ኢሳይያስ 38:1-22

  • ሕዝቅያስ ከሕመሙ አገገመ (1-22)

    • የምስጋና መዝሙር (10-20)

38  በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ ነበር።+ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ+ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህ ስለማይቀር ለቤተሰብህ መመሪያ ስጥ።’”+  በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ ፊቱን ወደ ግድግዳው አዙሮ ወደ ይሖዋ መጸለይ ጀመረ፦  “እባክህ ይሖዋ ሆይ፣ በታማኝነትና በሙሉ ልብ+ በፊትህ እንዴት እንደተመላለስኩ እንዲሁም በዓይኖችህ ፊት መልካም የሆነውን ነገር እንዳደረግኩ እንድታስታውስ አጥብቄ እለምንሃለሁ።”+ ሕዝቅያስም ምርር ብሎ አለቀሰ።  ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኢሳይያስ መጣ፦  “ተመልሰህ ሄደህ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦+ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ።+ እንባህንም አይቻለሁ።+ እነሆ በዕድሜህ* ላይ 15 ዓመት እጨምርልሃለሁ፤+  አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ከተማዋንም እጠብቃታለሁ።+  ይሖዋ የተናገረውን ቃል እንደሚፈጽም የሚያሳየው ይሖዋ የሰጠህ ምልክት ይህ ነው፦+  በአካዝ ደረጃ* ላይ ወደ ታች የወረደውን የፀሐይ ጥላ ወደ ኋላ አሥር ደረጃ እንዲመለስ አደርገዋለሁ።”’”+ በመሆኑም ወደ ታች ወርዶ የነበረው የፀሐይ ጥላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ።  የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከሕመሙ ከዳነ በኋላ የጻፈው* ጽሑፍ፦ 10  እኔ “በዕድሜዬ አጋማሽ ላይወደ መቃብር* በሮች እገባለሁ። ቀሪውን የሕይወት ዘመኔን እነፈጋለሁ” አልኩ። 11  እንዲህም አልኩ፦ “በሕያዋን ምድር ያህን፣* አዎ ያህን አላይም። ሁሉም ነገር ከሕልውና ውጭ በሆነበት ስፍራ ከሚኖሩት ጋር በምሆንበት ጊዜየሰው ልጆችን አልመለከትም።+ 12  መኖሪያዬ ልክ እንደ እረኛ ድንኳንተነቅሎ ተወስዶብኛል።+ ሕይወቴን እንደ ሸማኔ ጠቀለልኩ፤ተሠርቶ ያለቀ ጨርቅ ከሽመና መሣሪያው ላይ እንደሚቆረጥ እኔንም ይቆርጠኛል። ከማለዳ አንስቶ እስከ ምሽት ድረስ ትጨርሰኛለህ።+ 13  እስከ ጠዋት ድረስ ራሴን አረጋጋለሁ። አጥንቶቼን ሁሉ እንደ አንበሳ ይሰባብራል፤ከማለዳ አንስቶ እስከ ምሽት ድረስ ትጨርሰኛለህ።+ 14  እንደ ወንጭፊት ወይም እንደ ጭሪ* እጮኻለሁ፤+እንደ ርግብ አልጎመጉማለሁ።+ ወደ ላይ ከመመልከቴ የተነሳ ዓይኖቼ ፈዘዙ፦+ ‘ይሖዋ ሆይ፣ እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ድጋፍ ሁነኝ!’*+ 15  እንግዲህ ምን ማለት እችላለሁ? እሱ አናግሮኛል፤ ምላሽም ሰጥቷል። ከደረሰብኝ አስከፊ ጭንቀት* የተነሳበሕይወት ዘመኔ ሁሉ በትሕትና* እመላለሳለሁ። 16  ‘ይሖዋ ሆይ፣ ሁሉም ሰው በእነዚህ ነገሮች* በሕይወት ይኖራል፤በእነሱም የእኔ መንፈስ በሕይወት ይኖራል። አንተ ጤናዬን ትመልስልኛለህ፤ በሕይወትም ታኖረኛለህ።+ 17  እነሆ፣ ሰላም ከማግኘት ይልቅ በጣም ተመርሬ ነበር፤አንተ ግን ለእኔ* ካለህ ፍቅር የተነሳ፣ከጥፋት ጉድጓድ ጠበቅከኝ።+ ኃጢአቴን ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልክ።*+ 18  መቃብር* ከፍ ከፍ ሊያደርግህ አይችልምና፤+ሞትም ሊያወድስህ አይችልም።+ ወደ ጉድጓድ የሚወርዱ በታማኝነትህ ተስፋ ሊያደርጉ አይችሉም።+ 19  እኔ ዛሬ እንደማደርገው፣አንተን ሊያወድስ የሚችለው ሕያው፣ አዎ ሕያው የሆነ ሰው ነው። አባት ለልጆቹ ስለ አንተ ታማኝነት እውቀት ሊያካፍላቸው ይችላል።+ 20  ይሖዋ ሆይ፣ አድነኝ፤በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በይሖዋ ቤት፣+በባለ አውታር መሣሪያዎች መዝሙሮቼን እንዘምራለን።’”+ 21  ከዚያም ኢሳይያስ “ሕመሙ እንዲሻለው የደረቀ የበለስ ጥፍጥፍ አምጡና እባጩ ላይ አድርጉለት” አለ።+ 22  ሕዝቅያስ “ወደ ይሖዋ ቤት እንደምወጣ ማወቅ የምችልበት ምልክት ምንድን ነው?” ብሎ ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በቀኖችህ።”
እነዚህ ደረጃዎች በፀሐይ ጥላ አማካኝነት ሰዓትን ለመቁጠር ያገለግሉ የነበረ ይመስላል።
ወይም “ያጠናቀረው።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ቃል በቃል “ዋስ ሁነኝ።”
“ቁርዬ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ከነፍሴ ምሬት።”
ወይም “በዝግታ።”
የአምላክን ቃልና ተግባር ያመለክታል።
ወይም “ኃጢአቴን ሁሉ ከእይታህ አስወገድክ።”
ወይም “ለነፍሴ።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።