ዘፍጥረት 41:1-57

  • ዮሴፍ የፈርዖንን ሕልሞች ፈታለት (1-36)

  • ፈርዖን ዮሴፍን ከፍ ከፍ አደረገው (37-46ሀ)

  • ዮሴፍ እህል እንዲያከፋፍል ተሾመ (46ለ-57)

41  ሁለት ድፍን ዓመታት ካለፉ በኋላ ፈርዖን በሕልሙ አባይ ወንዝ ዳር ቆሞ አየ።+  ከዚያም ቁመናቸው ያማረ ሰባት የሰቡ ላሞች ከአባይ ወንዝ ሲወጡ አየ፤ እነሱም አባይ ወንዝ ዳር ያለውን ሣር ይበሉ ነበር።+  ከእነሱም ቀጥሎ አስቀያሚ መልክ ያላቸውና ከሲታ የሆኑ ሌሎች ሰባት ላሞች ከአባይ ወንዝ ወጡ፤ እነሱም አባይ ወንዝ ዳር ከነበሩት የሰቡ ላሞች አጠገብ ቆሙ።  ከዚያም አስቀያሚ መልክ ያላቸው ከሲታ የሆኑት ላሞች ያማረ ቁመና ያላቸውን የሰቡትን ሰባት ላሞች በሏቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ባነነ።  ከዚያም ፈርዖን በድጋሚ እንቅልፍ ወሰደው፤ ለሁለተኛ ጊዜም ሕልም አለመ። በሕልሙም በአንድ አገዳ ላይ የተንዠረገጉና ያማሩ ሰባት የእህል ዛላዎች ሲወጡ አየ።+  ከእነሱም በኋላ የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት የእህል ዛላዎች በቀሉ።  የቀጨጩት የእህል ዛላዎች የተንዠረገጉትንና የፋፉትን ሰባት የእህል ዛላዎች ዋጧቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ባነነ፤ ሕልም እንደሆነም ተገነዘበ።  በነጋም ጊዜ መንፈሱ ተረበሸ። በመሆኑም በግብፅ የሚገኙ አስማተኛ ካህናትን በሙሉ እንዲሁም ጥበበኞቿን በሙሉ አስጠራ። ፈርዖንም ያያቸውን ሕልሞች ነገራቸው፤ ሆኖም ለፈርዖን ሕልሞቹን ሊፈታለት የቻለ አንድም ሰው አልነበረም።  በዚህ ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “ኃጢአቴን ዛሬ ልናዘዝ። 10  ፈርዖን በአገልጋዮቹ ተቆጥቶ ነበር። በመሆኑም እኔንና የዳቦ ጋጋሪዎቹን አለቃ በዘቦቹ አለቃ ቤት በሚገኘው ወህኒ ቤት ውስጥ አስሮን ነበር።+ 11  ከዚያም ሁለታችንም በአንድ ሌሊት ሕልም አለምን። እኔም ሆንኩ እሱ ያለምነው ሕልም የተለያየ ፍቺ ነበረው።+ 12  ከእኛም ጋር የዘቦቹ አለቃ አገልጋይ+ የሆነ አንድ ወጣት ዕብራዊ ነበር። ያየናቸውንም ሕልሞች በነገርነው ጊዜ+ የእያንዳንዳችንን ሕልም ፈታልን። 13  ነገሩ ሁሉ ልክ እሱ እንደፈታልን ሆነ። እኔ ወደ ሹመቴ ተመለስኩ፤ ሌላኛው ሰው ግን ተሰቀለ።”+ 14  ስለሆነም ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ሰዎች ላከ፤+ እነሱም ከእስር ቤቱ* በፍጥነት ይዘውት መጡ።+ እሱም ተላጭቶና ልብሱን ለውጦ ወደ ፈርዖን ገባ። 15  ከዚያም ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “ሕልም አይቼ ነበር፤ የሚፈታልኝ ሰው ግን አልተገኘም። አንተ ሕልም ሰምተህ መፍታት እንደምትችል ሰማሁ።”+ 16  በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዖን “ኧረ እኔ እዚህ ግባ የምባል ሰው አይደለሁም! ለፈርዖን መልካም የሆነውን ነገር የሚያሳውቀው አምላክ ነው”+ ሲል መለሰለት። 17  ፈርዖንም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፦ “በሕልሜ አባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። 18  ከዚያም ቁመናቸው ያማረ የሰቡ ሰባት ላሞች ከአባይ ወንዝ ሲወጡ አየሁ፤ እነሱም አባይ ወንዝ ዳር ያለውን ሣር ይበሉ ጀመር።+ 19  ከእነሱ ቀጥሎም የተጎሳቆሉ እንዲሁም አስቀያሚ ቁመና ያላቸውና ከሲታ የሆኑ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ በመላው የግብፅ ምድር እንደ እነሱ ያሉ አስቀያሚ ላሞች ፈጽሞ አይቼ አላውቅም። 20  ከዚያም ከሲታ የሆኑት አስቀያሚ ላሞች የመጀመሪያዎቹን ሰባት የሰቡ ላሞች በሏቸው። 21  ከበሏቸው በኋላም ግን ቁመናቸው ልክ እንደቀድሞው አስቀያሚ ስለነበር ማንም ሰው እንደበሏቸው እንኳ ሊያውቅ አይችልም ነበር። በዚህ ጊዜ ከእንቅልፌ ባነንኩ። 22  “ከዚያ በኋላ የፋፉና ያማሩ ሰባት የእህል ዛላዎች በአንድ አገዳ ላይ ሲወጡ በሕልሜ አየሁ።+ 23  ከእነሱም በኋላ የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት የጠወለጉ የእህል ዛላዎች በቀሉ። 24  ከዚያም የቀጨጩት የእህል ዛላዎች ያማሩትን ሰባት የእህል ዛላዎች ዋጧቸው። እኔም ሕልሜን አስማተኛ ለሆኑት ካህናት ነገርኳቸው፤+ ሆኖም ሊያብራራልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም።”+ 25  ከዚያም ዮሴፍ ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች አንድ ዓይነትና ተመሳሳይ ናቸው። እውነተኛው አምላክ ወደፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን አሳውቆታል።+ 26  ሰባቱ ያማሩ ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው። በተመሳሳይም ሰባቱ ያማሩ የእህል ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው። ሕልሞቹ አንድ ዓይነትና ተመሳሳይ ናቸው። 27  ከእነሱ በኋላ የመጡት ሰባቱ ከሲታና አስቀያሚ ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ በምሥራቅ ነፋስ የተመቱት ሰባቱ ፍሬ አልባ የእህል ዛላዎች ረሃብ የሚከሰትባቸው ሰባት ዓመታት ይሆናሉ። 28  ቀደም ብዬ ለፈርዖን እንደተናገርኩት እውነተኛው አምላክ ወደፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን አሳይቶታል። 29  “በመላው የግብፅ ምድር እህል እጅግ የሚትረፈረፍባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። 30  ከዚያ በኋላ ግን ረሃብ የሚከሰትባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። በግብፅ ምድር እህል የተትረፈረፈበት ዘመን ፈጽሞ ይረሳል፤ ረሃቡም ምድሪቱን በእጅጉ ይጎዳል።+ 31  ከዚያ በኋላ በሚከሰተው ረሃብ የተነሳ በምድሪቱ እህል የተትረፈረፈበት ጊዜ ፈጽሞ አይታወስም፤ ምክንያቱም ረሃቡ በጣም አስከፊ ይሆናል። 32  ሕልሙ ለፈርዖን ሁለት ጊዜ መታየቱ ነገሩ በእውነተኛው አምላክ ዘንድ የተቆረጠ መሆኑን ያሳያል፤ እውነተኛውም አምላክ ይህን በቅርቡ ይፈጽመዋል። 33  “ስለሆነም አሁን ፈርዖን ልባምና ጠቢብ የሆነ ሰው ይፈልግና በግብፅ ምድር ላይ ይሹም። 34  ፈርዖን በምድሪቱ ላይ የበላይ ተመልካቾችን በመሾም እርምጃ ይውሰድ፤ እህል በሚትረፈረፍባቸው ሰባት ዓመታትም በግብፅ ምድር ከሚገኘው ምርት አንድ አምስተኛውን ያከማች።+ 35  እነሱም በመጪዎቹ መልካም ዓመታት የሚገኘውን እህል በሙሉ ይሰብስቡ፤ ለምግብነት የሚሆነውንም እህል በፈርዖን ሥልጣን ሥር በየከተማው ያከማቹ፤ የተከማቸውንም እህል ይጠብቁት።+ 36  በግብፅ ምድር ረሃብ በሚከሰትባቸው ሰባት ዓመታት ምድሪቱ በረሃቡ እንዳትጠፋ የተከማቸው እህል ለአገሪቱ ነዋሪዎች ይሰጣል።”+ 37  ፈርዖንና አገልጋዮቹ በሙሉ ይህን ሐሳብ መልካም ሆኖ አገኙት። 38  በመሆኑም ፈርዖን አገልጋዮቹን “ታዲያ የአምላክ መንፈስ ያለበት እንዲህ ያለ ሌላ ሰው ሊገኝ ይችላል?” አላቸው። 39  ከዚያም ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “አምላክ ይህን ሁሉ እንድታውቅ ስላደረገህ እንደ አንተ ያለ ልባምና ጠቢብ ሰው የለም። 40  አንተው ራስህ በቤቴ ላይ ትሾማለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ያላንዳች ማንገራገር ይታዘዝልሃል።+ እኔ ከአንተ የምበልጠው ንጉሥ በመሆኔ* ብቻ ይሆናል።” 41  በመቀጠልም ፈርዖን ዮሴፍን “ይኸው በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾሜሃለሁ” አለው።+ 42  ከዚያም ፈርዖን የማኅተም ቀለበቱን ከእጁ ላይ አውልቆ በዮሴፍ እጅ ላይ አደረገለት፤ ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስም አለበሰው፤ በአንገቱም ላይ የወርቅ ሐብል አጠለቀለት። 43  ከዚህም በላይ ከእሱ ቀጥሎ ባለው የክብር ሠረገላው ላይ አስቀመጠው፤ ሰዎችም ከፊት ከፊቱ እየሄዱ “አቭሬክ!”* እያሉ ይጮኹ ነበር። በዚህ መንገድ በመላው የግብፅ ምድር ላይ ሾመው። 44  በተጨማሪም ፈርዖን ዮሴፍን “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ሆኖም ያለአንተ ፈቃድ ማንም ሰው በመላው የግብፅ ምድር ላይ ምንም ነገር ማድረግ* አይችልም” አለው።+ 45  ከዚያም ፈርዖን ለዮሴፍ ጸፍናትፓነህ የሚል ስም አወጣለት፤ የኦን* ካህን የሆነውን የጶጥፌራን ልጅ አስናትንም+ አጋባው። ዮሴፍም መላውን የግብፅ ምድር መቃኘት* ጀመረ።+ 46  ዮሴፍ በግብፁ ንጉሥ በፈርዖን ፊት በቆመ* ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት+ ነበር። ከዚያም ዮሴፍ ከፈርዖን ፊት ወጣ፤ መላውን የግብፅ ምድርም ተዘዋውሮ ተመለከተ። 47  እህል ይትረፈረፍባቸዋል በተባሉት ሰባት ዓመታት ምድሪቱ የተትረፈረፈ* ምርት ሰጠች። 48  በእነዚያ ሰባት ዓመታት በግብፅ ምድር የተገኘውንም እህል በሙሉ እየሰበሰበ በየከተሞቹ ያከማች ነበር። በእያንዳንዱ ከተማ ዙሪያ ከሚገኘው እርሻ የተሰበሰበውን እህል በየከተማው ያከማች ነበር። 49  በመጨረሻም ሰዎቹ እህሉን መስፈር አቅቷቸው መስፈራቸውን እስኪተዉ ድረስ ዮሴፍ እንደ ባሕር አሸዋ በጣም ብዙ የሆነ እህል አከማቸ። 50  ዮሴፍ የረሃቡ ዓመት ከመጀመሩ በፊት የኦን* ካህን ከሆነው ከጶጥፌራ ልጅ ከአስናት ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደ።+ 51  ዮሴፍም “አምላክ የደረሰብኝን ችግር ሁሉና የአባቴን ቤት በሙሉ እንድረሳ አደረገኝ” በማለት ለበኩር ልጁ ምናሴ*+ የሚል ስም አወጣለት። 52  ሁለተኛውን ልጁን ደግሞ “መከራዬን ባየሁበት ምድር አምላክ ፍሬያማ አደረገኝ”+ በማለት ኤፍሬም*+ የሚል ስም አወጣለት። 53   ከዚያም በግብፅ ምድር እህል የተትረፈረፈባቸው ሰባት ዓመታት አበቁ፤+ 54  ልክ ዮሴፍ እንደተናገረውም ሰባቱ የረሃብ ዓመታት ጀመሩ።+ ረሃቡም በምድር ሁሉ ላይ እየሰፋ ሄደ፤ በመላው የግብፅ ምድር ግን ምግብ ነበር።+ 55  በመጨረሻም መላው የግብፅ ምድር በረሃቡ ተጠቃ፤ ሕዝቡም ምግብ ለማግኘት ወደ ፈርዖን ይጮኽ ጀመር።+ ፈርዖንም ግብፃውያንን ሁሉ “ወደ ዮሴፍ ሂዱ፤ የሚላችሁንም ሁሉ አድርጉ” ይላቸው ነበር።+ 56  ረሃቡም በመላው ምድር ላይ እየተስፋፋ ሄደ።+ ረሃቡ በግብፅ ምድር ላይ እየጸና ስለሄደ ዮሴፍ በመካከላቸው ያሉትን የእህል ጎተራዎች በሙሉ በመክፈት ለግብፃውያን እህል ይሸጥላቸው ጀመር።+ 57   በተጨማሪም ረሃቡ በመላው ምድር ላይ ክፉኛ ጸንቶ ስለነበር በመላው ምድር የሚኖሩ ሰዎች ከዮሴፍ እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ይመጡ ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ከውኃ ማጠራቀሚያው ጉድጓድ፤ ከጉድጓዱ።”
ወይም “በዙፋኔ።”
ይህ አነጋገር ሰዎች አክብሮት ማሳየት እንዳለባቸው የሚጠቁም መግለጫ ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “እጁንም ሆነ እግሩን ማንሳት።”
ሂልያፖሊስን ያመለክታል።
ወይም “በመላው የግብፅ ምድር መዘዋወር።”
ወይም “ፈርዖንን ማገልገል በጀመረ።”
ቃል በቃል “እፍኝ ሙሉ።”
ሂልያፖሊስን ያመለክታል።
“ማስረሻ፤ የሚያስረሳ” የሚል ትርጉም አለው።
“እጥፍ ፍሬያማ” የሚል ትርጉም አለው።