ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 9:1-33

  • ጳውሎስ ለሥጋዊ እስራኤላውያን አዘነላቸው (1-5)

  • የአብርሃም እውነተኛ ዘር (6-13)

  • የአምላክን ምርጫ በተመለከተ ጥያቄ ማንሳት አንችልም (14-26)

    • የቁጣና የምሕረት ዕቃዎች (22, 23)

  • “የሚድኑት ቀሪዎች ብቻ ናቸው” (27-29)

  • እስራኤል ተሰናከለ (30-33)

9  የክርስቶስ ተከታይ እንደመሆኔ መጠን የምናገረው እውነት ነው፤ ሕሊናዬ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚመሠክር አልዋሽም፤ 2  ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ሥቃይ በልቤ ውስጥ አለ። 3  የሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑት ስለ ወንድሞቼ ስል እኔ ራሴ የተረገምኩ ሆኜ ከክርስቶስ ብለይ በወደድኩ ነበርና። 4  እነሱ እስራኤላውያን ናቸው፤ አምላክ ልጆቹ አድርጎ የወሰዳቸው፣+ ክብር ያገኙት፣ ቃል ኪዳን የተገባላቸው፣+ ሕግ የተሰጣቸው፣+ ቅዱስ አገልግሎት የማቅረብ መብት ያገኙትና+ ተስፋ የተሰጣቸው+ እነሱ ናቸው። 5  አባቶችም የእነሱ ናቸው፤+ ክርስቶስም በሥጋ የተገኘው ከእነሱ ነው።+ የሁሉ የበላይ የሆነው አምላክ ለዘላለም ይወደስ። አሜን። 6  ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ከንቱ ሆኖ ቀርቷል ማለት አይደለም። ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ በእርግጥ “እስራኤል” አይደለምና።+ 7  በተጨማሪም የአብርሃም ዘር ስለሆኑ+ ሁሉም ልጆቹ ናቸው ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ “ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ይሆናል” ተብሎ ተጽፏል።+ 8  ይህም ሲባል በሥጋ ልጆች የሆኑ በእርግጥ የአምላክ ልጆች አይደሉም፤+ በተስፋው ልጆች+ የሆኑት ግን ዘሩ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ። 9  የተስፋው ቃል “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ እመጣለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” ይላልና።+ 10  ተስፋው የተሰጠው በዚያን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ርብቃ ከአባታችን ከይስሐቅ መንታ ልጆች በፀነሰች ጊዜ ጭምር ነው፤+ 11  ምርጫውን በተመለከተ የአምላክ ዓላማ በሥራ ሳይሆን በጠሪው ላይ የተመካ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ ልጆቹ ከመወለዳቸውና ጥሩም ሆነ ክፉ ከማድረጋቸው በፊት 12  ርብቃ “ታላቁ የታናሹ ባሪያ ይሆናል” ተብሎ ተነግሯት ነበር።+ 13  ይህም “ያዕቆብን ወደድኩ፤ ኤሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+ 14  እንግዲህ ምን እንበል? አምላክ ፍትሕ ያዛባል ማለት ነው? በፍጹም!+ 15  ሙሴን “ልምረው የምፈልገውን እምረዋለሁ፤ ልራራለት የምፈልገውን ደግሞ እራራለታለሁ” ብሎታልና።+ 16  ስለዚህ ይህ የተመካው በአንድ ሰው ፍላጎት ወይም ጥረት* ሳይሆን ምሕረት በሚያደርገው አምላክ ላይ ነው።+ 17  ቅዱስ መጽሐፉ ስለ ፈርዖን ሲናገር “በሕይወት ያቆየሁህ ኃይሌን በአንተ ለማሳየትና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ለማድረግ ነው” ይላል።+ 18  ስለዚህ አምላክ የፈለገውን ይምራል፤ የፈለገውን ደግሞ ግትር እንዲሆን ይፈቅዳል።+ 19  በመሆኑም “እንደዚህ ከሆነ ታዲያ ሰዎችን ለምን ይወቅሳል?* ደግሞስ ፈቃዱን ማን መቃወም ይችላል?” ትለኝ ይሆናል። 20  ለመሆኑ ለአምላክ የምትመልሰው አንተ ማን ነህ?+ አንድ ዕቃ ቅርጽ አውጥቶ የሠራውን ሰው “ለምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ?” ይለዋል?+ 21  ሸክላ ሠሪው ከዚያው ከአንዱ ጭቃ፣ አንዱን ዕቃ ክቡር ለሆነ አገልግሎት ሌላውን ዕቃ ደግሞ ክብር ለሌለው አገልግሎት ለመሥራት በጭቃው ላይ ሥልጣን እንዳለው+ አታውቅም? 22  አምላክ ቁጣውን ለማሳየትና ኃይሉ እንዲታወቅ ለማድረግ ቢፈልግም እንኳ ጥፋት የሚገባቸውን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ችሏቸው እንደሆነስ ምን ታውቃለህ? 23  ይህን ያደረገው ታላቅ ክብሩን አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው የምሕረት ዕቃዎች+ ላይ ለመግለጥ 24  ይኸውም ከአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብም+ በጠራን በእኛ ላይ ታላቅ ክብሩን ለመግለጥ ቢሆንስ? 25  ይህም በሆሴዕ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብሎ እንደተናገረው ነው፦ “ሕዝቤ ያልሆኑትን+ ‘ሕዝቤ’ ብዬ፣ ያልተወደደችውንም ‘የተወደደች’+ ብዬ እጠራለሁ፤ 26  ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ ተብሎ በተነገራቸው ስፍራም በዚያ ‘የሕያው አምላክ ልጆች’ ተብለው ይጠራሉ።”+ 27  ከዚህም በተጨማሪ ኢሳይያስ ስለ እስራኤል እንዲህ ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል፦ “የእስራኤል ልጆች ቁጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም እንኳ የሚድኑት ቀሪዎች ብቻ ናቸው።+ 28  ይሖዋ* በምድር የሚኖሩትን ይፋረዳልና፤ ይህን ደግሞ ሳይዘገይ* ይፈጽመዋል።”+ 29  ደግሞም ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ* ዘር ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆን፣ ገሞራንም በመሰልን ነበር።”+ 30  እንግዲህ ምን እንበል? አሕዛብ ጽድቅን ባይከታተሉም እንኳ ጽድቅን ይኸውም በእምነት አማካኝነት የሚገኘውን ጽድቅ አገኙ፤+ 31  ሆኖም እስራኤል የጽድቅን ሕግ ቢከታተልም ግቡ ላይ አልደረሰም፤ ይኸውም ሕጉን አልፈጸመም። 32  ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በእምነት ሳይሆን በሥራ የሚገኝ እንደሆነ አድርገው ስለተከታተሉት ነው። ስለዚህ “በማሰናከያ ድንጋይ” ተሰናከሉ፤+ 33  ይህም “እነሆ፣ በጽዮን የሚያደናቅፍ ድንጋይና የሚያሰናክል ዓለት አኖራለሁ፤+ በእሱ ላይ እምነት የሚጥል ግን አያፍርም”+ ተብሎ እንደተጻፈው ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በተመኘ ወይም በሮጠ።”
ወይም “በሰዎች ላይ ለምን ስህተት ይፈላልጋል?”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “በፍጥነት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።