ሁለተኛ ነገሥት 23:1-37

  • ኢዮስያስ ያካሄደው ተሃድሶ (1-20)

  • የፋሲካ በዓል ተከበረ (21-23)

  • ኢዮስያስ የወሰደው ተጨማሪ እርምጃ (24-27)

  • ኢዮስያስ ሞተ (28-30)

  • ኢዮዓካዝ በይሁዳ ላይ ነገሠ (31-33)

  • ኢዮዓቄም በይሁዳ ላይ ነገሠ (34-37)

23  ንጉሡም መልእክት ላከ፤ እነሱም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠሩ።+  ከዚያ በኋላ ንጉሡ ከይሁዳ ሰዎች፣ ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ ከካህናቱ፣ ከነቢያቱ እንዲሁም ትልቅ ትንሽ ሳይባል ከሕዝቡ ሁሉ ጋር ወደ ይሖዋ ቤት ወጣ። እሱም በይሖዋ ቤት የተገኘውን+ የቃል ኪዳኑን+ መጽሐፍ+ ቃል ሁሉ የተሰበሰቡት ሰዎች እየሰሙ አነበበላቸው።  ንጉሡ ዓምዱ አጠገብ ቆሞ በዚህ መጽሐፍ ላይ የሰፈሩትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት በመፈጸም በሙሉ ልቡና በሙሉ ነፍሱ* ይሖዋን ለመከተል እንዲሁም ትእዛዛቱን፣ ማሳሰቢያዎቹንና ደንቦቹን ለመጠበቅ በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ገባ።*+ ሕዝቡም ሁሉ በቃል ኪዳኑ ተስማማ።+  ከዚያም ንጉሡ ሊቀ ካህናቱን ኬልቅያስን፣+ በሁለተኛ ማዕረግ ያሉትን ካህናትና በር ጠባቂዎቹን ለባአል፣ ለማምለኪያ ግንዱና* ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ የተሠሩትን ዕቃዎች በሙሉ ከይሖዋ ቤተ መቅደስ እንዲያወጡ አዘዛቸው።+ ከዚያም ከኢየሩሳሌም ውጭ በቄድሮን ተዳፋት ላይ አቃጠላቸው፤ አመዱንም ወደ ቤቴል+ ወሰደው።  የይሁዳ ነገሥታት በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ በነበሩት ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች ላይ የሚጨስ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ የሾሟቸውን የባዕድ አምላክ ካህናት አባረረ፤ በተጨማሪም ለባአል፣ ለፀሐይ፣ ለጨረቃ፣ ዞዲያክ ለተባለው ኅብረ ከዋክብትና ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ+ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርቡ የነበሩትን በሙሉ አባረረ።  የማምለኪያ ግንዱን* ከይሖዋ ቤት አውጥቶ+ ወደ ኢየሩሳሌም ዳርቻ ወደ ቄድሮን ሸለቆ በመውሰድ በዚያ አቃጠለው፤+ አድቅቆም አመድ አደረገው፤ አመዱንም በሕዝቡ መቃብር ላይ በተነው።+  እንዲሁም በይሖዋ ቤት ውስጥ የነበሩትንና ሴቶች ለማምለኪያ ግንዱ* ቤተ መቅደስ የሚሆኑ ድንኳኖችን ይሸምኑባቸው የነበሩትን የቤተ መቅደስ ቀላጮች*+ ቤቶች አፈራረሰ።  ከዚያም ካህናቱን ሁሉ ከይሁዳ ከተሞች አስወጣ፤ እንዲሁም ካህናቱ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርቡባቸው የነበሩትን ከጌባ+ አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ+ ድረስ የሚገኙትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች አረከሰ። በተጨማሪም የከተማዋ አለቃ በሆነው በኢያሱ መግቢያ በር ላይ ይኸውም አንድ ሰው በከተማዋ በር ሲገባ በስተ ግራ በኩል በሚያገኘው በር ላይ የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች አፈራረሰ።  ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች ካህናት፣ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የይሖዋ መሠዊያ አያገልግሉ+ እንጂ ከወንድሞቻቸው ጋር ቂጣ* ይበሉ ነበር። 10  እሱም በሂኖም ልጆች ሸለቆ*+ ውስጥ የነበረውን ቶፌትን+ አረከሰ፤ ይህን ያደረገው ማንም ሰው በዚያ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት አሳልፎ እንዳይሰጥ ነው።+ 11  ደግሞም የይሁዳ ነገሥታት ለፀሐይ የሰጧቸው ፈረሶች የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን በሆነው በናታንሜሌክ ክፍል* ይኸውም በመተላለፊያዎቹ መሃል ባለው ክፍል በኩል አድርገው ወደ ይሖዋ ቤት እንዳይገቡ ከለከለ፤ የፀሐይንም+ ሠረገሎች በእሳት አቃጠለ። 12  እንዲሁም ንጉሡ የይሁዳ ነገሥታት በአካዝ ሰገነት ጣሪያ ላይ+ የሠሯቸውን መሠዊያዎችና ምናሴ በይሖዋ ቤት ሁለት ግቢዎች ውስጥ የሠራቸውን መሠዊያዎች አፈራረሰ።+ ከዚያም አደቀቃቸው፤ የደቀቀውንም በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ በተነው። 13  በተጨማሪም ንጉሡ፣ የእስራኤል ንጉሥ ሰለሞን ለሲዶናውያን አስጸያፊ የሴት አምላክ ለአስታሮት፣ ለሞዓባውያን አስጸያፊ አምላክ ለከሞሽ እንዲሁም ለአሞናውያን አስጸያፊ አምላክ+ ለሚልኮም+ የሠራቸውን በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ከጥፋት ተራራ* በስተ ደቡብ* የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች አረከሰ። 14  የማምለኪያ ዓምዶቹን ሰባበረ፤ የማምለኪያ ግንዶቹንም* ቆራረጠ፤+ ቦታውንም በሰው አፅም ሞላው። 15  በቤቴል የነበረውንም መሠዊያ ይኸውም እስራኤላውያን ኃጢአት እንዲሠሩ ያደረገው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም የሠራውን ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ አፈረሰ።+ ያን መሠዊያና ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ ካፈረሰ በኋላ ቦታውን አቃጠለው፤ ፈጭቶም አመድ አደረገው፤ የማምለኪያ ግንዱንም* አቃጠለ።+ 16  ኢዮስያስ ዞር ብሎ በተራራው ላይ ያሉትን መቃብሮች ባየ ጊዜ አፅሞቹን ከመቃብሮቹ ውስጥ አስወጥቶ በመሠዊያው ላይ በማቃጠል እነዚህ ነገሮች እንደሚሆኑ አስቀድሞ የተናገረው የእውነተኛው አምላክ ሰው ባወጀው የይሖዋ ቃል መሠረት መሠዊያውን አረከሰ።+ 17  ከዚያም “እዚያ ጋ የማየው የመቃብር ሐውልት የማን ነው?” አለ። በዚህ ጊዜ የከተማዋ ሰዎች “ከይሁዳ የመጣውና በቤቴል በሚገኘው መሠዊያ ላይ አንተ ያደረግካቸውን እነዚህን ነገሮች አስቀድሞ የተናገረው የእውነተኛው አምላክ ሰው+ መቃብር ነው” አሉት። 18  እሱም “በሉ ይረፍ ተዉት። ማንም ሰው አፅሙን አይረብሸው” አለ። በመሆኑም የእሱንም ሆነ ከሰማርያ የመጣውን ነቢይ አፅም ሳይነኩ ተዉት።+ 19  በተጨማሪም ኢዮስያስ የእስራኤል ነገሥታት አምላክን ለማስቆጣት በሰማርያ ከተሞች ውስጥ የሠሯቸውን ከፍ ባሉ የማምለኪያ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የአምልኮ ቤቶች በሙሉ አስወገደ፤+ በቤቴል ያደረገውንም ሁሉ በእነሱ ላይ አደረገ።+ 20  በዚህም መሠረት በዚያ የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች ካህናት በሙሉ በመሠዊያዎቹ ላይ ሠዋ፤ በላያቸውም ላይ የሰው አፅም አቃጠለ።+ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። 21  ንጉሡም ሕዝቡን ሁሉ “በዚህ የቃል ኪዳን መጽሐፍ ላይ በተጻፈው መሠረት ለአምላካችሁ ለይሖዋ ፋሲካን* አክብሩ”+ ሲል አዘዘ።+ 22  መሳፍንት እስራኤልን ያስተዳድሩ በነበረበት ዘመንም ሆነ በእስራኤል ነገሥታትና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ እንዲህ ያለ ፋሲካ ተከብሮ አያውቅም።+ 23  ንጉሥ ኢዮስያስ በነገሠ በ18ኛው ዓመት ግን ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለይሖዋ ተከበረ። 24  በተጨማሪም ኢዮስያስ ካህኑ ኬልቅያስ በይሖዋ ቤት ውስጥ ባገኘው መጽሐፍ+ ላይ የተጻፈውን የሕጉን ቃል ይፈጽም ዘንድ+ መናፍስት ጠሪዎችን፣ ጠንቋዮችን፣+ የተራፊም ቅርጻ ቅርጾችን፣*+ አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶችን* እንዲሁም በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም የነበሩ አስጸያፊ ነገሮችን በሙሉ አስወገደ። 25  በሙሴ ሕግ መሠረት በሙሉ ልቡ፣ በሙሉ ነፍሱና*+ በሙሉ ኃይሉ ወደ ይሖዋ የተመለሰ እንደ እሱ ያለ ንጉሥ ከእሱ በፊት አልነበረም፤ ከእሱ በኋላም እንደ እሱ ያለ ንጉሥ አልተነሳም። 26  ይሁንና ይሖዋ፣ ምናሴ እሱን ያስቆጣው ዘንድ በፈጸማቸው አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ የተነሳ በይሁዳ ላይ ከነደደው ቁጣው አልተመለሰም ነበር።+ 27  ይሖዋ “እስራኤልን እንዳስወገድኩ+ ሁሉ ይሁዳንም ከፊቴ አስወግዳለሁ፤+ የመረጥኳትን ይህችን ከተማ ኢየሩሳሌምን እንዲሁም ‘ስሜ በዚያ ይኖራል’+ ብዬ የተናገርኩለትን ቤት እተዋለሁ” አለ። 28  የቀረው የኢዮስያስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 29  በእሱ ዘመን የግብፁ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ ከአሦር ንጉሥ ጋር ለመገናኘት በኤፍራጥስ ወንዝ በኩል መጣ፤ ንጉሥ ኢዮስያስም ሊገጥመው ወጣ፤ ኒካዑም ባየው ጊዜ መጊዶ ላይ ገደለው።+ 30  በመሆኑም አገልጋዮቹ አስከሬኑን በሠረገላ ከመጊዶ ወደ ኢየሩሳሌም በማምጣት በራሱ መቃብር ውስጥ ቀበሩት። ከዚያም የምድሪቱ ሕዝብ የኢዮስያስን ልጅ ኢዮዓካዝን ቀብተው በአባቱ ምትክ አነገሡት።+ 31  ኢዮዓካዝ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 23 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ገዛ። እናቱ ሀሙጣል ትባል ነበር፤+ እሷም የሊብና ሰው የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 32  አባቶቹ እንዳደረጉት ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 33  ፈርዖን ኒካዑ፣+ ኢዮዓካዝ በኢየሩሳሌም ሆኖ እንዳይገዛ በሃማት ምድር በምትገኘው በሪብላ+ አሰረው፤ በምድሪቱም ላይ 100 የብር ታላንትና* አንድ የወርቅ ታላንት ቅጣት ጣለ።+ 34  በተጨማሪም ፈርዖን ኒካዑ የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ ምትክ አነገሠው፤ ስሙንም ቀይሮ ኢዮዓቄም አለው፤ ኢዮዓካዝን ግን ወደ ግብፅ ወሰደው፤+ እሱም በመጨረሻ በዚያ ሞተ።+ 35  ኢዮዓቄም ብሩንና ወርቁን ለፈርዖን ሰጠው፤ ይሁንና ፈርዖን የጠየቀውን ብር ለመስጠት በምድሪቱ ላይ ቀረጥ መጣል አስፈልጎት ነበር። እሱም እያንዳንዱ የምድሪቱ ነዋሪ ለፈርዖን ኒካዑ እንዲሰጥ ተገምቶ በተጣለበት ቀረጥ መሠረት ብርና ወርቅ እንዲከፍል አደረገ። 36  ኢዮዓቄም+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ።+ እናቱ ዘቢዳ ትባል ነበር፤ እሷም የሩማ ሰው የሆነው የፐዳያህ ልጅ ነበረች። 37  አባቶቹ እንዳደረጉት+ ሁሉ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ቃል ኪዳኑን አደሰ።”
ግብረ ሰዶማውያን ሆነው የሴት ዓይነት ሚና ያላቸውን ወንዶች ያመለክታል።
የቃላት መፍቻው ላይ “ገሃነም” የሚለውን ተመልከት።
ወይም “መመገቢያ አዳራሽ።”
የደብረ ዘይት ተራራ ሲሆን በተለይ ደግሞ የበደል ተራራ ተብሎም የሚጠራውን የተራራውን ደቡባዊ ጫፍ ያመለክታል።
ቃል በቃል “በስተ ቀኝ።” አንድ ሰው ፊቱን ወደ ምሥራቅ በሚያዞርበት ጊዜ ቦታው በስተ ደቡብ እንደሚገኝ ያመለክታል።
ወይም “የማለፍን በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ወይም “የቤት ውስጥ አማልክትን፤ ጣዖታትን።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።