ዘፀአት 34:1-35

  • አዲስ የድንጋይ ጽላቶች ተዘጋጁ (1-4)

  • ሙሴ የይሖዋን ክብር አየ (5-9)

  • ቃል ኪዳኑ የያዘው ዝርዝር ሐሳብ በድጋሚ ተነገረ (10-28)

  • የሙሴ ፊት አንጸባረቀ (29-35)

34  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ጥረብ፤+ እኔም በጽላቶቹ ላይ አንተ በሰበርካቸው+ በመጀመሪያዎቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት እጽፍባቸዋለሁ።+  አንተም በጠዋት ወደ ሲና ተራራ ወጥተህ በዚያ በተራራው አናት ላይ በፊቴ ስለምትቆም በጠዋት ለመሄድ ተዘጋጅ።+  ሆኖም ከአንተ ጋር ማንም ሰው አይውጣ፤ ደግሞም በተራራው ላይ በየትኛውም ቦታ ሌላ ማንም ሰው አይታይ። ሌላው ቀርቶ በጎችም ሆኑ ከብቶች እንኳ በተራራው ፊት ለፊት አይሰማሩ።”+  በመሆኑም ሙሴ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት የመጀመሪያዎቹን የሚመስሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ከጠረበ በኋላ በጠዋት ተነስቶ ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች በእጁ ይዞ ነበር።  ከዚያም ይሖዋ በደመና ውስጥ ወርዶ+ በዚያ ከእሱ ጋር ሆነ፤ ይሖዋ የተባለውንም ስሙን አወጀ።+  ይሖዋም በፊቱ እያለፈ እንዲህ ሲል አወጀ፦ “ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና+ ሩኅሩኅ*+ የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣+ ታማኝ ፍቅሩና*+ እውነቱ*+ እጅግ ብዙ የሆነ፣  ታማኝ ፍቅርን ለሺዎች የሚያሳይ፣+ ስህተትን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል፣+ ጥፋተኛውን ግን በምንም ዓይነት ሳይቀጣ የማያልፍ+ እንዲሁም አባቶች ለሠሩት ስህተት በልጆች፣ በልጅ ልጆች፣ በሦስተኛና በአራተኛ ትውልድ ላይ ቅጣትን የሚያመጣ።”+  ሙሴም ወዲያውኑ መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ።  ከዚያም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እባክህ ይሖዋ፣ እኛ ግትር* ሕዝብ ብንሆንም+ በመካከላችን ሆነህ አብረኸን ሂድ፤+ ደግሞም ስህተታችንንና ኃጢአታችንን ይቅር በል፤+ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን።” 10  እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ እኔ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፦ በመላው ምድርም ሆነ በብሔራት ሁሉ መካከል ፈጽሞ ተደርገው* የማያውቁ ድንቅ ነገሮችን በሕዝብህ ሁሉ ፊት አደርጋለሁ፤+ ለአንተ ስል የማደርገው ነገር የሚያስፈራ ስለሆነ በመካከላቸው የምትኖረው ሕዝቦች ሁሉ የይሖዋን ሥራ ያያሉ።+ 11  “እኔ ዛሬ የማዝህን ነገር ልብ በል።+ እኔም አሞራውያንን፣ ከነአናውያንን፣ ሂታውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ሂዋውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊትህ አስወጣቸዋለሁ።+ 12  በምትሄድበት ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳትጋባ ተጠንቀቅ፤+ አለዚያ ወጥመድ ይሆንብሃል።+ 13  ከዚህ ይልቅ መሠዊያዎቻቸውን ታፈራርሳላችሁ፤ የማምለኪያ ዓምዶቻቸውን ትሰባብራላችሁ፤ እንዲሁም የማምለኪያ ግንዶቻቸውን* ትቆራርጣላችሁ።+ 14  ይሖዋ፣ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ* አምላክ በመሆኑ የሚታወቅ ስለሆነ ለሌላ አምላክ አትስገድ።+ አዎ፣ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ ነው።+ 15  ከምድሪቱ ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳትጋባ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም እነሱ አማልክታቸውን በማምለክ ምንዝር በሚፈጽሙበትና ለአማልክታቸው በሚሠዉበት+ ጊዜ ከመካከላቸው አንዱ አንተን መጋበዙ አይቀርም፣ አንተም ካቀረበው መሥዋዕት ትበላለህ።+ 16  ከዚያም ሴቶች ልጆቻቸውን ከወንዶች ልጆችህ ጋር ታጋባለህ፤+ ሴቶች ልጆቻቸውም አማልክታቸውን በማምለክ ምንዝር መፈጸማቸው እንዲሁም ወንዶች ልጆችህ የእነሱን አማልክት በማምለክ ምንዝር እንዲፈጽሙ ማድረጋቸው አይቀርም።+ 17  “ከቀለጠ ብረት አማልክት አትሥራ።+ 18  “የቂጣን በዓል ታከብራለህ።+ ልክ ባዘዝኩህ መሠረት ቂጣ ትበላለህ፤ ከግብፅ የወጣኸው በአቢብ* ወር+ ስለሆነ በአቢብ ወር በተወሰነው ጊዜ ላይ ለሰባት ቀን ይህን ታደርጋለህ። 19  “በኩር የሆነ ወንድ ሁሉ* የእኔ ነው፤+ ደግሞም የመንጋህ በኩር ሁሉ፣ በኩር የሆነ በሬም ሆነ ተባዕት በግ የእኔ ነው።+ 20  የአህያን በኩር በበግ ዋጀው። የማትዋጀው ከሆነ ግን አንገቱን ስበረው። ከወንዶች ልጆችህ መካከል በኩር የሆነውን ሁሉ ትዋጀዋለህ።+ ማንም ባዶ እጁን ፊቴ አይቅረብ። 21  “ስድስት ቀን ትሠራለህ፤ በሰባተኛው ቀን ግን ታርፋለህ።*+ በሚታረስበትም ሆነ አዝመራ በሚሰበሰብበት ወቅትም እንኳ ታርፋለህ። 22  “የሳምንታት በዓልህን መጀመሪያ በደረሰው የስንዴ በኩር አክብር፤ የአዝመራ መክተቻን በዓልም* በዓመቱ ማብቂያ ላይ አክብር።+ 23  “የአንተ የሆነ ሰው* ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ የእስራኤል አምላክ በሆነው በእውነተኛው ጌታ በይሖዋ ፊት ይቅረብ።+ 24  ብሔራትን ከፊትህ አስወጣለሁና፤+ ክልልህንም ሰፊ አደርገዋለሁ፤ የአምላክህን የይሖዋን ፊት ለማየት በዓመት ሦስቴ በምትወጣበት ጊዜ ማንም ምድርህን አይመኝም። 25  “የመሥዋዕቴን ደም እርሾ ከገባበት ከማንኛውም ነገር ጋር አድርገህ አታቅርብ።+ የፋሲካ በዓል መሥዋዕት እስከ ጠዋት ድረስ መቆየት የለበትም።+ 26  “መጀመሪያ የደረሰውን የአፈርህን ምርጥ ፍሬ ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ቤት አምጣ።+ “የፍየልን ጠቦት በእናቱ ወተት አትቀቅል።”+ 27  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “ከአንተም ሆነ ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን የምገባው+ በእነዚህ ቃላት መሠረት ስለሆነ እነዚህን ቃላት ጻፍ”+ አለው። 28  እሱም በዚያ ከይሖዋ ጋር 40 ቀንና 40 ሌሊት ቆየ። እህል አልቀመሰም፤ ውኃም አልጠጣም።+ እሱም* በጽላቶቹ ላይ የቃል ኪዳኑን ቃላት ይኸውም አሥርቱን ትእዛዛት* ጻፈ።+ 29  ከዚያም ሙሴ ከሲና ተራራ ወረደ፤ ሁለቱንም የምሥክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ነበር።+ ከአምላክ ጋር ሲነጋገር ስለቆየ ከተራራው በወረደበት ጊዜ ፊቱ እንደሚያንጸባርቅ አላወቀም ነበር። 30  አሮንና እስራኤላውያን ሁሉ ሙሴን ሲያዩት ፊቱ እንደሚያንጸባርቅ አስተዋሉ፤ ወደ እሱ ለመቅረብም ፈሩ።+ 31  ሙሴ ግን ጠራቸው፤ በመሆኑም አሮንና የማኅበረሰቡ አለቆች በሙሉ ወደ እሱ መጡ፤ ሙሴም አነጋገራቸው። 32  ከዚያም እስራኤላውያን በሙሉ ወደ እሱ ቀረቡ፤ እሱም ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ የሰጠውን ትእዛዝ ሁሉ ሰጣቸው።+ 33  ሙሴም ከእነሱ ጋር ተነጋግሮ ሲጨርስ ፊቱን በመሸፈኛ ይሸፍን ነበር።+ 34  ሙሴ፣ ይሖዋ ፊት ቀርቦ ከእሱ ጋር ለመነጋገር ወደ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ግን ከዚያ እስከሚወጣበት ጊዜ ድረስ መሸፈኛውን ያነሳ ነበር።+ ከዚያም ወጥቶ የተቀበለውን ትእዛዝ ለእስራኤላውያን ይነግራቸው ነበር።+ 35  እስራኤላውያንም የሙሴ ፊት እንደሚያንጸባርቅ ተመለከቱ፤ ከዚያም ሙሴ አምላክን* ለማነጋገር ወደ ውስጥ እስከሚገባበት ጊዜ ድረስ መሸፈኛውን መልሶ ፊቱ ላይ አደረገው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ታማኝነቱ።”
ወይም “ፍቅራዊ ደግነቱና።”
ወይም “ቸር።”
ቃል በቃል “አንገተ ደንዳና።”
ወይም “ተፈጥረው።”
ወይም “ተቀናቃኞቹን የማይታገሥ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ማህፀን የሚከፍተው ሁሉ።”
ወይም “ሰንበትን ታከብራለህ።”
የዳስ (የማደሪያ ድንኳን) በዓል በመባልም ይታወቃል።
ወይም “ወንድ።”
ቃል በቃል “አሥርቱን ቃላት።”
እዚህ ላይ “እሱ” የሚለው ቃል ይሖዋን እንደሚያመለክት መረዳት ይቻላል። ዘፀ 34:1ን ተመልከት።
ቃል በቃል “እሱን።”