ዘፍጥረት 1:1-31

 • ሰማያትና ምድር ተፈጠሩ (1, 2)

 • ምድር የተሰናዳችባቸው ስድስት ቀናት (3-31)

  • የመጀመሪያ ቀን፦ ብርሃን፤ ቀንና ሌሊት (3-5)

  • ሁለተኛ ቀን፦ ጠፈር (6-8)

  • ሦስተኛ ቀን፦ የብስና ተክሎች (9-13)

  • አራተኛ ቀን፦ በሰማያት ላይ ያሉ ብርሃን ሰጪ አካላት (14-19)

  • አምስተኛ ቀን፦ ዓሣዎችና ወፎች (20-23)

  • ስድስተኛ ቀን፦ በምድር ላይ የሚኖሩ እንስሳትና ሰዎች (24-31)

1  በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።+  ምድርም ቅርጽ አልባና ባድማ ነበረች፤* ጥልቁም* ውኃ+ በጨለማ ተሸፍኖ ነበር፤ የአምላክም ኃይል*+ በውኃው ላይ ይንቀሳቀስ ነበር።+  አምላክም “ብርሃን ይሁን” አለ። ብርሃንም ሆነ።+  ከዚህ በኋላ አምላክ ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ አምላክም ብርሃኑን ከጨለማው ለየ።  አምላክም ብርሃኑን ‘ቀን’ ብሎ ጠራው፤ ጨለማውን ግን ‘ሌሊት’ ብሎ ጠራው።+ መሸ፣ ነጋም፤ የመጀመሪያ ቀን።  ከዚያም አምላክ “በውኃዎቹ መካከል ጠፈር+ ይሁን፣ ውኃዎቹም ከውኃዎቹ ይከፈሉ” አለ።+  ከዚያም አምላክ ጠፈርን ሠራ፤ ከጠፈሩ በታች ያሉትንም ውኃዎች ከጠፈሩ በላይ ካሉት ውኃዎች ለየ።+ እንዳለውም ሆነ።  አምላክ ጠፈሩን ‘ሰማይ’ ብሎ ጠራው። መሸ፣ ነጋም፤ ሁለተኛ ቀን።  በመቀጠልም አምላክ “ከሰማያት በታች ያሉት ውኃዎች አንድ ቦታ ላይ ይሰብሰቡና ደረቁ መሬት ይገለጥ” አለ።+ እንዳለውም ሆነ። 10  አምላክ ደረቁን መሬት ‘የብስ’+ ብሎ ጠራው፤ አንድ ላይ የተሰበሰቡትን ውኃዎች ግን ‘ባሕር’+ ብሎ ጠራቸው። አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ።+ 11  ቀጥሎም አምላክ “ምድር ሣርን፣ ዘር የሚሰጡ ተክሎችን እንዲሁም ዘር ያለው ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ታብቅል” አለ። እንዳለውም ሆነ። 12  ምድርም ሣርን፣ ዘር የሚሰጡ ተክሎችን+ እንዲሁም ዘር ያለው ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ማብቀል ጀመረች። ከዚያም አምላክ ይህ መልካም እንደሆነ አየ። 13  መሸ፣ ነጋም፤ ሦስተኛ ቀን። 14  አምላክም እንዲህ አለ፦ “ቀኑና ሌሊቱ እንዲለይ+ በሰማያት ጠፈር ላይ ብርሃን ሰጪ አካላት+ ይኑሩ፤ እነሱም ወቅቶችን፣ ቀናትንና ዓመታትን+ የሚጠቁሙ ምልክቶች ሆነው ያገለግላሉ። 15  በምድርም ላይ እንዲያበሩ በሰማያት ጠፈር ላይ ያሉ ብርሃን ሰጪ አካላት ሆነው ያገለግላሉ።” እንዳለውም ሆነ። 16  አምላክም ሁለቱን ታላላቅ ብርሃን ሰጪ አካላት ሠራ፤ ታላቁ ብርሃን ሰጪ አካል በቀን እንዲያይል፣+ ታናሹ ብርሃን ሰጪ አካል ደግሞ በሌሊት እንዲያይል አደረገ፤ ከዋክብትንም ሠራ።+ 17  በዚህ መንገድ አምላክ በምድር ላይ እንዲያበሩ በሰማያት ጠፈር ላይ አስቀመጣቸው፤ 18  በተጨማሪም በቀንና በሌሊት እንዲያይሉ እንዲሁም ብርሃኑን ከጨለማው እንዲለዩ አደረገ።+ አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ። 19  መሸ፣ ነጋም፤ አራተኛ ቀን። 20  ከዚያም አምላክ “ውኃዎቹ በሚርመሰመሱ ሕያዋን ፍጥረታት* ይሞሉ፤ እንዲሁም የሚበርሩ ፍጥረታት ከምድር በላይ በሰማያት ጠፈር ላይ ይብረሩ” አለ።+ 21  አምላክም ግዙፍ የባሕር ፍጥረታትን እንዲሁም በውኃዎቹ ውስጥ የሚንቀሳቀሱና የሚርመሰመሱ ሕያዋን ፍጥረታትን* ሁሉ እንደየወገናቸው ብሎም ክንፍ ያለውን እያንዳንዱን የሚበር ፍጥረት እንደየወገኑ ፈጠረ። አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ። 22  ከዚያም አምላክ “ብዙ ተባዙ፤ የባሕሩንም ውኃ ሙሉት፤+ የሚበርሩ ፍጥረታትም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው። 23  መሸ፣ ነጋም፤ አምስተኛ ቀን። 24  ቀጥሎም አምላክ “ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን* እንደየወገናቸው እንዲሁም የቤት እንስሳትን፣ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትንና* የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው ታውጣ” አለ።+ እንዳለውም ሆነ። 25  አምላክም በምድር ላይ ያሉ የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ የቤት እንስሳትን እንደየወገናቸው እንዲሁም መሬት ለመሬት የሚሄዱ ፍጥረታትን ሁሉ እንደየወገናቸው ሠራ። አምላክም ይህ መልካም እንደሆነ አየ። 26  ከዚያም አምላክ “ሰውን በመልካችን እንደ አምሳላችን+ እንሥራ፤+ እሱም በባሕር ዓሣዎች፣ በሰማያት ላይ በሚበርሩ ፍጥረታት፣ በቤት እንስሳትና በምድር ሁሉ እንዲሁም በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑረው”+ አለ። 27  አምላክም ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በአምላክ መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።+ 28  በተጨማሪም አምላክ ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤+ ግዟትም።+ እንዲሁም የባሕር ዓሣዎችን፣ በሰማያት ላይ የሚበርሩ ፍጥረታትንና በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታትን በሙሉ ግዟቸው።”+ 29  ቀጥሎም አምላክ እንዲህ አለ፦ “በመላው ምድር ላይ ያሉ ዘር የሚሰጡ ተክሎችን በሙሉ እንዲሁም ዘር ያለው ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን በሙሉ ይኸው ሰጥቻችኋለሁ። ምግብ ይሁኗችሁ።+ 30  በምድር ላይ ላለው የዱር እንስሳ ሁሉ፣ በሰማያት ላይ ለሚበር ፍጥረት ሁሉ እንዲሁም ሕይወት* ላለው በምድር ላይ ለሚንቀሳቀስ ነገር ሁሉ አረንጓዴ ተክሎችን በሙሉ ምግብ እንዲሆኗቸው ሰጥቻቸዋለሁ።”+ እንዳለውም ሆነ። 31  ከዚያ በኋላ አምላክ የሠራውን እያንዳንዱን ነገር ተመለከተ፤ እነሆ፣ እጅግ መልካም ነበር!+ መሸ፣ ነጋም፤ ስድስተኛ ቀን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ባዶ ነበረች።”
ወይም “የሚነዋወጠውም።”
ወይም “የአምላክም መንፈስ።”
ወይም “ነፍሳት።”
ወይም “ነፍሳትን።”
ወይም “ነፍሳትን።”
ይህ አገላለጽ በምድር ላይ የሚሳቡ እንስሳትን ጨምሮ ከሌሎች የእንስሳት ምድብ የማይመደቡትን እንስሳት ሊያመለክት ይችላል።
ወይም “ሕያው ነፍስ።”