የማቴዎስ ወንጌል 4:1-25

  • ዲያብሎስ ኢየሱስን ፈተነው (1-11)

  • ኢየሱስ በገሊላ መስበክ ጀመረ (12-17)

  • የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ተጠሩ (18-22)

  • ኢየሱስ ሰበከ፣ አስተማረ እንዲሁም ፈወሰ (23-25)

4  ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ+ ይፈትነው+ ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ መራው። 2  እሱም 40 ቀንና 40 ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ። 3  ፈታኙም+ ቀርቦ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። 4  እሱ ግን “‘ሰው ከይሖዋ* አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰ።+ 5  ከዚያም ዲያብሎስ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ+ ከወሰደው በኋላ በቤተ መቅደሱ አናት* ላይ አቁሞ+ 6  እንዲህ አለው፦ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ራስህን ወደ ታች ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዛል።’ እንዲሁም ‘እግርህን እንቅፋት እንዳይመታው በእጃቸው ያነሱሃል።’”+ 7  ኢየሱስም “‘አምላክህን ይሖዋን* አትፈታተነው’ ተብሎም ተጽፏል” አለው።+ 8  እንደገናም ዲያብሎስ በጣም ረጅም ወደሆነ ተራራ ወስዶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየው።+ 9  ከዚያም “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። 10  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ! ‘ይሖዋ* አምላክህን ብቻ አምልክ፤+ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’+ ተብሎ ተጽፏልና” አለው። 11  ከዚያም ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤+ እነሆም፣ መላእክት መጥተው ያገለግሉት ጀመር።+ 12  ኢየሱስ፣ ዮሐንስ እንደታሰረ+ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ሄደ።+ 13  ከዚያም ከናዝሬት ወጥቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አውራጃዎች፣ በባሕሩ* አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም+ መጥቶ መኖር ጀመረ፤ 14  ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረው የሚከተለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፦ 15  “ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ወደ ባሕሩ* በሚወስደው መንገድ አጠገብ ያላችሁ የዛብሎን ምድር፣ የንፍታሌም ምድርና የአሕዛብ ገሊላ ሆይ! 16  በጨለማ ውስጥ ያሉ ሰዎች ታላቅ ብርሃን አዩ፤ ሞት በሰዎች ላይ ባጠላበት ምድር ላሉም ብርሃን+ ወጣላቸው።”+ 17  ከዚያን ጊዜ አንስቶ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” እያለ ይሰብክ ጀመር።+ 18  በገሊላ ባሕር* አጠገብ ሲሄድ ሁለቱን ወንድማማቾች ማለትም ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራውን ስምዖንን+ እና ወንድሙን እንድርያስን አያቸው፤ እነሱም ዓሣ አጥማጆች+ ስለነበሩ መረባቸውን ወደ ባሕሩ እየጣሉ ነበር። 19  እሱም “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው።+ 20  እነሱም ወዲያውኑ መረቦቻቸውን ትተው ተከተሉት።+ 21  ከዚያ እልፍ እንዳለ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾችን ማለትም የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን አያቸው።+ እነሱም ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በጀልባ ላይ ሆነው መረቦቻቸውን እየጠገኑ ነበር፤ ኢየሱስም ጠራቸው።+ 22  እነሱም ወዲያውኑ ጀልባዋንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት። 23  ከዚያም በምኩራቦቻቸው+ እያስተማረና የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ እንዲሁም በሕዝቡ መካከል ያለውን ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ+ በመላዋ ገሊላ ተዘዋወረ።+ 24  ስለ እሱም የተወራው ወሬ በመላዋ ሶርያ ተዳረሰ፤ ሰዎችም በተለያየ በሽታና ከባድ ሕመም የሚሠቃዩትን፣+ ጋኔን የያዛቸውን፣+ የሚጥል በሽታ ያለባቸውንና+ ሽባዎችን ሁሉ ወደ እሱ አመጡ፤ እሱም ፈወሳቸው። 25  ከዚህም የተነሳ ከገሊላ፣ ከዲካፖሊስ፣* ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ማዶ የመጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ተከተሉት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

^ ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
^ ወይም “በቤተ መቅደሱ ጣሪያ ዙሪያ ያለ ግንብ፤ ጫፍ።”
^ ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
^ ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
^ ገሊላ ባሕርን ያመለክታል።
^ ሜድትራንያን ባሕር ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ግን ገሊላ ባሕር ነው ይላሉ።
^ በመሠረቱ ባሕር ሳይሆን ሐይቅ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌንሴሬጥ ሐይቅ፣ ገሊላ ባሕር እንዲሁም ጥብርያዶስ ባሕር ተብሎ ተጠርቷል።
^ ወይም “አሥሩ ከተሞች ከሚገኙበት ክልል።”