ኢሳይያስ 3:1-26

  • የይሁዳ መሪዎች ሕዝቡን ያስታሉ (1-15)

  • እየተጣቀሱ የሚሄዱት የጽዮን ሴቶች ተፈረደባቸው (16-26)

3  እነሆ፣ እውነተኛው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋኢየሩሳሌምና ይሁዳ ማንኛውም ዓይነት ድጋፍና አቅርቦትይኸውም የምግብና የውኃ አቅርቦት ሁሉ እንዲቋረጥባቸው ያደርጋል፤+   ኃያሉን ሰውና ተዋጊውን፣ዳኛውንና ነቢዩን፣+ ሟርተኛውንና ሽማግሌውን፣   የሃምሳ አለቃውን፣+ ባለሥልጣኑንና አማካሪውን፣በአስማት የተካነውንና በድግምት የላቀ ችሎታ ያለውን ያስወግዳል።+   በእነሱ ላይ ልጆችን መኳንንት አድርጌ እሾማለሁ፤ያልሰከነ* ሰውም ይገዛቸዋል።   ሕዝቡ አንዱ ሌላውን፣እያንዳንዱም ባልንጀራውን ይጨቁናል።+ ልጅ በሽማግሌ ላይ ጥቃት ይሰነዝራል፤ተራው ሰውም የተከበረውን ይዳፈራል።+   እያንዳንዱ ሰው በአባቱ ቤት የሚኖረውን ወንድሙን ይዞ “አንተ ካባ አለህ፤ ስለዚህ በእኛ ላይ አዛዥ ሁን። ይህን የፍርስራሽ ክምር ግዛ” ይለዋል።   እሱ ግን በዚያ ቀን እንዲህ ሲል ይቃወማል፦ “እኔ ቁስላችሁን አላክምም፤*በቤቴ ምግብም ሆነ ልብስ የለም። በሕዝቡ ላይ አዛዥ አድርጋችሁ አትሹሙኝ።”   ኢየሩሳሌም ተሰናክላለችና፤ይሁዳም ወድቃለች፤ምክንያቱም እነሱ በአንደበታቸውም ሆነ በሥራቸው ይሖዋን ይቃወማሉ፤በክብራማው አምላክ ፊት* አሻፈረን ይላሉ።+   የፊታቸው ገጽታ ይመሠክርባቸዋል፤ደግሞም እንደ ሰዶም+ ኃጢአታቸውን በይፋ ይናገራሉ፤ኃጢአታቸውን ለመደበቅ አይሞክሩም። በራሳቸው ላይ ጥፋት ስለሚያመጡ ወዮላቸው!* 10  ለጻድቃን መልካም እንደሚሆንላቸው ንገሯቸው፤ለሥራቸው ወሮታ ይከፈላቸዋል።*+ 11  ለክፉ ሰው ወዮለት! ጥፋት ይደርስበታል፤በሌሎች ላይ ሲያደርግ የነበረው በራሱ ላይ ይደርሳልና! 12  የሕዝቤ አሠሪዎች ጨቋኞች ናቸው፤ሴቶችም ይገዟቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፣ የሚመሯችሁ ሰዎች እንድትባዝኑናበየትኛው መንገድ እንደምትሄዱ ግራ እንድትጋቡ እያደረጓችሁ ነው።+ 13  ይሖዋ ለመክሰስ ተሰይሟል፤በሕዝቦች ላይ ብያኔውን ለማሰማት ተነስቷል። 14  ይሖዋ የሕዝቡን ሽማግሌዎችና አለቆች ይፋረዳል። “የወይኑን እርሻ አቃጥላችኋል፤ከድሃው የዘረፋችሁት ንብረትም በቤታችሁ ይገኛል።+ 15  ሕዝቤን የምታደቁት፣ የድሆችንም ፊት መሬት ላይ የምትፈጩትእንዴት ብትዳፈሩ ነው?”+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 16  ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የጽዮን ሴቶች ልጆች ትዕቢተኛ ስለሆኑ፣ራሳቸውን ቀና አድርገው* ስለሚራመዱ፣በዓይናቸው እየተጣቀሱና እየተውረገረጉ በመሄድእግራቸው ላይ ያደረጉትን አልቦ ስለሚያቃጭሉ፣ 17  ይሖዋ የጽዮንን ሴቶች አናት በቁስል ይመታል፤ደግሞም ይሖዋ ግንባራቸውን ይገልጣል።+ 18  በዚያ ቀን ይሖዋ ጌጦቻቸውን ሁሉ ይነጥቃል፦አልቦውን፣ የፀጉር ጌጡን፣ የጨረቃ ቅርጽ ያለውን ጌጥ፣+ 19  የጆሮ ጉትቻውን፣* አምባሩን፣ መከናነቢያውን፣ 20  የራስ መሸፈኛውን፣ የሰንሰለት አልቦውን፣ ጌጠኛውን መቀነት፣*የሽቶ ዕቃውን፣* ክታቡን፣ 21  የጣት ቀለበቱን፣ የአፍንጫ ቀለበቱን፣ 22  የክት ልብሱን፣ መደረቢያውን፣ ካባውን፣ የእጅ ቦርሳውን፣ 23  የእጅ መስተዋቱን፣+ የበፍታ ልብሶቹን፣*ጥምጥሙንና መከናነቢያውን ይወስድባቸዋል። 24  በበለሳን ዘይት+ መዓዛ ፋንታ የጠነባ ሽታ፣በመታጠቂያ ፋንታ ገመድ፣አምሮ በተሠራ ፀጉር ፋንታ መላጣነት፣+ባማረ ልብስ ፋንታ ማቅ፣+በውበትም ፋንታ ጠባሳ* ይሆናል። 25  ወንዶችሽ በሰይፍ፣ኃያላኖችሽም በውጊያ ይወድቃሉ።+ 26  የከተማዋም መግቢያዎች ያዝናሉ፣ ያለቅሳሉም፤+እሷም ባዶዋን ቀርታ በሐዘን መሬት ላይ ትቀመጣለች።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ወላዋይ።”
ወይም “ፈዋሻችሁ አልሆንም።”
ቃል በቃል “በክብሩ ዓይኖች ፊት።”
ወይም “ለነፍሳቸው ወዮ!”
ቃል በቃል “የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉ።”
ቃል በቃል “አንገታቸውን (ጉሮሯቸውን) አስግገው።”
ወይም “ዶቃውን።”
ወይም “ድጉን።”
ቃል በቃል “የነፍስ ቤቶቹን።”
ወይም “የውስጥ ልብሶቹን።”
የአንድን ባሪያ ወይም እስረኛ ሰውነት በጋለ ብረት በመተኮስ የሚደረግን ምልክት ያመለክታል።