አንደኛ ዜና መዋዕል 29:1-30

  • ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የተሰጡ መዋጮዎች (1-9)

  • ዳዊት ያቀረበው ጸሎት (10-19)

  • ሕዝቡ ተደሰተ፤ የሰለሞን ንግሥና (20-25)

  • ዳዊት ሞተ (26-30)

29  ንጉሥ ዳዊትም ለመላው ጉባኤ እንዲህ አለ፦ “አምላክ የመረጠው+ ልጄ ሰለሞን ገና ወጣት ነው፤ ተሞክሮም የለውም፤*+ ሥራው ደግሞ ታላቅ ነው፤ ቤተ መቅደሱ* የሚሠራው ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ አምላክ ነውና።+ 2  እኔም አቅሜ በፈቀደው መጠን ለአምላኬ ቤት በወርቅ ለሚሠራው ወርቅ፣ በብር ለሚሠራው ብር፣ በመዳብ ለሚሠራው መዳብ፣ በብረት ለሚሠራው ብረትና+ በሳንቃ ለሚሠራው ሳንቃ+ እንዲሁም ኦኒክስ ድንጋዮች፣ በማያያዣ የሚጣበቁ ድንጋዮች፣ እንደ ጌጥ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ሕብር ያላቸው ድንጋዮች፣ ማንኛውንም ዓይነት የከበረ ድንጋይና የአልባስጥሮስ ድንጋይ በብዛት አዘጋጅቻለሁ። 3  ከዚህም በላይ ለአምላኬ ቤት ካለኝ ፍቅር+ የተነሳ ለቅዱሱ ቤት አስቀድሞ ካዘጋጀሁት በተጨማሪ የግል ሀብቴ+ የሆነውን ወርቅና ብርም ለአምላኬ ቤት እሰጣለሁ፤ 4  ከዚህም ሌላ የቤቶቹን ግድግዳ ለመለበጥ 3,000 ታላንት* የኦፊር ወርቅና+ 7,000 ታላንት የተጣራ ብር፣ 5  በወርቅ ለሚሠራው ወርቅ፣ በብር ለሚሠራው ብር፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ለሚሠሩትም ሥራ ሁሉ የሚያስፈልገውን እሰጣለሁ። ታዲያ ዛሬ ለይሖዋ የሚሰጥ ስጦታ በእጁ ይዞ ለመቅረብ ፈቃደኛ የሆነ ማን ነው?”+ 6  በመሆኑም የአባቶች ቤቶች አለቆች፣ የእስራኤል ነገዶች አለቆች፣ የሺህ አለቆች፣ የመቶ አለቆችና+ የንጉሡን ጉዳይ የሚያስፈጽሙት አለቆች+ በፈቃደኝነት ቀረቡ። 7  ደግሞም ለእውነተኛው አምላክ ቤት አገልግሎት የሚውል 5,000 ታላንት ወርቅ፣ 10,000 ዳሪክ፣* 10,000 ታላንት ብር፣ 18,000 ታላንት መዳብና 100,000 ታላንት ብረት ሰጡ። 8  የከበሩ ድንጋዮች ያለው ሰው ሁሉ ጌድሶናዊው+ የሂኤል+ በኃላፊነት ለሚያስተዳድረው በይሖዋ ቤት ላለው ግምጃ ቤት ሰጠ። 9  ሕዝቡ በፈቃደኝነት መባ በመስጠታቸው እጅግ ተደሰቱ፤ በፈቃደኝነት ተነሳስተው ለይሖዋ መባ የሰጡት በሙሉ ልባቸው ነበርና፤+ ንጉሥ ዳዊትም እጅግ ደስ አለው። 10  ከዚያም ዳዊት በጉባኤው ሁሉ ፊት ይሖዋን አወደሰ። እንዲህም አለ፦ “የአባታችን የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ውዳሴ ይድረስህ። 11  ይሖዋ ሆይ፣ ታላቅነት፣+ ኃያልነት፣+ ውበት፣ ግርማና ሞገስ*+ የአንተ ነው፤ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነው።+ ይሖዋ ሆይ፣ መንግሥት የአንተ ነው።+ ከሁሉም በላይ ከፍ ከፍ ያልክ ራስ ነህ። 12  ሀብትና ክብር ከአንተ ነው፤+ አንተም ሁሉንም ነገር ትገዛለህ፤+ ኃይልና+ ብርታት+ በእጅህ ነው፤ እጅህ ሁሉንም ታላቅ ማድረግና+ ለሁሉም ብርታት መስጠት ይችላል።+ 13  አሁንም አምላካችን ሆይ፣ እናመሰግንሃለን፤ ውብ የሆነውን ስምህንም እናወድሳለን። 14  “ይሁንና በፈቃደኝነት ተነሳስተን እንዲህ ያለ መባ ማቅረብ እንችል ዘንድ እኔም ሆንኩ ሕዝቤ ማን ነን? ሁሉም ነገር የተገኘው ከአንተ ነውና፤ የሰጠንህም ከገዛ እጅህ የተቀበልነውን ነው። 15  እንደ አባቶቻችን ሁሉ እኛም በፊትህ የባዕድ አገር ሰዎችና ሰፋሪዎች ነንና።+ የሕይወት ዘመናችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው፤+ ተስፋም የለውም። 16  አምላካችን ይሖዋ ሆይ፣ ለቅዱስ ስምህ ቤት ለመሥራት ያዘጋጀነው ይህ ሁሉ ሀብት የተገኘው ከገዛ እጅህ ነው፤ ሁሉም የአንተ ነው። 17  አምላኬ ሆይ፣ አንተ ልብን እንደምትመረምርና+ በንጹሕ አቋም * ደስ እንደምትሰኝ+ በሚገባ አውቃለሁ። እኔ በልቤ ቅንነት፣ በፈቃደኝነት ተነሳስቼ ይህን ሁሉ ነገር ሰጥቻለሁ፤ ደግሞም እዚህ የተገኘው ሕዝብህ በፈቃደኝነት ተነሳስቶ ለአንተ መባ ሲያቀርብ በማየቴ እጅግ ደስ ብሎኛል። 18  የአባቶቻችን የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ሕዝብ እንዲህ ያለ የፈቃደኝነት መንፈስና ዝንባሌ ይዞ ለዘላለም እንዲኖርና በሙሉ ልቡ እንዲያገለግልህ እርዳው።+ 19  ልጄ ሰለሞንም ትእዛዛትህን፣ ማሳሰቢያዎችህንና ሥርዓቶችህን እንዲጠብቅ+ ሙሉ* ልብ ስጠው፤+ እነዚህን ሁሉ ነገሮች እንዲያደርግና እኔ ባዘጋጀሁለት ነገሮች ቤተ መቅደስ* እንዲገነባ እርዳው።”+ 20  ከዚያም ዳዊት ለመላው ጉባኤ “አሁን፣ አምላካችሁን ይሖዋን አወድሱ” አለ። ጉባኤውም ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን አወደሱ፤ ለይሖዋና ለንጉሡም በግንባራቸው ተደፍተው ሰገዱ። 21  በማግስቱም ለይሖዋ መሥዋዕት መሠዋታቸውንና ለይሖዋ የሚቃጠል መባ+ ማቅረባቸውን ቀጠሉ፤ 1,000 ወይፈኖች፣ 1,000 አውራ በጎች፣ 1,000 ተባዕት የበግ ጠቦቶችና የመጠጥ መባዎች+ አቀረቡ፤ ስለ እስራኤል ሁሉ ብዙ መሥዋዕት አቀረቡ።+ 22  በዚያ ዕለት በይሖዋ ፊት በታላቅ ደስታ ይበሉና ይጠጡ ነበር፤+ ደግሞም የዳዊትን ልጅ ሰለሞንን ለሁለተኛ ጊዜ አነገሡት፤ በይሖዋም ፊት መሪ አድርገው ቀቡት፤+ ሳዶቅንም ካህን አድርገው ቀቡት።+ 23  ሰለሞንም በአባቱ በዳዊት ፋንታ በይሖዋ ዙፋን+ ላይ ንጉሥ ሆኖ ተቀመጠ፤ እሱም ተሳካለት፤ እስራኤላውያንም ሁሉ ታዘዙለት። 24  መኳንንቱና+ ኃያላን ተዋጊዎቹ+ ሁሉ እንዲሁም የንጉሥ ዳዊት ወንዶች ልጆች+ ሁሉ ለንጉሥ ሰለሞን ተገዙለት። 25  ይሖዋም በእስራኤል ሁሉ ፊት ሰለሞንን እጅግ ታላቅ አደረገው፤ ደግሞም በእስራኤል ከእሱ በፊት የነበሩት ነገሥታት ያላገኙትን ንጉሣዊ ግርማ አጎናጸፈው።+ 26  በዚህ መንገድ የእሴይ ልጅ ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ገዛ፤ 27  በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ሆኖ የገዛበት ጊዜ ርዝመት* 40 ዓመት ነበር። በኬብሮን ለ7 ዓመት፣+ በኢየሩሳሌም ደግሞ ለ33 ዓመት ነገሠ።+ 28  እሱም አስደሳች የሆነ ብዙ ዘመን ኖሮ፣+ ዕድሜ* ጠግቦ እንዲሁም ብዙ ሀብትና ክብር አግኝቶ ሞተ፤ ልጁ ሰለሞንም በእሱ ፋንታ ነገሠ።+ 29  የንጉሥ ዳዊት ታሪክ ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ፣ ባለ ራእዩ* ሳሙኤል፣ ነቢዩ ናታንና+ ባለ ራእዩ ጋድ+ ባዘጋጇቸው ጽሑፎች ውስጥ ሰፍሯል፤ 30  በተጨማሪም ስለ ንግሥናውና ስለ ኃያልነቱ ሁሉ እንዲሁም ከእሱ፣ ከእስራኤልና በዙሪያው ካሉ መንግሥታት ሁሉ ጋር በተያያዘ ስለተከናወኑት ነገሮች ተጽፏል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ግንቡ፤ ቤተ መንግሥቱ።”
ወይም “አልበሰለም።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ዳሪክ የፋርስ የወርቅ ሳንቲም ነበር። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ክብር።”
ወይም “በታማኝነት፤ በቅንነት።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለአንተ ያደረ።”
ወይም “ግንብ፤ ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “ቀናት።”
ቃል በቃል “ቀናት።”
የዕብራይስጡ ቃል በአምላክ እርዳታ መለኮታዊውን ፈቃድ ማስተዋል የቻለን ሰው ያመለክታል።