ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 14:1-23

  • አንዳችሁ በሌላው ላይ አትፍረዱ (1-12)

  • ሌሎችን አታሰናክሉ (13-18)

  • ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ጥረት አድርጉ (19-23)

14  በእምነቱ ጠንካራ ያልሆነውን ሰው ተቀበሉት+ እንጂ በአመለካከት ልዩነት* ላይ ተመሥርታችሁ አትፍረዱ።  አንድ ሰው እምነቱ ማንኛውንም ነገር እንዲበላ ይፈቅድለታል፤ በእምነቱ ጠንካራ ያልሆነ ሰው ግን አትክልት ብቻ ይበላል።  ማንኛውንም ነገር የሚበላ የማይበላውን አይናቅ፤ የማይበላው ደግሞ በሚበላው ላይ አይፍረድ፤+ ይህን ሰው አምላክ ተቀብሎታልና።  በሌላው አገልጋይ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?+ እሱ ቢቆምም ሆነ ቢወድቅ ለጌታው ነው።+ እንዲያውም ይሖዋ* እንዲቆም ሊያደርገው ስለሚችል ይቆማል።  አንድ ሰው አንዱ ቀን ከሌላው ቀን የበለጠ እንደሆነ አድርጎ ያስባል፤+ ሌላው ደግሞ አንዱ ቀን ከሌሎቹ ቀናት ሁሉ የተለየ እንዳልሆነ ያስባል፤+ እያንዳንዱ ሰው ሙሉ በሙሉ ያመነበትን ውሳኔ ያድርግ።  አንድን ቀን የሚያከብር ለይሖዋ* ብሎ ያከብራል። ማንኛውንም ነገር የሚበላም አምላክን ስለሚያመሰግን ለይሖዋ* ብሎ ይበላል፤+ የማይበላም ለይሖዋ* ብሎ አይበላም፤ ይሁንና አምላክን ያመሰግናል።+  እንዲያውም ከመካከላችን ለራሱ ብቻ ብሎ የሚኖር የለም፤+ ለራሱ ብቻ ብሎም የሚሞት የለም።  ብንኖር የምንኖረው ለይሖዋ* ነውና፤+ ብንሞትም የምንሞተው ለይሖዋ* ነው። ስለዚህ ብንኖርም ሆነ ብንሞት የይሖዋ* ነን።+  ክርስቶስ የሞተውና ዳግም ሕያው የሆነው ለዚህ ዓላማ ይኸውም በሙታንም ሆነ በሕያዋን ላይ ጌታ ይሆን ዘንድ ነውና።+ 10  ታዲያ አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ?+ አንተ ደግሞ ወንድምህን ለምን ትንቃለህ? ሁላችንም በአምላክ የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና።+ 11  “‘በሕያውነቴ እምላለሁ’+ ይላል ይሖዋ፣* ‘ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ምላስም ሁሉ እኔ አምላክ መሆኔን በይፋ ይመሠክራል’” ተብሎ ተጽፏልና።+ 12  ስለዚህ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።+ 13  ስለሆነም ከእንግዲህ አንዳችን በሌላው ላይ አንፍረድ፤+ ከዚህ ይልቅ በአንድ ወንድም ፊት የሚያደናቅፍ ወይም የሚያሰናክል ነገር ላለማስቀመጥ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።+ 14  የጌታ ኢየሱስ ተከታይ እንደመሆኔ መጠን ማንኛውም ነገር በራሱ ርኩስ እንዳልሆነ አውቄአለሁ ደግሞም አምኛለሁ፤+ አንድ ነገር ለአንድ ሰው ርኩስ የሚሆነው ያ ነገር ርኩስ ነው ብሎ ሲያስብ ብቻ ነው። 15  አንተ በምግብ የተነሳ ወንድምህ ቅር እንዲሰኝ ካደረግክ በፍቅር መመላለስህን ትተሃል ማለት ነው።+ ስለዚህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ሰው በምትበላው ምግብ ምክንያት እንዲጠፋ አታድርግ።*+ 16  በመሆኑም መልካም ነው ብላችሁ የምታደርጉት ነገር በሌሎች ዘንድ በመጥፎ እንዳይነሳ ተጠንቀቁ። 17  የአምላክ መንግሥት በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ጽድቅ፣ ሰላምና ደስታ ነው እንጂ የመብልና የመጠጥ ጉዳይ አይደለም።+ 18  በዚህ መንገድ ክርስቶስን እንደ ባሪያ የሚያገለግል ሁሉ በአምላክ ፊት ተቀባይነት፣ በሰዎችም ዘንድ ሞገስ ያገኛልና። 19  ስለዚህ ሰላም የሚገኝበትንና+ እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን+ ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ። 20  ለምግብ ብለህ የአምላክን ሥራ ማፍረስ ተው።+ እርግጥ ነው፣ ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤ ሆኖም አንድ ሰው መብላቱ ሌሎችን የሚያደናቅፍ ከሆነ ጎጂ* ነው።+ 21  ወንድምህ የሚሰናከልበት ከሆነ ሥጋ አለመብላት፣ የወይን ጠጅ አለመጠጣት ወይም ማንኛውንም የሚያሰናክል ነገር አለማድረግ የተሻለ ነው።+ 22  እንግዲህ እምነትህ በአንተና በአምላክ መካከል ያለ ጉዳይ ይሁን። ትክክል ነው ብሎ ያመነበትን ነገር ካደረገ በኋላ መልሶ ራሱን የማይኮንን ሰው ደስተኛ ነው። 23  እየተጠራጠረ ከበላ ግን የበላው በእምነት ስላልሆነ ቀድሞውንም ተኮንኗል። ደግሞም በእምነት ያልተደረገ ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“በውስጥ በሚጉላሉ ጥያቄዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
እምነቱ ወይም የዘላለም ሕይወት ተስፋው እንዲጠፋ አለማድረግን ያመለክታል።
ወይም “ስህተት።”