ኢሳይያስ 57:1-21

  • ጻድቅ ሰውም ሆነ ታማኝ ሰዎች ይሞታሉ (1, 2)

  • እስራኤል የፈጸመችው መንፈሳዊ ምንዝር ተጋለጠ (3-13)

  • ለችግረኞች የተነገረ ማጽናኛ (14-21)

    • ክፉዎች የሚናወጥ ባሕር ናቸው (20)

    • “ክፉዎች ሰላም የላቸውም” (21)

57   ጻድቁ ሞቷል፤ይህን ግን ማንም ልብ አይልም። ታማኝ ሰዎች ተወስደዋል፤*+ሆኖም ጻድቁ የተወሰደውከመከራ የተነሳ እንደሆነ* የሚያስተውል የለም።   እሱ ሰላም ያገኛል። በቅንነት የሚሄዱ ሁሉ አልጋቸው* ላይ ያርፋሉ።   “ይሁንና እናንተ የአስማተኛዋ ወንዶች ልጆች፣የአመንዝራና የዝሙት አዳሪ ልጆች፣ኑ ወደዚህ ቅረቡ፦   የምታሾፉት በማን ላይ ነው? አፋችሁን የምትከፍቱትና ምላሳችሁን የምታወጡትስ በማን ላይ ነው? እናንተ የዓመፅ ልጆች፣የሐሰትም* ልጆች አይደላችሁም?+   በትላልቅ ዛፎች መካከል፣ቅጠሉ በተንዠረገገም ዛፍ ሥር ሁሉ በስሜት የተቃጠላችሁ፣+በሸለቆዎች* ውስጥ፣ በቋጥኞች መካከልልጆችን የምታርዱ አይደላችሁም?+   በሸለቆው* ውስጥ ያሉት ለስላሳ ድንጋዮች ድርሻዎችሽ ናቸው።+ አዎ፣ እነዚህ ዕጣ ፋንታዎችሽ ናቸው። ለእነሱም ጭምር የመጠጥ መባ አፍስሰሻል፤ ስጦታም አቅርበሻል።+ ታዲያ እኔ በእነዚህ ነገሮች ደስ ልሰኝ ይገባል?*   በረጅሙና ከፍ ባለው ተራራ ላይ አልጋሽን አነጠፍሽ፤+መሥዋዕት ለማቅረብም ወደዚያ ወጣሽ።+   ከበሩና ከመቃኑ ጀርባ የመታሰቢያ ምልክትሽን አደረግሽ። እኔን ተውሽኝ፤ እርቃንሽንም ገለጥሽ፤ወደ ላይ ወጣሽ፤ መኝታሽንም አሰፋሽ። ከእነሱም ጋር ቃል ኪዳን ገባሽ። በአልጋቸው ላይ አብረሽ መተኛት ወደድሽ፤+የወንድ ብልትም* አፍጥጠሽ አየሽ።   ዘይትና ብዛት ያለው ሽቶ ይዘሽወደ ሜሌክ* ወረድሽ። መልእክተኞችሽን ወደ ሩቅ ቦታ ላክሽ፤በመሆኑም ወደ መቃብር* ወረድሽ። 10  ብዛት ያላቸውን መንገዶችሽን በመከተል ደከምሽ፤ሆኖም ‘ተስፋ የለውም!’ አላልሽም። ጉልበትሽ ታደሰ። ተስፋ ያልቆረጥሽው* ለዚህ ነው። 11  መዋሸት የጀመርሽው+ ማን አስፈርቶሽ፣ማንስ ስጋት አሳድሮብሽ ነው? እኔን አላስታወስሽም።+ ልብ ያልሽውም ነገር የለም።+ እኔ ዝም አላልኩም? ደግሞስ ከመናገር አልተቆጠብኩም?*+ በመሆኑም እኔን አልፈራሽም። 12  ‘ጽድቅሽን’+ እና ሥራሽን+ እናገራለሁ፤እነሱም አይጠቅሙሽም።+ 13  እርዳታ ለማግኘት በምትጮኺበት ጊዜየሰበሰብሻቸው ጣዖቶች አይታደጉሽም።+ ነፋስ ሁሉንም ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤እስትንፋስ ይዟቸው ይሄዳል፤እኔን መጠጊያ የሚያደርግ ግን ምድሪቱን ይወርሳል፤ቅዱስ ተራራዬም ርስቱ ይሆናል።+ 14  እንዲህ ይባላል፦ ‘መንገድ ሥሩ! መንገድ ሥሩ! መንገዱን አዘጋጁ!+ ሕዝቤ ከሚሄድበት መንገድ ላይ ማንኛውንም እንቅፋት አስወግዱ።’” 15  ለዘላለም የሚኖረውና+ ስሙ ቅዱስ የሆነው፣+ከፍ ከፍ ያለውና እጅግ የከበረው እንዲህ ይላልና፦ “ከፍ ባለውና ቅዱስ በሆነው ስፍራ እኖራለሁ፤+ደግሞም የተሰበረ ልብ ካለውና መንፈሱ ከተደቆሰው ጋር እሆናለሁ፤ይህም የችግረኞችን መንፈስ አነሳሳ ዘንድ፣የተሰበረ ልብ ያላቸውንም አነቃቃ ዘንድ ነው።+ 16  ለዘላለም አልቃወማቸውም፤ወይም ለዘለቄታው አልቆጣም፤+በእኔ የተነሳ የሰው መንፈስ፣እኔ የሠራኋቸው እስትንፋስ ያላቸው ፍጥረታትም እንኳ ይዝላሉና።+ 17  በማጭበርበር ጥቅም ለማግኘት ሲል በፈጸመው ኃጢአት እጅግ ተቆጣሁ፤+በመሆኑም መታሁት፤ ፊቴን ሰወርኩ፤ ተቆጣሁም። እሱ ግን እንደ ከዳተኛ የልቡን መንገድ ተከትሎ መሄዱን ገፋበት።+ 18  መንገዶቹን አይቻለሁ፤ሆኖም እፈውሰዋለሁ፤+ እንዲሁም እመራዋለሁ፤+ለእሱም ሆነ ላዘኑ ወገኖቹ መጽናኛን እመልሳለሁ።”*+ 19  “የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ። በሩቅም ሆነ በቅርብ ያለው ዘላቂ ሰላም ያገኛል፤+እኔም እፈውሰዋለሁ” ይላል ይሖዋ። 20  “ክፉዎች ግን ጸጥ ማለት እንደማይችል የሚናወጥ ባሕር ናቸው፤ውኃውም የባሕር ውስጥ ዕፀዋትንና ጭቃን ያወጣል። 21  ክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል አምላኬ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ከመከራ እንዲተርፍ መሆኑን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
መሞትን ያመለክታል።
መቃብርን ያመለክታል።
ወይም “የማታለልም።”
ወይም “በደረቅ ወንዞች።”
ወይም “ራሴን ላጽናና ይገባል?”
ወይም “በደረቁ ወንዝ።”
የጣዖት አምልኮን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
“ወደ ንጉሡ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ያልዛልሽው።”
ወይም “ነገሮችን አልደበቅኩም?”
ወይም “እሱንም ሆነ ያዘኑ ወገኖቹን በማጽናናት እክሳቸዋለሁ።”