የማቴዎስ ወንጌል 13:1-58

  • የመንግሥቱ ምሳሌዎች (1-52)

    • ዘሪው (1-9)

    • ኢየሱስ ምሳሌዎችን የተጠቀመበት ምክንያት (10-17)

    • የዘሪው ምሳሌ ትርጉም (18-23)

    • ስንዴውና እንክርዳዱ (24-30)

    • የሰናፍጭ ዘርና እርሾ (31-33)

    • “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ” (34, 35)

    • የስንዴውና የእንክርዳዱ ምሳሌ ትርጉም (36-43)

    • የተደበቀ ውድ ሀብትና ዕንቁ (44-46)

    • መረቡ (47-50)

    • አዲስና አሮጌ ዕቃ የያዘ የከበረ ሀብት ማከማቻ (51, 52)

  • ኢየሱስን የአገሩ ሰዎች አልተቀበሉትም (53-58)

13  በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ ዳር ተቀመጠ።  እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እሱ መጥተው ተሰበሰቡ፤ በመሆኑም ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳር ቆመው ነበር።+  ከዚያም ብዙ ነገሮችን እንዲህ እያለ በምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፦+ “እነሆ፣ አንድ ዘሪ ሊዘራ ወጣ።+  በሚዘራበት ጊዜ አንዳንዶቹ ዘሮች መንገድ ዳር ወደቁ፤ ወፎችም መጥተው ለቀሟቸው።+  ሌሎቹ ደግሞ ብዙ አፈር በሌለው ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቁ፤ አፈሩም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያውኑ በቀሉ።+  ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ተቃጠሉ፤ ሥር ስላልነበራቸውም ደረቁ።  ሌሎቹ በእሾህ መካከል ወደቁ፤ እሾሁም አድጎ አነቃቸው።+  ሌሎቹ ደግሞ ጥሩ አፈር ላይ ወድቀው ፍሬ ማፍራት ጀመሩ፤ አንዱ 100፣ አንዱ 60፣ ሌላውም 30 እጥፍ አፈራ።+  ጆሮ ያለው ይስማ።”+ 10  ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ መጥተው “በምሳሌ የምትነግራቸው ለምንድን ነው?” አሉት።+ 11  እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ቅዱስ ሚስጥሮች የመረዳት ችሎታ ተሰጥቷችኋል፤+ ለእነሱ ግን አልተሰጣቸውም። 12  ላለው ሁሉ ይጨመርለታል፤ ደግሞም ይትረፈረፍለታል፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።+ 13  በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤ ቢያዩም የሚያዩት እንዲያው በከንቱ ነውና፤ ቢሰሙም የሚሰሙት እንዲያው በከንቱ ነው፤ ትርጉሙንም አያስተውሉም።+ 14  ደግሞም የኢሳይያስ ትንቢት በእነሱ ላይ እየተፈጸመ ነው። ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ ‘መስማቱን ትሰማላችሁ ግን በፍጹም ትርጉሙን አታስተውሉም፤ ማየቱን ታያላችሁ ግን በፍጹም ልብ አትሉም።+ 15  ምክንያቱም በዓይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው እንዲሁም በልባቸው አስተውለው ወደ እኔ እንዳይመለሱና እንዳልፈውሳቸው የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኗል፤ በጆሯቸው ሰምተው ምላሽ አልሰጡም፤ ዓይናቸውንም ጨፍነዋል።’+ 16  “እናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ደስተኞች ናችሁ።+ 17  እውነት እላችኋለሁ፣ ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ አሁን የምታዩትን ነገር ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ግን አላዩም፤+ አሁን የምትሰሙትን ነገር ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሰሙም። 18  “እንግዲህ እናንተ ዘር የዘራውን ሰው ምሳሌ ስሙ።+ 19  አንድ ሰው የመንግሥቱን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ከሆነ ክፉው+ መጥቶ በልቡ ውስጥ የተዘራውን ዘር ይነጥቀዋል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ይህ ነው።+ 20  በድንጋያማ መሬት ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሲሰማ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበል ሰው ነው።+ 21  ሆኖም ቃሉ በውስጡ ሥር ስለማይሰድ የሚቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ በቃሉ የተነሳም መከራ ወይም ስደት ሲደርስበት ወዲያው ይሰናከላል። 22  በእሾህ መካከል የተዘራው ደግሞ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ ይሁንና የዚህ ሥርዓት* ጭንቀት+ እንዲሁም ሀብት ያለው የማታለል ኃይል ቃሉን ያንቀዋል፤ የማያፈራም ይሆናል።+ 23  በጥሩ አፈር ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን የሚሰማና የሚያስተውል ነው፤ ፍሬም ያፈራል፤ አንዱ 100፣ አንዱም 60፣ ሌላውም 30 እጥፍ ይሰጣል።”+ 24  ደግሞም እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ ጥሩ ዘር ከዘራ ሰው ጋር ይመሳሰላል። 25  ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። 26  እህሉ አድጎ ፍሬ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም አብሮ ታየ። 27  ስለሆነም የቤቱ ጌታ ባሪያዎች፣ ወደ እሱ ቀርበው ‘ጌታ ሆይ፣ በእርሻህ ላይ የዘራኸው ጥሩ ዘር አልነበረም እንዴ? ታዲያ እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። 28  እሱም ‘ይህን ያደረገው ጠላት ነው’ አላቸው።+ ባሪያዎቹም ‘ታዲያ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ አሉት። 29  እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ‘እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ስለምትችሉ ተዉት። 30  እስከ መከር ጊዜ ድረስ አብረው ይደጉ፤ በመከር ወቅት አጫጆቹን፣ በመጀመሪያ እንክርዳዱን ሰብስቡና እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩ፤ ከዚያም ስንዴውን ሰብስባችሁ ወደ ጎተራዬ አስገቡ እላቸዋለሁ።’”+ 31  ደግሞም እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው ወስዶ እርሻው ውስጥ ከተከላት አንዲት የሰናፍጭ ዘር ጋር ይመሳሰላል፤+ 32  የሰናፍጭ ዘር ከሌሎች ዘሮች ሁሉ ያነሰች ብትሆንም ስታድግ ግን ከተክሎች ሁሉ በልጣ ዛፍ ስለምትሆን የሰማይ ወፎች መጥተው በቅርንጫፎቿ ላይ መስፈሪያ ያገኛሉ።” 33  አሁንም እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማያት አንዲት ሴት ወስዳ ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ ከሦስት ትላልቅ መስፈሪያ* ዱቄት ጋር ከደባለቀችው እርሾ ጋር ይመሳሰላል።”+ 34  ኢየሱስ ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ። እንዲያውም ያለምሳሌ አይነግራቸውም ነበር፤+ 35  ይህም የሆነው “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከምሥረታው* ጊዜ አንስቶ የተሰወሩትን ነገሮች አውጃለሁ” ተብሎ በነቢዩ የተነገረው እንዲፈጸም ነው።+ 36  ከዚያም ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ ቀርበው “በእርሻው ውስጥ ስላለው እንክርዳድ የተናገርከውን ምሳሌ አብራራልን” አሉት። 37  እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “ጥሩውን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ 38  እርሻው ዓለም ነው።+ ጥሩው ዘር ደግሞ የመንግሥቱ ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ ግን የክፉው ልጆች ናቸው፤+ 39  እንክርዳዱን የዘራው ጠላት፣ ዲያብሎስ ነው። መከሩ የዚህ ሥርዓት* መደምደሚያ ሲሆን አጫጆቹ ደግሞ መላእክት ናቸው። 40  በመሆኑም እንክርዳዱ ተሰብስቦ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዚህ ሥርዓት* መደምደሚያም እንዲሁ ይሆናል።+ 41  የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነሱም እንቅፋት የሚፈጥሩትን ነገሮች ሁሉና ዓመፅ የሚፈጽሙትን ሰዎች ከመንግሥቱ ይለቅማሉ፤ 42  ወደ እሳታማ እቶንም ይጥሏቸዋል።+ በዚያም ያለቅሳሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ። 43  በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ።+ ጆሮ ያለው ሁሉ ይስማ። 44  “መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ ከተደበቀ ውድ ሀብት ጋር ይመሳሰላል፤ አንድ ሰው ባገኘው ጊዜ ሸሸገው፤ ከመደሰቱም የተነሳ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ እርሻውን ገዛው።+ 45  “በተጨማሪም መንግሥተ ሰማያት ጥሩ ዕንቁ ከሚፈልግ ተጓዥ ነጋዴ ጋር ይመሳሰላል። 46  ከፍተኛ ዋጋ ያለው አንድ ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ወዲያውኑ በመሸጥ ዕንቁውን ገዛው።+ 47  “ደግሞም መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር ተጥሎ የተለያየ ዓይነት ዓሣ ከሰበሰበ መረብ ጋር ይመሳሰላል። 48  መረቡ በሞላ ጊዜ ወደ ባሕሩ ዳር ጎትተው አወጡት፤ ከዚያም ተቀምጠው ጥሩ ጥሩውን+ እየለዩ በዕቃ ውስጥ አስቀመጡ፤ መጥፎ መጥፎውን+ ግን ጣሉት። 49  በዚህ ሥርዓት* መደምደሚያም እንደዚሁ ይሆናል። መላእክት ተልከው ክፉዎችን ከጻድቃን ይለያሉ፤ 50  ወደ እሳታማ እቶንም ይጥሏቸዋል። በዚያም ያለቅሳሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጫሉ። 51  እሱም “የዚህ ሁሉ ትርጉም ገብቷችኋል?” አላቸው። እነሱም “አዎ” አሉት። 52  ከዚያም ኢየሱስ “እንደዚያ ከሆነ፣ ስለ መንግሥተ ሰማያት የተማረ ማንኛውም የሕዝብ አስተማሪ ከከበረ ሀብት ማከማቻው አዲስና አሮጌ ዕቃ ከሚያወጣ የቤት ጌታ ጋር ይመሳሰላል” አላቸው። 53   ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ተናግሮ ሲጨርስ ከዚያ ስፍራ ተነስቶ ሄደ። 54  ወደ ትውልድ አገሩ+ ከመጣ በኋላ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ጀመር፤ ሰዎቹም ተገርመው እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው ይህን ጥበብና እነዚህን ተአምራት የማድረግ ችሎታ ከየት አገኘ?+ 55  ይህ የአናጺው ልጅ አይደለም?+ እናቱስ ማርያም አይደለችም? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉም?+ 56  እህቶቹስ ሁሉ የሚኖሩት ከእኛ ጋር አይደለም? ታዲያ ይህን ሁሉ ከየት አገኘው?”+ 57   ከዚህም የተነሳ ተሰናከሉበት።+ ኢየሱስ ግን “ነቢይ በገዛ አገሩና በገዛ ቤቱ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ቦታ ሁሉ ይከበራል” አላቸው።+ 58  በእሱ ባለማመናቸው በዚያ ብዙ ተአምራት አልፈጸመም።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
በአጠቃላይ 10 ኪሎ ግራም ገደማ ይሆናል።
“ዓለም ከተመሠረተበት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።