የሉቃስ ወንጌል 6:1-49

  • ኢየሱስ “የሰንበት ጌታ ነው” (1-5)

  • እጁ የሰለለ አንድ ሰው ተፈወሰ (6-11)

  • የኢየሱስ 12 ሐዋርያት (12-16)

  • ኢየሱስ አስተማረ እንዲሁም ፈወሰ (17-19)

  • ደስታና ወዮታ (20-26)

  • ጠላትን መውደድ (27-36)

  • አትፍረዱ (37-42)

  • በፍሬው ይታወቃል (43-45)

  • በደንብ የተገነባ ቤት፤ ጠንካራ መሠረት የሌለው ቤት (46-49)

6  በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በእህል እርሻ መካከል እያለፈ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ+ ይበሉ ነበር።+  በዚህ ጊዜ አንዳንድ ፈሪሳውያን “በሰንበት ቀን በሕግ የተከለከለ ነገር የምታደርጉት ለምንድን ነው?” አሏቸው።+  ኢየሱስ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ዳዊት እሱና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ ያደረገውን ነገር ፈጽሞ አላነበባችሁም?+  ወደ አምላክ ቤት ገብቶ ከካህናት በስተቀር ማንም እንዲበላው ያልተፈቀደውን በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት ተቀብሎ እንደበላና ከእሱ ጋር ለነበሩት እንደሰጣቸው አላነበባችሁም?”+  ከዚያም “የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው” አላቸው።+  በሌላ የሰንበት ቀን+ ወደ ምኩራብ ገብቶ ያስተምር ጀመር። በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ* አንድ ሰው ነበር።+  ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ኢየሱስን የሚከሱበት ምክንያት ማግኘት ይፈልጉ ስለነበር በሰንበት ይፈውስ እንደሆነ ለማየት በትኩረት ይከታተሉት ነበር።  እሱ ግን ሐሳባቸውን አውቆ+ ስለነበር እጁ የሰለለበትን* ሰው “ተነሳና መሃል ላይ ቁም” አለው። ሰውየውም ተነስቶ በዚያ ቆመ።  ከዚያም ኢየሱስ “እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት* ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።+ 10  በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደተባለው አደረገ፤ እጁም ዳነለት። 11  እነሱ ግን እጅግ ተቆጡ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉም እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር። 12  በዚያው ሰሞን ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤+ ሌሊቱንም ሙሉ ወደ አምላክ ሲጸልይ አደረ።+ 13  በነጋ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱን ወደ እሱ ጠርቶ ከመካከላቸው 12 ሰዎች መረጠ፤ ሐዋርያት ብሎም ሰየማቸው፤ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦+ 14  ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው ስምዖን፣ ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣+ በርቶሎሜዎስ፣ 15  ማቴዎስ፣ ቶማስ፣+ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ “ቀናተኛው” የሚባለው ስምዖን፣ 16  የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና በኋላ ከሃዲ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ። 17  ከእነሱም ጋር ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎችም በዚያ ነበሩ፤ በተጨማሪም እሱን ለመስማትና ከበሽታቸው ለመፈወስ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም በባሕር ጠረፍ አካባቢ ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና የመጡ በጣም ብዙ ሰዎች ነበሩ። 18  በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩ ሰዎችም እንኳ ተፈወሱ። 19  ኃይል ከእሱ እየወጣ+ ሁሉንም ይፈውስ ስለነበር ሕዝቡ ሁሉ ሊነካው ይፈልግ ነበር። 20  ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ቀና ብሎ በመመልከት እንዲህ ይል ጀመር፦ “እናንተ ድሆች የሆናችሁ ደስተኞች ናችሁ፤ የአምላክ መንግሥት የእናንተ ነውና።+ 21  “እናንተ አሁን የምትራቡ ደስተኞች ናችሁ፤ ኋላ ትጠግባላችሁና።+ “እናንተ አሁን የምታለቅሱ ደስተኞች ናችሁ፤ ኋላ ትስቃላችሁና።+ 22  “ሰዎች፣ በሰው ልጅ ምክንያት በሚጠሏችሁ፣+ በሚያገሏችሁ፣+ በሚነቅፏችሁና ክፉ እንደሆናችሁ አድርገው ያለስማችሁ ስም በሚሰጧችሁ* ጊዜ ሁሉ ደስተኞች ናችሁ። 23  በሰማይ ታላቅ ሽልማት ስለሚጠብቃችሁ በዚያን ቀን ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤ አባቶቻቸው በነቢያት ላይ እንዲሁ ያደርጉ ነበርና።+ 24  “ነገር ግን እናንተ ሀብታሞች ወዮላችሁ፤+ መጽናኛችሁን* በሙሉ አግኝታችኋልና።+ 25  “እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ትራባላችሁና። “እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ታዝናላችሁና፤ እንዲሁም ታለቅሳላችሁ።+ 26  “ሰዎች ስለ እናንተ መልካም ነገር በሚናገሩበት ጊዜ ሁሉ ወዮላችሁ፤+ አባቶቻቸው ለሐሰተኛ ነቢያት እንዲህ ያለ ነገር አድርገው ነበርና። 27  “ለእናንተ ለምትሰሙ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ፤+ 28  የሚረግሟችሁን መርቁ፤ እንዲሁም ለሚሰድቧችሁ ጸልዩ።+ 29  አንዱን ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ስጠው፤ መደረቢያህን ለሚወስድብህ እጀ ጠባብህንም አትከልክለው።+ 30  ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤+ ንብረትህን የሚወስድብህንም ሰው እንዲመልስ አትጠይቀው። 31  “በተጨማሪም ልክ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ እንደምትፈልጉት ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው።+ 32  “የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምን የሚያስመሰግን ነገር አለው? ኃጢአተኞችም እንኳ የሚወዷቸውን ይወዳሉና።+ 33  መልካም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉስ ምን ዋጋ አለው? ኃጢአተኞችም እንኳ እንዲሁ ያደርጋሉ። 34  እንዲሁም ይመልስልኛል ብላችሁ ለምታስቡት ሰው ብታበድሩ* ምን ፋይዳ አለው?+ ኃጢአተኞችም እንኳ የሰጡትን ያህል መልሰው ለመቀበል ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። 35  ከዚህ ይልቅ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ደግሞም በምላሹ ምንም ሳትጠብቁ አበድሩ፤+ ሽልማታችሁም ታላቅ ይሆናል፤ ደግሞም የልዑሉ አምላክ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ደግ ነውና።+ 36  አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ ሁሉ እናንተም መሐሪዎች ሁኑ።+ 37  “በተጨማሪም በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤* በእናንተም ላይ ፈጽሞ አይፈረድባችሁም፤+ ሌሎችን አትኮንኑ፤ እናንተም ፈጽሞ አትኮነኑም። ምንጊዜም ሌሎችን ይቅር በሉ፤* እናንተም ይቅር ትባላላችሁ።*+ 38  ለሰዎች ስጡ፤ እነሱም ይሰጧችኋል።+ ተትረፍርፎ እስኪፈስ ድረስ በተጠቀጠቀና በተነቀነቀ ጥሩ መስፈሪያ ሰፍረው በእቅፋችሁ ይሰጧችኋል። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ መልሰው ይሰፍሩላችኋልና።” 39  ከዚያም እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላል? ሁለቱም ተያይዘው ጉድጓድ ውስጥ አይወድቁም?+ 40  ተማሪ* ከአስተማሪው አይበልጥም፤ በሚገባ የተማረ ሁሉ ግን እንደ አስተማሪው ይሆናል። 41  ታዲያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ?+ 42  በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን ‘ዓይንህ ውስጥ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ? አንተ ግብዝ! መጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ። 43  “መልካም ዛፍ ሆኖ ሳለ የበሰበሰ ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ የለም፤ እንዲሁም የበሰበሰ ዛፍ ሆኖ መልካም ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ የለም።+ 44  እያንዳንዱ ዛፍ በፍሬው ይታወቃል።+ ለምሳሌ ሰዎች ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፤ ወይም ከእሾሃማ ቁጥቋጦ ወይን አይቆርጡም። 45  ጥሩ ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር ጥሩ ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰው ግን ካከማቸው መጥፎ ነገር ክፉ ነገር ያወጣል፤ አንደበቱ የሚናገረው በልቡ ውስጥ የሞላውን ነውና።+ 46  “ታዲያ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!’ የምትሉኝ፣ የምለውን ግን የማታደርጉት ለምንድን ነው?+ 47  ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቃሌን የሚሰማና የሚያደርግ ሁሉ ከማን ጋር እንደሚመሳሰል ልንገራችሁ፦+ 48  ቤት ለመሥራት በጥልቀት ቆፍሮ በዓለት ላይ መሠረቱን ከጣለ ሰው ጋር ይመሳሰላል። በኋላም ጎርፍ በመጣ ጊዜ ወንዙ ቤቱን በኃይል መታው፤ ሆኖም ቤቱ በደንብ ስለተገነባ ሊያነቃንቀው አልቻለም።+ 49  በሌላ በኩል ደግሞ ቃሌን ሰምቶ የማይፈጽም ሰው+ ሁሉ መሠረት ሳይጥል፣ በአፈር ላይ ቤት ከሠራ ሰው ጋር ይመሳሰላል። ወንዙም ቤቱን በኃይል መታው፤ ወዲያውም ተደረመሰ፤ እንዳልነበረም ሆነ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ሽባ የሆነ።”
ወይም “ሽባ የሆነበትን።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ስማችሁን በሚያጥላሉበት።”
ወይም “ልታገኙ የምትችሉትን ነገር።”
ያለወለድ ማበደርን ያመለክታል።
ወይም “በነፃ ትለቀቃላችሁ።”
ወይም “በነፃ ልቀቁ።”
ወይም “መፍረዳችሁን ተዉ።”
ወይም “ደቀ መዝሙር።”