ዘዳግም 10:1-22
10 “በዚያን ጊዜ ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ ‘እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ጠርበህ+ ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፤ የእንጨት ታቦትም* ለራስህ ሥራ።
2 እኔም በጽላቶቹ ላይ አንተ በሰበርካቸው በመጀመሪያዎቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት እጽፋለሁ፤ አንተም ጽላቶቹን በታቦቱ ውስጥ አስቀምጣቸው።’
3 ስለዚህ ከግራር እንጨት ታቦት ሠራሁ፤ ከዚያም እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ የድንጋይ ጽላቶችን ከቀረጽኩ በኋላ ሁለቱን ጽላቶች ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ።+
4 እሱም በጽላቶቹ ላይ ቀደም ሲል ጽፏቸው የነበሩትን ቃላት+ ይኸውም ተሰብስባችሁ በነበረበት ቀን+ ይሖዋ በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ+ ለእናንተ ነግሯችሁ የነበሩትን አሥርቱን ትእዛዛት*+ ጻፈባቸው፤ ይሖዋም ጽላቶቹን ለእኔ ሰጠኝ።
5 እኔም ተመልሼ ከተራራው ወረድኩ፤+ ይሖዋም ባዘዘኝ መሠረት ጽላቶቹን፣ በሠራሁት ታቦት ውስጥ አስቀመጥኳቸው። እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ይገኛሉ።
6 “ከዚያም እስራኤላውያን ከበኤሮት ብኔያዕቃን ተነስተው ወደ ሞሴራ ሄዱ። አሮንም በዚያ ቦታ ሞቶ ተቀበረ፤+ ልጁ አልዓዛርም በእሱ ምትክ ካህን ሆኖ ማገልገል ጀመረ።+
7 ከዚያም ተነስተው ወደ ጉድጎዳ ተጓዙ፤ ከጉድጎዳም ተነስተው ጅረቶች* ወደሚፈስሱባት ምድር ወደ ዮጥባታ+ ሄዱ።
8 “በዚያን ጊዜ ይሖዋ፣ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት እንዲሸከም፣+ ይሖዋን ለማገልገል በፊቱ እንዲቆምና እስከ ዛሬ እንደሚያደርገው በስሙ እንዲባርክ+ የሌዊን ነገድ ለየ።+
9 ሌዊ ከወንድሞቹ ጋር ድርሻ ወይም ርስት ያልተሰጠው ለዚህ ነው። አምላክህ ይሖዋ በነገረው መሠረት ይሖዋ ርስቱ ነው።+
10 እኔም እንደ መጀመሪያው ጊዜ ሁሉ በተራራው ላይ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት ቆየሁ፤+ በዚህ ጊዜም ደግሞ ይሖዋ ሰማኝ።+ ይሖዋ ሊያጠፋህ አልፈለገም።
11 ከዚያም ይሖዋ ‘ለአባቶቻቸው ለመስጠት የማልኩላቸውን ምድር ገብተው እንዲወርሱ ተነስና ከሕዝቡ ፊት ፊት ሂድ’ አለኝ።+
12 “እንግዲህ እስራኤል ሆይ፣ አምላክህ ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?+ አምላክህን ይሖዋን እንድትፈራው፣+ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣+ እንድትወደው፣ አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህና በሙሉ ነፍስህ* እንድታገለግለው+
13 እንዲሁም ለገዛ ጥቅምህ ስትል እኔ ዛሬ የማዝህን የይሖዋን ትእዛዛትና ደንቦች እንድትጠብቅ ብቻ ነው።+
14 እነሆ ሰማያት፣ ሌላው ቀርቶ ሰማየ ሰማያት* እንዲሁም ምድርና በውስጧ ያለው ነገር ሁሉ የአምላክህ የይሖዋ ናቸው።+
15 ይሁንና ይሖዋ የቀረበውና ፍቅሩን የገለጸው ለአባቶችህ ብቻ ነው፤ ስለሆነም ይኸው ዛሬ እንደሆነው የእነሱ ዘር የሆናችሁትን እናንተን ከሕዝቦች ሁሉ መካከል መረጠ።+
16 ስለዚህ ልባችሁን አንጹ፤*+ ከእንግዲህም ወዲህ ግትር መሆናችሁን ተዉ።*+
17 ምክንያቱም አምላካችሁ ይሖዋ የአማልክት አምላክና+ የጌቶች ጌታ እንዲሁም ታላቅ፣ ኃያል፣ የሚያስፈራ፣ ለማንም የማያዳላና+ ጉቦ የማይቀበል አምላክ ነው።
18 አባት ለሌለው* ልጅና ለመበለት ይፈርዳል፤+ እንዲሁም የባዕድ አገሩን ሰው ይወደዋል፤+ ምግብና ልብስም ይሰጠዋል።
19 እናንተም የባዕድ አገሩን ሰው ውደዱ፤ ምክንያቱም በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ነበራችሁ።+
20 “አምላክህን ይሖዋን ፍራ፤ አገልግለው፤+ ከእሱም ጋር ተጣበቅ፤ በስሙም ማል።
21 ልታወድሰው የሚገባህ እሱን ነው።+ እሱ በዓይኖችህ ያየሃቸውን እነዚያን ታላላቅና አስፈሪ ነገሮች ሁሉ ያደረገልህ አምላክህ ነው።+
22 አባቶችህ ወደ ግብፅ ሲወርዱ 70* ነበሩ፤+ አሁን ግን አምላክህ ይሖዋ በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት ቁጥርህን አብዝቶታል።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ሣጥንም።”
^ ቃል በቃል “አሥርቱን ቃላት።”
^ ወይም “ደረቅ ወንዞች።”
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “እጅግ ከፍ ያሉት ሰማያት።”
^ ቃል በቃል “የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ።”
^ ቃል በቃል “አንገታችሁን አታደንድኑ።”
^ ወይም “ወላጅ አልባ ለሆነው።”
^ ወይም “70 ነፍስ።”