ምሳሌ 11:1-31
11 አባይ* ሚዛን በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ትክክለኛ መለኪያ* ግን ደስ ያሰኘዋል።+
2 እብሪት ከመጣ ውርደት ይከተላል፤+ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።+
3 ቅኖችን ንጹሕ አቋማቸው* ይመራቸዋል፤+ከዳተኞችን ግን ተንኮላቸው ያጠፋቸዋል።+
4 በቁጣ ቀን ሀብት ፋይዳ አይኖረውም፤*+ጽድቅ ግን ከሞት ይታደጋል።+
5 ነቀፋ የሌለበት ሰው የሚሠራው ጽድቅ መንገዱን ቀና ያደርግለታል፤ክፉ ሰው ግን በገዛ ክፋቱ ይወድቃል።+
6 ቅኖችን ጽድቃቸው ያድናቸዋል፤+ከዳተኞች ግን በገዛ ምኞታቸው ይጠመዳሉ።+
7 ክፉ ሰው ሲሞት ተስፋው መና ይቀራል፤በኃይሉ ተመክቶ ተስፋ የሚያደርገው ነገርም ይጠፋል።+
8 ጻድቅ ከመከራ ይድናል፤ክፉ ሰው ደግሞ በእሱ ቦታ ይተካል።+
9 ከሃዲ ሰው* በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፤ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ።+
10 በጻድቃን ጥሩነት ከተማ ሐሴት ታደርጋለች፤ክፉዎች ሲጠፉም እልልታ ይሆናል።+
11 በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤+የክፉዎች አፍ ግን ያፈራርሳታል።+
12 ማስተዋል* የጎደለው ሰው ባልንጀራውን ይንቃል፤*ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰው ግን ዝም ይላል።+
13 ስም የሚያጠፋ ሰው እየዞረ የሌሎችን ሚስጥር ይገልጣል፤+እምነት የሚጣልበት ሰው* ግን ሚስጥር ይጠብቃል።*
14 ጥበብ ያለበት አመራር ሲጓደል ሕዝብ ይጎዳል፤ብዙ አማካሪዎች ባሉበት ግን ስኬት* ይገኛል።+
15 የማያውቀው ሰው ለወሰደው ብድር ዋስ የሚሆን* ጉዳት ላይ መውደቁ አይቀርም፤+እጅ በመምታት* ቃል ከመግባት የሚቆጠብ* ግን ምንም አይደርስበትም።
16 ሞገስ ያላት* ሴት ክብር ታገኛለች፤+ጨካኞች ግን ሀብት ያካብታሉ።
17 ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል፤*+ጨካኝ ሰው ግን በራሱ ላይ መከራ* ያመጣል።+
18 ክፉ ሰው የሚያገኘው ደሞዝ እርባና የለውም፤+ጽድቅን የሚዘራ ግን እውነተኛ ብድራት ያገኛል።+
19 ለጽድቅ ጽኑ አቋም ያለው ሰው ሕይወት የማግኘት ተስፋ አለው፤+ክፋትን የሚያሳድድ ግን ለሞት መዳረጉ አይቀርም።
20 ይሖዋ ጠማማ ልብ ያላቸውን ሰዎች ይጸየፋል፤+ነቀፋ በሌለበት ጎዳና የሚመላለሱ ግን ደስ ያሰኙታል።+
21 ይህን አትጠራጠር፦ ክፉ ሰው ከቅጣት አያመልጥም፤+የጻድቃን ልጆች ግን ይድናሉ።
22 ማስተዋልን የምትንቅ ቆንጆ ሴት፣በአሳማ አፍንጫ ላይ እንዳለ የወርቅ ቀለበት ናት።
23 የጻድቅ ምኞት መልካም ነገር ያስገኛል፤+የክፉ ሰው ተስፋ ግን ወደ ቁጣ ይመራል።
24 አንዱ በልግስና ይሰጣል፤* ሆኖም ተጨማሪ ያገኛል፤+ሌላው ደግሞ ለመስጠት ይሰስታል፤ ነገር ግን ለድህነት ይዳረጋል።+
25 ለጋስ ሰው* ይበለጽጋል፤*+ሌሎችን የሚያረካም* እሱ ራሱ ይረካል።+
26 እህል ለመሸጥ ፈቃደኛ ያልሆነውን ሕዝቡ ይረግመዋል፤የሚሸጠውን ግን ይባርከዋል።
27 መልካም ነገር ለማድረግ የሚተጋ ሞገስ ለማግኘት ይጥራል፤+መጥፎ ነገር ለማድረግ የሚፈልግ ግን ክፋቱ በራሱ ላይ እንደሚመጣ የተረጋገጠ ነው።+
28 በሀብቱ የሚታመን ሰው ይወድቃል፤+ጻድቅ ግን እንዳማረ ቅጠል ይለመልማል።+
29 ቤተሰቡ ላይ ችግር* የሚያመጣ ሰው ሁሉ ነፋስን ይወርሳል፤+ሞኝ ሰውም ጥበበኛ ልብ ላለው ሰው አገልጋይ ይሆናል።
30 የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ነው፤+ነፍሳትንም* የሚማርክ ጥበበኛ ነው።+
31 በእርግጥ ጻድቅ በምድር ላይ የሚገባውን ብድራት የሚቀበል ከሆነክፉውና ኃጢአተኛው የሚቀበሉት ብድራትማ ምንኛ የከፋ ይሆን!+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “የተሟላ የድንጋይ መለኪያ።”
^ ወይም “የማታለያ።”
^ ወይም “ውድ ነገሮች ፋይዳ አይኖራቸውም።”
^ ወይም “አምላክ የለሽ ሰው።”
^ ቃል በቃል “ልብ።”
^ ወይም “ባልንጀራውን ያቃልላል።”
^ ቃል በቃል “በመንፈሱ የታመነ ሰው።”
^ ቃል በቃል “ነገርን ይሰውራል።”
^ ወይም “መዳን።”
^ ቃል በቃል “(ቃል መግባት) የሚጠላ።”
^ ወይም “በመጨበጥ።”
^ ወይም “ተያዥ የሚሆን።”
^ ወይም “የምትወደድ።”
^ ወይም “ታማኝ ፍቅር የሚያሳይ ሰው ነፍሱን ይጠቅማል።”
^ ወይም “ውርደት።”
^ ቃል በቃል “አንዱ ይበትናል።”
^ ወይም “ለጋስ ነፍስ።”
^ ቃል በቃል “ይሰባል።”
^ ቃል በቃል “እንደ ልብ የሚያጠጣም።”
^ ወይም “ውርደት።”
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።