  በአንድ አካል ላይ ብዙ የአካል ክፍሎች አሉን፤+ ደግሞም ሁሉም የአካል ክፍሎች አንድ ዓይነት ተግባር አያከናውኑም፤  ልክ እንደዚሁ እኛም ብዙ ብንሆንም እንኳ ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት አንድ አካል ነን፤ ደግሞም አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል ነን።+  በመሆኑም በተሰጠን ጸጋ መሠረት+ የተለያዩ ስጦታዎች ስላሉን ስጦታችን ትንቢት መናገር ከሆነ በተሰጠን እምነት መሠረት ትንቢት እንናገር፤  ማገልገል ከሆነ ማገልገላችንን እንቀጥል፤ የሚያስተምርም ቢሆን ማስተማሩን ይቀጥል፤+  የሚያበረታታም* ቢሆን ማበረታቻ መስጠቱን ይቀጥል፤+ የሚሰጥ* በልግስና ይስጥ፤+ የሚያስተዳድር* በትጋት ያስተዳድር፤+ የሚምር በደስታ ይማር።+  ፍቅራችሁ ግብዝነት የሌለበት ይሁን።+ ክፉ የሆነውን ተጸየፉ፤+ ጥሩ የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ። 10  በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።*+ 11  ታታሪዎች* ሁኑ እንጂ አትስነፉ።*+ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ።+ ይሖዋን* እንደ ባሪያ አገልግሉ።+ 12  በተስፋው ደስ ይበላችሁ። መከራን በጽናት ተቋቋሙ።+ ሳትታክቱ ጸልዩ።+ 13  ለቅዱሳን እንደየችግራቸው ያላችሁን አካፍሉ።+ የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል አዳብሩ።+ 14  ስደት የሚያደርሱባችሁን መርቁ፤+ መርቁ እንጂ አትርገሙ።+ 15  ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ። 16  ለራሳችሁ ያላችሁ ዓይነት አመለካከት ለሌሎችም ይኑራችሁ፤ የትዕቢት ዝንባሌ እንዳያድርባችሁ ተጠንቀቁ፤ ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ ይኑራችሁ።+ ጥበበኞች እንደሆናችሁ አድርጋችሁ አታስቡ።+ 17  ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ።+ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ጥረት አድርጉ። 18  ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።+ 19  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ “‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ”*+ ተብሎ ስለተጻፈ ለቁጣው* ዕድል ስጡ።+ 20  ነገር ግን “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ።”*+ 21  በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ይህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “በመደበው፤ ባከፋፈለው።”
ወይም “የሚመክርም።”
ወይም “የሚያዋጣ።”
ወይም “አመራር የሚሰጥ።”
ወይም “ተነሳሽነት ይኑራችሁ።”
ወይም “ትጉዎች፤ ቀናተኞች።”
ወይም “በሥራችሁ አትለግሙ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
የአምላክን ቁጣ ያመለክታል።
የሰውየው ልብ እንዲለሰልስና ቁጣው እንዲበርድ ማድረግን ያመለክታል።