ኢሳይያስ 1:1-31

  • አንድ አባትና ዓመፀኛ ልጆቹ (1-9)

  • ይሖዋ ለታይታ ተብሎ የሚቀርብን አምልኮ ይጠላል (10-17)

  • “የተፈጠረውን ችግር ተወያይተን እንፍታ” (18-20)

  • ጽዮን ዳግመኛ የታመነች ከተማ ትሆናለች (21-31)

1  የይሁዳ ነገሥታት+ በሆኑት በዖዝያ፣+ በኢዮዓታም፣+ በአካዝና+ በሕዝቅያስ+ ዘመን የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ* ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ፦+  2  ሰማያት ሆይ፣ ስሙ፤ ምድር ሆይ፣ አድምጪ፤+ይሖዋ እንዲህ ሲል ተናግሯልና፦ “ወንዶች ልጆችን ተንከባክቤ አሳደግኩ፤+እነሱ ግን በእኔ ላይ ዓመፁ።+  3  በሬ ጌታውን፣አህያም የባለቤቱን ጋጣ በሚገባ ያውቃል፤እስራኤል ግን እኔን* አላወቀም፤+የገዛ ሕዝቤም አላስተዋለም።”  4  ኃጢአተኛ የሆነው ብሔር፣+ከባድ በደል የተጫነው ሕዝብ፣የክፉዎች ዘር፣ ብልሹ የሆኑ ልጆች ወዮላቸው! እነሱ ይሖዋን ትተዋል፤+የእስራኤልን ቅዱስ አቃለዋል፤ጀርባቸውን ሰጥተውታል።  5  በዓመፅ ላይ ዓመፅ የምትጨምሩት፣ አሁን ደግሞ ምናችሁ ላይ መመታት ፈልጋችሁ ነው?+ መላው ራስ ታሟል፤መላው ልብም በበሽታ ተይዟል።+  6  ከእግር ጥፍር አንስቶ እስከ ራስ ፀጉር ድረስ አንድም ጤነኛ የአካል ክፍል የለም። በቁስልና በሰምበር ተሞልቷል፤ እንዲሁም ተተልትሏል፤ቁስሉ አልታከመም* ወይም አልታሰረም አሊያም በዘይት አለዘበም።+  7  ምድራችሁ ባድማ ሆኗል። ከተሞቻችሁ በእሳት ጋይተዋል። የባዕድ አገር ሰዎች ዓይናችሁ እያየ ምድራችሁን ይውጣሉ።+ ባዕዳን እንዳወደሙት ጠፍ መሬት ሆኗል።+  8  የጽዮን ሴት ልጅ በወይን እርሻ ውስጥ እንዳለ መጠለያ፣*በኪያር የእርሻ ቦታ እንዳለ ጎጆ፣እንደተከበበችም ከተማ ተትታለች።+  9  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ጥቂት ሰዎች ከጥፋት እንዲተርፉልን ባያደርግ ኖሮእንደ ሰዶም በሆንን፣ገሞራንም በመሰልን ነበር።+ 10  እናንተ የሰዶም+ አምባገነኖች፣* የይሖዋን ቃል ስሙ። እናንተ የገሞራ+ ሰዎች፣ የአምላካችንን ሕግ* አዳምጡ። 11  የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል?”+ ይላል ይሖዋ። “የሚቃጠሉ የአውራ በግ መባዎችና+ የደለቡ እንስሳት ስብ+ በቅቶኛል፤በወይፈኖች፣+ በበግ ጠቦቶችና በፍየሎች+ ደም+ ደስ አልሰኝም። 12  በፊቴ ለመቅረብ የምትመጡት፣+ይህን እንድታደርጉ፣የቤተ መቅደሴን ግቢ እንድትረግጡ ማን ጠይቋችሁ ነው?+ 13  ከንቱ የሆኑትን የእህል መባዎች ከዚህ በኋላ አታምጡ። ዕጣናችሁ በፊቴ አስጸያፊ ነው።+ የአዲስ ጨረቃ+ በዓልንና ሰንበትን+ ታከብራላችሁ፤ ስብሰባም+ ትጠራላችሁ። በአንድ በኩል የተቀደሱ ጉባኤዎችን እያከበራችሁ በሌላ በኩል የምትፈጽሙትን አስማታዊ ድርጊት+ መታገሥ አልችልም። 14  የአዲስ ጨረቃ በዓሎቻችሁንና ሌሎች በዓሎቻችሁን ጠልቻለሁ።* ለእኔ ሸክም ሆነውብኛል፤እነሱንም ከመሸከሜ የተነሳ ዝያለሁ። 15  እጆቻችሁን ስትዘረጉዓይኖቼን ከእናንተ እሰውራለሁ።+ ጸሎት ብታበዙም እንኳ+አልሰማችሁም፤+እጆቻችሁ በደም ተሞልተዋል።+ 16  ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤+ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አስወግዱ፤መጥፎ ድርጊት መፈጸማችሁን አቁሙ።+ 17  መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን ፈልጉ፤+ጨቋኙ እንዲታረም አድርጉ፤አባት የሌለውን ልጅ* መብት አስከብሩ፤ለመበለቲቱም ተሟገቱ።”+ 18  “ኑና በመካከላችን የተፈጠረውን ችግር ተወያይተን እንፍታ” ይላል ይሖዋ።+ “ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላእንደ በረዶ ይነጣል፤+እንደ ደማቅ ቀይ ጨርቅ ቢቀላምእንደ ነጭ የሱፍ ጨርቅ ይሆናል። 19  እሺ ብትሉና ብትታዘዙየምድሪቱን መልካም ፍሬ ትበላላችሁ።+ 20  እንቢ ብትሉና ብታምፁ ግንሰይፍ ይበላችኋል፤+የይሖዋ አፍ ይህን ተናግሯልና።” 21  ታማኝ የነበረችው ከተማ+ እንዴት ዝሙት አዳሪ ሆነች!+ ፍትሕ የሞላባትና+ጽድቅ የሰፈነባት ነበረች፤+አሁን ግን የነፍሰ ገዳዮች ጎሬ ሆናለች።+ 22  ብርሽ እንደ ዝቃጭ ሆኗል፤+መጠጥሽ* በውኃ ተበርዟል። 23  አለቆችሽ ግትሮችና የሌባ ግብረ አበሮች ናቸው።+ ሁሉም ጉቦ የሚወዱና እጅ መንሻ የሚያሳድዱ ናቸው።+ አባት የሌለው ልጅ ፍትሕ እንዲያገኝ* አያደርጉም፤የመበለቲቱም አቤቱታ ወደ እነሱ አይደርስም።+ 24  ስለዚህ እውነተኛው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣የእስራኤል ኃያል አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እንግዲያው ስሙ! ባላጋራዎቼን አጠፋለሁ፤ጠላቶቼንም እበቀላለሁ።+ 25  እጄን በአንቺ ላይ አነሳለሁ፤በመርዝ የማጥራት ያህል ቆሻሻሽን አቅልጬ አወጣለሁ፤ዝቃጭሽንም ሁሉ አስወግዳለሁ።+ 26  መጀመሪያ ላይ እንደነበረው ፈራጆችሽን፣እንደቀድሞውም አማካሪዎችሽን መልሼ አመጣለሁ።+ ከዚያ በኋላ የጽድቅ መዲና፣ የታመነች ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።+ 27  ጽዮን በፍትሕ፣የሚመለሱት ነዋሪዎቿም በጽድቅ ይቤዣሉ።+ 28  ዓመፀኞችና ኃጢአተኞች በአንድ ላይ ይደቅቃሉ፤+ይሖዋን የሚተዉም ያከትምላቸዋል።+ 29  እናንተ በተመኛችኋቸው ግዙፍ ዛፎች ያፍራሉና፤+በመረጣችኋቸው የአትክልት ቦታዎች* የተነሳም ትዋረዳላችሁ።+ 30  ቅጠሉ እንደጠወለገ ትልቅ ዛፍ፣+ውኃም እንደሌለው የአትክልት ቦታ ትሆናላችሁና። 31  ብርቱውም ሰው እንደ ተልባ እግር* ይሆናል፤የሥራውም ውጤት እንደ እሳት ብልጭታ ይሆናል፤ሁለቱም አብረው ይቃጠላሉ፤እሳቱንም ማጥፋት የሚችል ማንም የለም።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

“የይሖዋ ማዳን” ማለት ነው።
ወይም “ጌታውን።”
ቃል በቃል “አልፈረጠም።”
ወይም “ዳስ።”
ወይም “ገዢዎች።”
ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”
ወይም “ነፍሴ ጠልታለች።”
ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን ልጅ።”
ወይም “ከስንዴ የሚዘጋጀው ጠላሽ።”
ወይም “ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆች ፍትሕ እንዲያገኙ።”
ከጣዖት አምልኮ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ዛፎችና የአትክልት ቦታዎች የሚያመለክት ይመስላል።
ተቀጣጣይ የሆነ ገመድ መሰል ቃጫ።