ዘፍጥረት 16:1-16

  • አጋርና እስማኤል (1-16)

16  የአብራም ሚስት ሦራ ለአብራም ልጆች አልወለደችለትም ነበር፤+ ይሁንና አጋር+ የምትባል አንዲት ግብፃዊት አገልጋይ ነበረቻት።  በመሆኑም ሦራ አብራምን እንዲህ አለችው፦ “እንግዲህ እንደምታየው ይሖዋ ልጆች እንዳልወልድ አድርጎኛል። እባክህ ከአገልጋዬ ጋር ግንኙነት ፈጽም። ምናልባትም በእሷ አማካኝነት ልጆች ላገኝ እችላለሁ።”+ ስለሆነም አብራም የሦራን ቃል ሰማ።  አብራም በከነአን ምድር ለአሥር ዓመት ያህል ከኖረ በኋላ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት አገልጋይዋን አጋርን ወስዳ ሚስት እንድትሆነው ለባሏ ለአብራም ሰጠችው።  በመሆኑም አብራም ከአጋር ጋር ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ፀነሰች። መፀነሷን ባወቀች ጊዜም እመቤቷን መናቅ ጀመረች።  በዚህ ጊዜ ሦራ አብራምን እንዲህ አለችው፦ “ለደረሰብኝ በደል ተጠያቂው አንተ ነህ። አገልጋዬን በእቅፍህ ያደረግኩልህ እኔው ራሴ ነበርኩ፤ እሷ ግን መፀነሷን ባወቀች ጊዜ ትንቀኝ ጀመር። ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ።”  በመሆኑም አብራም ሦራን “እንግዲህ አገልጋይሽ እንደሆነች በእጅሽ ናት። መልካም መስሎ የታየሽን ነገር አድርጊባት” አላት። ከዚያም ሦራ አገልጋይዋን አዋረደቻት፤ ስለዚህም ጥላት ኮበለለች።  በኋላም የይሖዋ መልአክ አጋርን በምድረ በዳ በሚገኝ አንድ የውኃ ምንጭ አጠገብ ማለትም ወደ ሹር+ በሚወስደው መንገድ ላይ ባለው ምንጭ አጠገብ አገኛት።  እሱም “የሦራ አገልጋይ አጋር፣ ለመሆኑ የመጣሽው ከየት ነው? ወዴትስ እየሄድሽ ነው?” አላት። እሷም መልሳ “ከእመቤቴ ከሦራ ኮብልዬ እየሄድኩ ነው” አለች።  የይሖዋም መልአክ “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለእሷም በትሕትና ተገዢላት” አላት። 10  ከዚያም የይሖዋ መልአክ “ከብዛቱ የተነሳ የማይቆጠር እስኪሆን ድረስ ዘርሽን እጅግ አበዛዋለሁ”+ አላት። 11  በተጨማሪም የይሖዋ መልአክ እንዲህ አላት፦ “እንግዲህ ይኸው ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ። ስሙንም እስማኤል* ትይዋለሽ፤ ምክንያቱም ይሖዋ የሥቃይ ጩኸትሽን ሰምቷል። 12  እሱም እንደ ዱር አህያ* ይሆናል። ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ እጁን ያነሳል፤ ያገኘውም ሰው ሁሉ እጁን ያነሳበታል፤ ከወንድሞቹም ሁሉ ፊት ለፊት ይኖራል።”* 13  ከዚያም አጋር “የሚያየኝን አሁን በእርግጥ አየሁት ማለት ነው?” ብላ ስላሰበች እያነጋገራት የነበረውን ይሖዋን ስሙን ጠርታ “አንተ የምታይ አምላክ ነህ”+ አለች። 14  የውኃ ጉድጓዱ ብኤርላሃይሮዒ* ተብሎ የተጠራው በዚህ የተነሳ ነው። (ጉድጓዱም በቃዴስና በቤሬድ መካከል ይገኛል።) 15  ስለዚህ አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ አብራምም አጋር የወለደችለትን ልጅ እስማኤል+ ብሎ ስም አወጣለት። 16  አጋር ለአብራም እስማኤልን በወለደችለት ጊዜ አብራም የ86 ዓመት ሰው ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“አምላክ ይሰማል” የሚል ትርጉም አለው።
እዚህ ላይ የተጠቀሰው እንስሳ አንዳንዶች የሜዳ አህያ እንደሆነ አድርገው ቢያስቡም የዱር አህያ ዝርያ ነው። ይህም በራስ የመመራት ባሕርይን ለማመልከት የገባ ሳይሆን አይቀርም።
“ከወንድሞቹ ሁሉ ጋር በጠላትነት ይኖራል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“የሚያየኝ ሕያው አምላክ የውኃ ጉድጓድ” የሚል ትርጉም አለው።