ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 16:1-27

  • ጳውሎስ ፌበንን አስተዋወቀ (1, 2)

  • ለሮም ክርስቲያኖች የቀረበ ሰላምታ (3-16)

  • ክፍፍል ከሚፈጥሩ ነገሮች መራቅ (17-20)

  • የጳውሎስ የሥራ አጋሮች ያቀረቡት ሰላምታ (21-24)

  • ተሰውሮ የቆየው ቅዱስ ሚስጥር ተገልጧል (25-27)

16  በክንክራኦስ+ ጉባኤ የምታገለግለውን እህታችንን ፌበንን ላስተዋውቃችሁ እወዳለሁ፤  በጌታ የእምነት ባልደረባችሁ እንደመሆኗ መጠን ለቅዱሳን በሚገባ ሁኔታ* ተቀበሏት፤ የምትፈልገውንም እርዳታ ሁሉ አድርጉላት፤+ ምክንያቱም እሷ እኔን ጨምሮ ለብዙ ወንድሞች ድጋፍ ሆናለች።  በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩት ለጵርስቅላና ለአቂላ+ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤  እነሱ ለእኔ* ሲሉ ሕይወታቸውን* ለአደጋ አጋልጠዋል፤+ እኔ ብቻ ሳልሆን በአሕዛብ መካከል የሚገኙ ጉባኤዎችም ሁሉ ያመሰግኗቸዋል።  በቤታቸው ላለው ጉባኤም ሰላምታ አቅርቡልኝ።+ በእስያ ከመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ተከታዮች አንዱ የሆነውን የምወደውን ኤጲኔጦስን ሰላም በሉልኝ።  ለእናንተ ብዙ የደከመችውን ማርያምን ሰላም በሉልኝ።  ዘመዶቼ+ የሆኑትንና አብረውኝ የታሰሩትን እንዲሁም በሐዋርያት ዘንድ ስመጥር የሆኑትንና ከእኔ ቀደም ብለው የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑትን አንድሮኒኮስንና ዩኒያስን ሰላም በሉልኝ።  በጌታ ለምወደው ለአምጵልያጦስ ሰላምታዬን አቅርቡልኝ።  በክርስቶስ አብሮን የሚሠራውን ኡርባኖስንና የምወደውን እስጣኩስን ሰላም በሉልኝ። 10  በክርስቶስ ዘንድ መልካም ስም ያተረፈውን አጵሌስን ሰላም በሉልኝ። የአርስጦቡሉስ ቤተሰብ ለሆኑት ሰላምታ አቅርቡልኝ። 11  ዘመዴን ሄሮድዮንን ሰላም በሉልኝ። የጌታ ተከታዮች የሆኑትን የናርኪሰስን ቤተሰቦች ሰላም በሉልኝ። 12  በጌታ ሆነው በትጋት የሚሠሩትን ጥራይፊናና ጥራይፎሳ የተባሉትን ሴቶች ሰላም በሉልኝ። የምንወዳትን ጰርሲስን ሰላም በሉልኝ፤ በጌታ ሥራ ብዙ ደክማለችና። 13  የጌታ ምርጥ አገልጋይ ለሆነው ለሩፎስ እንዲሁም እኔም እንደ እናቴ ለማያት ለእናቱ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 14  አሲንክሪጦስን፣ ፍሌጎንን፣ ሄርሜስን፣ ጳጥሮባን፣ ሄርማስንና ከእነሱ ጋር ያሉትን ወንድሞች ሰላም በሉልኝ። 15  ፊሎሎጎስንና ዩልያን፣ ኔርዩስንና እህቱን፣ ኦሊምጳስን እንዲሁም ከእነሱ ጋር ያሉትን ቅዱሳን ሁሉ ሰላም በሉልኝ። 16  በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ። የክርስቶስ ጉባኤዎች በሙሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 17  እንግዲህ ወንድሞች፣ ክፍፍል ከሚፈጥሩና ለእንቅፋት ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን ከሚያመጡ ሰዎች እንድትጠነቀቁ አሳስባችኋለሁ፤ እነዚህ ነገሮች የተማራችሁትን ትምህርት የሚጻረሩ ናቸው፤ ይህን ከሚያደርጉ ሰዎች ራቁ።+ 18  እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ለጌታችን ለክርስቶስ ሳይሆን ለራሳቸው ፍላጎት* ባሪያዎች ናቸው፤ በለሰለሰ አንደበትና በሽንገላ ቃላት የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ። 19  ታዛዥነታችሁ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ሆኗል፤ ስለዚህ እኔ በእናንተ እጅግ እደሰታለሁ። ይሁንና ለመልካም ነገር ጥበበኞች እንድትሆኑ፣ ለክፉ ነገር ደግሞ አላዋቂዎች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ።+ 20  ሰላም የሚሰጠው አምላክ በቅርቡ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ይጨፈልቀዋል።+ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። 21  የሥራ አጋሬ ጢሞቴዎስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ ዘመዶቼ+ የሆኑት ሉክዮስ፣ ያሶንና ሶሲጳጥሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 22  ይህን ደብዳቤ በጽሑፍ ያሰፈርኩት እኔ ጤርጥዮስም በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ። 23  እኔንም ሆነ መላውን ጉባኤ የሚያስተናግደው ጋይዮስ+ ሰላም ይላችኋል። የከተማዋ የግምጃ ቤት ሹም* ኤርስጦስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ ወንድሙ ቁአስጥሮስም ሰላም ይላችኋል። 24  *—— 25  አምላክ ለረጅም ዘመናት ተሰውሮ ከቆየው ቅዱስ ሚስጥር+ መገለጥ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እኔ በማውጀው ምሥራችና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚሰበከው መልእክት መሠረት ሊያጸናችሁ ይችላል። 26  አሁን ግን ሕዝቦች ሁሉ እምነት እንዲኖራቸውና እሱን እንዲታዘዙ ቅዱሱ ሚስጥር፣ በዘላለማዊው አምላክ ትእዛዝ መሠረት ትንቢታዊ በሆኑ ቅዱሳን መጻሕፍት አማካኝነት በሕዝቦች ሁሉ መካከል እንዲገለጥና እንዲታወቅ ተደርጓል፤ 27  እሱ ብቻ ጥበበኛ+ ለሆነው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ቅዱሳን ሌሎችን በሚቀበሉበት መንገድ።”
ወይም “ለነፍሴ።”
ቃል በቃል “አንገታቸውን።”
ወይም “ለገዛ ሆዳቸው።”
ወይም “መጋቢ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።