ኢሳይያስ 5:1-30

  • ስለ ይሖዋ የወይን እርሻ የተዘመረ መዝሙር (1-7)

  • በይሖዋ የወይን እርሻ ላይ የተነገረ ወዮታ (8-24)

  • በሕዝቡ ላይ የነደደው የአምላክ ቁጣ (25-30)

5  እስቲ ለወዳጄ መዝሙር ልዘምር።መዝሙሩ ስለ ወዳጄና ስለ ወይን እርሻው+ የሚገልጽ ነው። ወዳጄ ለም በሆነ ኮረብታ ላይ የወይን እርሻ ነበረው።   እሱም መሬቱን ቆፈረ፤ ድንጋዮቹንም አስወገደ። ምርጥ የሆነ ቀይ ወይን ተከለ፤በመካከሉ ማማ ገነባ፤ድንጋይ ፈልፍሎም የወይን መጭመቂያ ጉድጓድ ሠራ።+ ከዚያም ‘ወይኑ ጥሩ ፍሬ ያፈራል’ ብሎ ይጠብቅ ጀመር፤ይሁንና መጥፎ ፍሬ ብቻ አፈራ።+   “እናንተ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፣በእኔና በወይን እርሻዬ መካከል እስቲ ፍረዱ።+   ለወይን እርሻዬ ከዚህ በላይ ላደርግለት የሚገባምን ነገር አለ?+ ‘ጥሩ ወይን ያፈራል’ ብዬ ስጠብቅመጥፎ ወይን ብቻ ያፈራው ለምንድን ነው?   እንግዲህ በወይን እርሻዬ ላይምን እንደማደርግ ልንገራችሁ፦ በዙሪያው ያለውን የቁጥቋጦ አጥር እነቅላለሁ፤ለእሳትም ይማገዳል።+ የድንጋይ ቅጥሩን አፈርሳለሁ፤በእግርም ይረጋገጣል።   ቦታውን ጠፍ መሬት አደርገዋለሁ፤+የወይን ተክሉ አይገረዝም እንዲሁም አይኮተኮትም። ቁጥቋጦና አረም ይወርሰዋል፤+ደመናቱም ዝናብ እንዳያዘንቡበት ትእዛዝ እሰጣለሁ።+   የሠራዊት ጌታ የይሖዋ የወይን እርሻ የእስራኤል ቤት ነውና፤+የይሁዳ ሰዎች እሱ ይወደው የነበረው የአትክልት ቦታ ናቸው።* ፍትሕን ሲጠብቅ+እነሆ፣ ግፍ ይፈጸማል፤‘ጽድቅ ይሰፍናል’ ብሎ ሲጠብቅእነሆ፣ የጭንቅ ጩኸት ይሰማል።”+   ቦታ እስኪጠፋ ድረስበቤት ላይ ቤት ለሚጨምሩና+በመሬት ላይ መሬት ለሚይዙ ወዮላቸው!+እናንተም በምድሪቱ ላይ ብቻችሁን ትቀመጣላችሁ።   የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ጆሮዬ እየሰማ እንዲህ ሲል ማለ፦ብዙ ቤቶች ታላላቅና ያማሩ ቢሆኑም እንኳአንድም ነዋሪ የማይገኝባቸውአስፈሪ ቦታዎች ይሆናሉ።+ 10  ከአራት ሄክታር* የወይን እርሻ አንድ የባዶስ* መስፈሪያ ብቻ ይገኛል፤ከአንድ የሆሜር* መስፈሪያ ዘርም አንድ የኢፍ* መስፈሪያ ብቻ ይገኛል።+ 11  የሚያሰክር መጠጥ ለመጠጣት በማለዳ ለሚነሱ፣+የወይን ጠጅ እስከሚያቃጥላቸው ድረስ እስከ ሌሊት ለሚያመሹ ወዮላቸው! 12  በግብዣቸው ላይ በገና፣ ባለ አውታር መሣሪያ፣አታሞና ዋሽንት እንዲሁም የወይን ጠጅ አለ፤እነሱ ግን ይሖዋ ያከናወነውን ተግባር አያስቡም፤የእጁንም ሥራ አይመለከቱም። 13  ስለዚህ ሕዝቤ እውቀት በማጣቱ+ተማርኮ ይወሰዳል፤በመካከላቸው የሚገኙ የተከበሩ ሰዎች ይራባሉ፤+ሕዝባቸውም እንዳለ በውኃ ጥም ይቃጠላል። 14  በመሆኑም መቃብር* ራሷን* አሰፋች፤አፏንም ያለልክ ከፈተች፤+የከተማዋ ውበት፣* የሚንጫጫው ሕዝቧና በውስጧ የሚፈነጥዙት ሰዎችወደዚያ ይወርዳሉ። 15  ሰውም አንገቱን ይደፋል፤የሰው ልጅ ኀፍረት ይከናነባል፤የትዕቢተኞችም ዓይን ይዋረዳል። 16  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በሚሰጠው ፍርድ* ከፍ ከፍ ይላል፤ቅዱስ+ የሆነው እውነተኛው አምላክ በጽድቅ ራሱን ይቀድሳል።+ 17  የበግ ጠቦቶችም በገዛ መሰማሪያቸው እንደተሰማሩ ሆነው ይግጣሉ፤የባዕድ አገር ሰዎች፣ የሰቡ እንስሳት ይኖሩባቸው በነበሩ ወና የሆኑ ቦታዎች ይበላሉ። 18  በደላቸውን በአታላይ ገመድ የሚስቡ፣ኃጢአታቸውንም በሠረገላ ገመድ የሚጎትቱ ወዮላቸው፤ 19  “ሥራውን ያፋጥን፤እናየውም ዘንድ ቶሎ ይምጣ። እናውቀውም ዘንድየእስራኤል ቅዱስ አምላክ ዓላማ* ይፈጸም” የሚሉ ወዮላቸው!+ 20  ጥሩውን መጥፎ፣ መጥፎውንም ጥሩ የሚሉ፣+ጨለማውን በብርሃን፣ ብርሃኑን በጨለማ የሚተኩጣፋጩን መራራ፣ መራራውን ጣፋጭ አድርገው የሚያቀርቡ ወዮላቸው! 21  በገዛ ዓይናቸው ጥበበኛ የሆኑናበራሳቸው አመለካከት ልባም የሆኑ ወዮላቸው!+ 22  የወይን ጠጅ በመጠጣት ረገድ ብርቱዎች የሆኑ፣መጠጥ በመደባለቅም የተካኑ ወዮላቸው፤+ 23  ጉቦ በመቀበል ክፉውን ከበደል ነፃ የሚያደርጉ፣+ጻድቁንም ፍትሕ የሚነፍጉ ወዮላቸው!+ 24  የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፣የደረቀም ሣር በነበልባል በንኖ እንደሚጠፋየእነሱም ሥር ይበሰብሳል፤አበባቸውም ልክ እንደ ዱቄት በየቦታው ይበናል፤ምክንያቱም እነሱ የሠራዊት ጌታ የሆነውን የይሖዋን ሕግ* ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል፣የእስራኤል ቅዱስ የተናገረውንም ቃል ንቀዋል።+ 25  የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ የነደደው በዚህ ምክንያት ነው፤እሱም እጁን በእነሱ ላይ ይዘረጋል፤ ይመታቸዋልም።+ ተራሮችም ይናወጣሉ፤አስከሬናቸውም በጎዳናዎች ላይ እንዳለ ቆሻሻ ይሆናል።+ ከዚህ ሁሉ የተነሳ ቁጣው አልተመለሰም፤ይልቁንም እጁ ለመምታት ገና እንደተዘረጋ ነው። 26  በሩቅ ላለ ታላቅ ሕዝብም ምልክት* አቁሟል፤+ከምድር ዳርቻ እንዲመጡ በፉጨት ጠርቷቸዋል፤+እነሆም፣ ሕዝቡ በከፍተኛ ፍጥነት እየመጣ ነው።+ 27  ከእነሱ መካከል የደከመም ሆነ የሚደናቀፍ አንድም ሰው የለም። የሚያንጎላጅም ሆነ የሚተኛ የለም። በወገባቸውም ላይ ያለው ቀበቶ አልተፈታም፤እንዲሁም የጫማቸው ማሠሪያ አልተበጠሰም። 28  ፍላጻዎቻቸው ሁሉ የሾሉ፣ደጋኖቻቸውም በሙሉ የተወጠሩ* ናቸው። የፈረሶቻቸው ኮቴ እንደ ባልጩት ድንጋይ ነው፤የሠረገሎቻቸውም መንኮራኩሮች* እንደ አውሎ ነፋስ ናቸው።+ 29  ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤እንደ ደቦል አንበሳ ያገሳሉ።+ የጉርምርምታ ድምፅ እያሰሙ አድብተው ይይዛሉ፤ከእጃቸውም የሚያስጥል ስለሌለ ተሸክመውት ይሄዳሉ። 30  በዚያም ቀን እንደ ባሕር ሞገድያጉረመርሙበታል።+ ምድሪቷን ትኩር ብሎ የሚመለከት ማንኛውም ሰው የሚያስጨንቅ ጨለማ ያያል፤ብርሃኑም እንኳ ከደመናው የተነሳ ጨልሟል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ተክል ናቸው።”
ቃል በቃል “አሥር ጥማድ ከሚያውል።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ታላላቅ ሰዎቿ።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ነፍሷን።”
ወይም “በሚሰጠው ፍትሕ።”
ወይም “ውሳኔ፤ ምክር።”
ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”
ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶ።”
ወይም “ፍላጻ ለማስፈንጠር የተዘጋጁ።”
ተሽከርካሪ እግር።