ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 2:1-29

  • አምላክ በአይሁዳውያንና በግሪካውያን ላይ ይፈርዳል (1-16)

    • ሕሊና የሚሠራበት መንገድ (14, 15)

  • አይሁዳውያንና ሕጉ (17-24)

  • የልብ ግርዘት (25-29)

2  ስለዚህ አንተ ሰው፣ ማንም ሆንክ ማን+ በሌላው ላይ የምትፈርድ ከሆነ ምንም የምታመካኝበት ነገር የለህም፤ በሌላው ላይ ስትፈርድ ራስህንም ኮነንክ ማለት ነው፤ ምክንያቱም በሌላው ላይ የምትፈርድ አንተ ራስህ እነዚያኑ ነገሮች በተደጋጋሚ ታደርጋለህ።+  አምላክ እንዲህ ያሉትን ነገሮች በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ እንደሚፈርድ እናውቃለን፤ ፍርዱ ደግሞ ከእውነት ጋር የሚስማማ ነው።  ይሁን እንጂ አንተ ሰው፣ እንዲህ ያሉትን ነገሮች በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ እየፈረድክ አንተ ግን እነዚያኑ ነገሮች የምታደርግ ከሆነ ከአምላክ ፍርድ አመልጣለሁ ብለህ ታስባለህ?  ወይስ አምላክ በደግነቱ ወደ ንስሐ ሊመራህ+ እየሞከረ እንዳለ ሳታውቅ የደግነቱን፣+ የቻይነቱንና+ የትዕግሥቱን+ ብዛት ትንቃለህ?  እንግዲህ በግትርነትህና ንስሐ በማይገባው ልብህ የተነሳ በራስህ ላይ ቁጣ ታከማቻለህ። ይህ ቁጣ አምላክ የጽድቅ ፍርድ በሚፈርድበት ቀን ይገለጣል።+  እሱም ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይከፍለዋል፦+  በመልካም ሥራ በመጽናት ክብርን፣ ሞገስንና ሊጠፋ የማይችል ሕይወትን+ ለሚፈልጉ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል፤  ይሁን እንጂ ጠብ ወዳዶች በሆኑትና ለእውነት ከመታዘዝ ይልቅ ለዓመፅ በሚታዘዙት ላይ ቁጣና መዓት ይወርድባቸዋል።+  ክፉ ሥራ በሚሠራ ሰው ሁሉ* ላይ ይኸውም በመጀመሪያ በአይሁዳዊ ከዚያም በግሪካዊ ላይ መከራና ጭንቀት ይመጣል፤ 10  ሆኖም መልካም ሥራ የሚሠራ ሁሉ ይኸውም በመጀመሪያ አይሁዳዊ+ ከዚያም ግሪካዊ+ ክብር፣ ሞገስና ሰላም ያገኛል። 11  በአምላክ ዘንድ አድልዎ የለምና።+ 12  ሕግ ሳይኖራቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ ያለሕግ ይጠፋሉና፤+ ሆኖም ሕግ እያላቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል።+ 13  ምክንያቱም በአምላክ ፊት ጻድቅ የሆኑት ሕግን የሚሰሙ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ጻድቃን ናችሁ የሚባሉት ሕግን የሚፈጽሙ ናቸው።+ 14  ሕግ የሌላቸው+ አሕዛብ በተፈጥሮ በሕጉ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሲያደርጉ እነዚህ ሰዎች ሕግ ባይኖራቸውም እንኳ እነሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና። 15  የሕጉ መሠረታዊ ሐሳብ በልባቸው እንደተጻፈ የሚያሳዩት እነሱ ራሳቸው ናቸው፤ ሕሊናቸው ከእነሱ ጋር ሆኖ በሚመሠክርበት ጊዜ ሐሳባቸው በውስጣቸው* እየተሟገተ አንዴ ይከሳቸዋል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥፋተኛ አይደላችሁም ይላቸዋል። 16  ይህ የሚሆነው እኔ በማውጀው ምሥራች መሠረት አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ሰዎች በስውር በሚያስቧቸውና በሚያደርጓቸው ነገሮች ላይ በሚፈርድበት+ ቀን ነው። 17  አንተ አይሁዳዊ ተብለህ የምትጠራ፣+ በሕጉ የምትመካ፣ ከአምላክ ጋር ባለህ ዝምድና የምትኩራራ፣ 18  ፈቃዱን የምታውቅ፣ በሕጉ ውስጥ ያለውን ነገር የተማርክ*+ በመሆንህ የላቀ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች በሚገባ የምትገነዘብ፣ 19  ለዕውር መሪ፣ በጨለማ ላሉት ብርሃን ነኝ ብለህ የምታምን፣ 20  ማስተዋል የጎደላቸውን የማሠለጥንና ሕፃናትን የማስተምር ነኝ የምትል እንዲሁም በሕጉ ውስጥ ያሉትን የእውቀትና የእውነት መሠረታዊ ገጽታዎች የምታውቅ ከሆንክ፣ 21  ታዲያ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርም?+ አንተ “አትስረቅ”+ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህ? 22  አንተ “አታመንዝር”+ የምትል ታመነዝራለህ? አንተ ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህ? 23  አንተ በሕግ የምትኩራራ ሕጉን በመተላለፍ አምላክን ታዋርዳለህ? 24  ይህም “በእናንተ ምክንያት የአምላክ ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+ 25  መገረዝ+ ጥቅም የሚኖረው ሕጉን እስካከበርክ ድረስ ነው፤+ ሕጉን የምትተላለፍ ከሆነ ግን መገረዝህ እንደ አለመገረዝ ይቆጠራል። 26  ያልተገረዘ ሰው+ በሕጉ ውስጥ ያሉትን የጽድቅ መሥፈርቶች የሚጠብቅ ከሆነ አለመገረዙ እንደ መገረዝ አይቆጠርም?+ 27  እንግዲህ አንተ የተጻፈ ሕግ ያለህና የተገረዝክ ሆነህ ሳለ ሕግን የምትጥስ ከሆነ በሥጋ ያልተገረዘ ሆኖ ሕግን የሚፈጽም ሰው ይፈርድብሃል። 28  ምክንያቱም እውነተኛ አይሁዳዊነት በውጫዊ ገጽታ የሚገለጽ አይደለም፤+ ግርዘቱም ውጫዊና ሥጋዊ ግርዘት አይደለም።+ 29  ከዚህ ይልቅ በውስጡ አይሁዳዊ የሆነ እሱ አይሁዳዊ ነው፤+ ግርዘቱም በተጻፈ ሕግ ሳይሆን በመንፈስ+ የሆነ የልብ ግርዘት ነው።+ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ውዳሴ የሚያገኘው ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ሰው ነፍስ ሁሉ።”
ቃል በቃል “እርስ በርሱ።”
ወይም “በቃል የተማርክ።”