ዘፍጥረት 18:1-33

  • ሦስት መላእክት ወደ አብርሃም መጡ (1-8)

  • ሣራ ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ቃል ተገባላት፤ እሷም ሳቀች (9-15)

  • አብርሃም ስለ ሰዶም ያቀረበው ጥያቄ (16-33)

18  ከዚያም አብርሃም በጣም ሞቃታማ በሆነው የቀኑ ክፍለ ጊዜ ድንኳኑ ደጃፍ ላይ ተቀምጦ ሳለ ይሖዋ+ በማምሬ ትላልቅ ዛፎች+ አጠገብ ተገለጠለት።  ቀና ብሎም ሲመለከት እሱ ካለበት ትንሽ ራቅ ብሎ ሦስት ሰዎች ቆመው አየ።+ ሰዎቹን ባያቸው ጊዜም ከድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ወደ እነሱ እየሮጠ ሄደ፤ ወደ መሬት ዝቅ ብሎም ሰገደ።  ከዚያም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ፣ እንግዲህ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እባክህ አገልጋይህን አልፈኸው አትሂድ።  እባካችሁ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁና እግራችሁን ታጠቡ፤+ ከዚያም ከዛፉ ሥር አረፍ በሉ።  ወደ አገልጋያችሁ ከመጣችሁ አይቀር፣ ብርታት እንድታገኙ* ትንሽ እህል ላምጣላችሁና ቅመሱ፤ ከዚያም ጉዟችሁን ትቀጥላላችሁ።” በዚህ ጊዜ እነሱ “እሺ፣ እንዳልከው አድርግ” አሉት።  በመሆኑም አብርሃም ሣራ ወዳለችበት ወደ ድንኳኑ በፍጥነት ሄዶ “ቶሎ በይ! ሦስት መስፈሪያ* የላመ ዱቄት ወስደሽ አቡኪና ቂጣ ጋግሪ” አላት።  በመቀጠልም አብርሃም ወደ መንጋው ሮጦ በመሄድ ሥጋው ገር የሆነ ፍርጥም ያለ ወይፈን መረጠ። ለአገልጋዩም ሰጠው፤ እሱም ለማዘጋጀት ተጣደፈ።  ከዚያም ቅቤና ወተት እንዲሁም ያዘጋጀውን ወይፈን ወስዶ ምግቡን አቀረበላቸው። እየበሉ ሳሉም ዛፉ ሥር አጠገባቸው ቆሞ ነበር።+  እነሱም “ሚስትህ ሣራ+ የት አለች?” አሉት። እሱም “እዚህ ድንኳኑ ውስጥ ናት” አላቸው። 10  ከመካከላቸውም አንዱ ንግግሩን በመቀጠል “የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ በእርግጥ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች”+ አለ። በዚህ ጊዜ ሣራ ከሰውየው በስተ ጀርባ ባለው በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ሆና ታዳምጥ ነበር። 11  አብርሃምና ሣራ አርጅተው፣ ዕድሜያቸውም ገፍቶ ነበር።+ ሣራ ልጅ የመውለጃዋ ዕድሜ አልፎ ነበር።*+ 12  በመሆኑም ሣራ “አሁን እንዲህ አርጅቼ ጌታዬም ዕድሜው ገፍቶ እያለ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ደስታ ላገኝ እችላለሁ?”+ ብላ በማሰብ በልቧ ሳቀች። 13  ከዚያም ይሖዋ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ሣራ ‘እንዲህ ካረጀሁ በኋላም እንኳ ልወልድ ነው ማለት ነው?’ በማለት የሳቀችው ለምንድን ነው? 14  ለይሖዋ የሚሳነው ነገር አለ?+ የዛሬ ዓመት በዚሁ በተወሰነው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች።” 15  ሣራ ግን ስለፈራች “ኧረ አልሳቅኩም!” ስትል ካደች። በዚህ ጊዜ “እንዴ! ሳቅሽ እንጂ” አላት። 16  ሰዎቹም ለመሄድ በተነሱና ቁልቁል ወደ ሰዶም+ በተመለከቱ ጊዜ አብርሃም ሊሸኛቸው አብሯቸው ሄደ። 17  ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “እኔ ላደርገው ያሰብኩትን ነገር ከአብርሃም ደብቄ አውቃለሁ?+ 18  አብርሃም በእርግጥ ታላቅና ኃያል ብሔር ይሆናል፤ የምድር ብሔራትም ሁሉ በእሱ አማካኝነት ይባረካሉ።*+ 19  እኔ ከአብርሃም ጋር የተዋወቅኩት ትክክለኛና ተገቢ የሆነውን ነገር በማድረግ የይሖዋን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእሱ በኋላ የሚመጣውን ቤተሰቡን እንዲያዝዝ ነው፤+ እንዲህ ካደረገ ይሖዋ አብርሃምን አስመልክቶ ቃል የገባውን ነገር ይፈጽምለታል።” 20  ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚሰማው ጩኸት በእርግጥም ታላቅ ነው፤+ ኃጢአታቸውም እጅግ ከባድ ሆኗል።+ 21  ድርጊታቸው እኔ ዘንድ እንደደረሰው ጩኸት መሆን አለመሆኑን ለማየት ወደዚያ እወርዳለሁ። ነገሩ እንደዚያ ካልሆነም ማወቅ እችላለሁ።”+ 22  ሰዎቹም ከዚያ ተነስተው ወደ ሰዶም አቀኑ፤ ይሖዋ+ ግን እዚያው ከአብርሃም ጋር ቀረ። 23  ከዚያም አብርሃም ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፦ “በእርግጥ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብረህ ታጠፋለህ?+ 24  እስቲ በከተማዋ ውስጥ 50 ጻድቅ ሰዎች አሉ እንበል። ታዲያ ሁሉንም ዝም ብለህ ታጠፋቸዋለህ? በውስጧ ስለሚኖሩት 50 ጻድቃን ስትል ስፍራውን አትምርም? 25  በጻድቁም ሆነ በኃጢአተኛው ላይ ተመሳሳይ ነገር እንዲደርስ የሚያደርግ እንዲህ ዓይነት እርምጃ በመውሰድ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አንድ ላይ ትገድላለህ ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው!+ ይህ በአንተ ዘንድ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው።+ የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?”+ 26  ከዚያም ይሖዋ “በሰዶም ከተማ ውስጥ 50 ጻድቅ ሰዎች ባገኝ ስለ እነሱ ስል ስፍራውን በሙሉ እምራለሁ” አለ። 27  አብርሃም ግን እንደገና እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መቼም እኔ ትቢያና አመድ ሆኜ ሳለሁ አንዴ ደፍሬ ከይሖዋ ጋር መነጋገር ጀምሬያለሁ። 28  ከ50ዎቹ ጻድቃን መካከል አምስት ጎደሉ እንበል። ታዲያ በአምስቱ የተነሳ መላዋን ከተማ ታጠፋለህ?” እሱም “በዚያ 45 ባገኝ ከተማዋን አላጠፋም”+ አለ። 29  አብርሃም ግን በድጋሚ “በዚያ 40 ተገኙ እንበል” አለው። እሱም መልሶ “ስለ 40ዎቹ ስል አላደርገውም” አለ። 30  አብርሃም ግን በመቀጠል “ይሖዋ እባክህ፣ አትቆጣና+ አሁንም ልናገር፤ እንደው በዚያ 30 ብቻ ቢገኙስ?” አለ። እሱም “በዚያ 30 ካገኘሁ አላደርገውም” ሲል መለሰ። 31  አብርሃም ግን እንዲህ በማለት ቀጠለ፦ “መቼም አንዴ ደፍሬ ከይሖዋ ጋር መነጋገር ጀምሬያለሁ፤ እንደው በዚያ 20 ብቻ ቢገኙስ?” እሱም መልሶ “ስለ 20ዎቹ ስል አላጠፋትም” አለ። 32  በመጨረሻም አብርሃም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እባክህ፣ አትቆጣና አንድ ጊዜ ብቻ ልናገር፤ በዚያ አሥር ብቻ ቢገኙስ?” እሱም መልሶ “ስለ አሥሩ ስል አላጠፋትም” አለ። 33  ይሖዋም ከአብርሃም ጋር ተነጋግሮ ሲጨርስ ጉዞውን ቀጠለ፤+ አብርሃም ደግሞ ወደ ስፍራው ተመለሰ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ልባችሁን እንድታበረቱ።”
ቃል በቃል “የሲህ መስፈሪያ።” አንድ ሲህ 7.33 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “በሴቶች ላይ የሚታየው ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር።”
ወይም “ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።”