ዘፍጥረት 26:1-35

  • ይስሐቅና ርብቃ በጌራራ ኖሩ (1-11)

    • አምላክ የሰጠውን ተስፋ በድጋሚ ለይስሐቅ አረጋገጠለት (3-5)

  • በውኃ ጉድጓዶች የተነሳ የተፈጠረ ግጭት (12-25)

  • ይስሐቅ ከአቢሜሌክ ጋር የገባው ቃል ኪዳን (26-33)

  • ሁለቱ የኤሳው ሂታውያን ሚስቶች (34, 35)

26  በአብርሃም ዘመን ከተከሰተው ከመጀመሪያው ረሃብ+ ሌላ በምድሪቱ ላይ ረሃብ ተከሰተ፤ ስለዚህ ይስሐቅ በጌራራ ወደሚገኘው ወደ ፍልስጤማውያን ንጉሥ ወደ አቢሜሌክ ሄደ።  ከዚያም ይሖዋ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፦ “ወደ ግብፅ አትውረድ። እኔ በማሳይህ ምድር ተቀመጥ።  በዚህ ምድር እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነህ ተቀመጥ፤+ እኔም ከአንተ ጋር መሆኔን እቀጥላለሁ፤ እንዲሁም እባርክሃለሁ። ምክንያቱም ይህችን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘሮችህ እሰጣለሁ፤+ ደግሞም ለአባትህ ለአብርሃም እንዲህ ስል የማልሁለትን መሐላ እፈጽማለሁ፦+  ‘ዘርህን በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤+ ይህችንም ምድር በሙሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤+ የምድርም ብሔራት ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።’+  ይህን የማደርገውም አብርሃም ቃሌን ስለሰማ እንዲሁም ሥርዓቶቼን፣ ትእዛዛቴን፣ ደንቦቼንና ሕጎቼን ጠብቆ ስለኖረ ነው።”+  በመሆኑም ይስሐቅ በጌራራ መኖሩን ቀጠለ።+  የዚያ አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በተደጋጋሚ ሲጠይቁት “እህቴ ናት” ይላቸው ነበር።+ “የዚህ አገር ሰዎች በርብቃ የተነሳ ሊገድሉኝ ይችላሉ” ብሎ ስላሰበ “ሚስቴ ናት” ለማለት ፈርቶ ነበር፤ ምክንያቱም ርብቃ ቆንጆ ነበረች።+  ከተወሰነ ጊዜ በኋላም የፍልስጤማውያን ንጉሥ አቢሜሌክ በመስኮት ወደ ውጭ ሲመለከት ይስሐቅ ለሚስቱ ለርብቃ ፍቅሩን ሲገልጽላት*+ አየ።  አቢሜሌክም ወዲያው ይስሐቅን ጠርቶ “መቼም እሷ ሚስትህ እንደሆነች ግልጽ ነው! ታዲያ ‘እህቴ ናት’ ያልከው ለምንድን ነው?” አለው። በዚህ ጊዜ ይስሐቅ “እንዲህ ያልኩት በእሷ የተነሳ ሕይወቴን እንዳላጣ ስለፈራሁ ነው” አለው።+ 10  አቢሜሌክ ግን “እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ታደርግብናለህ?+ ከእኛ ሰዎች አንዱ ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ይችል ነበር፤ እኛንም በደለኞች አድርገህ ታስቆጥረን ነበር!”+ አለው። 11  ከዚያም አቢሜሌክ “ይህን ሰውም ሆነ ሚስቱን የነካ ማንኛውም ሰው ያለምንም ጥርጥር ይገደላል!” በማለት ለሕዝቡ ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ። 12  ይስሐቅም በዚያ ምድር ዘር መዝራት ጀመረ፤ ይሖዋም ስለባረከው በዚያ ዓመት፣ የዘራውን 100 እጥፍ አመረተ።+ 13  ሰውየውም ባለጸጋ ሆነ፤ እጅግ ባለጸጋ እስኪሆንም ድረስ በሀብት ላይ ሀብት እየጨመረ ሄደ። 14  የበግና የከብት መንጋው በዛለት፤ አገልጋዮቹም ብዙ ሆኑ፤+ ፍልስጤማውያንም ይቀኑበት ጀመር። 15  በመሆኑም ፍልስጤማውያን የአባቱ አገልጋዮች በአብርሃም ዘመን የቆፈሯቸውን የውኃ ጉድጓዶች+ በሙሉ አፈር በመሙላት ደፈኗቸው። 16  ከዚያም አቢሜሌክ ይስሐቅን “ከእኛ ይልቅ እየበረታህ ስለመጣህ አካባቢያችንን ለቅቀህ ሂድልን” አለው። 17  በመሆኑም ይስሐቅ ከዚያ ተነስቶ በመሄድ በጌራራ+ ሸለቆ* ሰፈረ፤ በዚያም መኖር ጀመረ። 18  ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ዘመን ተቆፍረው የነበሩትንና አብርሃም ከሞተ በኋላ ፍልስጤማውያን የደፈኗቸውን የውኃ ጉድጓዶች እንደገና ቆፈረ፤+ ቀደም ሲል አባቱ ባወጣላቸው ስምም ጠራቸው።+ 19  የይስሐቅ አገልጋዮችም በሸለቆው ውስጥ* ሲቆፍሩ ለመጠጥ የሚሆን ውኃ ያለበት አንድ ጉድጓድ አገኙ። 20  የጌራራ እረኞች “ውኃው የእኛ ነው!” በማለት ከይስሐቅ እረኞች ጋር ጠብ አነሱ። ከእሱ ጋር ስለተጣሉም የውኃ ጉድጓዱን ስም ኤሴቅ* አለው። 21  እነሱም ሌላ የውኃ ጉድጓድ ቆፈሩ፤ በዚህም ጉድጓድ ጠብ አነሱ። በመሆኑም የጉድጓዱን ስም ሲጥና* አለው። 22  ከዚያም ያን ቦታ ትቶ በመሄድ ሌላ የውኃ ጉድጓድ ቆፈረ፤ እነሱም በዚህ ጉድጓድ ጠብ አላነሱበትም። በመሆኑም “አሁን ይሖዋ ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ በምድርም ላይ እንድንበዛ አድርጎናል”+ በማለት የጉድጓዱን ስም ረሆቦት* አለው። 23  በኋላም ከዚያ ተነስቶ ወደ ቤርሳቤህ+ ወጣ። 24  ይሖዋም በዚያ ሌሊት ተገለጠለትና እንዲህ አለው፦ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ።+ እኔ ከአንተ ጋር ስለሆንኩ አትፍራ፤+ ስለ አገልጋዬ ስለ አብርሃም ስል እባርክሃለሁ እንዲሁም ዘርህን አበዛዋለሁ።”+ 25  በመሆኑም በዚያ መሠዊያ ሠራ፤ የይሖዋንም ስም ጠራ።+ እንዲሁም ይስሐቅ ድንኳኑን በዚያ ተከለ፤+ አገልጋዮቹም በዚያ የውኃ ጉድጓድ ቆፈሩ። 26  ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አቢሜሌክ የግል አማካሪው ከሆነው ከአሁዛትና ከሠራዊቱ አዛዥ ከፊኮል+ ጋር በመሆን ከጌራራ ተነስቶ ወደ ይስሐቅ መጣ። 27  በዚህ ጊዜ ይስሐቅ “ጠልታችሁኝ ከአካባቢያችሁ ካባረራችሁኝ በኋላ አሁን ለምን ወደ እኔ መጣችሁ?” አላቸው። 28  እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ይሖዋ ከአንተ ጋር እንደሆነ በግልጽ ማየት ችለናል።+ በመሆኑም እንዲህ አልን፦ ‘በእኛና በአንተ መካከል በመሐላ የጸና ስምምነት ይኑር፤ ከአንተም ጋር ቃል ኪዳን እንጋባ።+ 29  በአንተ ላይ ምንም ጉዳት እንዳላደረስንብህ ከዚህ ይልቅ በሰላም በማሰናበት መልካም እንዳደረግንልህ ሁሉ አንተም በእኛ ላይ ምንም መጥፎ ነገር እንደማታደርግብን ማልልን። አንተ አሁን ይሖዋ የባረከህ ሰው ነህ።’” 30  እሱም ግብዣ አዘጋጀላቸው፤ እነሱም በሉ፣ ጠጡም። 31  በማግስቱም በማለዳ ተነስተው እርስ በርሳቸው ተማማሉ።+ ከዚያም ይስሐቅ አሰናበታቸው፤ እነሱም ከእሱ ዘንድ በሰላም ሄዱ። 32  በዚያኑ ዕለት የይስሐቅ አገልጋዮች መጥተው ስለቆፈሩት+ የውኃ ጉድጓድ ነገሩት፤ እነሱም “ውኃ እኮ አገኘን!” አሉት። 33  በመሆኑም የጉድጓዱን ስም ሳቤህ አለው። የከተማዋ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ+ ተብሎ የሚጠራው በዚህ የተነሳ ነው። 34  ኤሳው 40 ዓመት ሲሆነው የሂታዊውን የቤኤሪን ልጅ ዮዲትን እንዲሁም የሂታዊውን የኤሎንን ልጅ ባሴማትን አገባ።+ 35  እነሱም ይስሐቅንና ርብቃን ለከፍተኛ ሐዘን ዳረጓቸው።*+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ርብቃን ሲያቅፋት።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “በደረቁ ወንዝ ውስጥ።”
“ጠብ” የሚል ትርጉም አለው።
“ክስ” የሚል ትርጉም አለው።
“ሰፋፊ ቦታዎች” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “የይስሐቅንና የርብቃን መንፈስ አስመረሩ።”