ሁለተኛ ዜና መዋዕል 4:1-22

  • መሠዊያው፣ ባሕሩና ገንዳዎቹ (1-6)

  • መቅረዞቹ፣ ጠረጴዛዎቹና ግቢዎቹ (7-11ሀ)

  • የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች ተሠርተው ተጠናቀቁ (11ለ-22)

4  ከዚያም ርዝመቱ 20 ክንድ፣ ወርዱ 20 ክንድ፣ ከፍታውም 10 ክንድ የሆነ የመዳብ መሠዊያ ሠራ።+  ባሕሩን*+ በቀለጠ ብረት ሠራ። ባሕሩ ክብ ቅርጽ የነበረው ሲሆን ከአንዱ ጠርዝ እስከ ሌላኛው ጠርዝ 10 ክንድ፣ ከፍታው ደግሞ 5 ክንድ ነበር፤ መጠነ ዙሪያውም በመለኪያ ገመድ ሲለካ 30 ክንድ ሆነ።+  በባሕሩም ዙሪያ ከሥሩ በእያንዳንዱ ክንድ ላይ በቅል+ ቅርጽ የተሠሩ አሥር ጌጦች ነበሩ። ቅሎቹም ከባሕሩ ጋር አንድ ወጥ ሆነው በሁለት ረድፍ ቀልጠው ተሠርተው ነበር።  ባሕሩ 3ቱ ወደ ሰሜን፣ 3ቱ ወደ ምዕራብ፣ 3ቱ ወደ ደቡብ እንዲሁም 3ቱ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ፊታቸውን ባዞሩ 12 በሬዎች+ ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ባሕሩም ላያቸው ላይ ነበር፤ የሁሉም ሽንጥ ወደ መሃል ገባ ያለ ነበር።  የውኃ ማጠራቀሚያው ውፍረት አንድ ጋት* ነበር፤ ጠርዙ የጽዋ ከንፈር ይመስል የነበረ ሲሆን በአበባ ቅርጽ የተሠራ ነበር። የውኃ ማጠራቀሚያው 3,000 የባዶስ መስፈሪያ* መያዝ ይችላል።  በተጨማሪም ለመታጠቢያ የሚሆኑ አሥር የውኃ ገንዳዎች ሠርቶ አምስቱን በስተ ቀኝ፣ አምስቱን ደግሞ በስተ ግራ አስቀመጣቸው።+ ገንዳዎቹን የሚቃጠለውን መባ+ ለማቅረብ የሚያገለግሉትን ነገሮች ለማጠብ ይጠቀሙባቸው ነበር። ባሕሩ ግን የካህናቱ መታጠቢያ ነበር።+  ከዚያም በተሰጠው መመሪያ መሠረት+ አሥር የወርቅ መቅረዞችን+ ሠርቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አምስቱን በስተ ቀኝ፣ አምስቱን ደግሞ በስተ ግራ አስቀመጣቸው።+  በተጨማሪም አሥር ጠረጴዛዎችን ሠርቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አምስቱን በስተ ቀኝ፣ አምስቱን በስተ ግራ አስቀመጣቸው፤+ ከዚያም 100 ጎድጓዳ የወርቅ ሳህኖችን ሠራ።  ከዚያም የካህናቱን+ ግቢ+ እንዲሁም ትልቁን ግቢና+ የግቢውን በሮች ሠራ፤ የግቢዎቹንም በሮች በመዳብ ለበጣቸው። 10  ባሕሩንም በስተ ቀኝ በኩል፣ በስተ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ አስቀመጠው።+ 11  በተጨማሪም ኪራም አመድ ማጠራቀሚያዎቹን፣ አካፋዎቹንና ጎድጓዳ ሳህኖቹን ሠራ።+ ኪራምም በእውነተኛው አምላክ ቤት ለንጉሥ ሰለሞን ያከናውን የነበረውን ሥራ ጨረሰ፤+ 12  ሁለቱን ዓምዶች፣+ በሁለቱ ዓምዶች አናት ላይ የነበሩትን የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸው የዓምድ ራሶች፣ በዓምዶቹ አናት ላይ የነበሩትን የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸውን ሁለቱን ክብ የዓምድ ራሶች የሚያስጌጡትን ሁለት መረቦች፣+ 13  ለሁለቱ መረቦች የተሠሩትን 400 ሮማኖች+ ማለትም በዓምዶቹ አናት ላይ የነበሩትን የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸውን ሁለት የዓምድ ራሶች ለማስጌጥ የተሠሩትን በእያንዳንዱ መረብ ላይ በሁለት ረድፍ የተደረደሩትን ሮማኖች፣+ 14  አሥሩን ጋሪዎችና* በጋሪዎቹ ላይ የነበሩትን አሥር የውኃ ገንዳዎች፣+ 15  ባሕሩንና ከሥሩ የነበሩትን 12 በሬዎች፣+ 16  አመድ ማጠራቀሚያዎቹን፣ አካፋዎቹን፣ ሹካዎቹንና+ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ዕቃዎች ሁሉ ኪራምአቢቭ+ ለይሖዋ ቤት መገልገያ እንዲሆኑ ለንጉሥ ሰለሞን ከተወለወለ መዳብ ሠራ። 17  ንጉሡ እነዚህ ነገሮች በዮርዳኖስ አውራጃ፣ በሱኮትና+ በጸሬዳህ መካከል በሚገኝ ስፍራ በሸክላ ጭቃ ውስጥ ቀልጠው እንዲሠሩ አደረገ። 18  ሰለሞን የሠራቸው ዕቃዎች እጅግ ብዙ ነበሩ፤ የመዳቡም ክብደት ምን ያህል እንደሆነ አልታወቀም።+ 19  ሰለሞን ለእውነተኛው አምላክ ቤት መገልገያ የሚሆኑትን የሚከተሉትን ነገሮች+ ሠራ፦ የወርቅ መሠዊያውን፣+ ገጸ ኅብስቱ የሚቀመጥባቸውን+ ጠረጴዛዎች፣+ 20  በመመሪያው መሠረት በውስጠኛው ክፍል ፊት የሚበሩትን ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ መቅረዞችና መብራቶቻቸውን፣+ 21  ከወርቅ ይኸውም እጅግ ከጠራ ወርቅ የተሠሩትን የፈኩ አበቦች፣ መብራቶችና መቆንጠጫዎች፣ 22  ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩትን የእሳት ማጥፊያዎች፣ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ ጽዋዎችና መኮስተሪያዎች እንዲሁም ከወርቅ የተሠሩትን የቤቱን መግቢያ፣ የቅድስተ ቅዱሳኑን+ የውስጥ በሮችና የቤተ መቅደሱን ቤት በሮች።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ውኃ ማጠራቀሚያውን።”
አንድ ጋት 7.4 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ባዶስ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “የውኃ መጫኛ ጋሪዎችና።”