ለተሰሎንቄ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 4:1-18

  • ከፆታ ብልግና እንዲርቁ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (1-8)

  • እርስ በርስ ተዋደዱ (9-12)

    • ‘በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ’ (11)

  • በክርስቶስ የሞቱት ቀድመው ይነሳሉ (13-18)

4  በመጨረሻም ወንድሞች፣ አምላክን ማስደሰት እንድትችሉ እንዴት መመላለስ እንዳለባችሁ አስተምረናችኋል፤+ ደግሞም በዚሁ መንገድ እየተመላለሳችሁ ነው፤ በመሆኑም ይህንኑ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማድረጋችሁን እንድትቀጥሉ በጌታ ኢየሱስ ስም እንጠይቃችኋለን እንዲሁም እንለምናችኋለን።  በጌታ ኢየሱስ ስም የሰጠናችሁን መመሪያዎች ታውቃላችሁና።  የአምላክ ፈቃድ እንድትቀደሱና+ ከፆታ ብልግና* እንድትርቁ ነው።+  ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን አካል* በመቆጣጠር+ እንዴት በቅድስናና+ በክብር መያዝ እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል።  ይህም አምላክን እንደማያውቁት አሕዛብ+ ስግብግብነት በሚንጸባረቅበት ልቅ የፍትወት ስሜት አይሁን።+  ማንም ሰው በዚህ ጉዳይ ከገደቡ ማለፍና ወንድሙን መጠቀሚያ ማድረግ አይኖርበትም፤ ምክንያቱም አስቀድመን እንደነገርናችሁና በጥብቅ እንዳስጠነቀቅናችሁ ይሖዋ* በእነዚህ ነገሮች ሁሉ የተነሳ የቅጣት እርምጃ ይወስዳል።  አምላክ የጠራን ለቅድስና ነው እንጂ ለርኩሰት አይደለም።+  እንግዲህ ለዚህ ንቀት የሚያሳይ ሰው የሚንቀው ሰውን ሳይሆን ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጣችሁን+ አምላክ ነው።+  ይሁን እንጂ እናንተ ራሳችሁ እርስ በርስ እንድትዋደዱ ከአምላክ ስለተማራችሁ+ የወንድማማች ፍቅርን በተመለከተ+ እንድንጽፍላችሁ አያስፈልግም። 10  ደግሞም በመላው መቄዶንያ ለሚገኙ ወንድሞች ሁሉ ይህን እያደረጋችሁ ነው። ሆኖም ወንድሞች፣ ይህን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማድረጋችሁን እንድትቀጥሉ እናሳስባችኋለን። 11  ከዚህ በፊት እንዳዘዝናችሁ በሰላም ለመኖር፣+ በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባትና+ በገዛ እጃችሁ ለመሥራት ተጣጣሩ፤+ 12  ይህም በውጭ ባሉት* ሰዎች ፊት ሥርዓት ባለው መንገድ እንድትመላለሱና+ ምንም ነገር የሚጎድላችሁ እንዳትሆኑ ነው። 13  በተጨማሪም ወንድሞች፣ ተስፋ እንደሌላቸው+ እንደ ሌሎቹ ሰዎች እንዳታዝኑ በሞት አንቀላፍተው ስላሉት+ ሳታውቁ እንድትቀሩ አንፈልግም። 14  ኢየሱስ እንደሞተና ከሞት እንደተነሳ የምናምን ከሆነ+ ከኢየሱስ ጋር አንድነት ኖሯቸው በሞት ያንቀላፉትንም አምላክ ሕይወት ሰጥቶ ከእሱ ጋር እንዲሆኑ ያደርጋል።+ 15  የይሖዋን* ቃል መሠረት አድርገን የምንነግራችሁ ይህ ነውና፤ ጌታ እስከሚገኝበት ጊዜ ድረስ በሕይወት የምንኖር በሞት አንቀላፍተው ያሉትን በምንም መንገድ አንቀድምም፤ 16  ምክንያቱም ጌታ ራሱ በትእዛዝ ድምፅ፣ በመላእክት አለቃ+ ድምፅና በአምላክ መለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳል፤ ከክርስቶስ ጋር አንድነት ኖሯቸው የሞቱትም ቀድመው ይነሳሉ።+ 17  ከዚያም በሕይወት ቆይተን የምንተርፈው እኛ በአየር ላይ ከጌታ ጋር ለመገናኘት+ ከእነሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤+ በዚህም መንገድ ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።+ 18  ስለሆነም በእነዚህ ቃላት ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ዕቃ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የክርስቲያን ጉባኤ አባል ባልሆኑት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።