ዘፍጥረት 42:1-38

  • የዮሴፍ ወንድሞች ወደ ግብፅ ሄዱ (1-4)

  • ዮሴፍ ከወንድሞቹ ጋር ተገናኘ፤ እንዲሁም ፈተናቸው (5-25)

  • የዮሴፍ ወንድሞች ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ተመለሱ (26-38)

42  ያዕቆብ በግብፅ እህል መኖሩን+ ባወቀ ጊዜ ወንዶች ልጆቹን “ለምን ዝም ብላችሁ እርስ በርስ ትተያያላችሁ?” አላቸው።  ከዚያም “በግብፅ እህል እንዳለ ሰምቻለሁ። በሕይወት እንድንኖር ወደዚያ ወርዳችሁ እህል ግዙልን፤ አለዚያ ማለቃችን ነው” አላቸው።+  ስለሆነም አሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች+ እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ወረዱ።  ሆኖም ያዕቆብ የዮሴፍን ወንድም ቢንያምን+ “ምናልባት አደጋ ሊደርስበትና ሊሞትብኝ ይችላል” ብሎ ስላሰበ ከሌሎቹ ወንድሞቹ ጋር አላከውም።+  ረሃቡ እስከ ከነአን ምድር ድረስ ተስፋፍቶ ስለነበር የእስራኤል ወንዶች ልጆች እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ከሚመጡት ሰዎች ጋር አብረው መጡ።+  በዚያን ጊዜ በምድሩ ላይ አስተዳዳሪ የነበረውና+ ለምድር ሕዝቦች ሁሉ እህል የሚሸጠው ዮሴፍ ነበር።+ በመሆኑም የዮሴፍ ወንድሞች መጥተው መሬት ላይ በመደፋት ሰገዱለት።+  ዮሴፍም ወንድሞቹን ሲያያቸው ወዲያውኑ አወቃቸው፤ እሱ ግን ማንነቱን ከእነሱ ደበቀ።+ በመሆኑም “የመጣችሁት ከየት ነው?” በማለት በቁጣ ተናገራቸው፤ እነሱም “እህል ለመግዛት ከከነአን ምድር ነው የመጣነው” አሉት።+  ዮሴፍ ወንድሞቹን ያወቃቸው ቢሆንም እነሱ ግን አላወቁትም።  ዮሴፍም ስለ እነሱ ያያቸው ሕልሞች ወዲያው ትዝ አሉት፤+ እሱም “እናንተ ሰላዮች ናችሁ! የመጣችሁት ምድሪቱ በየት በኩል ለጥቃት እንደተጋለጠች* ለማየት ነው!” አላቸው። 10  እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ኧረ እንደዚያ አይደለም ጌታዬ፤ እኛ አገልጋዮችህ የመጣነው እህል ለመግዛት ነው። 11  ሁላችንም የአንድ ሰው ልጆች ነን። እኛ ንጹሐን ሰዎች ነን። አገልጋዮችህ ሰላዮች አይደለንም።” 12  እሱ ግን “በፍጹም አይደለም! የመጣችሁት ምድሪቱ በየት በኩል ለጥቃት እንደተጋለጠች ለማየት ነው!” አላቸው። 13  በዚህ ጊዜ እንዲህ አሉት፦ “እኛ አገልጋዮችህ 12 ወንድማማቾች ነን።+ በከነአን ምድር የሚኖር የአንድ ሰው ልጆች ነን፤+ ትንሹ ወንድማችን አሁን ከአባታችን ጋር ነው፤+ አንደኛው ግን የለም።”+ 14  ይሁን እንጂ ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፦ “‘እናንተ ሰላዮች ናችሁ!’ አልኳችሁ እኮ፤ 15  እንግዲህ ሰላዮች መሆን አለመሆናችሁ በዚህ ይረጋገጣል፤ በፈርዖን ሕይወት እምላለሁ፣ ትንሹ ወንድማችሁ ወደዚህ ካልመጣ በስተቀር ከዚህች ንቅንቅ አትሉም።+ 16  እናንተ እዚሁ ታስራችሁ እያላችሁ ከመካከላችሁ አንዱን ላኩትና ወንድማችሁን ይዞት ይምጣ። በዚህ መንገድ የተናገራችሁት ነገር እውነት መሆን አለመሆኑ ይረጋገጣል። አለዚያ ግን በፈርዖን ሕይወት እምላለሁ፣ እናንተ ሰላዮች ናችሁ።” 17  ከዚያም ለሦስት ቀን አንድ ላይ እስር ቤት አቆያቸው። 18  በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ እኔ አምላክን ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ። 19  እንዳላችሁት ንጹሐን ሰዎች ከሆናችሁ ከመካከላችሁ አንዱ ወንድማችሁ እዚሁ እስር ቤት ውስጥ ይቆይ፤ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁ መሄድ ትችላላችሁ።+ 20  የተናገራችሁት ቃል እውነት መሆኑ እንዲረጋገጥና ከሞት እንድትተርፉ ትንሹን ወንድማችሁን ወደ እኔ ይዛችሁት ኑ።” እነሱም እንደተባሉት አደረጉ። 21  ከዚያም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “ይህ ሁሉ እየደረሰብን ያለው በወንድማችን ላይ በፈጸምነው ግፍ የተነሳ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፤+ ምክንያቱም ተጨንቆ* እንድንራራለት ሲማጸነን እኛ ግን አልሰማነውም። ይህ ሁሉ መከራ እየደረሰብን ያለው በዚህ ምክንያት ነው።” 22  በዚህ ጊዜ ሮቤል እንዲህ አላቸው፦ “‘በዚህ ልጅ ላይ ክፉ ነገር አታድርጉ’ ብያችሁ አልነበረም? እናንተ ግን አልሰማችሁኝም።+ ይኸው አሁን ደሙ ከእጃችን እየተፈለገ ነው።”+ 23  ይሁንና ዮሴፍ ያነጋገራቸው በአስተርጓሚ ስለነበር ምን እየተባባሉ እንዳለ እንደሚሰማ አላወቁም ነበር። 24  በመሆኑም ከፊታቸው ዞር ብሎ አለቀሰ።+ ከዚያም ወደ እነሱ ተመልሶ በመምጣት በድጋሚ ካነጋገራቸው በኋላ ስምዖንን+ ከእነሱ ለይቶ በመውሰድ ዓይናቸው እያየ አሰረው።+ 25  በኋላም ዮሴፍ በየከረጢቶቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው አዘዘ፤ በተጨማሪም የእያንዳንዳቸውን ገንዘብ በየከረጢቶቻቸው መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጉዟቸው የሚሆን ስንቅ እንዲሰጧቸው ትእዛዝ አስተላለፈ። ልክ እንዳለውም ተደረገላቸው። 26  እነሱም እህላቸውን በአህዮቻቸው ላይ ጭነው ጉዞ ጀመሩ። 27  ከእነሱ መካከል አንዱ ባረፉበት ቦታ ለአህያው መኖ ለመስጠት ከረጢቱን ሲፈታ ገንዘቡን ከረጢቱ አፍ ላይ አገኘው። 28  እሱም በዚህ ጊዜ ወንድሞቹን “ኧረ ገንዘቤ ተመልሶልኛል፤ ይኸው እዚህ ከረጢቴ ውስጥ አገኘሁት!” አላቸው። እነሱም ልባቸው በፍርሃት ራደ፤ እየተንቀጠቀጡም እርስ በርሳቸው “አምላክ ያደረገብን ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ። 29  በከነአን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ በደረሱም ጊዜ ያጋጠማቸውን ሁሉ እንዲህ በማለት ነገሩት፦ 30  “የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው በቁጣ ተናገረን፤+ አገሪቱን ለመሰለል እንደሄድን አድርጎም ቆጠረን። 31  እኛ ግን እንዲህ አልነው፦ ‘እኛ ንጹሐን ሰዎች ነን። ሰላዮች አይደለንም።+ 32  እኛ የአንድ አባት ልጆች የሆን 12 ወንድማማቾች ነን።+ አንዱ የለም፤+ ትንሹ ወንድማችን ደግሞ አሁን ከአባታችን ጋር በከነአን ምድር ይገኛል’፤+ 33  ሆኖም የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው እንዲህ አለን፦ ‘እንግዲህ ንጹሐን ሰዎች መሆን አለመሆናችሁን በዚህ አውቃለሁ፤ አንዱ ወንድማችሁ እዚህ እኔ ጋ እንዲቆይ አድርጉ።+ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተሰቦቻችሁ የሆነ ነገር ይዛችሁ ሂዱ።+ 34  ንጹሐን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁንም እንዳውቅ ትንሹን ወንድማችሁን ወደ እኔ ይዛችሁት ኑ። ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም በምድሪቱ መነገድ ትችላላችሁ።’” 35  እያንዳንዳቸውም ከረጢታቸውን ሲያራግፉ ገንዘባቸውን እንደተቋጠረ በከረጢታቸው ውስጥ አገኙት። እነሱም ሆኑ አባታቸው የተቋጠረውን ገንዘብ ሲያዩ ደነገጡ። 36  አባታቸው ያዕቆብም “ለሐዘን የዳረጋችሁት እኔን ነው!+ ዮሴፍ የለም፤+ ስምዖንም የለም፤+ አሁን ደግሞ ቢንያምን ልትወስዱት ነው! ኧረ ምን ጉድ ነው የመጣብኝ!” አላቸው። 37  ሮቤል ግን አባቱን “ልጁን መልሼ ባላመጣልህ ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ግደላቸው።+ ለእኔ በኃላፊነት ስጠኝ፤ እኔ ራሴ መልሼ አስረክብሃለሁ” አለው።+ 38  እሱ ግን እንዲህ አለ፦ “ልጄ ከእናንተ ጋር ወደዚያ አይወርድም። ምክንያቱም ወንድሙ ሞቷል፤ አሁን የቀረው እሱ ብቻ ነው።+ ከእናንተ ጋር አብሮ ሲሄድ መንገድ ላይ አደጋ ቢደርስበትና ቢሞት ሽበቴን በሐዘን+ ወደ መቃብር*+ ታወርዱታላችሁ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የምድሪቱን ደካማ ጎን።”
ወይም “ነፍሱ ተጨንቃ።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።