የጴጥሮስ ሁለተኛው ደብዳቤ 3:1-18

  • ፌዘኞች ‘ጥፋት አይመጣም’ ይላሉ (1-7)

  • ይሖዋ አይዘገይም (8-10)

  • “ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል!” (11-16)

    • “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” (13)

  • ተታላችሁ እንዳትወሰዱ ተጠንቀቁ (17, 18)

3  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ይህ አሁን የምጽፍላችሁ ሁለተኛ ደብዳቤ ነው። በመጀመሪያው ደብዳቤዬ እንዳደረግሁት አሁንም ልጽፍላችሁ የተነሳሁት ማሳሰቢያ በመስጠት በትክክል ማሰብ እንድትችሉ ለማነቃቃት ሲሆን+  ይህም ቀደም ሲል ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃል* እንዲሁም ጌታችንና አዳኛችን በሐዋርያት* አማካኝነት የሰጠውን ትእዛዝ እንድታስታውሱ ለመርዳት ነው።  ከሁሉ አስቀድሞ ይህን እወቁ፦ በመጨረሻዎቹ ቀናት የራሳቸውን ምኞት እየተከተሉ የሚያፌዙ ፌዘኞች ይመጣሉ።+  እነዚህ ፌዘኞች “‘እገኛለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ?+ አባቶች በሞት ካንቀላፉበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ እንዳለ ይቀጥላል” ይላሉ።+  በጥንት ዘመን ሰማያት እንደነበሩ እንዲሁም ደረቁ ምድር በአምላክ ቃል ከውኃ በላይ ጸንቶ እንደቆመና በውኃ መካከል እንደነበረ የሚያረጋግጠውን ሐቅ ሆን ብለው ችላ ይላሉ።+  በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም በእነዚህ ነገሮች ጠፍቷል። ይህም የሆነው መላዋ ምድር በውኃ በተጥለቀለቀች ጊዜ ነው።+  ሆኖም በዚያው ቃል አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቀው ይቆያሉ።+  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናንተ ግን በይሖዋ* ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመት ደግሞ እንደ አንድ ቀን መሆኑን ልትዘነጉ አይገባም።+  አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ይሖዋ* የገባውን ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤+ ከዚህ ይልቅ እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው።+ 10  ይሁንና የይሖዋ* ቀን+ እንደ ሌባ ይመጣል፤+ በዚያም ቀን ሰማያት በነጎድጓድ ድምፅ* ያልፋሉ፤+ ንጥረ ነገሮቹም በኃይለኛ ሙቀት ይቀልጣሉ፤ ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ።+ 11  እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚቀልጡ ከሆነ ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል! 12  ሰማያት በእሳት ተቃጥለው የሚጠፉበትንና+ ንጥረ ነገሮቹም በኃይለኛ ሙቀት የሚቀልጡበትን የይሖዋን* ቀን መምጣት* እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ* ልትኖሩ ይገባል!+ 13  በሌላ በኩል ግን አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤+ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል።+ 14  ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህን ነገሮች እየተጠባበቃችሁ ስለሆነ በመጨረሻ በእሱ ፊት ቆሻሻና እድፍ ሳይኖርባችሁ በሰላም እንድትገኙ የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ።+ 15  በተጨማሪም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ በተሰጠው ጥበብ እንደጻፈላችሁ የጌታችንን ትዕግሥት እንደ መዳን ቁጠሩት፤+ 16  እንዲያውም በሁሉም ደብዳቤዎቹ ላይ ስለ እነዚህ ነገሮች ጽፏል። ይሁንና በደብዳቤዎቹ ውስጥ ለመረዳት የሚከብዱ አንዳንድ ነገሮች አሉ፤ እውቀት የጎደላቸውና* የሚወላውሉ ሰዎች ሌሎቹን ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ ሁሉ እነዚህንም ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ። 17  ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ ሕግ የሚተላለፉ ሰዎች በሚፈጽሙት ስህተት ከእነሱ ጋር ተታልላችሁ እንዳትወሰዱና ጽኑ አቋማችሁ እንዳይናጋ ተጠንቀቁ።+ 18  ከዚህ ይልቅ በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እድገት አድርጉ። አሁንም ሆነ ለዘላለም ለእሱ ክብር ይሁን። አሜን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የተነበዩአቸውን ነገሮች።”
ቃል በቃል “በሐዋርያዎቻችሁ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “በፈጣን ድምፅ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “መገኘት።”
ወይም “እየናፈቃችሁ።” ቃል በቃል “እያፋጠናችሁ።”
ወይም “ያልተማሩና።”