የማቴዎስ ወንጌል 5:1-48
5 ሕዝቡንም ባየ ጊዜ ወደ ተራራ ወጣ፤ በዚያ ከተቀመጠ በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ መጡ።
2 ከዚያም ኢየሱስ መናገር ጀመረ፤ እንዲህም ሲል አስተማራቸው፦
3 “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ* ደስተኞች ናቸው፤+ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።
4 “የሚያዝኑ ደስተኞች ናቸው፤ መጽናኛ ያገኛሉና።+
5 “ገሮች*+ ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።+
6 “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው፤+ ይጠግባሉና።*+
7 “መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው፤+ ምሕረት ይደረግላቸዋልና።
8 “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤+ አምላክን ያያሉና።
9 “ሰላም ፈጣሪዎች* ደስተኞች ናቸው፤+ የአምላክ ልጆች ይባላሉና።
10 “ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው፤+ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።
11 “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣+ ስደት ሲያደርሱባችሁና+ ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ።+
12 በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ+ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤+ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና።+
13 “እናንተ የምድር ጨው+ ናችሁ፤ ሆኖም ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን እንዴት መልሶ ሊያገኝ ይችላል? ከዚህ በኋላ ወደ ውጭ ተጥሎ+ በሰው ከመረገጥ በቀር ለምንም ነገር አያገለግልም።
14 “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ።+ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አትችልም።
15 ሰዎች መብራት አብርተው እንቅብ* አይደፉበትም፤ ከዚህ ይልቅ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል፤ በቤት ውስጥ ላሉትም ሁሉ ያበራል።+
16 በተመሳሳይም ሰዎች መልካም ሥራችሁን+ አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ+ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።+
17 “ሕጉን ወይም የነቢያትን ቃል ልሽር እንደመጣሁ አድርጋችሁ አታስቡ። ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም።+
18 እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይና ምድር ቢያልፉ እንኳ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እስኪከናወኑ ድረስ ከሕጉ አነስተኛዋ ፊደል ወይም የአንዷ ፊደል ጭረት ሳትፈጸም አትቀርም።+
19 በመሆኑም አነስተኛ ከሆኑት ከእነዚህ ትእዛዛት አንዷን የሚጥስና ሌሎች ሰዎችም እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ታናሽ* ይባላል። እነዚህን ትእዛዛት የሚያከብርና የሚያስተምር ሰው ግን በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ* ይባላል።
20 ጽድቃችሁ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ+ በምንም ዓይነት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማትገቡ+ ልነግራችሁ እወዳለሁ።
21 “በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘አትግደል፤+ ሰው የገደለ ሁሉ ግን በፍርድ ቤት ይጠየቃል’+ እንደተባለ ሰምታችኋል።
22 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በወንድሙ ላይ ተቆጥቶ ቁጣው የማይበርድለት+ ሁሉ በፍርድ ቤት ይጠየቃል፤ ወንድሙንም ጸያፍ በሆነ ቃል የሚያጥላላ ሁሉ በከፍተኛ ፍርድ ቤት* ይጠየቃል፤ ‘አንተ የማትረባ ጅል’ የሚለው ደግሞ ለእሳታማ ገሃነም* ሊዳረግ ይችላል።+
23 “እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ+ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ
24 መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።+
25 “ክስ ከመሠረተብህ ባላጋራ ጋር ወደ ፍርድ ቤት እየሄዳችሁ ሳለ ፈጥነህ ታረቅ፤ አለዚያ ባላጋራህ ለዳኛው፣ ዳኛው ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ዘብ አሳልፎ ይሰጥህና እስር ቤት ልትገባ ትችላለህ።+
26 እውነት እልሃለሁ፣ የመጨረሻዋን ሳንቲምህን* ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ፈጽሞ ከዚያ አትወጣም።
27 “‘አታመንዝር’+ እንደተባለ ሰምታችኋል።
28 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት+ ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።+
29 ስለዚህ ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው።+ መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም* ከሚወረወር ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።+
30 እንዲሁም ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው።+ መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም* ከሚጣል ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።+
31 “በተጨማሪም ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ይስጣት’+ ተብሏል።
32 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና* ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ ምንዝር ለመፈጸም እንድትጋለጥ ያደርጋታል፤ እንዲሁም በዚህ መንገድ የተፈታችን ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።+
33 “ከዚህም ሌላ በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘በከንቱ አትማል፤+ ይልቁንም ለይሖዋ* የተሳልከውን ፈጽም’+ እንደተባለ ሰምታችኋል።
34 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ፈጽሞ አትማሉ።+ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የአምላክ ዙፋን ነውና፤
35 በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግሩ ማሳረፊያ ነችና፤+ በኢየሩሳሌምም ቢሆን አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ነችና።+
36 በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከፀጉርህ አንዷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ማድረግ አትችልምና።
37 ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን፤+ ከዚህ ውጭ የሆነ ግን ከክፉው+ ነው።
38 “‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’+ እንደተባለ ሰምታችኋል።
39 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ክፉን ሰው አትቃወሙት፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት።+
40 አንድ ሰው ፍርድ ቤት ሊያቀርብህና እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢፈልግ መደረቢያህንም ጨምረህ ስጠው፤+
41 እንዲሁም አንድ ባለሥልጣን አንድ ኪሎ ሜትር* እንድትሄድ ቢያስገድድህ* ሁለት ኪሎ ሜትር አብረኸው ሂድ።
42 ለሚለምንህ ስጥ፤ ሊበደርህ የሚፈልገውንም ሰው* ፊት አትንሳው።+
43 “‘ባልንጀራህን ውደድ፤+ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል።
44 እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ+ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ፤+
45 ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤+ እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል።+
46 የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምን ብድራት ታገኛላችሁ?+ ቀረጥ ሰብሳቢዎችስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም?
47 ደግሞስ ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም ብትሉ ምን የተለየ ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም?
48 በሰማይ ያለው አባታችሁ ፍጹም* እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “መንፈስ ለማግኘት የሚለምኑ፤ ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ።”
^ ወይም “የዋሆች።”
^ ወይም “ይረካሉና።”
^ ወይም “ሰላማውያን።”
^ እንደ ስንዴ ያሉ የእህል ዓይነቶችን ለመስፈር የሚያገለግል ዕቃ።
^ “መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ብቁ ያልሆነ” ማለት ነው።
^ “መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ብቁ የሆነ” ማለት ነው።
^ የአይሁዳውያንን የሳንሄድሪን ሸንጎ ያመለክታል።
^ ከኢየሩሳሌም ውጭ ቆሻሻ የሚቃጠልበት ቦታ ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “የግዳጅ አገልግሎት እንድትፈጽም ቢያስገድድህ።”
^ ያለወለድ መበደር የሚፈልግን ሰው ያመለክታል።
^ ወይም “ሙሉ።”