ዘፍጥረት 32:1-32

  • መላእክት ያዕቆብን አገኙት (1, 2)

  • ያዕቆብ ከኤሳው ጋር ለመገናኘት ተዘጋጀ (3-23)

  • ያዕቆብ ከአንድ መልአክ ጋር ታገለ (24-32)

    • ያዕቆብ፣ እስራኤል ተባለ (28)

32  ከዚያም ያዕቆብ ጉዞውን ቀጠለ፤ የአምላክ መላእክትም አገኙት።  ያዕቆብም ልክ እንዳያቸው “ይህ የአምላክ ሰፈር ነው!” አለ። በመሆኑም የቦታውን ስም ማሃናይም* አለው።  ከዚያም ያዕቆብ በኤዶም+ ክልል* ሴይር+ በተባለው ምድር ወደሚኖረው ወንድሙ ወደ ኤሳው መልእክተኞችን አስቀድሞ ላከ፤  እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ “ጌታዬን ኤሳውን እንዲህ በሉት፦ ‘አገልጋይህ ያዕቆብ እንዲህ ይላል፦ “ከላባ ጋር እስካሁን ድረስ ለረጅም ጊዜ ኖሬአለሁ።*+  አሁን በሬዎች፣ አህዮች፣ በጎች እንዲሁም ወንድና ሴት አገልጋዮች+ አሉኝ፤ ይህን መልእክት ለጌታዬ የላክሁት በፊትህ ሞገስ እንዳገኝ ለመጠየቅ ነው።”’”  ከተወሰነ ጊዜ በኋላም መልእክተኞቹ ወደ ያዕቆብ ተመልሰው በመምጣት እንዲህ አሉት፦ “ወንድምህን ኤሳውን አግኝተነው ነበር፤ እሱም ከአንተ ጋር ለመገናኘት ወደዚህ እየመጣ ነው፤ ከእሱም ጋር 400 ሰዎች አሉ።”+  ያዕቆብም እጅግ ፈራ፤ በጭንቀትም ተዋጠ።+ በመሆኑም አብረውት ያሉትን ሰዎች፣ መንጎቹን፣ ከብቶቹንና ግመሎቹን በሁለት ቡድን ከፈላቸው።  እሱም “ምናልባት ኤሳው በአንደኛው ቡድን ላይ ጥቃት ቢሰነዝር፣ ሌላኛው ቡድን ሊያመልጥ ይችላል” አለ።  ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ አለ፦ “‘ወደ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፤ እኔም መልካም ነገር አደርግልሃለሁ’ ያልከኝ የአባቴ የአብርሃም አምላክና የአባቴ የይስሐቅ አምላክ የሆንከው ይሖዋ ሆይ፣+ 10  እኔ ባሪያህ ይህን ያህል ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ልታሳየኝ+ የሚገባኝ ሰው አልነበርኩም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር ከበትር ሌላ ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ቡድን ሆኛለሁ።+ 11  ከወንድሜ ከኤሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤+ ምክንያቱም መጥቶ በእኔም ሆነ በእነዚህ እናቶችና በልጆቻቸው ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝር ፈርቻለሁ።+ 12  አንተው ራስህ ‘በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፤ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሳ ሊቆጠር እንደማይችል የባሕር አሸዋ አደርገዋለሁ’ ብለኸኛል።”+ 13  እሱም በዚያ ሌሊት እዚያው አደረ። ከንብረቱም መካከል የተወሰነውን ወስዶ ለወንድሙ ለኤሳው ስጦታ አዘጋጀ፤+ 14  ስጦታውም የሚከተለው ነበር፦ 200 እንስት ፍየሎች፣ 20 ተባዕት ፍየሎች፣ 200 እንስት በጎች፣ 20 አውራ በጎች 15  እንዲሁም 30 የሚያጠቡ ግመሎች፣ 40 ላሞች፣ 10 በሬዎች፣ 20 እንስት አህዮችና 10 ተባዕት አህዮች።+ 16  እሱም በመንጋ በመንጋ ለይቶ ለአገልጋዮቹ ሰጣቸው። አገልጋዮቹንም “ቀድማችሁኝ ተሻገሩ፤ አንዱን መንጋ ከሌላው መንጋ አራርቁት” አላቸው። 17  በተጨማሪም የመጀመሪያውን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ወንድሜ ኤሳው ቢያገኝህና ‘ለመሆኑ አንተ የማን ነህ? የምትሄደው ወዴት ነው? እነዚህ የምትነዳቸው እንስሳትስ የማን ናቸው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፣ 18  ‘የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው። ይህ ለጌታዬ ለኤሳው የተላከ ስጦታ ነው፤+ እንዲያውም እሱ ራሱ ከኋላችን እየመጣ ነው’ በለው።” 19  እንዲሁም ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውንና መንጎቹን የሚነዱትን በሙሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ኤሳውን ስታገኙት ይህንኑ ንገሩት። 20  ‘አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን እየመጣ ነው’ ማለት እንዳለባችሁም አትዘንጉ።” ይህን ያላቸው ‘ስጦታውን አስቀድሜ በመላክ ቁጣው እንዲበርድለት ካደረግኩ ከእሱ ጋር ስገናኝ በጥሩ ሁኔታ ይቀበለኝ ይሆናል’ ብሎ ስላሰበ ነው።+ 21  በመሆኑም ስጦታው ከእሱ ቀድሞ ተሻገረ፤ እሱ ግን እዚያው የሰፈረበት ቦታ አደረ። 22  በኋላም በዚያው ሌሊት ተነሳ፤ ሁለቱን ሚስቶቹን፣+ ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹንና+ 11ዱን ወንዶች ልጆቹን ይዞ በያቦቅ+ መልካ* ተሻገረ። 23  እነሱንም ወስዶ ወንዙን* አሻገራቸው፤ ያለውንም ነገር ሁሉ አሻገረ። 24  በመጨረሻም ያዕቆብ ብቻውን ቀረ። ከዚያም አንድ ሰው ጎህ እስኪቀድ ድረስ ሲታገለው ቆየ።+ 25  ሰውየውም ሊያሸንፈው እንዳልቻለ ሲያይ የጭኑን መጋጠሚያ ነካው፤ ያዕቆብም ከእሱ ጋር በሚታገልበት ጊዜ የጭኑ መጋጠሚያ ከቦታው ተናጋ።+ 26  በኋላም ሰውየው “ጎህ እየቀደደ ስለሆነ ልቀቀኝና ልሂድ” አለው። እሱም “ካልባረክኸኝ አለቅህም” አለው።+ 27  በመሆኑም ሰውየው “ስምህ ማን ነው?” አለው፤ እሱም “ያዕቆብ” ሲል መለሰለት። 28  ሰውየውም “ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል* እንጂ ያዕቆብ አይባልም፤+ ምክንያቱም ከአምላክም ሆነ ከሰዎች ጋር ታግለህ+ በመጨረሻ አሸንፈሃል” አለው። 29  ያዕቆብም መልሶ “እባክህ ስምህን ንገረኝ” አለው። እሱ ግን “ስሜን የምትጠይቀኝ ለምንድን ነው?” አለው።+ እንዲህ ካለው በኋላም በዚያ ስፍራ ባረከው። 30  በመሆኑም ያዕቆብ “አምላክን ፊት ለፊት አይቼ እንኳ ሕይወቴ ተርፏል”*+ በማለት የቦታውን ስም ጰኒኤል*+ አለው። 31  ያዕቆብ ጰኑኤልን* እንዳለፈ ፀሐይ ወጣችበት፤ እሱም ጭኑ በመጎዳቱ ምክንያት ያነክስ ነበር።+ 32  የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ በጭን መጋጠሚያ ላይ ያለውን ጅማት የማይበሉት ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም ሰውየው በያዕቆብ ጭን መጋጠሚያ ላይ ያለውን ጅማት ነክቶ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ሁለት ሰፈር” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ሜዳ።”
ወይም “እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆኜ ኖሬአለሁ።”
ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።
ወይም “ደረቁን ወንዝ።”
“ከአምላክ ጋር የታገለ (በጽናት የተጣበቀ)” ወይም “አምላክ ይታገላል” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ነፍሴ ተርፋለች።”
“የአምላክ ፊት” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ጰኒኤልን።”