አንደኛ ዜና መዋዕል 11:1-47

  • እስራኤላውያን በሙሉ ዳዊትን ንጉሥ አድርገው ቀቡት (1-3)

  • ዳዊት ጽዮንን ያዘ (4-9)

  • የዳዊት ኃያላን ተዋጊዎች (10-47)

11  ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን በሙሉ በኬብሮን+ ወደሚገኘው ወደ ዳዊት ተሰብስበው እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህም ቁራጭ ነን።+  ባለፉት ዘመናት ሳኦል ንጉሥ በነበረበት ጊዜ እስራኤል ወደ ጦርነት ሲወጣ የምትመራው አንተ ነበርክ።+ አምላክህ ይሖዋም ‘ሕዝቤን እስራኤልን እረኛ ሆነህ ትጠብቃለህ፤ በሕዝቤ በእስራኤልም ላይ መሪ ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።”+  በመሆኑም የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን ከእነሱ ጋር በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ገባ። ከዚያም በሳሙኤል አማካኝነት በተነገረው የይሖዋ ቃል መሠረት+ ዳዊትን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ቀቡት።+  በኋላም ዳዊትና መላው እስራኤል ወደ ኢየሩሳሌም ይኸውም ኢያቡሳውያን+ ይኖሩበት ወደነበረው ምድር ወደ ኢያቡስ+ ሄዱ።  የኢያቡስ ነዋሪዎችም ዳዊትን “ፈጽሞ ወደዚህ አትገባም!” በማለት ተሳለቁበት።+ ይሁን እንጂ ዳዊት በአሁኑ ጊዜ የዳዊት ከተማ+ ተብላ የምትጠራውን የጽዮንን+ ምሽግ ያዘ።  ስለሆነም ዳዊት “ኢያቡሳውያንን በመጀመሪያ የሚመታ ሰው አለቃና መኮንን ይሆናል” አለ። የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ+ በመጀመሪያ ወደዚያ ወጣ፤ እሱም አለቃ ሆነ።  ከዚያም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ መኖር ጀመረ። ከዚህም የተነሳ ስፍራውን የዳዊት ከተማ አሉት።  እሱም ከጉብታው አንስቶ በዙሪያው እስካሉት ቦታዎች ድረስ ከተማዋን ዙሪያዋን ገነባ፤ ኢዮዓብ ደግሞ ቀሪውን የከተማዋን ክፍል መልሶ ሠራ።  በዚህ ሁኔታ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ፤+ የሠራዊት ጌታ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር። 10  የዳዊት ኃያላን ተዋጊዎች መሪዎች እነዚህ ናቸው፤ እነሱም ከመላው የእስራኤል ሕዝብ ጋር ሆነው ይሖዋ ለእስራኤል ቃል በገባው መሠረት ንጉሥ+ እንዲሆን ብርቱ ድጋፍ አድርገውለታል። 11  የዳዊት ኃያላን ተዋጊዎች ስም ዝርዝር ይህ ነው፦ የሦስቱ መሪ+ የሆነው የሃክሞናዊው ልጅ ያሾብአም።+ እሱም ጦሩን ሰብቆ በአንድ ጊዜ 300 ሰው ገደለ።+ 12  ከእሱ ቀጥሎ የአሆሐያዊው+ የዶዶ ልጅ አልዓዛር ነበር።+ እሱም ከሦስቱ ኃያላን ተዋጊዎች መካከል አንዱ ነው። 13  ፍልስጤማውያን ለጦርነት ተሰብስበው በነበረበት ጊዜ በጳስዳሚም+ ከዳዊት ጋር አብሮ ነበር። በዚያም የገብስ ሰብል የሞላበት መሬት ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጤማውያን የተነሳ ከአካባቢው ሸሹ። 14  እሱ ግን በእርሻው መካከል ካለበት ንቅንቅ ሳይል መሬቱ እንዳይያዝ አደረገ፤ ፍልስጤማውያንንም መታቸው፤ በመሆኑም ይሖዋ ታላቅ ድል አጎናጸፈ።+ 15  የፍልስጤም ሠራዊት በረፋይም ሸለቆ+ ሰፍሮ በነበረበት ጊዜ፣ ከ30ዎቹ መሪዎች መካከል ሦስቱ ዓለታማ ወደሆነውና ዳዊት ወደሚገኝበት ወደ አዱላም ዋሻ ወረዱ።+ 16  በዚያን ጊዜ ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበር፤ የፍልስጤማውያንም ሠራዊት በቤተልሔም ነበር። 17  ከዚያም ዳዊት “በቤተልሔም+ በር አቅራቢያ ካለው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ የምጠጣው ውኃ ባገኝ ምንኛ ደስ ባለኝ!” በማለት ምኞቱን ገለጸ። 18  በዚህ ጊዜ ሦስቱ ወደ ፍልስጤማውያን ሰፈር ጥሰው በመግባት በቤተልሔም በር አቅራቢያ ከሚገኘው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ውኃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት፤ ዳዊት ግን ለመጠጣት ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ውኃውን ለይሖዋ አፈሰሰው። 19  እንዲህም አለ፦ “ለአምላኬ ካለኝ አክብሮት የተነሳ ይህን ማድረግ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው! ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሄዱትን የእነዚህን ሰዎች ደም ልጠጣ ይገባል?+ ውኃውን ያመጡት በሕይወታቸው ቆርጠው ነውና።” በመሆኑም ውኃውን ለመጠጣት ፈቃደኛ አልሆነም። ሦስቱ ኃያላን ተዋጊዎቹ ያደረጓቸው ነገሮች እነዚህ ነበሩ። 20  የኢዮዓብ+ ወንድም አቢሳ+ የሌሎች ሦስት ሰዎች መሪ ነበር፤ እሱም ጦሩን ሰብቆ 300 ሰው ገደለ፤ እንደ ሦስቱም ሰዎች ዝነኛ ነበር።+ 21  ከሌሎቹ ሦስት ሰዎች መካከል እሱ ከሁለቱ የበለጠ ታዋቂ ነበር፤ የእነሱም አለቃ ነበር፤ ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ሰዎች ያህል ማዕረግ አላገኘም። 22  የዮዳሄ ልጅ በናያህ+ በቃብጽኤል+ ብዙ ጀብዱ የፈጸመ ደፋር ሰው ነበር። እሱም የሞዓቡን የአርዔልን ሁለት ወንዶች ልጆች ገደለ፤ እንዲሁም በረዶ በሚጥልበት ዕለት ወደ አንድ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ወርዶ አንበሳ ገደለ።+ 23  ደግሞም ቁመቱ አምስት ክንድ የሆነ እጅግ ግዙፍ+ ግብፃዊ ገደለ። ግብፃዊው የሸማኔ መጠቅለያ+ የሚመስል ጦር በእጁ ይዞ የነበረ ቢሆንም በትር ብቻ ይዞ በመግጠም የግብፃዊውን ጦር ከእጁ ቀምቶ በገዛ ጦሩ ገደለው።+ 24  የዮዳሄ ልጅ በናያህ ያደረጋቸው ነገሮች እነዚህ ነበሩ፤ እሱም እንደ ሦስቱ ኃያላን ተዋጊዎች ዝነኛ ነበር። 25  ከሠላሳዎቹም ይበልጥ ታዋቂ የነበረ ቢሆንም የሦስቱን ሰዎች ያህል ማዕረግ አላገኘም።+ ይሁን እንጂ ዳዊት የራሱ የክብር ዘብ አለቃ አድርጎ ሾመው። 26  በሠራዊቱ ውስጥ የነበሩት ኃያላን ተዋጊዎች የሚከተሉት ናቸው፦ የኢዮዓብ ወንድም አሳሄል፣+ የቤተልሔሙ የዶዶ ልጅ ኤልሃናን፣+ 27  ሃሮራዊው ሻሞት፣ ጴሎናዊው ሄሌጽ፣ 28  የተቆአዊው የኢቄሽ ልጅ ኢራ፣+ አናቶታዊው አቢዔዜር፣+ 29  ሁሻዊው ሲበካይ፣+ አሆሐያዊው ኢላይ፣ 30  ነጦፋዊው ማህራይ፣+ የነጦፋዊው የባአናህ ልጅ ሄሌድ፣+ 31  ከቢንያማውያን+ ወገን የሆነው የጊብዓው የሪባይ ልጅ ኢታይ፣ ጲራቶናዊው በናያህ፣ 32  የጋአሽ+ ደረቅ ወንዞች ሰው የሆነው ሁራይ፣ አርባዊው አቢዔል፣ 33  ባሁሪማዊው አዝማዌት፣ ሻአልቢማዊው ኤሊያህባ፣ 34  የጊዞናዊው የሃሼም ወንዶች ልጆች፣ የሃራራዊው የሻጌ ልጅ ዮናታን፣ 35  የሃራራዊው የሳካር ልጅ አሂዓም፣ የዑር ልጅ ኤሊፋል፣ 36  መከራታዊው ሄፌር፣ ጴሎናዊው አኪያህ፣ 37  ቀርሜሎሳዊው ሄጽሮ፣ የኤዝባይ ልጅ ናአራይ፣ 38  የናታን ወንድም ኢዩኤል፣ የሃግሪ ልጅ ሚብሃር፣ 39  አሞናዊው ጼሌቅ፣ የጽሩያ ልጅ የኢዮዓብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ናሃራይ፤ 40  ይትራዊው ኢራ፣ ይትራዊው ጋሬብ፣ 41  ሂታዊው ኦርዮ፣+ የአህላይ ልጅ ዛባድ፣ 42  የሮቤላዊው የሺዛ ልጅ አዲና የሮቤላውያን መሪ ነበር፤ ከእሱም ጋር 30 ሰዎች ነበሩ፤ 43  የማአካ ልጅ ሃናን፣ ሚትናዊው ዮሳፍጥ፣ 44  አስታሮታዊው ዑዚያ፣ የአሮዔራዊው የሆታም ልጆች ሻማ እና የኢዔል፤ 45  የሺምሪ ልጅ የዲአዔል፣ ቲጺያዊው ወንድሙ ዮሃ፤ 46  ማሃዋዊው ኤሊዔል፣ የኤልናዓም ልጆች የሪባይ እና ዮሻውያህ፣ ሞዓባዊው ይትማ፤ 47  ኤሊዔል፣ ኢዮቤድ እና መጾባዊው ያአሲዔል።

የግርጌ ማስታወሻዎች