ኢሳይያስ 58:1-14

  • እውነተኛ ጾምና የይስሙላ ጾም (1-12)

  • ሰንበትን በማክበር መደሰት (13, 14)

58  “ጉሮሮህ እስኪሰነጠቅ ጩኽ፤ ምንም አትቆጥብ! ድምፅህን እንደ ቀንደ መለከት አሰማ። ለሕዝቤ ዓመፃቸውን፣ለያዕቆብ ቤት ኃጢአታቸውን አውጅ።+   እነሱ በየዕለቱ እኔን ይፈልጉኛል፤ጽድቅ ይሠራ የነበረ፣የአምላኩንም ፍትሕ ያልተወ ብሔር የሆኑ ይመስል+መንገዶቼን ማወቅ ደስ እንደሚያሰኛቸው ይገልጻሉ። በጽድቅ እንድፈርድላቸው ይጠይቃሉ፤ወደ አምላክ መቅረብ ደስ ያሰኛቸዋል፦+   ‘ስንጾም የማታየው ለምንድን ነው?+ ራሳችንን* ስናጎሳቁል የማታስተውለውስ ለምንድን ነው?’+ በምትጾሙበት ቀን የራሳችሁን ጥቅም* ስለምታሳድዱናሠራተኞቻችሁን ስለምትጨቁኑ ነው።+   ጾማችሁ በጭቅጭቅና በጥል ያበቃል፤እንዲሁም ያለርኅራኄ በቡጢ ትማታላችሁ። ዛሬ እንደምትጾሙት እየጾማችሁ ድምፃችሁ በሰማይ ሊሰማ አይችልም።   እኔ የመረጥኩት ጾም እንዲህ ሊሆን ይገባል?ሰው ራሱን* የሚያጎሳቁልበት፣እንደ እንግጫ ራሱን የሚደፋበት፣መኝታውን በማቅና በአመድ ላይ የሚያነጥፍበት ቀን መሆን አለበት? እናንተ ጾም የምትሉት፣ ይሖዋንም ደስ የሚያሰኝ ቀን ብላችሁ የምትጠሩት ይህን ነው?   አይደለም፤ እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነው፦ የክፋትን የእግር ብረት እንድታስወግዱ፣የቀንበርን ማሰሪያ እንድትፈቱ፣+የተጨቆኑትን በነፃ እንድትለቁ፣+ቀንበርንም ሁሉ እንድትሰብሩ ነው፤   ምግብህን ለተራበው እንድታካፍል፣+ድሆችንና ቤት የሌላቸውን ወደ ቤትህ እንድታስገባ፣የተራቆተ ሰው ስታይ እንድታለብስ፣+ለሥጋ ዘመድህም ጀርባህን እንዳትሰጥ ነው።   በዚህ ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ጮራ ይፈነጥቃል፤+ፈውስህም ፈጥኖ ይመጣል። ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፤የይሖዋም ክብር ደጀን ይሆንልሃል።+   የዚያን ጊዜ ትጣራለህ፤ ይሖዋም ይመልስልሃል፤እርዳታ ለማግኘት ትጮኻለህ፤ እሱም ‘አለሁልህ!’ ይልሃል። ከመካከልህ ቀንበሩን ብታስወግድእንዲሁም ጣትህን መቀሰርና ተንኮል ያዘለ ንግግር መናገር ብትተው፣+ 10  ለተራበው ሰው አንተ ራስህ* የምትፈልገውን ነገር ብታደርግለት፣+የተጎሳቆሉትንም ብታረካ፣*ያን ጊዜ ብርሃንህ በጨለማ እንኳ ቦግ ብሎ ይበራል፤ጨለማህም እንደ ቀትር ብርሃን ይሆናል።+ 11  ይሖዋ ምንጊዜም ይመራሃል፤ደረቅ በሆነ ምድርም እንኳ ፍላጎትህን ያረካል፤*+አጥንቶችህን ያበረታል፤አንተም ውኃ እንደሚጠግብ የአትክልት ቦታናውኃው እንደማይቋረጥ ምንጭ ትሆናለህ።+ 12  ከአንተም የተነሳ የጥንቶቹን ፍርስራሾች መልሰው ይገነባሉ፤+ያለፉትን ትውልዶች መሠረቶች ታድሳለህ።+ አንተም የፈረሱትን* ግንቦች የሚያድስ፣በመኖሪያ ቦታዎች አካባቢ የሚገኙ ጎዳናዎችን የሚጠግን ተብለህ ትጠራለህ።+ 13  ሰንበትን በማክበር በተቀደሰው ቀኔ የራስህን ጥቅም* ከማሳደድ ብትቆጠብ፣*+ሰንበትንም ሐሴት፣ የተቀደሰ የይሖዋ ቀንና ሊከበር የሚገባው ቀን ብለህ ብትጠራው+እንዲሁም የራስህን ጥቅም ከማሳደድና ከንቱ ቃል ከመናገር ይልቅ ብታከብረው፣ 14  ያን ጊዜ በይሖዋ ሐሴት ታደርጋለህ፤ደግሞም በምድር ከፍ ያሉ ቦታዎች ላይ እንድትጋልብ አደርግሃለሁ።+ ከአባትህ ከያዕቆብ ርስት አበላሃለሁ፤*+የይሖዋ አፍ ተናግሯልና።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነፍሳችንን።”
ወይም “ደስታ።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “የተጎሳቆሉትንም ነፍሳት ብታረካ።”
ወይም “የገዛ ነፍስህ።”
ወይም “ነፍስህን ያረካል።”
ቃል በቃል “ክፍተት ያላቸውን።”
ወይም “ደስ የሚያሰኝህን።”
ቃል በቃል “እግርህን ብትመልስ።”
ወይም “በአባትህ በያዕቆብ ርስት እንድትደሰት አደርጋለሁ።”