ኢሳይያስ 17:1-14

  • በደማስቆ ላይ የተላለፈ ፍርድ (1-11)

  • ይሖዋ ብሔራትን ይገሥጻቸዋል (12-14)

17  በደማስቆ ላይ የተላለፈ ፍርድ፦+ “እነሆ፣ ደማስቆ ከተማ መሆኗ ይቀራል፤የፍርስራሽ ክምርም ትሆናለች።+   የአሮዔር+ ከተሞች ወና ይሆናሉ፤የመንጎች ማረፊያ ይሆናሉ፤የሚያስፈራቸውም አይኖርም።   የተመሸጉ ከተሞች ከኤፍሬም፣+መንግሥትም ከደማስቆ ይወገዳል፤+የተረፉት የሶርያ ሰዎች ክብርምልክ እንደ እስራኤላውያን ክብር ይጠፋል” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።   “በዚያን ቀን የያዕቆብ ክብር ይከስማል፤ጤናማ የሆነው ሰውነቱም* ይከሳል።   አጫጁ በማሳ ውስጥ ያለውን እህል በሚሰበስብበትናበእጁ ዛላውን በሚቆርጥበት ጊዜ እንደሚሆነው፣ደግሞም ሰው በረፋይም ሸለቆ*+ እህል በሚቃርምበት ጊዜ እንደሚሆነው እንዲሁ ይሆናል።   የወይራ ዛፍ ሲመታከፍ ባለው ቅርንጫፍ ላይ ሁለት ወይም ሦስት የወይራ ፍሬዎች ብቻ፣ ፍሬ በሚይዙት ቅርንጫፎችም ላይ አራት ወይም አምስት ፍሬዎች ብቻ እንደሚቀሩ፣በእሱም ላይ ቃርሚያ ብቻ ይቀራል”+ ይላል የእስራኤል አምላክ ይሖዋ።  በዚያም ቀን ሰው ወደ ሠሪው ይመለከታል፤ ዓይኖቹም የእስራኤልን ቅዱስ ትኩር ብለው ያያሉ።  የእጁ ሥራ+ ወደሆኑት መሠዊያዎች አይመለከትም፤+ ጣቶቹ የሠሯቸውን የማምለኪያ ግንዶችም* ሆነ የዕጣን ማጨሻዎች አተኩሮ አያይም።   በዚያም ቀን፣ የተመሸጉ ከተሞቹ በጫካ እንዳለ የተተወ ቦታ፣+በእስራኤላውያን ዘንድ እንደተተወ ቅርንጫፍ ይሆናሉ፤ቦታው ጠፍ መሬት ይሆናል። 10  አንቺ፣* አዳኝ አምላክሽን ረስተሻልና፤+መሸሸጊያ ዓለትሽንም+ አላስታወስሽም። ያማሩ ተክሎችን ያለማሽውናበመካከሉም የባዕድ* ቡቃያ የተከልሽው ለዚህ ነው። 11  በቀን በተክሎችሽ ዙሪያ አጥር ትሠሪያለሽ፤በማለዳም ዘርሽ እንዲበቅል ታደርጊያለሽ፤ይሁን እንጂ በበሽታና በማይሽር ሕመም ቀን አዝመራው ይጠፋል።+ 12  አዳምጡ! እንደሚናወጥ ባሕር ያለየብዙ ሕዝቦች ትርምስ ይሰማል! እንደ ኃይለኛ ውኃዎች ድምፅ ያለየሚያስገመግም የብሔራት ጫጫታ ይሰማል! 13  ብሔራት እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ ያለ የሚያስገመግም ድምፅ ያሰማሉ። እሱ ይገሥጻቸዋል፤ እነሱም ወደ ሩቅ ቦታ ይሸሻሉ፤በተራራ ላይ እንዳለ በነፋስ እንደሚበን ገለባናአውሎ ነፋስ እያሽከረከረ እንደሚወስደው ኮሸሽላ ይሆናሉ። 14  ሲመሽ ሽብር ይነግሣል። ከመንጋቱም በፊት በዚያ አንዳቸውም አይገኙም። የዘረፉን ሰዎች ድርሻ፣የበዘበዙንም ሰዎች ዕጣ ይህ ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የሥጋውም ውፍረት።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ኢየሩሳሌምን ያመለክታል።
ወይም “የእንግዳ አምላክ።”