ዘፍጥረት 31:1-55

  • ያዕቆብ በድብቅ ወደ ከነአን ኮበለለ (1-18)

  • ላባ ያዕቆብን ተከታትሎ ደረሰበት (19-35)

  • ያዕቆብ ከላባ ጋር የገባው ቃል ኪዳን (36-55)

31  ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ፣ የላባ ልጆች “ያዕቆብ የአባታችንን ንብረት እንዳለ ወስዷል፤ ይህን ሁሉ ሀብት ያካበተው እኮ ከአባታችን ንብረት ነው”+ ሲሉ ሰማ።  ያዕቆብ የላባን ፊት ሲመለከት ፊቱ እንደተለወጠበት አስተዋለ።+  በመጨረሻም ይሖዋ ያዕቆብን “ወደ አባቶችህና ወደ ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤+ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” አለው።  ከዚያም ያዕቆብ ራሔልና ሊያ መንጎቹን ወዳሰማራበት መስክ እንዲመጡ መልእክት ላከባቸው፤  እንዲህም አላቸው፦ “አባታችሁን ሳየው ፊቱ ተለውጦብኛል፤+ የአባቴ አምላክ ግን ከእኔ አልተለየም።+  መቼም አባታችሁን ባለኝ አቅም ሁሉ እንዳገለገልኩት እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ።+  አባታችሁ ሊያጭበረብረኝ ሞክሯል፤ ደሞዜንም አሥር ጊዜ ቀያይሮብኛል፤ አምላክ ግን ጉዳት እንዲያደርስብኝ አልፈቀደለትም።  ‘ደሞዝህ ዥጉርጉር የሆኑት ይሆናሉ’ ሲለኝ መንጎቹ ሁሉ ዥጉርጉር ወለዱ፤ ‘ደሞዝህ ሽንትር ያለባቸው ይሆናሉ’ ሲለኝ ደግሞ መንጎቹ ሁሉ ሽንትር ያለባቸው ወለዱ።+  ስለዚህ አምላክ የአባታችሁን ከብቶች ከእሱ እየወሰደ ለእኔ ይሰጠኝ ነበር። 10  በአንድ ወቅት፣ መንጎቹ ለስሪያ በሚነሳሱበት ጊዜ እንስቶቹን የሚያጠቁት አውራ ፍየሎች ሽንትር ያለባቸው፣ ዥጉርጉር የሆኑና ጠቃጠቆ ያለባቸው መሆናቸውን በሕልሜ አየሁ።+ 11  ከዚያም የእውነተኛው አምላክ መልአክ በሕልሜ ‘ያዕቆብ!’ ሲል ጠራኝ፤ እኔም ‘አቤት’ አልኩት። 12  እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘እንስቶቹን የሚያጠቁት አውራ ፍየሎች ሁሉ ሽንትር ያለባቸው፣ ዥጉርጉር የሆኑና ጠቃጠቆ ያለባቸው መሆናቸውን እባክህ ቀና ብለህ ተመልከት፤ ምክንያቱም ላባ እየፈጸመብህ ያለውን ነገር ሁሉ ተመልክቻለሁ።+ 13  ዓምድ አቁመህ የቀባህበትና በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልክበት የቤቴል+ እውነተኛው አምላክ እኔ ነኝ።+ በል አሁን ተነስተህ ከዚህ ምድር ውጣ፤ ወደተወለድክበትም ምድር ተመለስ።’”+ 14  በዚህ ጊዜ ራሔልና ሊያ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “እንደው ለመሆኑ በአባታችን ቤት ልንወርሰው የምንችለው የቀረ ነገር ይኖራል? 15  እሱ እኛን የሸጠንና ለእኛ የተሰጠውን ገንዘብ የበላው እንደ ባዕድ ስለሚያየን አይደለም?+ 16  አምላክ ከአባታችን ላይ የወሰደበት ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው።+ ስለሆነም አምላክ አድርግ ያለህን ነገር ሁሉ አድርግ።”+ 17  ከዚያም ያዕቆብ ተነሳ፤ ልጆቹንና ሚስቶቹን ግመል ላይ አስቀመጣቸው፤+ 18  እንዲሁም መንጎቹን ሁሉና ያከማቸውን ንብረት ሁሉ፣+ በጳዳንአራም ሳለ ያገኛቸውንም ከብቶች ሁሉ እየነዳ በከነአን ምድር ወደሚገኘው ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ለመሄድ ጉዞ ጀመረ።+ 19  በዚህ ጊዜ ላባ በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፤ ራሔልም የአባቷን+ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾች*+ ሰረቀች። 20  ያዕቆብም ቢሆን ለአራማዊው ለላባ ሳይነግረው ሊኮበልል በመነሳቱ አታሎታል። 21  ያዕቆብም ያለውን ሁሉ ይዞ ኮበለለ፤ ወንዙንም*+ ተሻግሮ ሄደ። ከዚያም ጊልያድ+ ወደተባለው ተራራማ አካባቢ አቀና። 22  በሦስተኛውም ቀን የያዕቆብ መኮብለል ለላባ ተነገረው። 23  በመሆኑም ላባ ያዕቆብ ላይ ለመድረስ ወንድሞቹን* አስከትሎ የሰባት ቀን መንገድ ተጓዘ፤ ከዚያም ጊልያድ በተባለው ተራራማ አካባቢ ደረሰበት። 24  ከዚያም አምላክ ለአራማዊው+ ለላባ ሌሊት በሕልም ተገልጦለት+ “ክፉም ሆነ ደግ ያዕቆብን ስለምትናገረው ነገር ተጠንቀቅ”* አለው።+ 25  ያዕቆብ በተራራው ላይ ድንኳኑን ተክሎ ሳለ ላባ ወደ ያዕቆብ ቀረበ፤ ላባም ከወንድሞቹ ጋር ጊልያድ በተባለው ተራራማ አካባቢ ሰፈረ። 26  ከዚያም ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግከው ነገር ምንድን ነው? እኔን ለማታለል የተነሳሳኸውና ሴት ልጆቼን በሰይፍ እንደተማረከ ምርኮኛ አስገድደህ የወሰድካቸው ለምንድን ነው? 27  ምንም ሳትነግረኝ ተደብቀህ የሸሸኸውና ያታለልከኝስ ለምንድን ነው? ነግረኸኝ ቢሆን ኖሮ በደስታና በዘፈን፣ በአታሞና በበገና እሸኝህ ነበር። 28  አንተ ግን የልጅ ልጆቼንና* ሴቶች ልጆቼን ስሜ እንድሰናበት እንኳ ዕድል አልሰጠኸኝም። የሠራኸው የሞኝነት ሥራ ነው። 29  እናንተን መጉዳት እችል ነበር፤ ሆኖም ትናንት ሌሊት የአባታችሁ አምላክ ‘ክፉም ሆነ ደግ ያዕቆብን ስለምትናገረው ነገር ተጠንቀቅ’ አለኝ።+ 30  እሺ፣ አንተ ለመሄድ የተነሳኸው ወደ አባትህ ቤት ለመመለስ ስለናፈቅክ ነው፤ ሆኖም አማልክቴን+ የሰረቅከው ለምንድን ነው?” 31  ያዕቆብ ለላባ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እንዲህ ያደረግኩት ‘ሴቶች ልጆችህን በኃይል ነጥቀህ ታስቀርብኛለህ’ ብዬ ስለፈራሁ ነው። 32  አማልክትህን ያገኘህበት ማንኛውም ሰው ይገደል። በወንድሞቻችን ፊት ንብረቴን ፈትሽና የእኔ ነው የምትለውን ውሰድ።” ይሁንና ያዕቆብ ራሔል ጣዖቶቹን እንደሰረቀች አላወቀም ነበር። 33  በመሆኑም ላባ ወደ ያዕቆብ ድንኳን ገባ፤ ከዚያም ወደ ሊያ ድንኳን እንዲሁም ወደ ሁለቱ ሴት ባሪያዎች+ ድንኳን ገባ፤ ሆኖም ምንም አላገኘም። ከዚያም ከሊያ ድንኳን ወጥቶ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ። 34  በዚህ ጊዜ ራሔል የተራፊም ቅርጻ ቅርጾቹን በግመል ኮርቻ ላይ በሚገኘው የሴቶች ዕቃ ማስቀመጫ ውስጥ ከትታ በላያቸው ላይ ተቀምጣ ነበር። በመሆኑም ላባ ድንኳኑን በሙሉ በረበረ፤ ሆኖም ምንም አላገኘም። 35  ከዚያም ራሔል አባቷን “ጌታዬ፣ ስላልተነሳሁልህ አትቆጣ፤ የሴቶች ልማድ+ ደርሶብኝ ነው” አለችው። ስለዚህ ላባ በጥንቃቄ ፈተሸ፤ ይሁንና የተራፊም ቅርጻ ቅርጾቹን+ አላገኘም። 36  በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ተቆጣ፤ ላባንም ወቀሰው። ከዚያም ላባን እንዲህ አለው፦ “እስቲ የፈጸምኩት በደል ምንድን ነው? እንደዚህ በቁጣ ገንፍለህ የምታሳድደኝ ምን ኃጢአት ሠርቼ ነው? 37  ይኸው ዕቃዬን ሁሉ ፈትሸሃል፤ ታዲያ የቤትህ ንብረት የሆነ ምን ነገር አገኘህ? እስቲ በወንድሞቼና በወንድሞችህ ፊት አስቀምጠውና እነሱ በሁለታችን መካከል ይፍረዱ። 38  ከአንተ ጋር አብሬ በኖርኩባቸው በእነዚህ 20 ዓመታት ውስጥ በጎችህና ፍየሎችህ ጨንግፈው አያውቁም፤+ እኔም ከመንጋህ መካከል አንዲት በግ እንኳ አልበላሁም። 39  አውሬ የቦጫጨቀውን እንስሳ+ አምጥቼልህ አላውቅም። ኪሳራውን በራሴ ላይ ቆጥሬ እከፍልህ ነበር። በቀንም ይሁን በሌሊት አንድ እንስሳ ቢሰረቅ ታስከፍለኝ ነበር። 40  ቀን በሐሩር፣ ሌሊት ደግሞ በቁር ስሠቃይ ኖሬአለሁ፤ እንቅልፍም በዓይኔ አይዞርም ነበር።+ 41  እንግዲህ 20 ዓመት ሙሉ በቤትህ የኖርኩት በዚህ ሁኔታ ነበር። ለሁለት ሴቶች ልጆችህ ስል 14 ዓመት፣ ለመንጋህ ስል ደግሞ 6 ዓመት አገለገልኩህ። አንተ ግን ደሞዜን አሥር ጊዜ ትቀያይርብኝ ነበር።+ 42  የአባቴ አምላክ፣+ የአብርሃም አምላክና ይስሐቅ የሚፈራው አምላክ*+ ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ ባዶ እጄን ታሰናብተኝ ነበር። አምላክ ጉስቁልናዬንና ልፋቴን አየ፤ ትናንት ሌሊት የገሠጸህም ለዚህ ነው።”+ 43  ከዚያም ላባ ለያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ሴቶቹ የገዛ ልጆቼ ናቸው፤ ልጆቹም ቢሆኑ ልጆቼ ናቸው፤ መንጋውም ቢሆን የእኔው መንጋ ነው፤ የምታየው ነገር ሁሉ የእኔና የሴት ልጆቼ ነው። ታዲያ ዛሬ በእነዚህም ሆነ በወለዷቸው ልጆቻቸው ላይ ምን ማድረግ እችላለሁ? 44  በል አሁን ና፣ እኔና አንተ ቃል ኪዳን እንጋባ፤ ይህም በእኔና በአንተ መካከል ምሥክር ሆኖ ያገለግላል።” 45  ስለዚህ ያዕቆብ ድንጋይ ወስዶ እንደ ዓምድ አቆመው።+ 46  ከዚያም ያዕቆብ ወንድሞቹን “ድንጋይ ሰብስቡ!” አላቸው። እነሱም ድንጋይ እያመጡ ከመሩ። በኋላም እዚያው ድንጋዩ ክምር ላይ በሉ። 47  ላባም የድንጋዩን ክምር ያጋርሳሃዱታ* አለው፤ ያዕቆብ ግን ጋልኢድ* ሲል ጠራው። 48  ከዚያም ላባ “ይህ የድንጋይ ክምር ዛሬ በእኔና በአንተ መካከል ምሥክር ነው” አለ። ከዚህም የተነሳ ያዕቆብ ጋልኢድ+ 49  እና መጠበቂያ ግንብ የሚል ስም አወጣለት፤ ምክንያቱም ላባ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እርስ በርስ በማንተያይበት ጊዜ ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ጠባቂ ይሁን። 50  ልጆቼን ብትበድላቸውና በእነሱ ላይ ሌሎች ሚስቶችን ብታገባ ማንም ሰው ባያይም እንኳ አምላክ በእኔና በአንተ መካከል ምሥክር እንደሆነ አትርሳ።” 51  ላባም ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “የድንጋይ ክምሩ ይኸው፤ በእኔና በአንተ መካከል ያቆምኩት ዓምድም ይኸው። 52  እኔ አንተን ለመጉዳት ይህን የድንጋይ ክምር አልፌ ላልመጣ፣ አንተም እኔን ለመጉዳት ይህን የድንጋይ ክምርና ይህን ዓምድ አልፈህ ላትመጣ ይህ የድንጋይ ክምር ምሥክር ነው፤+ ዓምዱም ቢሆን ምሥክር ይሆናል። 53   የአብርሃም አምላክና*+ የናኮር አምላክ የሆነው የአባታቸው አምላክ በእኛ መካከል ይፍረድ።” ያዕቆብም አባቱ ይስሐቅ በሚፈራው አምላክ*+ ማለ። 54  ከዚያ በኋላ ያዕቆብ በተራራው ላይ መሥዋዕት አቀረበ። ወንድሞቹንም ምግብ እንዲበሉ ጋበዛቸው። እነሱም ምግብ በሉ፤ በተራራውም ላይ አደሩ። 55  ላባም በማግስቱ ጠዋት ተነስቶ የልጅ ልጆቹንና*+ ሴቶች ልጆቹን ስሞ መረቃቸው።+ ተነስቶም ወደ ቤቱ ተመለሰ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የቤት ውስጥ አማልክት፤ ጣዖታት።”
ኤፍራጥስ ወንዝን ያመለክታል።
ወይም “ዘመዶቹን።”
ቃል በቃል “ከያዕቆብ ጋር ከደግ እስከ ክፉ እንዳትነጋገር ተጠንቀቅ።”
ቃል በቃል “ወንዶች ልጆቼንና።”
ቃል በቃል “የይስሐቅ ፍርሃት።”
“የምሥክር ክምር” የሚል ትርጉም ያለው የአራማውያን አባባል ነው።
“የምሥክር ክምር” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ አባባል ነው።
ሶርያዊው ላባ በተራፊሞች ያምን ስለነበር እዚህ ላይ የተጠቀሰው ቃል ‘አማልክትን’ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በአባቱ በይስሐቅ ፍርሃት።”
ቃል በቃል “ወንዶች ልጆቹንና።”