መሳፍንት 2:1-23

  • የይሖዋ መልአክ የሰጠው ማስጠንቀቂያ (1-5)

  • ኢያሱ ሞተ (6-10)

  • እስራኤልን የሚታደጉ መሳፍንት ተነሱ (11-23)

2  የይሖዋም መልአክ+ ከጊልጋል+ ወደ ቦኪም ወጣ፤ እንዲህም አለ፦ “ከግብፅ አውጥቼ ለአባቶቻችሁ ወደማልኩላቸው ምድር አስገባኋችሁ።+ በተጨማሪም እንዲህ አልኩ፦ ‘እኔ ከእናንተ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ፈጽሞ አላፈርስም።+ 2  እናንተም ከዚህች ምድር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን አትግቡ፤+ መሠዊያዎቻቸውንም አፈራርሱ።’+ እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም።+ እንዲህ ያደረጋችሁት ለምንድን ነው? 3  በዚህም የተነሳ ‘እነሱን ከፊታችሁ አላስወጣቸውም፤+ ለእናንተም ወጥመድ ይሆኑባችኋል፤+ አማልክታቸውም ያታልሏችኋል’+ አልኩ።” 4  የይሖዋም መልአክ ለእስራኤላውያን በሙሉ ይህን በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ። 5  ስለሆነም የዚያን ስፍራ ስም ቦኪም* አሉት፤ በዚያም ለይሖዋ መሥዋዕት አቀረቡ። 6  ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ እስራኤላዊ ምድሪቱን ለመውረስ ወደየርስቱ ሄደ።+ 7  ሕዝቡም ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከኢያሱ በኋላ በሕይወት በኖሩትና ይሖዋ ለእስራኤል ሲል ያደረገውን ታላቅ ነገር በሙሉ በተመለከቱት ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ ይሖዋን አገለገለ።+ 8  ከዚያም የይሖዋ አገልጋይ የሆነው የነዌ ልጅ ኢያሱ በ110 ዓመቱ ሞተ።+ 9  እነሱም ከጋአሽ ተራራ+ በስተ ሰሜን በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ በሚገኘው ርስቱ በቲምናትሄረስ+ ቀበሩት። 10  ያም ትውልድ ሁሉ ወደ አያቶቹ ተሰበሰበ፤* ከእነሱም በኋላ ይሖዋንም ሆነ እሱ ለእስራኤል ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሳ። 11  በመሆኑም እስራኤላውያን በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረጉ፤ ባአልንም አገለገሉ።* + 12  በዚህ መንገድ ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን ተዉ።+ በዙሪያቸው ያሉት ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን ሌሎች አማልክት ተከተሉ፤+ ለእነሱም በመስገድ ይሖዋን አስቆጡት።+ 13  ይሖዋን ትተው ባአልንና የአስታሮትን ምስሎች አገለገሉ።+ 14  በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ በመሆኑም ለሚዘርፏቸው ዘራፊዎች አሳልፎ ሰጣቸው።+ በዙሪያቸው ላሉ ጠላቶቻቸው ሸጣቸው፤+ ከዚያ ወዲህ ጠላቶቻቸውን መቋቋም አልቻሉም።+ 15  ይሖዋ አስቀድሞ በተናገረውና ይሖዋ ለእነሱ በማለው መሠረት+ በሄዱበት ቦታ ሁሉ ጥፋት ያመጣባቸው+ ዘንድ የይሖዋ እጅ በእነሱ ላይ ነበር፤ እነሱም በከባድ ጭንቀት ተውጠው ነበር።+ 16  በመሆኑም ይሖዋ ከዘራፊዎቻቸው እጅ የሚያድኗቸውን መሳፍንት አስነሳላቸው።+ 17  እነሱ ግን መሳፍንቱን እንኳ ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ እንዲያውም ከሌሎች አማልክት ጋር አመነዘሩ፤ ለእነሱም ሰገዱ። የይሖዋን ትእዛዛት ያከብሩ የነበሩ አባቶቻቸው ከሄዱበት መንገድ ፈጥነው ዞር አሉ።+ እነሱ እንዳደረጉት ማድረግ ሳይችሉ ቀሩ። 18  ይሖዋ መሳፍንትን በሚያስነሳላቸው+ ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ከመስፍኑ ጋር ይሆን ነበር፤ በመስፍኑም ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ ያድናቸው ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ በሚጨቁኗቸውና+ በሚያንገላቷቸው ሰዎች የተነሳ ሲቃትቱ ያዝናል።*+ 19  መስፍኑ በሚሞትበት ጊዜ ግን ሌሎች አማልክትን በመከተልና በማገልገል እንዲሁም ለእነሱ በመስገድ በድጋሚ ከአባቶቻቸው ይበልጥ መጥፎ ድርጊት ይፈጽማሉ።+ መጥፎ ሥራቸውን ያልተዉ ከመሆኑም ሌላ በእንቢተኝነታቸው ገፍተውበታል። 20  በመጨረሻም የይሖዋ ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤+ እንዲህም አለ፦ “ይህ ብሔር ከአባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ስላፈረሰና+ ቃሌን ስላልሰማ+ 21  እኔም ኢያሱ በሞተ ጊዜ ሳያጠፋ ከተዋቸው ብሔራት መካከል አንዳቸውንም ከፊቱ አላባርርም።+ 22  ይህን የማደርገው እስራኤላውያን አባቶቻቸው እንዳደረጉት እነሱም በይሖዋ መንገድ በመሄድ መንገዱን ይጠብቁ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመፈተን ነው።”+ 23  ስለዚህ ይሖዋ እነዚህ ብሔራት እዚያው እንዲኖሩ ፈቀደ። ወዲያውኑም አላስወጣቸውም፤ ለኢያሱም አሳልፎ አልሰጣቸውም።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“አልቃሽ” የሚል ትርጉም አለው።
ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።
ወይም “አመለኩ።”
ወይም “ይጸጸታል።”