ዘፍጥረት 29:1-35

  • ያዕቆብ ከራሔል ጋር ተገናኘ (1-14)

  • ያዕቆብ ራሔልን ወደዳት (15-20)

  • ያዕቆብ ሊያንና ራሔልን አገባ (21-29)

  • ያዕቆብ ከሊያ የወለዳቸው አራት ወንዶች ልጆች፦ ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊና ይሁዳ (30-35)

29  ከዚያ በኋላ ያዕቆብ ጉዞውን ቀጠለ፤ ወደ ምሥራቅ ሰዎች ምድርም ሄደ።  እዚያም በሜዳ ላይ አንድ የውኃ ጉድጓድ ተመለከተ፤ እረኞች የበግ መንጎቻቸውን ሁልጊዜ የሚያጠጡት ከዚያ የውኃ ጉድጓድ ስለነበር በአቅራቢያው ሦስት የበግ መንጎች ተኝተው አየ። በጉድጓዱም አፍ ላይ ትልቅ ድንጋይ ነበር።  መንጎቹ በሙሉ እዚያ ከተሰበሰቡ በኋላ እረኞቹ በውኃ ጉድጓዱ አፍ ላይ ያለውን ድንጋይ ያንከባልሉና መንጎቹን ያጠጣሉ፤ ከዚያም ድንጋዩን ወደ ቦታው በመመለስ የጉድጓዱን አፍ ይገጥሙታል።  ያዕቆብም “ወንድሞቼ፣ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነሱም “ከካራን+ ነው የመጣነው” አሉት።  እሱም “የናኮርን+ የልጅ ልጅ ላባን+ ታውቁታላችሁ?” አላቸው፤ እነሱም “አዎ፣ እናውቀዋለን” አሉት።  እሱም “ለመሆኑ ደህና ነው?” አላቸው። እነሱም “አዎ፣ ደህና ነው። እንዲያውም ልጁ ራሔል+ ይኸው በጎች ይዛ እየመጣች ነው!” አሉት።  ከዚያም እሱ “እንደምታዩት ገና እኩለ ቀን ነው። አሁን እኮ መንጎች የሚገቡበት ሰዓት አይደለም፤ በጎቹን አጠጧቸውና ወደ ግጦሽ አሰማሯቸው” አላቸው።  እነሱም “መንጎቹ ሁሉ ካልተሰባሰቡና እረኞቹ ድንጋዩን ከጉድጓዱ አፍ ላይ ካላንከባለሉት እንዲህ ማድረግ አንችልም፤ በጎቹን ማጠጣት የምንችለው ከዚያ በኋላ ነው” አሉት።  እሱም ገና ከእነሱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ ራሔል እረኛ ስለነበረች የአባቷን በጎች እየነዳች መጣች። 10  ያዕቆብ የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልንና የላባን በጎች ሲያይ ወዲያውኑ ወደ ጉድጓዱ ሄዶ ድንጋዩን ከጉድጓዱ አፍ ላይ አንከባለለ፤ የእናቱን ወንድም የላባን በጎችም አጠጣ። 11  ከዚያም ያዕቆብ ራሔልን ሳማት፤ ጮክ ብሎም አለቀሰ። 12  ያዕቆብም ለራሔል የአባቷ ዘመድና* የርብቃ ልጅ መሆኑን ነገራት። እሷም እየሮጠች ሄዳ ለአባቷ ነገረችው። 13  ላባም+ የእህቱ ልጅ ስለሆነው ስለ ያዕቆብ ሲሰማ ወደ እሱ እየሮጠ ሄዶ አቅፎ ሳመው፤ ወደ ቤቱም አስገባው። ያዕቆብም ሁኔታውን ሁሉ ለላባ ነገረው። 14  ላባም “በእርግጥም አንተ የአጥንቴ ፍላጭ የሥጋዬ ቁራጭ* ነህ” አለው። በመሆኑም ያዕቆብ ከእሱ ጋር አንድ ወር ሙሉ ተቀመጠ። 15  ከዚያም ላባ ያዕቆብን “ዘመዴ*+ ስለሆንክ ብቻ እኔን በነፃ ልታገለግለኝ ይገባል? ንገረኝ፣ ደሞዝህ ምንድን ነው?”+ አለው። 16  ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት። የታላቋ ስም ሊያ ሲሆን የታናሿ ስም ደግሞ ራሔል ነበር።+ 17  ሊያ ዓይነ ልም* ነበረች፤ ራሔል ግን ዓይን የምትማርክ ውብ ሴት ነበረች። 18  ያዕቆብ ራሔልን ይወዳት ስለነበር “ለታናሿ ልጅህ ለራሔል ስል ሰባት ዓመት ላገለግልህ ፈቃደኛ ነኝ” አለው።+ 19  ላባም “ለሌላ ሰው ከምሰጣት ለአንተ ብሰጥህ ይሻለኛል፤ አብረኸኝ ተቀመጥ” አለው። 20  ያዕቆብም ለራሔል ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤+ ይሁንና ራሔልን ይወዳት ስለነበር ሰባቱ ዓመታት ለእሱ እንደ ጥቂት ቀናት ነበሩ። 21  ከዚያም ያዕቆብ ላባን “እንግዲህ የተባባልነው ጊዜ ስላበቃ ሚስቴን ስጠኝ፤ ከእሷም ጋር ልተኛ” አለው። 22  ስለዚህ ላባ የአካባቢውን ሰዎች በሙሉ ጠራ፤ ግብዣም አደረገ። 23  ሆኖም ሲመሽ ላባ ልጁን ሊያን ወስዶ ከእሷ ጋር እንዲተኛ ለያዕቆብ ሰጠው። 24  በተጨማሪም ላባ የእሱ አገልጋይ የሆነችውን ዚልጳን አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለሊያ ሰጣት።+ 25  በማግስቱ ጠዋት ያዕቆብ አብራው ያደረችው ሊያ መሆኗን አወቀ! በመሆኑም ያዕቆብ ላባን “ያደረግክብኝ ነገር ምንድን ነው? ያገለገልኩህ ለራሔል ስል አልነበረም? ታዲያ ለምን አታለልከኝ?”+ አለው። 26  ላባም እንዲህ አለው፦ “በአካባቢያችን በኩሯ እያለች ታናሺቱን መዳር የተለመደ አይደለም። 27  ሳምንቱን ከዚህችኛዋ ጋር ተሞሸር። ከዚያም ለምታገለግለኝ ተጨማሪ ሰባት ዓመታት ሌላኛዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ።”+ 28  ያዕቆብም እንደተባለው አደረገ፤ ሳምንቱን ከዚህችኛዋ ጋር ተሞሸረ። ከዚያም ላባ ልጁን ራሔልን ሚስት እንድትሆነው ሰጠው። 29  በተጨማሪም ላባ አገልጋዩ የሆነችውን ባላን+ አገልጋይዋ እንድትሆን ለልጁ ለራሔል ሰጣት።+ 30  ከዚያም ያዕቆብ ከራሔል ጋር ተኛ፤ ራሔልንም ከሊያ ይልቅ ወደዳት። ላባንም ሌላ ሰባት ዓመት አገለገለው።+ 31  ይሖዋም ሊያ እንዳልተወደደች* ሲመለከት መፀነስ እንድትችል አደረጋት፤*+ ራሔል ግን መሃን ነበረች።+ 32  ሊያም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እሷም “ይህ የሆነው ይሖዋ መከራዬን ስላየልኝ ነው፤+ ከእንግዲህ ባሌ ይወደኛል” ስትል ስሙን ሮቤል*+ አለችው። 33  ዳግመኛም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እሷም “ይሖዋ እንዳልተወደድኩ ስለሰማ ይሄኛውንም ልጅ ሰጠኝ” አለች። ስሙንም ስምዖን*+ አለችው። 34  አሁንም ደግሞ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እሷም “ሦስት ወንዶች ልጆች ስለወለድኩለት አሁን ባሌ ይቀርበኛል” አለች። በዚህም የተነሳ ሌዊ*+ ተባለ። 35  አሁንም እንደገና ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እሷም “አሁን ይሖዋን አወድሰዋለሁ” አለች። ስለሆነም ይሁዳ*+ አለችው። ከዚያ በኋላ መውለድ አቆመች።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ወንድምና።”
ወይም “የሥጋ ዘመዴ።”
ቃል በቃል “ወንድሜ።”
ወይም “ፈዛዛ።”
ቃል በቃል “እንደተጠላች።”
ቃል በቃል “ማህፀኗን ከፈተላት።”
“እነሆ፣ ወንድ ልጅ!” የሚል ትርጉም አለው።
“መስማት” የሚል ትርጉም አለው።
“አጥብቆ ደገፈ፤ ተባበረ” የሚል ትርጉም አለው።
“የተመሰገነ፤ ምስጉን” የሚል ትርጉም አለው።