ዘፍጥረት 17:1-27

  • አብርሃም የብዙ ብሔራት አባት ይሆናል (1-8)

    • አብራም፣ አብርሃም ተባለ (5)

  • የግርዘት ቃል ኪዳን (9-14)

  • ሦራ፣ ሣራ ተባለች (15-17)

  • ይስሐቅ የሚባል ልጅ እንደሚወልድ ቃል ተገባለት (18-27)

17  አብራም ዕድሜው 99 ዓመት ሲሆን ይሖዋ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፦ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ። በፊቴ ተመላለስ፤ እንከን* የሌለብህ መሆንህንም አስመሥክር።  ከአንተ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤+ አንተንም እጅግ አበዛሃለሁ።”+  በዚህ ጊዜ አብራም በግንባሩ ተደፋ፤ አምላክም እንዲህ በማለት እሱን ማነጋገሩን ቀጠለ፦  “በእኔ በኩል ከአንተ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳኔ እንደጸና ነው፤+ አንተም በእርግጥ የብዙ ብሔር አባት ትሆናለህ።+  ከእንግዲህ ስምህ አብራም* አይባልም፤ የብዙ ብሔር አባት ስለማደርግህ ስምህ አብርሃም* ይሆናል።  እጅግ አበዛሃለሁ፤ ብዙ ብሔርም አደርግሃለሁ፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ።+  “ለአንተም ሆነ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ዘሮችህ አምላክ እሆን ዘንድ በእኔና በአንተ እንዲሁም መጪዎቹን ትውልዶቻቸውን ሁሉ ጨምሮ ከአንተ በኋላ በሚመጡት ዘሮችህ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን ዘላለማዊ ቃል ኪዳን አድርጌ እጠብቀዋለሁ።+  ባዕድ ሆነህ የኖርክበትን አገር ይኸውም መላውን የከነአን ምድር ለአንተና ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ዘሮችህ ዘላቂ ርስት አድርጌ እሰጣለሁ፤+ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።”+  በተጨማሪም አምላክ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “በአንተ በኩል፣ አንተም ሆንክ ከአንተ በኋላ የሚመጡት ዘሮችህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ቃል ኪዳኔን መጠበቅ አለባችሁ። 10  እናንተም ሆናችሁ ከእናንተ በኋላ የሚመጡት ዘሮቻችሁ ልትጠብቁት የሚገባው በእኔና በእናንተ መካከል ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው፦ በእናንተ መካከል ያለ ወንድ ሁሉ መገረዝ አለበት።+ 11  ሸለፈታችሁን መገረዝ አለባችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ቃል ኪዳን እንደ ምልክት ሆኖ ያገለግላል።+ 12  በትውልዶቻችሁ ሁሉ በመካከላችሁ ያለ ስምንት ቀን የሞላው ማንኛውም ወንድ መገረዝ አለበት፤+ በቤት የተወለደም ሆነ ዘርህ ያልሆነ ወይም ደግሞ ከባዕድ ሰው ላይ በገንዘብ የተገዛ ማንኛውም ወንድ ሁሉ ይገረዝ። 13  በቤትህ የተወለደ ማንኛውም ወንድ እንዲሁም በገንዘብህ የተገዛ ማንኛውም ወንድ መገረዝ አለበት፤+ በሥጋችሁ ላይ ያለው ይህ ምልክት ከእናንተ ጋር ለገባሁት ዘላቂ ቃል ኪዳን ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል። 14  ሸለፈቱ እንዲገረዝ የማያደርግ ያልተገረዘ ወንድ ካለ ያ ሰው* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።* ይህ ሰው ቃል ኪዳኔን አፍርሷል።” 15  ከዚያም አምላክ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ሚስትህን ሦራን+ በተመለከተ ሦራ* ብለህ አትጥራት፤ ምክንያቱም ከእንግዲህ ስሟ ሣራ* ይሆናል። 16  እኔም እባርካታለሁ፤ ከእሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ።+ እባርካታለሁ፤ እሷም ብዙ ብሔር ትሆናለች፤ የሕዝቦች ነገሥታትም ከእሷ ይወጣሉ።” 17  በዚህ ጊዜ አብርሃም በግንባሩ ተደፋ፤ እየሳቀም በልቡ እንዲህ አለ፦+ “እንዲያው ምንስ ቢሆን 100 ዓመት የሆነው ሰው የልጅ አባት ሊሆን ይችላል? ዘጠና ዓመት የሆናት ሣራስ ብትሆን ልጅ ልትወልድ ትችላለች?”+ 18  ስለዚህ አብርሃም እውነተኛውን አምላክ “ምነው እስማኤልን ብቻ በባረክልኝ!”+ አለው። 19  አምላክም እንዲህ አለው፦ “ሚስትህ ሣራ በእርግጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይስሐቅ*+ ትለዋለህ። እኔም ከእሱ በኋላ ለሚመጡት ዘሮቹ ጭምር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን እንዲሆን ከእሱ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ።+ 20  እስማኤልን በተመለከተም ልመናህን ሰምቻለሁ። እሱንም ቢሆን እባርከዋለሁ፤ ፍሬያማ አደርገዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ። ደግሞም 12 አለቆች ከእሱ ይወጣሉ፤ ታላቅ ብሔርም አደርገዋለሁ።+ 21  ሆኖም የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ+ ከይስሐቅ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ።”+ 22  አምላክ ከአብርሃም ጋር ተነጋግሮ ሲያበቃ ከእሱ ተለይቶ ወደ ላይ ወጣ። 23  ከዚያም አብርሃም ልጁን እስማኤልን፣ በቤቱ የተወለዱትንና በገንዘቡ የገዛቸውን ወንዶች ሁሉ እንዲሁም በአብርሃም ቤት የሚገኙትን ወንዶች ሁሉ ወስዶ ልክ አምላክ በነገረው መሠረት በዚያኑ ዕለት ሸለፈታቸውን ገረዘ።+ 24  አብርሃም ሸለፈቱን ሲገረዝ የ99 ዓመት ሰው ነበር።+ 25  ልጁ እስማኤል ሸለፈቱን በተገረዘበት ጊዜ ደግሞ 13 ዓመቱ ነበር።+ 26  በዚሁ ዕለት አብርሃም ተገረዘ፤ ልጁ እስማኤልም ተገረዘ። 27  በተጨማሪም በቤቱ የሚገኙ ወንዶች ሁሉ፣ በቤት የተወለዱ ሁሉ እንዲሁም ከባዕድ ሰው በገንዘብ የተገዙ ሁሉ ከእሱ ጋር ተገረዙ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነቀፋ።”
“አብ ከፍ ከፍ ያለ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
“የብዙ ሕዝብ አባት፤ የብዙዎች አባት” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ይገደል።”
ወይም “ነፍስ።”
“ተጨቃጫቂ” ማለት ሳይሆን አይቀርም።
“ልዕልት” የሚል ትርጉም አለው።
“ሳቅ” የሚል ትርጉም አለው።