ዘፍጥረት 22:1-24

  • አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት እንዲያደርግ ተጠየቀ (1-19)

    • በአብርሃም ዘር አማካኝነት የሚገኝ በረከት (15-18)

  • የርብቃ ቤተሰብ (20-24)

22  ከዚህ በኋላ እውነተኛው አምላክ አብርሃምን ፈተነው፤+ “አብርሃም!” ሲል ጠራው፤ እሱም መልሶ “አቤት!” አለ።  ከዚያም አምላክ እንዲህ አለው፦ “እባክህ ልጅህን፣ በጣም የምትወደውን አንድ ልጅህን+ ይስሐቅን+ ይዘህ ወደ ሞሪያ+ ምድር ሂድ፤ በዚያም እኔ በማሳይህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መባ አድርገህ አቅርበው።”  ስለዚህ አብርሃም በማለዳ ተነስቶ አህያውን ከጫነ በኋላ ከአገልጋዮቹ መካከል ሁለቱን ከልጁ ከይስሐቅ ጋር ይዞ ለመሄድ ተነሳ። ለሚቃጠል መባ የሚሆን እንጨትም ፈለጠ፤ ከዚያም ተነስቶ እውነተኛው አምላክ ወዳሳየው ስፍራ ተጓዘ።  በሦስተኛውም ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ።  በዚህ ጊዜ አብርሃም አገልጋዮቹን “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ በመሄድ በአምላክ ፊት ሰግደን ወደ እናንተ እንመለሳለን” አላቸው።  ስለዚህ አብርሃም ለሚቃጠል መባ የሚሆነውን እንጨት ወስዶ ልጁን ይስሐቅን አሸከመው። እሱ ደግሞ እሳቱንና ቢላውን* ያዘ፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ።  ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን “አባዬ!” ሲል ጠራው። እሱም መልሶ “አቤት ልጄ!” አለው። ይስሐቅም “እሳቱና እንጨቱ ይኸውና፤ ለሚቃጠል መባ የሚሆነው በግ ግን የት አለ?” አለው።  በዚህ ጊዜ አብርሃም “ልጄ፣ ለሚቃጠል መባ የሚሆነውን በግ+ አምላክ ራሱ ያዘጋጃል” አለው። ሁለቱም አብረው ጉዟቸውን ቀጠሉ።  በመጨረሻም እውነተኛው አምላክ ወዳሳየው ስፍራ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያ ሠርቶ እንጨቱን ረበረበበት። ልጁን ይስሐቅንም እጁንና እግሩን አስሮ በመሠዊያው ላይ በተረበረበው እንጨት ላይ አጋደመው።+ 10  ከዚያም አብርሃም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላውን* አነሳ።+ 11  ሆኖም የይሖዋ መልአክ ከሰማይ ጠርቶት “አብርሃም፣ አብርሃም!” አለው፤ እሱም መልሶ “አቤት!” አለ። 12  መልአኩም እንዲህ አለው፦ “በልጁ ላይ እጅህን አታሳርፍበት፤ ምንም ነገር አታድርግበት፤ ምክንያቱም ልጅህን፣ አንድ ልጅህን ለእኔ ለመስጠት ስላልሳሳህ አምላክን የምትፈራ ሰው እንደሆንክ አሁን በእርግጥ አውቄአለሁ።”+ 13  በዚህ ጊዜ አብርሃም ቀና ብሎ ሲመለከት ከእሱ ትንሽ እልፍ ብሎ ቀንዶቹ በጥሻ የተያዙ አውራ በግ አየ። በመሆኑም አብርሃም አውራውን በግ ካመጣ በኋላ በልጁ ምትክ የሚቃጠል መባ አድርጎ አቀረበው። 14  አብርሃምም ያን ስፍራ ይሖዋ ይርኤ* ብሎ ጠራው። እስከ ዛሬም ድረስ “ይሖዋ በተራራው ላይ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ያቀርባል”+ የሚባለው በዚህ የተነሳ ነው። 15  የይሖዋም መልአክ ከሰማይ ለሁለተኛ ጊዜ አብርሃምን ጠራው፤ 16  እንዲህም አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በራሴ እምላለሁ፤+ ይህን ስላደረግክ እንዲሁም ልጅህን፣ አንድ ልጅህን ለመስጠት ስላልሳሳህ+ 17  በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ በእርግጥ አበዛዋለሁ፤+ ዘርህም የጠላቶቹን በር* ይወርሳል።+ 18  ቃሌን ስለሰማህ የምድር ብሔራት ሁሉ በዘርህ+ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።’”+ 19  ከዚያ በኋላ አብርሃም ወደ አገልጋዮቹ ተመለሰ፤ ተነስተውም አብረው ወደ ቤርሳቤህ+ ተመለሱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ መኖሩን ቀጠለ። 20  ከዚህ በኋላ ለአብርሃም እንዲህ ተብሎ ተነገረው፦ “ሚልካም ለወንድምህ ለናኮር+ ወንዶች ልጆችን ወልዳለታለች፤ 21  እነሱም የበኩር ልጁ ዑጽ፣ ወንድሙ ቡዝ፣ የአራም አባት የሆነው ቀሙኤል፣ 22  ኬሰድ፣ ሃዞ፣ ፒልዳሽ፣ ይድላፍ እና ባቱኤል+ ናቸው።” 23  ባቱኤልም ርብቃን+ ወለደ። ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር እነዚህን ስምንቱን ወለደችለት። 24  ቁባቱ የሆነችው ረኡማም ተባህ፣ ጋሃም፣ ታሃሽ እና ማአካ የተባሉ ወንዶች ልጆችን ወለደች።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ማረጃ ቢላውን።”
ወይም “ማረጃ ቢላውን።”
“ይሖዋ ያቀርባል፤ ይሖዋ ይፈጽመዋል” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ከተሞች።”