ዘፍጥረት 25:1-34

  • አብርሃም በድጋሚ አገባ (1-6)

  • አብርሃም ሞተ (7-11)

  • የእስማኤል ወንዶች ልጆች (12-18)

  • ያዕቆብና ኤሳው ተወለዱ (19-26)

  • ኤሳው የብኩርና መብቱን ሸጠ (27-34)

25  አብርሃም ኬጡራ የምትባል ሌላ ሚስት አገባ።  እሷም ከጊዜ በኋላ ዚምራንን፣ ዮቅሻንን፣ ሚዳንን፣ ምድያምን፣+ ይሽባቅን እና ሹሃን+ ወለደችለት።  ዮቅሻንም ሳባን እና ዴዳንን ወለደ። የዴዳን ወንዶች ልጆች ደግሞ አሹሪም፣ ለጡሺም እና ለኡሚም ነበሩ።  የምድያም ወንዶች ልጆች ኤፋ፣ ኤፌር፣ ሃኖክ፣ አቢዳዕ እና ኤልዳዓ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ወንዶች ልጆች ነበሩ።  በኋላም አብርሃም ያለውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፤+  ከቁባቶቹ ለወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ግን ስጦታ ሰጣቸው። ከዚያም ገና በሕይወት እያለ ከልጁ ከይስሐቅ እንዲርቁ በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ወደ ምሥራቅ ምድር ላካቸው።+  አብርሃም በሕይወት የኖረበት ዘመን 175 ዓመት ነበር።  ከዚያም አብርሃም እስትንፋሱ ቀጥ አለ፤ ሸምግሎ፣ በሕይወቱ ረክቶና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።*  ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤልም የሂታዊው የጾሃር ልጅ በሆነው በኤፍሮን የእርሻ ቦታ ውስጥ ባለው በማምሬ ፊት ለፊት በሚገኘው በማክፈላ ዋሻ ቀበሩት፤+ 10  ይህ የእርሻ ቦታ አብርሃም ከሄት ወንዶች ልጆች የገዛው ነው። አብርሃምም ከሚስቱ ከሣራ ጋር በዚያ ስፍራ ተቀበረ።+ 11  አብርሃም ከሞተ በኋላም አምላክ የአብርሃምን ልጅ ይስሐቅን መባረኩን ቀጠለ፤+ ይስሐቅ በብኤርላሃይሮዒ+ አቅራቢያ ይኖር ነበር። 12  የሣራ አገልጋይ የነበረችው ግብፃዊቷ አጋር+ ለአብርሃም የወለደችለት የአብርሃም ልጅ የእስማኤል+ ታሪክ ይህ ነው። 13  የእስማኤል ወንዶች ልጆች ስም በየስማቸውና በየቤተሰብ የዘር ሐረጋቸው ሲዘረዘር የሚከተለው ነው፦ የእስማኤል የበኩር ልጅ ነባዮት+ ከዚያም ቄዳር፣+ አድበዔል፣ ሚብሳም፣+ 14  ሚሽማ፣ ዱማ፣ ማሳ፣ 15  ሃዳድ፣ ቴማ፣ የጡር፣ ናፊሽ እና ቄድማ። 16  የእስማኤል ወንዶች ልጆች በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው* ሲዘረዘሩ ስማቸው ይህ ነው፤ እነሱም በየነገዳቸው 12 የነገድ አለቆች ናቸው።+ 17  እስማኤል 137 ዓመት ኖረ። ከዚያም እስትንፋሱ ቀጥ አለና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።* 18  እነሱም ከግብፅ አጠገብ በሹር+ አቅራቢያ ከምትገኘው ከሃዊላ+ አንስቶ እስከ አሦር ድረስ ባለው አካባቢ ሰፍረው ነበር። በወንድሞቹም ሁሉ አቅራቢያ ሰፈረ።*+ 19  የአብርሃም ልጅ+ የይስሐቅ ታሪክ ይህ ነው። አብርሃም ይስሐቅን ወለደ። 20  ይስሐቅ በጳዳንአራም የሚኖረውን የአራማዊውን የባቱኤልን ሴት ልጅ+ ማለትም የአራማዊውን የላባን እህት ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው 40 ዓመት ነበር። 21  ይስሐቅ ሚስቱ መሃን ስለነበረች ስለ እሷ አዘውትሮ ይሖዋን ይለምን ነበር፤ ይሖዋም ልመናውን ሰማው፤ ሚስቱ ርብቃም ፀነሰች። 22  በሆዷ ውስጥ ያሉት ልጆችም እርስ በርስ ይታገሉ ጀመር፤+ በመሆኑም “እንዲህ ከሆነስ ብሞት ይሻለኛል” አለች። ስለዚህ ይሖዋን ጠየቀች። 23  ይሖዋም እንዲህ አላት፦ “በማህፀንሽ ውስጥ ሁለት ብሔራት አሉ፤+ ከውስጥሽም ሁለት ሕዝቦች ተለያይተው ይወጣሉ።+ አንደኛው ብሔር ከሌላኛው ብሔር ይበረታል፤+ ታላቁም ታናሹን ያገለግላል።”+ 24  የመውለጃዋም ጊዜ ሲደርስ በማህፀኗ ውስጥ መንታ ልጆች ነበሩ። 25  መጀመሪያ የወጣው መልኩ ቀይ ሲሆን ፀጉራም ካባ የለበሰ ይመስል ሰውነቱ በሙሉ በፀጉር የተሸፈነ ነበር፤+ በመሆኑም ስሙን ኤሳው*+ አሉት። 26  ከዚያም ወንድሙ ወጣ፤ በእጁም የኤሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤+ በዚህም የተነሳ ስሙን ያዕቆብ* አለው።+ ርብቃ እነሱን ስትወልድ ይስሐቅ 60 ዓመቱ ነበር። 27  ልጆቹም እያደጉ ሲሄዱ ኤሳው ውጭ መዋል የሚወድ የተዋጣለት አዳኝ ሆነ፤+ ያዕቆብ ግን አብዛኛውን ጊዜውን በድንኳን የሚያሳልፍ+ ነቀፋ የሌለበት ሰው ነበር። 28  ይስሐቅ ኤሳውን ይወደው ነበር፤ ምክንያቱም እያደነ ያበላው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወደው ነበር።+ 29  አንድ ቀን ኤሳው ውጭ ውሎ በጣም ደክሞት ሲመጣ ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ነበር። 30  በመሆኑም ኤሳው ያዕቆብን “ቶሎ በል እባክህ፣ በጣም ስለደከመኝ* ከዚያ ከቀዩ ወጥ የተወሰነ* ስጠኝ!” አለው። ስሙ ኤዶም*+ የተባለውም በዚህ የተነሳ ነው። 31  በዚህ ጊዜ ያዕቆብ “በመጀመሪያ የብኩርና መብትህን+ ሽጥልኝ!” አለው። 32  ኤሳውም “እኔ ለራሴ ልሞት ደርሻለሁ! ታዲያ የብኩርና መብት ምን ይጠቅመኛል?” አለው። 33  ያዕቆብም “በመጀመሪያ ማልልኝ!” አለው። እሱም ማለለት፤ የብኩርና መብቱንም ለያዕቆብ ሸጠለት።+ 34  ከዚያም ያዕቆብ ለኤሳው ዳቦና ምስር ወጥ ሰጠው፤ እሱም በላ፣ ጠጣም፤ ተነሥቶም ሄደ። በዚህ መንገድ ኤሳው የብኩርና መብቱን አቃለለ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።
ወይም “በግንብ በታጠሩት ሰፈሮቻቸው።”
ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።
“ከወንድሞቹም ሁሉ ጋር በጠላትነት ኖረ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ፀጉራም” የሚል ትርጉም አለው።
“ተረከዝ የሚይዝ፤ የሚተካ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “በጣም ስለራበኝ።”
ወይም “አንድ ጉርሻ።”
“ቀይ” የሚል ትርጉም አለው።